መንግሥት ከአምስቱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ምሰሶ ለሆነው የማዕድን ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። ይሁን እንጂ ዘርፉ ገና ያልተነካ፣ በብዙ ያልተሠራበትና በአግባቡ ያልተመራ እንደመሆኑ የሠለጠነና ብቁ የሆነ የሰው ኃይል የሚያስፈልገው እንደሆነም ይነገራል።
በተለይ ዘርፉ እውቀትና ብቃት ባለው የሰው ኃይል እንዲመራ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሚናቸው የጎላ ነው። በዚህም በዘርፉ የሰለጠነ ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት በጥናትና ምርምር የመደገፍ ሥራዎች እንዲሠሩ ይጠበቃል። ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ የሆነው ባህርዳር ዩኒቨርሲቲም ይህንኑ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። የማዕድን ዘርፉን ከመደገፍ አንጻር የሠራቸው በርካታ ሥራዎች እንዳሉም ተመላክቷል።
ዶክተር አሸብር ሰውአለ የባህር ዳር ዩኒቪርሲቲ እስኩል ኦፍ እርዝሳይንስ ዳይሬክተር ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እስኩልኦፍ እርዝሳይንስ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ በማዕድናና ውሃ ሀብት ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ ታስቦ ነው። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የማዕድን ዘርፍ እንደመሆኑ በተለይም በአማራ ክልል ያሉ ማዕድናት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል።
ቀደም ሲል በ2010 ዓ.ም በክልሉ የሚገኙ የኦፓል ማዕድናት በተመለከተ በአምስት ወረዳዎች ጥናት በመካሄድ ያለው የኦፓል አቅምና የጂኦሎጂካል አቀማመጥ የሚያሳይ ካርታ በመሥራቱን አሸብር (ዶክተር) ያመላክታሉ። ቀጥሎም የክልሉ ማዕድን ሀብት ለማልማት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተሠርቶ እንዳለቀ በሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት ሥራው እንደተቋረጠ ይናገራሉ።
በፍኖተ ካርታ ከተለዩት ችግሮች አንዱ በክልሉ ማዕድን ዘርፍ የመዋቅር ችግር እንደነበር አንስተዋል። የመዋቅር ችግሩን ለመፍታት የክልሉ ማዕድን የሚመራው አካል በቢሮ ደረጃ እንዲቋቋም የቀረበበት ሁኔታ ስለነበር አሁን ላይ ጥናቱ ተቀባይነት አግኝቶ የክልሉ ማዕድን ኤጀንሲ በቢሮ ደረጃ እንዲያድግ ተደርጓል። ፍኖተ ካርታው ለክልሉ ካቢኔ ቀርቦ ባይጸድቅም ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁንም ፎኖተ ካርታው አሁናዊ ሁኔታዎችን እንዲያካትት ተደርጎ ማሻሻል ተሠርቶለት የተጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡም ለሚመለከታቸው አካላት የሚቀርብ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
‹‹በፍኖተ ካርታ እንደተመላከተው የክልሉ የማዕድን ሀብት እንደሌላው ዘርፍ ባለሀብቶች ተንደርድሮ የሚገባበት አይደለም›› የሚሉት አሸብር (ዶክተር)፤ ማዕድን ማልማት በጣም አደጋ እንዳለው መገንዘብን የሚጠይቅ ነው። አደጋውም የማዕድን ሀብቱን ለማልማት የሆነ ቦታ ላይ ማዕድን አገኛለሁ ተብሎ ብዙ ኢንቨስትመንት ወጥቶበት ምንም ላይገኝ ይችላል፤ ይህም በጥንቃቄ መመራት እንዳለበት ያሳያል። የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው እንደ መንግሥት በተለይ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ተቋም የማዕድን አለኝታ ቦታዎች (minerals potential area) በመለየት ወርቅ፣ ብረት እና መሰል ማዕድናት የትኞቹ አካባቢዎች ላይ ይገኛሉ የሚለው አጥንቶ ቅድሚያ ማሳየት ይጠበቅበታል። ነገር ግን አሁን ባለው ሂደት የሀገሪቱ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ኢንስቲትዩት በብዛት ወርቅ የሚገኝባቸው ቦታዎች ላይ ብቻ ተወስኖ ነው አመላካች ካርታ የሠራው ሲሉ ያስረዳሉ።
በክልሉ ያለው የጂኦሎጂካል ካርታ በራሱ በጣም ደካማ ስለሆነ ይህ ክፍተት ለመሙላት ጥናቶች መጠናት እንዳለባቸው ያመላክታሉ። ዩኒቨርሲቲውም ከክልሉ የማዕድን ቢሮ ጋር የሚሠራቸው ሥራዎች እንዳሉ ሆነው በራሱ በጀት ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ይገልጻሉ። ቀደም ሲል ከተጀመሩት የኦፓል ማዕድን ጥናት በተጨማሪ በመርጦለማርያም አካባቢ ለሲሚንቶ ግብዓት የሚውል የድንጋይ ከሰል እና የብረት ማዕድናት ጥናት አጥንቶ ሰነዱን ለማዕድን ቢሮ ማስረከቡን ጠቅሰው፤ ቢሮውም ጥናቱን መሠረት በማድረግ በእነዚህ ዘርፍ ባለሀብቶች እንዲሠማሩበት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገርም ወንበርማ ጉመር በሚባል አካባቢ የወርቅ ማዕድን ጥናት ተካሂዷል። ጓንጓ ወረዳ ላይ የጂኦሎጂካል ካርታ ተሠርቷል። እብናት ወረዳም እንዲሁ የብረት ማዕድናት ጥናት ተካሂዷል። በአጠቃላይ በክልሉ ማዕድን ቢሮ በጀት አምሰት ፕሮጀክቶች ተሠርተዋል። እነዚህ ሦስቱን ፕሮጀክቶች በዚህ ዓመት የተጠናቀቁ ለቢሮ የተሰጡ ሲሆን የኦፓልና የመርጦለማርያም አካባቢ ጥናት በባለፈው ዓመት የተካሄዱ መሆኑን አንስተዋል።
ፕሮጀክቶቹ የተጀመሩ ከሦስትና ከሁለት ዓመት በፊት ሲሆን ተጠናቅቀው የተረከቡት ዘንድሮ ነው ያሉት አሸብር (ዶ/ር)፤ በተደረጉት ጥናቶች የማዕድን ዘርፉ ለማልማት መሠረት የሆኑ አመላካቾችን ማሳየት እንደሚያስችሉ ገልጸዋል። ለአብነትም አንድ ወረዳ ላይ አንድ ባለሀብት የወርቅ ማዕድን እንዲፈልግ ብናደርግ ወርቅ ለማጥናት በጣም ብዙ ኢንቨስትመንት፣ ሳይንሳዊ ትንታኔና ጥናትና ምርምር ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህ ደግሞ ባለሀብቱ ብዙ ወጪ አውጥቶ በዘርፉ ለመሰማራት ያለውን ፍላጎት ይቀንሳል። በመሆኑም ቅድሚያ በዘርፉ ያለውን አቅም የሚያሳይ ሳይንሳዊ ትንታኔና ጥናትና ምርምር ማድረግ የግድ ይላል።
‹‹በጂኦሎጂ ሳይንስ አንድ ማዕድን የት አካባቢ ከየትኞቹ አለቶች ጋር ሊገኝ ይችላል፤ ለምሳሌ ወርቅ ከምን አይነት አለቶች ጋር ሊገኝ ይችላል የሚለው የራሱ የሆነ ሳይንሳዊ አካሄድ አለው። ማዕድን ባለሀብት ስለሆንን ብር ስላለን ብቻ የምንሠራው ነገር ሳይሆን ሳይንሳዊ ምርምር የሚጠይቅ ነው›› ያሉት አሸብር (ዶ/ር)፤ ማዕድኑ የትኛው አካባቢ ላይ ይገኛል፤ ምን ያህል አቅም አለው የሚለው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፤ በሳይንሳዊ ምርምር ግን ወርቅ ሊገኝበት የሚችል ቦታ ማመላከት ይቻላል። አዋጭነቱን በተመለከተ ግን ሌላ ጥናት የሚጠይቅ በመሆኑ በዘርፉ ለመሠማራት የሚፈልገው ባለሀብት አዋጭነቱን አጥንቶ ማዕድን ወደ ማውጣት ለመግባት ሁኔታዎችን ቀለል ያደርጋል።
ማዕድን መኖሩ ካልታወቀ ማዕድን የማውጣቱ ሥራ አደጋ ያለውና ማዕድን ሊገኝም ላይገኝም ይችላል። ነገር ግን መጀመሪያው መንግሥት አጥንቶ አመላካች ቦታውን ካሳየ ባለሀብቱ ደግሞ ማዕድን አላቸው ተብለው የተለዩ ቦታዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይችላል። ይህም አደጋውን የሚቀንስ ይሆናል። ያም ሆኖ ማዕድን ማውጣት ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አቅምን ይጠይቃል ሲሉ አብራርተዋል።
‹‹በተለይ ማዕድን ማውጣት ላይ መሠረታዊ የሆነ ጂኦሎጂካል ካርታ ካለ ማዕድን ያለበትን ቦታ መለየት ይቻላል። በክልሉ አቅም የተለዩ ቦታዎች በአብዛኛው ትኩረት ተሠጥቷቸው የተሠሩ ሲሆን በዚህ መሰረት አመላካች ጂኦሎጂካል ካርታ መሥራት ተችሏል›› ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በራሱ በጀት በሚያሠራው የማዕድን ጥናት አማካኝነት በወሎ የማንጋኒዝ እና ቡሬ የወርቅ ማዕድናት ላይ ጥናት ያደረገ ሲሆን የጥናቱም ውጤት ለክልሉ ማዕድን ቢሮ መሰጠቱን አመላክተዋል። ‹‹ከማዕድን ቢሮ ጋር የተሻለ ግንኙነት ስላለን ብዙ ሥራዎች አብረን እየሠራን ነው። ለአብነትም በነዳጅ ማዕድን ወሎ ወረኢሉ አካባቢ ጥናት የተካሄደ ሲሆን የተገኘው ውጤት ገለጻ ተደርጎል። ዩኒቨርሲቲው እንደዚህ አይነት ተያያዥነት ያላቸው ፕሮጀክቶችን በመሥራት ለቢሮ እያቀረበ ይገኛል›› ሲሉ አስረድተዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከማዕድን ቢሮ በተደረገ ስምምነት መሠረታዊ የጂኦሎጂካል ካርታ እየተሠራ ነው። የአለቱን አይነት፣ ስርጭት እና ሁኔታን በማጥናት በዚህ መነሻነት ደግሞ በክልሉ ምን አይነት ማዕድናት ሊገኙ ይችላሉ የሚለውን ጭምር አመላካች ካርታ ይሠራል። ይህ ሥራ ለአንድ ዓመት ያህል የሚቆይ ሲሆን፤ ሥራው በየጊዜው የተለያዩ ሂደቶች መሻገር ይጠበቅበታል። አሁን ላይ በቅድሚያ የሳተላይት ምስሎች፣ ከዚህ ቀደም ከተሠሩ ሥራዎችና ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በመውሰድ ይሠራሉ። በመቀጠልም የመጀመሪያ ዳሰሳ ስራ የሚሰራ ሲሆን፤ ከዚያም በእቅዱ መሰረት በጥልቀት ያለውን ጂኦሎጂካል ካርታ ሥራ ይሠራል። በዚህ ሂደት የተገኘው ናሙና ሀገር ውስጥ የሚሠራውን ሀገር ውስጥ እንዲሠራ፤ ውጭ ሀገር የሚላከውን ወደ ውጭ አገር በመላክ ትንተናው ተሠርቶ ካለቀ በኋላ ሪፖርት በማድረግ ካርታው የሚሠራ ይሆናል።
እስካሁን የተሠራው አብዛኛው ሥራ የጂኦሎጂካል ካርታ ነው፤ በማዕድን ፍለጋ ዙሪያ የተወሰኑ ሥራዎች መሠራታቸውን አመላክተዋል። የማዕድን ጥናት የተለያየ ሂደት ስላለው ማዕድኑ ወዳለበት አካባቢን እያጠበቡ አለኝታ ወደሆነበት አካባቢ መሄድን የሚጠይቅ እንደሆነ ይገልጻሉ። ‹‹ይህም በዞኑ የወርቅ ማዕድን አለ ካልን፤ ያን የወርቅ ክምችቱ ምን ያህል ነው የሚለውንም ማየት ይቻላል›› ብለዋል።
‹‹በማንኛውም አለት ውስጥ መጠኑ በጣም ጥቂት ሊሆን ይችላል እንጂ ወርቅ አለ›› የሚሉት አሸብር (ዶ/ር)፤ ‹‹አንድን ድንጋይ ተፈጭቶ ሂደቶችን አልፎ አዋጭ የሚሆነው እንደ ገበያው የወርቅ ዋጋ ቢለያይም በአንድ ቶን አለት ውስጥ 1 ነጥብ 5 ግራም ወርቅ ካለ አዋጭ ነው ማለት ነው። ከዚህ በታች ከሆነ ያንን ወርቅ ለማውጣት የሚደረገው ጥረት አዋጭ ላይሆን ይችላል›› ሲሉ አስገንዝበዋል።
የዳሰሳ ጥናት በተደረገባቸው አካባቢዎች የማዕድን አለኝታነትና ያለውን አቅም በመለየት አመላካቾች የተጠቆሙበት ሁኔታ መኖሩን ይገልጻሉ። ለምሳሌ ወንበርማ አካባቢ በተደረገው ጥናት ወርቅ መኖሩን አመላካቾች ተገኝተዋል። ነገር ግን ምን ያህል የወርቅ ክምችት በምን ያህል ርቀት የሚለውን ለማወቅ ጥልቀት ያለው ጥናት ማድረግን ይጠይቃል። በተለይ ውድ ለሆነ እንደ ወርቅ አይነት ማዕድናት ላይ ጥልቅ ጥናት ሳይደረግ እንደዚህ አይነት ክምችት አለን ማለት እንደማይቻል አስታውቀዋል።
የጂኦሎጂካል ካርታ መሠራቱ ዋና ዓላማ ክልሉ ላይ በማዕድን ዘርፍ ለመሠማራት የሚፈልግ ባለሀብት ሲመጣ የትቦታ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚችል ለማመላከት ታስቦ ነው። ያሉት አሸብር (ዶ/ር)፤ ማዕድኑ የት ቦታ ላይ በተሻለ መልኩ ይገኛል የሚለው በሚያጠና እንደመሆኑ ጂኦሎጂካል ካርታው መሥራቱ ለክልሉ የሚሰጠው ጠቀሜታ ብዙ እንደሆነ ይናገራሉ። ሥራው ሲያልቅ ክልሉ ማዕድን አመላካች ካርታ ይኖረዋል ማለት ስለሆነ አንድ ባለሀብት የብረት ማዕድን ላይ ኢንቨስት ማድረግ እፈልጋለሁ ብሎ ቢመጣ ክልሉ የብረት ማዕድን ያለበት አካባቢ በቀላሉ በመጠቆም ባለሀብቱ ቦታው ላይ በመሄድ ጥልቅ ጥናት እንዲያደርግና አዋጭ ከሆነ እንዲሠማራበት ለማድረግ ያስችለዋል። ነገር ግን እንደዚህ አይነት ጥናቶች ከሌሉ ባለሀብቱ የት ቦታ ላይ ኢንቨስት እንደሚያደርግ ስለማያወቅ ተግዳሮት ይሆንበታል ብለዋል።
ቀደም ሲል በተሠራው ፍኖተ ካርታ እንደተመላከተው የክልሉን ማዕድን ለማወቅ የክልሉ መሠረታዊ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ አለመሥራት እንደተግዳሮት ተወስዷል። ያሉት አሸብር (ዶክተር)፤ በክልሉ ማዕድን አመላካች ለመሥራት የተሞከረ ሙከራ ቢኖርም እንኳን በደንብ ተቀናብሮ በጥናት ተደግፍ የተሠራ የክልሉ ማዕድን አመላካች ካርታ የለም። በመሆኑም ጂኦሎጂካል ካርታ መሠራቱ በዋነኛነት ይህን ክፍተት ለመሙላት ያስችላል። ሌላኛው የመዋቅር ችግር እንደነበር የተመላከተ ሲሆን፤ አሁን ላይ በተወሰነ መልኩ የተፈታበት ሁኔታ መኖሩን ይገልጻሉ።
በፍኖተ ካርታ የእውቀት ክፍተት አንዱ ተግዳሮት እንደሆነ ተመላክቷል። የእውቀት ክፍተቱን ለመሙላት በክልሉ ማዕድን ቢሮ ያሉትን ባለሙያዎች ከዩኒቨርሲቲ ጋር በማቀናጀት ልምድና እውቀት እንዲያገኙ፣ የተሠራው ሥራም በቀላሉ እንዲረዱትና እንዲተነትኑ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። በተጨማሪ የአቅም ችግር ለመቅረፍ የአጭር ጊዜ ሥልጠናዎች እና የእውቀት ሽግግር እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የማዕድን ዘርፉ ዋነኛ ዓላማ ያሉትን የማዕድን ሀብቶች ተጠቅሞ የክልሉን ሕዝብ ከድህነት ማላቀቅ ነው ያሉት አሸብር (ዶ/ር)፤ ይህም በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልግ ባለሀብት በጥናት የተደገፈ መረጃ እንዲያገኝ እድሉ መፍጠር ነው። ‹‹በአጠቃላይ ክልሉንም ሆነ ሀገር ሊያሳድግ የሚችል ኢንቨስትመንት ሲመጣ የተሟላ ሳይንሳዊ የሆነ መረጃ ማቅረብ አለብን›› ሲሉ አስገንዝበዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ለማንኛውም የማዕድን ኢንቨስትመንት መሠረታዊ ጂኦሎጂካል ካርታ መሠራት ያስፈልጋል። ጂኦሎጂካል ካርታ ካለ ባለሀብቱ ወደ ቀጣይ ሂደት በቀላሉ ሊሄድ ይችላል። እንደክልል ያለው የማዕድን ሀብት ለማወቅ ጥናት በማጥናት ስለሚያስፈልግ ዩኒቨርሲቲውም ባሉት ባለሙያዎች በመታገዝ ኃላፊነት ወሰዶ የክልሉ የማዕድን ሀብት እንዲለማ የሚያስችሉ ሥራዎች እየሠራ ነው።
ማዕድን እንደሀገር ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ በመሆኑም በክልሉ አሁን ላይ ጥሩ ጅማሮዎች አሉ የሚሉት አሸብር (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው በጥናት ሆነ በሳይንሳዊ ትንታኔም ያሉ ክፍተቶችን በመሙላት በማዕድን ኢንቨስትመንት ባዶ የነበረው መረጃ እያሟላ መሆኑን ያመላክታሉ። ‹‹ማዕድን በአንዴ ተሰርቶ የሚያልቅ ባለመሆኑ በሂደት የክልሉን ሙሉ መሠረታዊ የሆነ የጂኦሎጂካል ካርታ እና የማዕድን አለኝታ ኖሮ ለማዕድን የተመቻቸ አካባቢያዊ እንፈጥራለን›› ሲሉ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክና የምርምር ተቋማት እንደመሆኑ በላብራቶሪ በኩል ያለውን ክፍተት በመሙላት ለመደገፍ ባለፉት አራት ዓመታት ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ላብራቶሪ ማሽኖች ገዝቶ መትከል ችሏል። በቀጣይ መሠረታዊ የሚባሉትን አስፈላጊ ቁሳቁሶች እያሟላ ለማዕድን ዘርፉ መፍትሔ መስጠቱን ይቀጥላል። የክልሉ ማዕድን ሀብት በማልማት ረገድ በላብራቶሪና በጥናት ድጋፍ እያደረገ ነው።
በተጨማሪም የአጭርና የረጅም ጊዜ ሥልጠናዎች በማዘጋጀት ለባለሙያዎች ይሰጣል። እንዲሁም በአካዳሚክ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ የጂኦሎጂ ትምህርት ዘርፍ የሚሰጥ ቢሆንም ትምህርቱ ማዕድን፣ የከርሰምድር ውሃው፣ አካባቢ እና ኢንጂነሪግ ያካተተ ጠቅለል ያለ ትምህርት የሚሰጥበት ነው። በቅርቡም ሁለተኛ ዲግሪ (በማስተር ደረጃ) በማሳደግ ኢኮኖሚክ ጂኦሎጂ ዘርፍ (በሚኒራል ዲፖዚት) ዘርፍ ትምህርት እንዲሰጥ ተደርጓል። ይህም በዘርፉ የሠለጠነና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ያስችላል።
‹‹በማዕድን ዘርፉ የሚሠሩ ሥራዎች ከዩኒቨርሲቲው ዓላማ ጋር አብሮ የሚሄዱና በክልሉ የማዕድን ቢሮ ተቀባይነት ያላቸው ናቸው። እኛም እንደዩኒቨርሲቲ በምንሠራው ሥራ የሚቀበለን ስላለ ደስተኞች ነን። በእውቀትና ክህሎት፣ በአጭርና ረጅም ሥልጠናዎች እና ጥናት እና በላብራቶሪ በኩል ድጋፍ በማድረግ አገልግሎት እየሠጠን ነው›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2016