የኢትዮጵያ ባሕል ለስደተኞች የሕግ ማዕቀፍ

ስደተኝነት (refugee) ዓለም አቀፍ ጽንሰ ሀሳብ ነው:: የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛው ኮሚሽን እንደሚለው፤ ስደተኛ ማለት አንድን የተፈጠረ ችግር ለማምለጥ ሀገሩን ለቆ በመሄድ የተሻለ ሠላም ለማግኘት በሌላ ሀገር የሚኖር ማለት ነው:: በተባበሩት መንግሥታት በስደተኞች ጉዳይ ላይ እገዛ ማድረግ ከተጀመረ ከ70 ዓመታት በላይ ሆኖታል:: የስደተኞች ስምምነት (ኮንቬንሽን) በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደነገገው እና ስደተኝነት የሕግ ማዕቀፍ ያገኘው ከ73 ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1951 ነው::

ከዚህ ሁሉ በፊት ኢትዮጵያ ምን ነበረች? የሚለውን እንመልከት:: ለዚህም የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በጥር ወር 2016 ዓ.ም ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ያቀረበውን ጥናት ዋቢ አድርገናል:: ተቋሙ በተለያዩ የዲጂታል አማራጮች ያሰራጫቸውን መረጃዎችን እና የተቋሙ ባለሙያዎች ያቀረቧቸውን ጥናቶች ዋቢ አድርገን የኢትዮጵያን የስደተኞች የሕግ ማዕቀፍ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ባሕል በራሱ ለስደተኞች የሕግ ማዕቀፍ የተመቸ መሆኑን እንመልከት::

ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ ረጅም ታሪክ ያላት ሀገር ስትሆን፤ በታሪክ በማሳያነት ከሚጠቀሱት ውስጥ በ7ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ የእስልምና ተከታዮች በሃይማኖታቸው ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ በስደት መምጣታቸው አንዱ ነው:: ይህ እንግዲህ ከአንድ ሺህ 400 ምናምን ዓመታት በፊት ማለት ነው:: በሌላ በኩል በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ከእስያና ከአውሮፓ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው፣ በአፍሪካ ሀገራት በነበረው የፀረ ኮሎኒያሊዝም ትግልና የእርስ በእርስ ጦርነቶች ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ይገኙበታል::

በዚህም ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ስደተኞችን ተቀብሎ የማስተናገድና በክብር ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ታሪክ ውስጥ ያለባትን ኃላፊነት በመወጣት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከፍተኛ አድናቆትንና ተቀባይነትን አግኝታለች:: ይህ የሆነው ደግሞ የማኅበረሰቡ ሥነ ልቦና እና ባሕል ለስደተኞችና ለተገፉ ሰዎች የሚሰጠው ቦታ ጥሩ በመሆኑ ለስደተኞች ከለላ ምቹና በስደተኞችም ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል::

እዚህ ላይ የኢትዮጵያን ባሕል ልብ ብሎ ማስተዋል ያስፈልጋል:: ‹‹ቤት ለእንግዳ ነው›› የሚል የቆየ ባሕል አለ:: የሀገሬው ሰው ‹‹አልጋውን ለእንግዳ ለቆ መሬት ላይ ይተኛል›› የሚለው በተደጋጋሚ የተገለጸና የታወቀ ነው:: በሃይማኖት እና በባሕል የተገነባው ሥነ ልቦናው ይህን ለማድረግ ያስገድደዋል:: የሞራል ልዕልና ፈጥሮለታል:: ‹‹እንግዳ መጣልኝ›› የሚለው የሀገሬው ሕዝብ ሥነ ልቦና ጠንካራ ነው:: በቤቱ ውስጥ አለ የተባለውን ነገር ሁሉ ይጠቀማል:: ይህ ባሕል ነው ኢትዮጵያን በስደተኞች ተቀባይነት እንድትታወቅ ያደረጋት::

ለምሳሌ፤ በብዙ ሀገራት የዘረኝነት ጥቃቶችን እናያለን እንሰማለን:: ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ቢያንስ የራሱ የእርስ በእርስ መነቋቆርና መጋጨት ቢኖርም የሌላ ሀገር ዜጋን የማጥቃት ልማድ ግን የለም:: ይህም ከራስ በላይ ሌሎችን የማክበር ሞራል ስላለ ነው:: እርስ በእርስ መነቋቆሩ ነውር ቢሆንም፣ ልናወግዘውና ልናስወግደው የሚገባ ቢሆንም፤ የሌላን ሀገር ዜጋ የማጥቃት ልማድ ግን የለም:: በዚህ ምክንያት ነው ኢትዮጵያ በስደተኞች ተመራጭ እና ተመስጋኝ የሆነችው::

ለመሆኑ በኢትዮጵያ በየትኞቹ አካባቢዎች ስደተኞች ይበዛሉ? የሚለውን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት መረጃን ዋቢ አድርገን ስናይ፤ በድንበር አዋሳኝ አካባቢዎች ባሉት ይበዛሉ፤ ይህም ነባራዊ ሁኔታው ያደረገው ነው::

ከስድስት ወራት በፊት (ታኅሣሥ 2016 ዓ.ም) በነበረው መረጃ፤ ከፍተኛው የስደተኛ ቁጥር ያለው በጋምቤላ ክልል ሲሆን፤ 385 ሺህ 205 ስደተኞች ይገኛሉ:: ሁለተኛው የሶማሌ ክልል ሲሆን፤ 310 ሺህ 411 ስደተኞች ይገኙበታል:: ሦስተኛው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሲሆን፤ 79 ሺህ 863 ስደተኞችን ይዟል:: መረጃው የአዲስ አበባን፣ አፋር ክልልን፣ አማራ ክልልን፣ ኦሮሚያ ክልልን እና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልልን የያዘ ሲሆን ዝቅተኛውን የስደተኛ ቁጥር የያዘው የትግራይ ክልል ነው፤

2 ሺህ 37 ስደተኞችን ይዟል:: ከክልሎች በተጨማሪ ደግሞ በተበታተኑ አካባቢዎች የሚኖሩ 14 ሺህ 909 ስደተኞች አሉ:: የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ይህን መረጃ ሲሠራ ዋቢ ያደረገው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንን ነው::

ለመሆኑ ስደተኞች በብዛት ከየትኞቹ ሀገራት የሚመጡ ናቸው? የሚለውን ስንመለከት ደግሞ በብዛት ከአጎራባች ሀገራት የሚመጡ ናቸው:: ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ሲሆኑ፤ 43 በመቶ የሚሆነውን ቁጥር ይይዛሉ:: በሁለተኛ ደረጃ የሶማሊያ ስደተኞች ሲሆኑ፤ 32 በመቶ ድርሻ አላቸው:: ሦስተኞቹ ኤርትራውያን ሲሆኑ፤ 17 በመቶ ናቸው:: ከሱዳን፣ ከየመን እና ከሌሎች ሀገራት የሚመጡ ስደተኞችም ተመዝግበዋል::

አኅዛዊ መረጃዎችን ማስቀመጥ የፈለግንበት ምክንያት ነባራዊ ሁኔታውን ስለሚያሳይ ነው:: ለምሳሌ፤ ወደ ጋምቤላ የሄደ ሰው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ሲያስተውል ለምን እዚህ አካባቢ በዛ? የሚል ጥያቄ ሊፈጠርበት ይችላል:: ነባራዊ ሁኔታው ግን ለደቡብ ሱዳን አዋሳኝ ስለሆነ ነው:: በመረጃው ላይ እንደታየው የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ይበዛሉ:: ከኢትዮጵያ አካባቢዎችም በጋምቤላ ይበዛል ማለት ነው:: የዕድሜና የፆታ መረጃዎችን እንተዋቸውና ቁጥሩ ግን የሀገሬው ሰው በዓይኑ የሚያየውን እውነታ ያሳያል ማለት ነው::

ለምሳሌ፤ ብዙ ሰው የየመንና የሶሪያ ስደተኞችን በአዲስ አበባ ውስጥ ያስተውላል:: መረጃው እንደሚያሳየውም፤ ከሶርያ፣ ሊቢያ፣ ኢራቅ፣ ሊባኖስ፣ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ አፍጋኒስታን፣ ፍልስጤም፣ ጅቡቲ፣ ዮርዳኖስ የመጡ ስደተኞች ይገኛሉ::

ለእነዚህ ስደተኞች፤ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ተቋም በጋምቤላ ክልል 6፣ በትግራይ ክልል 2፣ በአማራ ክልል አንድ፣ በአፋር ክልል 2፣ ኦሮሚያ ክልል 2፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 3፣ በሶማሌ ክልል 8 እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንድ፤ በአጠቃላይ 25 የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች በማቋቋም እንዲሁም የከተማ ስደተኞችን በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች የሚኖሩ ስደተኞች ያስተዳድራል::

ኢትዮጵያ የ1951 የስደተኞች ኮንቬንሽንን እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1969 በማፅደቅ የሀገሪቱ የሕግ አካል አድርጋለች:: ነገር ግን ስምምነቱን ስታፀድቅ የመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት ዕድል እና የቅጥር ሥራ ላይ መሰማራትን በተመለከተ ገደብ አስቀምጣለች:: በተመሳሳይ የ1969 የአፍሪካ የስደተኞች ኮንቬንሽንን በመፈረምና በማፅደቅ ስምምነቱ የሚያስቀምጣቸውን የአፍሪካ የተለዩ የስደት ሁኔታዎችን የሀገሪቱ ሕግ አካል አድርጋለች::

ከላይ የተገለፁትን ዓለም አቀፍና አሕጉራዊ የሕግ ሰነዶችን በሚገባ ሥራ ላይ ለማዋል ብሔራዊ ሕግ በማውጣት ሕጋዊና አስተዳደራዊ መዋቅር በመመስረት ስደተኞችን በመቀበል፣ ደኅንነታቸውን መንከባከብና በተቻለ መጠን የዘለቄታዊ መፍትሔ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ በመሆኑ የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 409/1996 በማውጣት ስትሠራ መቆየቷ ይታወሳል::

ሆኖም አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ የስደተኞች ድጋፍ ሁኔታ ላይ ባጋጠሙ የተለያዩ ችግሮች የተነሳ የሚገኘው ድጋፍ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ በገባቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ውስጥ የተቀመጡ የስደተኞችን መብቶች በተሻለ የሚያስከብርና ከለላ የሚሰጥ እንዲሁም ለችግሮቻቸው ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ የሚያስችል በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች መሠረት የተሟላ የሕግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ፤ በአዲስ መልክ የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1110/2011 እንዲፀድቅ ተደርጓል::

አዋጁን ለማስፈፀም የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ሦስት መመሪያዎችን በሥራ ላይ እንዲውሉ ያደረገ ሲሆን፣ እነርሱም፤ ስደተኞች በሥራ ላይ የሚሰማሩበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ የአሠራር መመሪያ፣ ስደተኞች ከመጠለያ ጣቢያ ውጭ የሚንቀሳቀሱበትና የሚኖሩበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ መመሪያ እና የስደተኞች ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ መመሪያ ናቸው::

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕሪዋ ስደተኞችን በማስተናገድ ተመስጋኝ እንድትሆን አድርጓታል:: የኢትዮጵያ ባህል ሕዝቡን ሁሉ ዲፕሎማት አድርጎታል ማለት ነው::

ዋለልኝ አየለ

 አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2016 ዓ.ም

Recommended For You