ደንቢ ሎጅና ፏፏቴ ፕሮጀክት – ለወጣቶች የፈጠረው ተስፋ

በጫካ ውስጥ ተደብቆ በኃይለኛ ድምጽ እያስገመገመ ቁልቁል ወደታች ይወርዳል። ንጣቱም የተገመደ ጥጥ ይመስላል። ሌላኛው ጢስ ዓባይ በየት በኩል መጣ ብዬ በአግራሞት እያየሁ ውሽፍሩን ልብ አላልኩትም። ከድንጋይ ጋር እየተላተመ የሚረጨው ውሃ ልብሴን አርሶታል። አካባቢውንም አርጥቦታል።

አረንጓዴ ከለበሰው ከአካባቢው ገጽታ ጋር ተዳምሮ ቀልብ ይይዛል። ድንቅ የሆነ የተፈጥሮ ፀጋ የተላበሰ አካባቢ። ቤንች ሸካ ዞን ድምቀት ስለሆነው ደንቢ ወንዝ ነው የምነግራችሁ። ይህ ድንቅ የተፈጥሮ ፀጋ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸካ ዞን ውስጥ ነው የሚገኘው።

ለዘመናት በጫካ ውስጥ የሚፈሰው የደንቢ ወንዝ በገበታ ለትውልድ ዐሻራ ተገልጧል። መስህብ ሆኖ ቱሪስቶችን ለመሳብ፣ በፀጋውም የአካባቢውን ማህበረሰብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ በዚያው ደንቢ ወንዝ ላይ ደንቢ ሎጅና ፏፏቴ የሚል ስያሜ የተሰጠው መዝናኛ እየተገነባ ነው። በአካባቢው ላይ ግንባታው እንዲከናወን ተነሳሽነቱን የወሰዱት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ናቸው።

በደንቢ ሎጅና ፏፏቴ ፕሮጀክት ግንባታ ወጣቶች በተለያየ ሥራ በስፋት ተሠማርተዋል። በሥራው ላይ ካገኘናቸው መካከል ወጣት ባርኮት አሰፋ አንዷ ናት። ጠይም፣ አጠር ያለች፣ የደስደስ ያላት። ፈገግታዋና ሳቋ የሚጋባ፣ ቅልጥፍናዋም የሚስብ መልካምነቷ የበዛ ፍልቅልቅ ወጣት ናት። ባሬላ ተሸክማ ሥራዋን ስታቀላጥፍ አብረዋት የሚሠሩትን ጭምር በሥራ ታነቃቃለች።

ወጣት ባርኮት እኛ ስናገኛት በግንባታው ሥራ ሶስተኛ ወሯን ደፍና ነበር። የሥራ ድርሻዋ ለግንበኞች የሚያስፍልገውን ግብዓት በባሬላ ማቅረብ፣ ቀድመው የተገነቡትን ውሃ ማጠጣት ነው። እርስዋ እንዳለችው እንዲህ ያለው የፕሮጀክት ሥራ እንኳን ለእርስዋ ለአካባቢውም አዲስ ነው። እንዲህ ያለ የፕሮጀክት ሥራ ባለመኖሩ የቀን ሥራም በአካባቢው ላይ አልተለመደም። ለዚህም ነው እርስዋን ጨምሮ የአካባቢው ወጣቶች ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳዩት።

ሥራውን ስትጀምር ከብዷት ነበር። በሂደት ግን ለምዳዋለች። ሥራውንም እየወደደችው ነው። እግረመንገዷንም ሥለግንባታ የተለያየ እውቀት እንዲኖራት ዕድል እየተፈጠረላት ነው። የቤተሰብን እጅ ከማየት የራስን ገቢ መፍጠር አንዱ ጥቅም ሆኖ አግኝታዋለች። በኢኮኖሚም በሙያም ተጠቃሚ መሆኗ አስደስቷታል። በጊዜ ቆይታም ባለሙያዎች የሚሠሩትን ሁሉ መሞከር ጀምራለች። ‹‹ማን ያውቃል አንድ ቀን የግንባታ ባለሙያ ሆኗ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመያዝ ልሠራ የምችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል›› ስትልም ተስፋዋን ገልጻልናለች።

ወጣት ባርኮት፤ አብሲኒያ ከተባለ የግል ኮሌጅ በእስተዳደር (ማኔጅመንት) ከተመቀረች ገና አጭር ጊዜ ነው። የተመረቀችበት የትምህርት ዘርፍና አሁን የተሰማራችበት የሥራ ዘርፍ የተለያዩ ናቸው። ሥራውም የጉልበት ሥራ ነው። ወጣት ባርኮት በግንባታው ውስጥ ለመሥራት የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሏት ትገልጻለች።

እርስዋ እንዳለችው በተማረችው የትምህርት ዘርፍ ሥራ እስክታገኝ ማንኛውንም ሥራ መሥራቱ ጥሩ ነው የሚለው አንዱ ምክንያቷ ነው። ፕሮጀክቱ ለአካባቢው አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ በተማረችው የትምህርት ዘርፍ የመቀጠር ዕድል እንደሚኖራትም ተስፋ አድርጋለች።

በግንባታው ዘርፍም እግረመንገድ ተሞክሮ ማግኘትም ሌላው አማራጭ ነው። በግንባታው በሙያ ልምድ ያላቸው በእድሜም ከፍ ያሉ እንዲሁም ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙበት መሆኑ የሥራ ባህልን ጨምሮ የተለያዩ ተሞክሮዎችን መቅሰም እንዳስቻላትም ገልጻለች። ዘመድም አፍርቻለሁ ትላለች። በሥራ አጋጣሚ ወደሌላ አካባቢ የመሄድ እድሉን ብታገኝ እንኳን እንደማትቸገር ነው የተናገረችው። ይህን ሁሉ ዕድል ማግኘት መቻሏ እድለኛ እንደሆነች ይሰማታል።

ወጣት ባርኮት ስለፕሮጀከቱ ምን ያህል ግንዛቤ እንዳላትም ጠይቀናት፤ ፕሮጀክቱ ለመዝናኛ የሚውል በተለይም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ቱሪስቶችን በመሳብ ጥቅም እንዲሰጥ ተደርጎ የሚከናወን እንደሆነ ነው የገለጸችው። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ብዙ ቱሪስቶች ለጉብኝት እንደሚሄዱ መረጃው አላት። አሁን ደግሞ እርስዋ በምትኖርበት አካባቢ ለቱሪስት መስህብ የሚሆን ግንባታ መከናወኑ አስደስቷታል።

ወጣት ባርኮት እንዳጫወተችን፤ የፕሮጀክት ግንባታው የሚከናወንበት ስፍራ ቀደም ሲል ደን ነው የነበረው። ደኑ ስለሚያስፈራ ማንም ወደ አካባቢው አይሄድም። ደንቢ በርቀት ነው የሚታወቀው። ደንቢ ላይ እንዲህ ያለ ፕሮጀክት ይሠራል የሚል እምነትም ተስፋም አልነበረም። ይህ በመሆኑ እርስዋ ብቻ ሳይትሆን ሌሎች የአካባቢው ተወላጆች በተለይም ወጣቶች ደስተኛ እንደሆኑ እና በተለያየ አጋጣሚ ሲገናኙ ስለፕሮጀክቱ ሲያወሩ መስማቷንም አጫውታናለች። ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በተለያየ ሥራ ላይ ለመሠማራት የሚያስችል ተስፋ የሚሰጥ ፕሮጀክት እንደሆነም ገልጻለች።

ሌላው በግንባታ ሥራው ላይ ያገኘነው ወጣት አሳዬ ተስፋዬ ይባላል። በሥራው ላይ ከአምስት ወር በላይ ሆኖታል። በትምህርቱ በተለያየ ምክንያት ከስምንተኛ ክፍል በላይ መቀጠል አልቻለም። ያለትምህርትና ሥራ ከባድ እንደነበርና በአካባቢው ይሄ ፕሮጀከት መኖሩ እንደጠቀመው ይገልጻል።

በፕሮጀክቱ ውስጥ አርማታ ከማቡካት ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ የገለጸልን ወጣት አሳዬ፤ ቀደም ሲል አርማታ በሰው እጅ ይቦካ እንደነበርና በኋላ ላይ ግን በማሽን ማቡካት እንደተጀመረ ያስረዳል።

በሰው ጉልበትና በማሽን ማቡካት ያለውን ሰፊ ልዩነት ግንዛቤ ከመያዙ በተጨማሪ የሰውን ድካም የሚያቀል፣ ጊዜንም የሚቆጥብና ብክነትን የሚያስቀር ቴክኖሎጂ መኖሩን ያወቀው በፕሮጀክቱ ውስጥ ሲሠራ መሆኑንና እውቀትም እንዳገኘበት ተናግሯል።

ፕሮጀክቱ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በአካባቢው ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ እንደሆነ ተገንዝቧል። በፕሮጀክቱ ውስጥ ተቀጥሮ በሚያገኘው ገቢ እና በሥራው አጋጣሚ ባገኘው እውቀት ተጠቃሚ ከመሆኑ በተጨማሪ በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ሥራ የእርሱም ዐሻራ መኖሩ እንዳስደሰተው ነው የገለጸው። ፕሮጀክቱ ሲያልቅ እርሱም የሚዝናናበት እንደሆነም ተናግሯል።

ወጣት አሳዬ አካባቢው ላይ እንዲህ ያለ መዝናኛ ይኖራል ብሎ አስቦ እንደማያውቅ ነው የተናገረው። እርሱ እንዳለው የአካባቢው ወጣቶች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበትና የሚዝናኑበት የላቸውም። ከዚህ በኋላ እንዲህ ያሉ ፕሮጀክቶች እንደሚስፋፉ ተስፋ ያደርጋል። በተለይም ባለሀብቶች የሚሠሩበት ዕድል ቢመቻችላቸው ፕሮጀክቶቹ ሊሰፉ እንደሚችሉም ያምናል።

የደንቢ ሎጅና ፏፏቴ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅም እንዲሁ ወጣት ነው። ኢንጂነር አብዱልቃድር እንዲሪስ ይባላል። እርሱም በገበታ ለትውልድ በሚከናወነው በዚህ ፕሮጀክት ተሳታፊ መሆኑ፣ እንዲህ ከከተማ ርቆ በሚገኝ ፕሮጀክት ላይ መሥራቱ ያሳደረበትን ስሜት ገልጾልናል።

‹‹ፕሮጀክቱ ከስያሜው እንደምንረዳው ወጣቱን ማዕከል ያደረገ ነው። ወጣቱ በተሠራው መዝናኛ ወይንም ሥራ መጠቀም ብቻ ሳይሆን፣ በሥራውም ተሳታፊ መሆን አለበት። የራሱንም ዐሻራ ማኖር ይጠበቅበታል። በተለያዩ አካባቢዎች የሥራ ልምዶች ሲኖሩት ሰፋ ያለ እውቀት ይኖረዋል።

እኔም ደንቢ ሎጅና ፏፏቴ ፕሮጀክት ሥራ ላይ ለመሳተፍ ስወስን ወደፊት ሰፋፊ በሆኑ ፕሮጀክቶች ላይም ለመሥራት የሚያስችል እድል ለማግኘትና በተለይም ገበታ ለትውልድ ላይ ዐሻራም እንዲኖረኝ ነው። አሁን የምገኝበት ሥራ ተነሳሽነትንም ፈጥሮልኛል።›› በማለት አስረድቷል።

ከከተማ ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ወጣ ብሎ መሥራቱ ምን እንደሚመስል፣ ያለውን ፈተናና ጫና ተቋቁሞ ማለፍና መልካም ነገሮችንም ማየት እንደሚያስፈልግም ወጣት አብዱልቃድር ይገልጻል። ደንቢ ሎጅና ፏፏቴ ፕሮጀክት ሥራ ከጀመረ ጀምሮ ከአካባቢው ርቆ እንዳልሄደና ውሎውና አዳሩ በፕሮጀክቱ ሥራ ላይ እንደሆነ ነው የነገረን።

ኢንጂነር አብዱልቃድር ደንቢ ሎጅ ፏፏቴ ፕሮጀክት የመጀመሪያው አይደለም። በተለያዩ አካባቢዎች በተከናወኑ ወደ አራት የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ በኃላፊነት ሠርቷል። ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ በ2011ዓም ነው በሲቪል ምህንድስና ነው የተመረቀው።

ስለደንቢ ሎጅ ፏፏቴ ፕሮጀክት አጠቃላይ ሥራ በተመለከተ ኢንጂነር አብዱርቃድር እንደገለጸው፤ ፕሮጀክቱን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የታቀደ ሲሆን፣ ለፕሮጀክቱ የተያዘው በጀትም ወደ 180 ሚሊዮን ብር ነው። ገንዘቡ የፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ ሆኖ ግን አይታሰብም። የፕሮጀክቱ ግንባታ ወደ 45 በመቶ ደርሷል። የፕሮጀክቱ አማካሪና ኢንጂነሪንጉን የያዘው ጉባላፍቶ የተባለ ድርጅት ሲሆን፣ ተቋራጩ ደግሞ ራስመስ አዲስ የተባለ ኩባንያ ነው። ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ደግሞ ተቋራጭም ተቆጣጣሪም ሆኖ እየሠራ ይገኛል።

ደንቢ ወንዝ ወይንም ሐይቅ ዳርቻ ላይ እየተገነባ የሚገኘው ደንቢ ሎጅና ፏፏቴ፤ የመስብሰቢያ አዳራሽ ጨምሮ ፣ በአንድ ጊዜ ከ 155 ሰዎች በላይ የማስተናገድ አቅም ያለው ካፌና ሬስቶራንት እንዲሁም በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ማረፊያ ክፍሎች አለው። ሁለት ባለሁለት መኝታ፣ ሁለት ባለሶስት መኝታ 11 ባለአንድ መኝታ፣ ከነዚህ ውስጥም ዘጠኙ ሁለት ሁለት ክፍሎች ሁለቱ ደግሞ አንዳንድ ክፍሎች ይኖራቸዋል።

ከግንባታው ተጠናቅቆ አገልግሎት ላይ ሲውል ለደንምበኞች የሚቀርብ ምግብ በአካባቢው ላይ ምቹ እንዲሆን ጎን ለጎን ደንቢ ሐይቅ ላይ የአሣ እርባታ የሚከናወንበት ሁኔታም ለማመቻቸት ታቅዷል።

በግንባታ ሥራ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እንደሚኖሩ ይጠበቃል። በዚህ ረገድ ስላለው ሁኔታና ተግዳሮቶችንም ተቋቁሞ ሥራውን ለማከናወን እየተደረገ ስላለው ጥረት የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አብዱልቃድር እንደገለጸልን፤ በእቅዱ መሠረት ለመሄድ ተግዳሮት የሆነው አንዱ አካባቢው ዝናባማ በመሆኑ በዝናብ ወቅት ሥራ ይቋረጣል። ለግንባታ የሚውል ድንጋይ፣ ጠጠር፣ አሸዋ የመሳሰሉ ግብዓቶች በአካባቢው ላይ አለመገኘቱ ሌላው ተግዳሮት ነው። ከርቀት ቦታ ተጓጎዞ ነው የሚቀርበው።

የወባ በሽታም በስፋት በመኖሩ ሠራተኞች ታመው ከሥራ ይቀራሉ። በነዚህ ምክንያቶች እየተፈጠሩ ያሉ መዘግየቶችን የእርፍት ቀናቶችን ጨምሮ እስከ ምሽት ድረስ በመሥራት የባከነውን ጊዜ በማካካስ ነው ችግሮችን ለመቋቋም ጥረት እየተደረገ ያለው።

ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያም በግንባታ ፕሮጀክቱ ሥራ ላይ በስፋት እየተሳተፉ የሚገኙት የአካባቢው ወጣቶች ሲሆኑ፣ ካለው የሰው ኃይልም ወደ ሁለት መቶ የሚሆኑት የአካባቢው ወጣቶች ናቸው። ከፍ ባለ ሙያ ላይ ልምድ ያላቸው ከአዲስ አበባ ከተማ በማስመጣት እንዲሠሩ እየተደረገ ቢሆንም በአካባቢው ላይ መጠነኛ የሆነ እውቀት ያላቸው ሲገኙ በሥልጠና እና ልምድ ካላቸውም የእውቀት ሽግግር በማድረግ ሙያ በሚጠይቅ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው። ፕሮጀክቱ የቀን የሥራ ዕድል ብቻ ሳይሆን፣ በግንባታው ዘርፍ ባለሙያም እየፈጠረ ነው። በገበታ ለትውልድ የተከናወኑ ፕሮጀክቶች በተለይም በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ መነቃቃት እየፈጠሩ እንደሆነ ይታወቃል።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2016

Recommended For You