የበለፀጉ ሀገራት አሳሳቢ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመግታት የአረንጓዴ ኢኮኖሚና መሰል ስምምነቶች እንዲሁም ፖሊሲዎችን ነድፈን እየሠራን ነው ይላሉ፤ ይሁንና በተግባር ሲታይ መሬት ላይ ጠብ ያለ ነገር አይስተዋልም። እነዚህ የበለፀጉ ሀገራት የሚለቅቁት በካይ ጋዝ በማደግ ላይ የሚገኙ እንደ አፍሪካ ያሉ ሀገራትን እያሳሰበ ነው። በመሆኑም ይህን ለመቀነስ ‘‘ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና መሰል ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለመተግበር እየተንቀሳቀሱ ነው።
የጥንቱ የኢትዮጵያ ምድር 120 ሚሊዮን ሄክታር ማለትም 60 በመቶው በደን የተሸፈነ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ዲያቆን ተረፈ ወርቁ፣ “አረንጓዴ አሻራ ከዓጤ ምኒልክ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)” በተሰኘ ጽሑፋቸው እንደተየቡት ከሆነ፤ ዓፄ ምኒልክ ስለደን ሀብት ጠቃሚነት ‹‹የንጉሥ የደን ክልል›› በሚል እሳቤ አፅንዖት በመስጠት በንግሥና ዘመናቸው የመጀመሪያውን የደን ሥርዓት መሥርተው ነበር። የደን ሕግ ለማርቀቅም የውጭ አገር ባለሙያዎችን ቀጥረው ያሠሩ እንደነበር ጽሑፉ ያብራራል።
ኢትዮጵያን በደን ለማልማት ካላቸው ቀና አመለካከት የተነሣም በፍጥነት የሚያድጉ ዛፎችን ከሌሎች አገራት ያስመጡ የነበር ሲሆን፣ ሕዝቡ የተፈጥሮ የደን ሀብትን እንዲንከባከብ ያበረታቱ እንደነበር ስለንጉሡ የተጻፉ ታሪኮች ያስረዳሉ። ንጉሡ፣ የደን አጠባበቅን በተመለከተ ያወጡት ሕግ ደንን አላግባብ የሚጨፈጭፉ ሰዎች ንብረታቸውን በመውረስና እስከ ሞትም በሚያደርስ የቅጣት ርምጃ ይወሰድባቸው ነበር። ከዓፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ኢትዮጵያን የመሩ መንግሥታትም በየዘመናቸው እንደየድርሻቸው የደን ሀብትን ለመጠበቅ ሠርተዋል።
ከ15 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ‘‘ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ’’ ስትራቴጂን ቀርፃ መንቀሳቀስ የጀመረችው በአቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት ነው፣ በዘርፉ የበርካታ አገሮችን ትኩረት መሳብ ችላለች። እንደ አሜሪካ ያሉ የበለፀጉ ሀገራት ኢትዮጵያ እየተገበረችው ላለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ድጋፋቸውን እየሰጡ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
ኢትዮጵያ ሀገራችን የነደፈችውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ተከትላ በሀገር ውስጥ የምታከናውናቸው ሥራዎች የራሷን ልማትና ዕድገት የሚያፋጥኑ፣ ለዓለም ሥጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከልና አደጋዎቹን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ውሎ ያደረ ሐቅ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ መንበረ ሥልጣናቸው ከመጡ ወዲህ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በትኩረት እየተሠራ ይገኛል። አረንጓዴ ኢኮኖሚን፣ የአካባቢ ጥበቃንና የተፈጥሮ ሀብት መንከባከብን ትኩረት ያደረገ ነው። የተፈጥሮ ሀብትም ሆነ የዕፅዋቶችና የደኖች መመናመን ጉዳይ በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለው ጥፋትና ቀውስ ከፍተኛ መሆኑ ከግምት ውስጥ በመውሰድ መላው ሕዝብ ከጎናቸው በማሰለፍ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ሌጋሲን እያስቀጠሉ ነው።
ባለፈው ዓመት ‹‹በአረንጓዴ ዐሻራ›› ዘመቻ በሀገሪቱ ሁሉም ክልሎች በተደረገው የችግኝ ተከላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ትልቅ ትኩረትን የሳበ ነበር። ይህ መርሐግብር ኢትዮጵያን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ሞዴል የማድረግ እንቅስቃሴው የበርካታዎችን ይሁንታንና ድጋፍን እያገኘ መሆኑንም በስፋት እያስተዋልን ነው። ይህን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሀገር በሁሉም ዘርፍ እንድትለማ ማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ቢሆንም በግንባር ቀደምትነት የአመራሩ ድርሻ ይጠቀሳል።
“ስለደን ጥቅም እውቁ” የሥነጽሑፍ ሰው ፈቃደ አዘዘ (ዶ/ር) (1994 ዓ.ም. ጀርመን/ሀምቡርግ) በሚል የግጥም መድብላቸው፤
አንድ ዛፍ ቆርጣችሁ፣
ሁለት ካልተካችሁ፣
የተፈጥሮ ጠላት፣
የደን አሸባሪ፣
የሰው ልጅ አዋኪ፣
የተፈጥሮ ፀሯ- ነፍሰ ገዳይ ናችሁ። በማለት የሰው ልጅ ስለዛፍ ጥቅም እንዲገነዘብ ለማድረግ ሞክረዋል።
ኢትዮጵያ የያዘችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና ዝቅተኛ የካርበን ልቀት መጠን እንዲኖር የሚያደርግ ግብ ነው። ታዲያ ይህ ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ልማት እና ዕድገት የሚያቀላጥፍ፤ ዘላቂነቱን አስተማማኝ የሚያደርግ አካባቢ እንደሚፈጥር ጥናቶች ይጠቁማሉ። ተፈጥሮን ከመንከባከብና ተጠቃሚ ከመሆን በተጨማሪ ለብክለትና ለውድመት ከሚዳርጉ አደጋዎች ጠብቆ ለማቆየት ሁነኛ መፍትሔ የያዘ መሆኑ ታምኖበት እየተሠራበት ያለ ሥራ ነው።
የችግኞች ጠቀሜታ በሳይንሳዊ ትርጓሜ የሰው ልጅ የሚተነፍሰውን አየር በመቀበል መልሰው ለትንፈሳ እንደሚለቁት ይተረጉማሉ። ይህ ማለት ጤናማ ትንፈሳ እንዲኖር፣ ሕይወት እንዲቀጥልና እንዲያንሰራራ በማድረግ ኑሮ እንዲቀጥል ያስችላል። የዘርፉ ምሑራንም እንደሚያስረዱትም፤ ችግኞች ወይም ደኖች ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለፍጡራን ብሎም የሰው ልጅ ለሚጠቀምባቸው እንደ ቡና፤ አቮካዶና መሰል የአትክልትና ፍራፍሬዎች ውጤታማ መሆን አስፈላጊ ናቸው።
በኢትዮጵያ አርሶ አደሩ ማኅበረሰብ ‹‹አንድ ልጅ ስትወልድ አንድ ችግኝ ትከል›› የሚል ብሂል አለው። ይህ አባባል ችግኝ መትከል ማለት ልጅን እንደማሳደግ የሚቆጠር ነው። ልጅን ወልዶ ለቁም ነገር እስኪበቃ ወላጅ አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ ይተጋል። ችግኞችንም እንደ ልጆች መንከባከብ ሕይወትን ያስቀጥላል። አርሶ አደሮች፣ ዛፍ ሲኖር ዝናብ ሲጥል መጠጊያ እንዲሁም ፀሐይም ሲሆን መጠለያ አለፍ ሲልም ለቁሳቁስ መሥሪያ ስለሚሆኑ እንደሚንከባከቧቸው ይናገራሉ።
ችግኞችን በመትከል መንከባከብ የንጹሕ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆንን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ንጹሕ አየር በማግኘቱ ረገድ የማይተካ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን መዘንጋት አያስፈልግም። በተጨማሪም ወረርሽኝ የሆኑ በሽታዎችን ከመከላከልና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚደርሱ ጉዳቶችን በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ አላቸው። ኢትዮጵያም የዚህን አስፈላጊነት በመረዳት በትኩረት እየሠራች ትገኛለች።
ከዚህ አንጻርም የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ከ2011 ዓ.ም እስከ 2014 የተከናወነ ሲሆን፣ በእነዚህ ጊዜያት 25 ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ አረንጓዴ ውበት ብሎም ጤነኛ ዜጋ ይኖራት ዘንድ ችግኝ መትከል፣ ዕፅዋቶችን መንከባከብ፣ ደኖቻችንን ከጭፍጨፋ መከላከል ከሁሉም ሰው የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው። ስለሆነም በተያዘው ክረምት በመጪው ሰኞ የሚጀምረው 500 ሚሊዮን ችግኞች የመትከል መርሐ ግብር ላይ ሁሉም ዜጋ በኃላፊነት ችግኝ በመትከልና የተተከሉትንም በመንከባበከብ ለኢትዮጵያ አረንጓዴ ሕይወትና ውበት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል እንላለን።
በግርማ ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2016