ከተረጂነት አመለካከት የመውጫው መንገድ

ኢትዮጵያውያን እንደ ድርቅ ያሉ የተፈጥሮ ክስተቶች በአንድ በኩል፣ እንደ ግጭትና ጦርነት ያሉት ቀውሶች ደግሞ በሌላ በኩል በተደጋጋሚ ተመላልሰውባቸዋል። እነዚህ አደጋዎች በየዘመኑ እየተከሰቱ የአያሌ ዜጎችን ሕይወት ቀጥፈዋል፤ አያሌዎችንም ለመፈናቀል ዳርገዋል፤ ችግሮቹ ጥለውባቸው ባለፉት ጠባሳዎች ለውስብስብ የጤናና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተዳረጉትም እጅግ ብዙ ናቸው።

አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች አንደ ዓይናቸው ብሌን የሚጠብቋቸው ከብቶች እንደ ቅጠል ረግፈዋል፤ ብዙ ተስፋ የተሰነቀበት ቡቃያቸው ብቅ ባለበት ቀርቷል፤ የሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት በሚፈለገው መልኩ እንዳይቀጥል፣ ሀገር ለተረጂነት በእጅጉ እንድትጋለጥ ሲያደርጉ ኖረዋል። በተለይ የድርቅ ክስተቶቹ የሀገር ገጽታ በማበላሽትም ይጠቀሳሉ።

ችግሮቹ ካስከተሏቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች ለመውጣት በሀገሪቱ መንግሥታት በሀገር ውስጥ ይደረጉ ከነበሩ ጥረቶች በተጓዳኝ የውጭ ድርጅቶችና ሀገሮች ለተጎጂዎች ድጋፍ የሚያደርጉበትን መንገድ መፈለግም አንዱ መንገድ ሆኖ ተሰርቶበታል።

በእዚህም ለዓለም አቀፍ ለጋሽ ተቋማትና ለጋሽ ሀገሮች ጥሪዎችን በማድረግ ዜጎችን ከድርቅና መሰል አደጋዎች እንዲሁም እነዚህ አደጋዎች ከሚያስከትሉት አኮኖሚያዊና ማህበራዊ ውጥንቅጥ ለመታደግ ብዙ ተሠርቷል። በዚህም አያሌ ዜጎችን መታደግ ተችሏል።

በእርግጥ ድርቅ በተከሰተባቸው ዘመናት ርዳታ መጠየቅ ሳይሆን፣ አለመጠየቅ ነው ጥፋት ሊሆን የሚችለው። እንኳስ በምጣኔ ሀብት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለች ሀገር ባደጉት ሀገሮችም ቢሆን መሰል አደጋዎች ሲከሰቱ እርዳታዎች ሊጠየቁ ይችላሉ፤ ችግሩን የመፍታቱ ሥራ በባህሪው መረዳዳትን ይፈልጋልና። ወዳጆችም ችግሩ መድረሱን እንደሰሙ የወዳጅነታቸውን ድጋፍ ያደርጋሉ።

ችግሮቹ እንደተከሰቱ እሳት ወደ ማጥፋት መግባትም ስህተት አይሆንም፤ ብልህነት ነው። በቅድሚያ የመቀመጪዬን እንዳለችው እንስሳ፤ ጥፋት ይሆን የነበረው ገጽታን ለመጠበቅ ሲባል ክስተቱን ደብቆ በመያዝ ሕዝብን ለበለጠ ጉዳት መዳረግ ነው።

ዜጎች በከፍተኛ የድርቅ አደጋ የተጠቁበት የንጉሡ ዘመን ትልቁ ችግር አደጋው መከሰቱ አልነበረም፤ አደጋው በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ በመንግሥት ይፋ አለመደረጉና ተጎጂዎችን በመታደግ ላይ ርብርብ ለማድረግ አለመሠራቱ ነው። ያ ሁኔታ ለንጉሡ አገዛዝ መውደቅ ምክንያት ከሚባሉት መካከል በመሆን ሲጠቀስ ይሰማል። በ1977 ዓ.ም አስከፊ ድርቅ በተከሰተበት ወቅት የደርግ መንግሥት ችግሩን ለዓለም ማሳወቅ ላይ አልሠራበትም በመባል ይወቀሳል።

ከዚያም በኋላ ቢሆን የድርቅ አደጋዎች ተከስተዋል። ችግሩን በመንግሥት አቅም ብቻ መፍታት እንደማይቻል ታምኖበት ርዳታ መጠየቅ ላይ ተሠርቷል፤ በዚህም ዜጎችን ከድርቁ አደጋና አደጋው ያስከትል ከነበረው ችግር ለመታደግ ብዙ ጥረት ተደርጓል።

የድርቅ አደጋዎቹ በተከሰቱባቸው ዘመናት ሥልጣን ላይ የነበሩ መንግሥታት ዜጎች በእነዚህ ችግሮች ሳቢያ ለከፋ ጉዳት እንዳይዳረጉ በማሰብ በፍጥነት ተንቀሳቅሰው ርዳታ እየጠየቁ ለተጎጂዎች አድርሰው ከሆነ ሃላፊነት የሚሰማቸው መንግሥታት ያደረጉትን አድርገዋልና የመታደግ ጥረታቸው በአዎንታዊ ይታያል። ጓዳውን ካዝናውን የተመለከተ፣ የዜጎቹን አቅም የተረዳ መንግሥት ማድረግ ካለበት አንዱ ይኸው ነው። ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይረዳም እንደሚባለው ፣ ይህን አይነቱን ችግር የመቋቋም ሥራ በሆነ መልኩም ቢሆን መረዳዳትን የግድ ይላልና ጥሪ ማቅረብ ትክክል ነው።

ሌላው ትልቁ ሃላፊነት ክፉ ቀኑ ካለፈ በኋዋላ መካሄድ ያለበት ነው። የድርቅ አደጋዎቹ ለምን ተከሰቱ አይባልም፤ አደጋዎቹ ሲከሰቱ የሚያደርሱትን ጉዳት እንዴት መቀነስ ይቻላል? በድርቅ አደጋው የተጎዱትን እንዴት መልሶ ማቋቋም ይቻላል? ድርቅ በተደጋጋሚ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችንስ በዘላቂነት እንዴት መታደግ ይቻላል? አንደ ሀገር የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አጠቃላይ ልማትን ለማምጣት ምን መሠራት አለበት? በሚሉት ላይ መሥራት ያስፈልጋል። ይህን አለማድረግ ‹‹ሞኝን ሁለቴ እባብ ነከሰው›› እንደተባለው አይነት ይሆናል። በተደጋጋሚ በችግሩ መጎዳትን ያስከትላልና።

ያለፉት መንግሥታት ችግሮቹ ሲያልፉ እጃቸውን አጣጥፈው የተቀመጡ ናቸው ተብሎም ሊወሰድ አይችልም። ከችግሩ ስፋት አኳያ ጥቂት ናቸው ሊባል ይችላል እንጂ አንዳንድ ጥረቶች ተደርገዋል። ከደርግ መንግሥት ጀምሮ የድርቅ አደጋው እንዲከሰት፣ በአደጋው በዜጎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት፣ ችግሮቹ ሲከሰቱ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎች ተሞካክረዋል።

የደርግ መንግሥት በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቁ አካባቢዎችን ነዋሪዎች ለም ወደ ሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወስዶ በማስፈር ምርታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ሠርቷል፣ ሕዝብን በማነቃነቅ የተፈጥሮ ሀብት መመናመንን ለመከላከል የሚያስችሉ የእርከን፣ የተፋሰስ ልማት፣ የደን ልማት ላይ ሥራዎችን ለመሥራት ጥረት አድርጓል፡፡

የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንደ አረንጓዴ ዘመቻ ያሉትን የልማት አቅጣጫዎች ይዞ ሠርቷል። ለእዚህም በፓዊ በግልገል በለስ ወንዝ፣ በጋምቤላ በኦልዌሮ ግድብ በመስኖ ልማት የተጀማመሩ ሥራዎች በአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

በኢህአዴግ ዘመንም እንዲሁ ሰፈራው በክልል ውስጥ ይሁን እንጂ ተሠርቶበታል። በተፋሰስ ልማትም ላይም እንዲሁ ተሠርቷል፤ በተለይ በሴፍቲኔት መርሀ ግብር ለምነቱ የተሟጠጠ መሬት መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ በተሠሩ ሥራዎች የደረቁ ምንጮች ውሃ መስጠት የጀመሩበት፣ አካባቢውን ጥለው ተሰደው ከነበሩ የዱር እንስሳት አንዳንዶቹ የተመለሱበት ሁኔታ መፈጠሩ ሲገለጽ እንደነበር ይታወቃል።

በሴፍቲኔት ልማቱ የተሳተፉ የየአካባቢዎቹ አርሶ አደሮች አካባቢውን በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ከመጠበቃቸው በተጨማሪ በልማቱ በሚያገኙት ገንዘብ ጥሪት ማፍራት የቻሉበትና ሌሎች የልማት ሥራዎች የተሸጋገሩበትና ድርቅ ለሚያስከትለው ችግር ያላቸውን ተጋላጭነት እየቀነሱበት መፈጠሩን ሲገለጽ ሠምተናል።

በለውጡ መንግሥትም እንዲሁ እንደ ኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ባሉ ለድርቅ ተጋላጭ አካባቢዎች በዝናብ ወቅት የሚገኘውን ውሃ መያዝ የሚችሉ ግድቦችን በመገንባት ለሰውና ለከብቶች አልፎም ተርፎ ለመኖ ልማት የሚውል ውሃ እየተያዘ ያለበት ሁኔታም ሌላው የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የተከናወነ ተግባር ነው።

ዓላማው ሰፊ የሆነው በሀገሪቱ እየተካሄደ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እንዲሁም በበጋ ወቅት በስፋት እየተካሄደ ያለው የተፋሰስ ልማት ሥራም በረጅም ጊዜ ውስጥም ቢሆን የድርቅ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ላይ በትኩረት እየሠራ ያለበት ሁኔታም እንዲሁ ለድርቅ አደጋ የሚኖረውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በድርቅና በመሳሰሉት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እለት ደራሽ ምግብ ከማቅረብ ጎን ለጎን ተጎጂዎች በፍጥነት ወደ ልማታቸው እንዲመለሱ የሚያስችሉ የተለያዩ ድጋፎች ተደርገዋል።

ችግሮቹ ግን መመላለሳቸው አልቀረም፤ ይህም የሚያመለክተው ከአንዱ ችግር በመማር ሌላ ችግር እንዳይደገም መሥራት ላይ ብዙ ርቀት አለመኬዱን ነው። ሥራው ጠብ ሲል ሲደፍን አይነት መሆኑን ነው። በዚህ በብዙ መልኩ እንደጠቀመን በማንክደው ርዳታ አማካኝነት የርዳታ ጠባቂነት አመላከከትና እንዲጠናወተን ተደርገናል። ሠርቶ ከመለወጥ ይልቅ ርዳታ የመጠበቅ በሽታ እንዲጣባን ተደርጓል።

በዚህ የተነሳም የድርቅ አደጋ በተከሰተ ቁጥር ርዳታ መጠበቅ ተለምዷል። ለተጎጂዎች የሚውል አቅርቦት በመጠባበቂያነት ብዙም በሌለባት ሀገር ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት ርዳታ ማቅረብም ሆነ መጠየቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለ ነውና ርዳታ መጠየቁ ብዙም ችግር ላይኖረው ይችላል። እንደ ሀገር በራስ አቅም ችግሩን ለመፍታት ዝግጁ ሆኖ አለመገኘት ግን በእጅጉ ሊያሳስብ ይገባል። ይህ ያልሆነው ደግሞ ብዙ አቅሞች ባሉባት ሀገር መሆኑ በእርግጥም ያሳስባል።

እንደሚታወቀው፤ ሀገራችን ለእርሻ ሥራ ሊውል የሚችል ከበቂ በላይ መሬት አላት፤ ለዚያውም ለም። በዝናብ፣ በከርሰ ምድርና ገጸ ምድር የውሃ ሀብትም የበለጸገች ናት። በከብት፣ በማአድን፣ በቱሪዝም፣ ወዘተ ሀብቶችም ባለጸጋ ናት።

በግብርና ሥራ ሊሠማራ የሚችል በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ወጣት ሃይል አላት፤ እውቀትና ቴክኖሎጂ ሊያሻግር የሚችል የተማረ የሰው ሃይል በሀገር ውስጥ በውጭም ሞልቷታል። ለኢንዱስትሪና ለመሳሰሉት ልማት በስፋት ሊውል የሚችል የኤሌክትሪክ ሃይል አላት፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማረፊያ ከሆኑት ጥቂት ሀገሮች አንዷ ናት። እነዚህ ከሀገሪቱ የልማት እምቅ አቅሞች ከብዙ በጥቂቱ ናቸው።

ሀገሪቱ ይህን እምቅ አቅም እና ሕዝቡን አስተባብሮ ወደ ልማቱ የሚያስገባ መንግሥት በአሁኑ ወቅት እንዳላትም ይታወቃል። ሀገሪቱ በዚህ መንግሥት አነሳሽነት የተከናወኑ፣ ለመልማት እንደሚቻል ማሳያ የሆኑ ሥራዎች እየተሠሩባት ትገኛለች።

ለመስኖ ልማት ሊውል የሚችል ከ10 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እንዳላት ስትጠቀስ የኖረች ሀገር በዚህ ሀብት በቅጡ መሥራት የጀመረችው በዚህ የለውጥ መንግሥት በቅርቡ ነው፤ በ2016 በጀት ዓመት ብቻ የተከናወነውን ብንመለከት ከዚህ መሬት በሶሰት ሚሊዮን ሄክታሩ ላይ በበጋ መስኖ ልማት ስንዴ አልምታለች። ከዚህም ከአንድ መቶ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴም አግኝታለች። በኤሌክትሪክ ሃይል በኩልም እንዲሁ እምርታዎች እየታዩ ናቸው። አጠቃላይ ዓመታዊ የግብርና ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል፡፡

ይህ ሁሉ የመልማት አቅምና መልማት የሚያስችል ማሳያም እያለ ታዲያ ርዳታ መጠየቅና የርዳታ አመለካከት ጥንውት ለምን ሆኑብን? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። መንግሥት ሕዝቡንና ሀገሪቱን ከእነዚህ ሥር የሰደዱ የርዳታ ጠባቂነት አመለካከቶች ፣ የርዳታ ፍላጎቶችና የቅልውጥ አባዜዎች መላቀቅ እንደሚገባ እያስገነዘበ ይገኛል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የክልል ከተሞች ከተካሄዱ መድረኮች መረዳት እንደሚቻለውም ከርዳታ ጠባቂነት ለመላቀቅ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል። የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ ርዳታ ሊያስፈልግ ቢችልም ይህን ርዳታ ግን በራስ አቅም ለመሸፈን መሥራት ላይ በስፋት መንቀሳቀስ የግድ መሆን ይኖርበታል፡፡

ባለው ተሞክሮና ጥናት መሠረትም እንደ ድርቅ ያሉ አደጋዎች ሲከሰቱ ለሀገሪቱ የሚያስፈልገውን የምግብ ርዳታ መጠን ኢትዮጵያውያን በያዙት የግብርና ልማት አቅጣጫ አልምተው ሊሸፍኑት የሚችሉት መሆኑ እየተነገረን ነው። ፍላጎቱን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተገኘ ያለውን ምርት የማይደርስ ምርት በቂ መሆኑ እየተጠቆመም ይገኛል። ለእዚህ የሚሆን በቂ መሬት፣ ውሃ እና ተሞከሮም እንዳለም እናውቃለን፤ በሚመለከታቸው አካላት በሚገባ እየተነገረን ነው።

ድርቅና የመሳሰሉት አደጋዎችን ማቆም ባይቻልም፣ ድግግሞሻቸውንና ሊያስከትሉ የሚችሉትን ተጋላጭነት ለመቋቋምና ለመቀነስ ግን ይቻላል። ካደጉት ሀገሮች ተሞክሮም መረዳት የሚቻለው ለማእበል፣ የመሬት መንቀጥቀጥና መሰል አደጋዎች ሲጋለጡ ርዳታ በመፈለግ በኩል ብዙም ድምጻቸው አይሰማም፤ ወዳጅ ሀገሮች አጋርነታቸውን ለማረጋገጥ ሲሉ ርዳታዎችን ፈጥነው ሲያቀርቡ ከመስተዋላቸው ውጪ የጉዳዩ ባለቤቶች ብዙም ልመና ውስጥ ሲገቡ አይስተዋሉም። ችግሩን ዋጥ አድርገው ነው የሚያስቀሩት። ምክንያቱ ለእዚህ ክፉ ቀን የሚሆን በቂ አቅምና ክምችት ከመያዝ ይመነጫል። የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ መሥራት ላይ ብርቱ ስለሆኑና የለሙ በመሆናቸው ነው።

እነሱ የደረሱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ጊዜ ሊወስድ ቢችልም፣ ሥራው ውስጥ በስፋት መግባት ግን ያስፈልገናል። ይህን ማድረግ ደግሞ እንችላለን፤ ሥራው ብዙም የሚከብደን ላለመሆኑም ባለፉት ዓመታት በተለይ በግብርና መስክ አከናውነን ያገኘናቸው ውጤት ማሳያዎች ናቸው። ይህም ወደ እዚህ ሥራ ለመግባት አስቀድመን የጠረግናቸው መንገዶችም እንዳሉን ያመለክታል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሀገሪቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በምግብ ዋስትና ራሷን እንደምትችል ጥሩ ማሳያ ነው። ዓመቱን ሙሉ ተሠርቶ ይገኝ ከነበረው በላይ ስንዴ በበጋ መስኖ ልማት እየተገኘ ነው፤ ይህ ተሞክሮ ወደ ሩዝና ሌሎች ሰብሎች ልማት እየሰፋ ይገኛል።

በሌማት ቱሩፋት በእንቁላል.፣ በዶሮ፣ በወተት ሀብት ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በፍራፍሬና በቡና ልማት እየታየ ያለው ለውጥ ከተረጂነትና ከተረጂነትና ከፈጠረብን መጥፎ አመለካከት ለመውጣት ተስፋ የሚጣልበት ነው።

አጠቃላይ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም በስፋት እየተሰራ ነው። ግብርናውን ሜካናይዝድ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል። ማሳ ከተበጣጠሰ ማሳ ለሜካናይዜሽን ምቹ ወደ ሆነው ኩታ ገጠማ ማሳ እየተቀየረ ነው። በልማት ባንክ፣ በህብረት ሥራ ማህበራትና በመሳሰሉት በኩል ለአርሶ አደሩ በሊዝ ፋይናንሲንግ እየቀረቡ ያሉ ትራክተሮች፣ ኮምባይነሮችና የመሳሰሉት ልማቱ ምን ያህል እንዲዘምን እየተደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ። የግብርናው ዘርፍ በእጅጉ ሲፈልገው የኖረውን ፋይናንስ በማቅረብ በኩልም ለውጦች እየታዩ ናቸው።

በተለይ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እንዲሁም ግብርናውን ሜካናይዝ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ተግባር ምርትና ምርታማነቱ እያደገ አንዲሄድ እያደረጉ ይገኛሉ። ሀገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ በማውጣት በየአመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴ ከውጭ ማስገባት ያቆመችው በእዚሀ ልማት በተከናወነው ተግባር በተገኘ ውጤት ነው፡፡

እነዚህ ስኬቶች በቀጣይም ስኬት ለማስመዝገብ እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች ከርዳታ ጠባቂነትና አመለካከቱ ለመውጣት እንደሚቻል የሚያመላከቱ ናቸው። የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ከተቻለ፣ የመጠባበቂያ ክምችትን በሀገር ውስጥ መሙላት ከተቻለ፣ ተጋላጭነትን የሚቀንሱ እንደ ሴፍትኔት መርሀ ግብር፣ የሌማት ቱሩፋት ያሉ ሥራዎች አሁን በጀመሩት ፍጥነት በዘላቂነት የሚቀጥሉ ከሆነ እነዚህን የሀገርን ገጽታ ያጎደፉ፣ የዜጎችን አእምሮ የሰለቡ የርዳታ ጠባቂነት አመለካከቶችን መስበር የማይቻልበት ምክንያት አይኖርም፡፡

ያለ ርዳታ አንድ ስንዝር የማንጓዝ አድርገው የሚመለከቱንም ጥቂት አይደሉም፤ ለእነዚህ አካላት በስንዴ ልማቱ በቂ መልስ ተሰጥቷቸዋል። በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በውጭ ሃይሎች የተፈጠረብንን ጫና ተከትሎ ርዳታ በተከለከልንበት ወቅት የርዳታ አቅርቦቱን በራሳችን መሸፈን መቻላችን ለእነዚህ አካላት ሁነኛ መልስ ሠጥቷል፡፡

ከገባንበት የርዳታ ጠባቂነት ማጥ ለመውጣት የምንችለው በራሳችን ጥረት እንጂ በሌላ ሃይል በሚደረግልን ድጋፍ ወይም ዳረጎትም እንዳልሆነ ተገንዝበን ርብርብ ማድረግ ይኖርብናል። ውጤታማ የግብርናና የሌሎች ዘርፎች የልማት ሥራዎቻችንን በዘላቂነት አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅብናል።

የርዳታ ጠባቂነት አመለካከትን አውልቆ በመጣል ታሪክ ለመሥራት ሌላ ትልቅ ነገር ማማተር የለብንም። በያዝነው የልማት መንገድ በሚገባ መጓዝ ብቻ ይበቃናል፤ በልማት መንገዳችን የሚታዩ የሚጨበጡ ለብዙዎች ሊተርፉ የሚችሉ ስኬቶችን አስመዝገበናል፤ ይህንኑ አጠናከረን መቀጠል ከምንጠብቀው ግብ ያደርሰናል።

ዘካርያስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You