የቴክኒክና ሙያ ሳምንት መዘጋጀቱ ዘርፉ የደረሰበትን ደረጃ ለኅብረተሰቡ ለማሳየት ዕድል ፈጥሯል

አዲስ አበባ፡የቴክኒክና ሙያ ሳምንት መዘጋጀቱ ዘርፉ የደረሰበትን ደረጃ ለኅብረተሰቡ ለማሳየት ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው 14ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ሳምንት የማጠቃለያ መርሐ ግብር በትናትናው ዕለት ተካሂዷል፡፡

በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ደረጃ የኢንተርፕራይዝና ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መክብብ ወልደሃና እንደገለጹት፤ ሳምንቱ መዘጋጀት ዘርፉ የደረሰበት የቴክኖሎጂና የፈጠራ ደረጃ ለኅብረተሰቡ ለማስገንዘብና የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ትስስር ለማጠናከር ያስቻለ ነው። በዚህም የሙያ ባለቤት የሆኑ ወጣቶች የኅብረተሰቡን ችግሮች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ተነሳሽነት እንዲፈጠሩ አስችሏል፡፡

እንደ አቶ መክብብ ገለጻ፤ ቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ተወዳዳሪና የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በልዩ ትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡ በሳምንቱ የቀረቡ የፈጠራ ውጤቶች ተባዝተው የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙና ተኪ ምርቶችን በስፋት ለማምረት ተነሳሽነትን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡

የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ተደራሽ ለማድረግም በትኩረት ይሠራል ብለዋል። የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በመፍጠር የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ በቀጣይ የአቅም ግንባታ ሥራ እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡

ቴክኒክና ሙያዎች ምርታማነትን በማሳደግ በሚፈለገው ጥራት እና ብዛት፣ ተኪ እንዲሆኑና ችግር እንዲፈቱ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ምርቶቹ መሬት ላይ ካለው ችግር ጋር በማያያዝ ውጤት እንዲያመጡ ቢሮው በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡ የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በሳምንቱ የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ የዕደ ጥበብና የፋሽን ሾው ውድድሮችን ጨምሮ የተለያዩ ሁነቶች የተካሄዱ ሲሆን በከተማው የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሥራ ፈጠራ ባለቤቶች ወጣቶች ምርትና አገር በቀል ሥራዎች ለእይታ ሲቀርቡ ቆይተዋል።

ከሰኔ 15 አስከ 20 ሲካሄድ የቆየው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ከ50 ሺህ በላይ በሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጎብኝቷል። በመርሐ ግብሩ በተለያዩ ዘርፎች ተወዳድረው ያሸነፉ ባለሙያዎችና ኮሌጆች የዋንጫና የተለያዩ የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

14ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ሳምንት በከንቲባ አዳነች አቤቤ መከፈቱ የሚታወስ ሲሆን በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2016

Recommended For You