ባለፉት 11 ወራት ለዓባይ ግድብ ከአንድ ቢሊዮን 320 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፡በበጀት ዓመቱ ባለፉት 11 ወራት ለዓባይ ግድብ ግንባታ ከአንድ ቢሊዮን 320 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡ ለግድቡ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ 19 ቢሊዮን 551 ሚሊዮን 206 ሺህ 518 ብር ተሰብስቧል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በበጀት ዓመቱ ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ከኅብረተሰብ ተሳትፎ አንድ ቢሊዮን 320 ሚሊየን 870 ሺህ 918 ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡

በበጀት ዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ባለፉት 11 ወራት አንድ ቢሊየን 320 ሚሊዮን 870 ሺህ 918 ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 66 በመቶ ማሳካት መቻሉን ጽሕፈት ቤቱ የላከው መግለጫ ያሳያል፡፡

የተሰበሰበው ገንዘብ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ10 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል፡፡ ባለፈው ግንቦት ወር ከኅብረተሰብ ተሳትፎ 106 ሚሊዮን 985 ሺህ 373 ብር መሰብሰቡን የጠቆመው መግለጫው፤ የተሰበሰበው ብር ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ10 ነጥብ አራት በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን አስታውቋል፡፡

ከኅብረተሰብ ተሳትፎ የተሰበሰበው ብር ከሀገር ውስጥ ቦንድ ስጦታ፣ ከዲያስፖራ ቦንድ ስጦታ፣ ከፒን ሽያጭ ገቢ፣ በ8100 አጭር የጽሑፍ መልዕክት እንዲሁም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የስጦታ አካውንት መሆኑን ጊዜያዊ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በላከው መግለጫ አመላክቷል፡፡

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አጠቃላይ ከተሰበሰበው 19 ቢሊዮን 551 ሚሊዮን 206 ሺህ 518 ብር ውስጥ 17 ቢሊየን 115 ሚሊዮን 836 ሺህ 526 ብር በመሰብሰብ የሀገር ውስጥ ቦንድ ሽያጭ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2016

Recommended For You