አምራችነት – የኢኮኖሚው ቀኝ እጅ የኢንቨስትመንት ትከሻ

በሀገራችን የሆልቲካልቸር ኢንዱስትሪ በተቀናጀ መልኩ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከአስራስምንት ዓመታት በላይ ዕድሜን አላስቆጠረም:: በአበባው ዘርፍ የተሻለ የሚባል እንቅስቃሴ ቢኖርም የአትክልትና ፍራፍሬው ዘርፍ ግን ሀገራችን ካላት እምቅ ሀብት አኳያ በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባ ይታመናል::

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአሁኑ ጊዜ በአትክልትና ፍራፍሬ ሽያጭ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ዋጋ ከአምስት መቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኖ ተመዝግቧል:: በዚሁ ዘርፍ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ወደ ውጭ ልካ የምታገኘው ገቢ ግን ከ 50 ሚሊዮን ዶላር ያልበለጠ ነው:: ሀገራችን ለምለምና ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋዎችን የታደለች ምድር ናት:: በማህጸኗም ጥራት ያላቸው የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር እምቅ ሀብቶችን ይዛለች:: ሌሎች በወጉ ያልታደሉትን ዓመቱን ሙሉ ጸሀይ የማግኘት በረከት ርቋት አያውቅም:: በሚሊዮን የሚቆጠር አምራች ሃይልም በእጇ ነው:: ለአውሮፓና ለመካከለኛው ምስራቅ ገበያ መዳረሻ አመቺነቷም ተፈላጊና ተመራጭ ደርጋታል::

ከዚህ አኳያ ዘርፉን በስፋት መጠቀም ከቻለች የዓለም ገበያን የመቆጣጠር ዕድል በደጇ ነው:: በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት በኩል ለኢንዱስትሪው የተሰጡ ማበረታቻዎች መልካም የሚባሉ ናቸው:: ይህ እውነታም በዓለም ላይ በዘርፉ ተሠማርተው ከሚገኙ ጥቂት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንድትሆን አስችሏታል::

የኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬዎች አምራች፣ ላኪዎች ማህበር 130 አባላቶችን ይዞ የሚንቀሳቀስ ግዙፍ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ነው:: ማህበሩ በአበባ፣ አትክልት፣ በቅንጥብ አበባና ፍራፍሬ ዘርፍ አምርቶ መላክ ላይ የተሠማሩ ዓለምአቀፍ ኢንቨስተሮችን ያሳትፋል:: ከአስራኤል፣ ከኒዘርላንድ፣ ከህንድና ኢኳዶር ኢንቨስተሮች ጋር በመቀናጀት ይሠራል ::

በቅርቡ ማህበሩ በስፋት በሚንቀሳቀስባቸው የቆቃና ቢሸፍቱ የልማት ማሳያዎች ከተለያዩ ሚዲያዎች የተውጣጡ የጋዜጠኞች ቡድን በሥፍራው ተገኝቶ ጉብኝት አድርጓል:: የመጀመሪያው ቆይታ የተከወነው ቆቃ በሚገኘውና ‹‹ሬድ ፎክስ ኢትዮጵያ›› በተሰኘው ኩባንያ ነበር:: ይህን ኩባንያ ለየት የሚያደርገው በጠንካራዎቹ ሴት የሥራ መሪዎች መዘወሩ ነው:: ቀዳሚ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኩባንያው ባለፉት ዓመታት ሲመራ የቆየው በውጭ ሀገራት ዜጎች ብቻ ነበር::

የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ዮርዳኖስ ጀማል እንደሚሉት መገኛው ቆቃ ምድር ላይ የሆነው ‹‹ሬድ ፎክስ ኢትዮጵያ›› የሥራ ጅማሬ የሚነሳው እኤአ በ2003 ላይ ነው:: በጀርመናውያን ዱበን ቤተሰቦች መሥራችነት ስሩን የሰደደው ሬድ ፎክስ አርባ ሄክታር መሬትን በምርቱ በረከት ይሸፍናል::

ኩባንያው በምርት ዘመኑ ከ2500 በላይ ትጉህ ሠራተኞችን ያሰማራል:: በቋሚነትም 1 ሺህ 300 ሠራተኞች አሉት:: ሬድ ፎከስ 72 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚሸፍነው በሴት ሠራተኞቹ ጠንካራ ክንድ ነው:: በቆቃ ምድር በብዛት የሚመረተው ቅንጥብ አበባ ከዓመት እስከ ዓመት በተለየ ጥንቃቄና የአመራረት ሂደት በሰፊው የእርሻ ቦታ ተንጣሎ ይታያል::

በየዓመቱ ኩባንያው ‹‹ዱመን ኦሬንጅ›› በተባለ የእርሻ ቦታው ከ120 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ቅንጥቦችን እያመረተ ለዓለም ገበያ ያቀርባል:: አበባን ከአበባ በማዳቀል ሂደትም ውጤታማ ለመሆን የቻለ ኩባንያ ነው:: ለቅንጥብ አበባው ምርት ህልውና የውሃ ምንጭ ሆኖ የሚቀዳው የአዋሽ ወንዝ በረከት በዙሪያው ይፈሳል:: በየጊዜው ከዚህ ወንዝ የሚደርሰው ውሃ ግን እንደደረሰ ወደ እርሻው አይለቀቅም:: በወጉ ተጣርቶ፣ ታክሞ ለምርቱ አገልግሎት እንዲደርስ ይሆናል::

በኩባንያው አሠራር አንዲትም ጠብታ ውሃ አትባክንም:: ውሃን ሳይባክን መልሶ የመጠቀም ሂደት በአረንጓዴው ሥፍራ በሳይንሳዊ ሂደት በተግባር ተረጋግጧል:: በአቅራቢያው የሚገኙ ሌሎች ወንዞችን ጠልፎ መጋራትም የአገልግሎቱ ሌላው የማሳያ ግብዓት ነው ::

ከምንም በላይ በገሀድ የሚስተዋለው እውነታ ለቅንጥቦቹ ደህንነት ሲባል የሚደረገው ጥንቃቄ ነው:: በዚህ ሥፍራ ምንጊዜም ከንክኪ ነጻ የሚባል የንጽህና አጠባበቅ ሂደትን መተግበር ግድ ነው:: በምርት ቦታው ከመነሻ እስከፍጻሜው ንጹህ ሆኖ ጀምሮ ንጹህ ሆኖ ማጠናቀቅን ይጠይቃል:: ይህ እውነት ደግሞ እንደ መርህ ሆኖ በጽናት ይተገበራል::

አሁን የጋዜጠኞቹ ቡድን ወደ አረንጓዴው የአበባ ቅንጥቦች መንደር ለማምራት በዝግጅት ላይ ነው:: ወደ ዱመን ኦሬንጅ ክልል ለመግባት ግን እግሮች እንደዋዛ ጉዞ አይጀምሩም:: እያንዳንዱ ሰው ጥንቃቄ በሞላው ልዩ የንጽህና ሂደት ማለፍ ይጠበቅበታል:: ወደ ውስጥ ለመሻገር ቀድመው የተዘጋጁ ሸርጦች፣ የእጅ ጓንቶችና ነጠላ ጫማዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ:: የግል ንብረቶችም በአደራ ይቀመጣሉ::

በየቦታው በሚኖር ዝውውር እጅን እስከ ክንድ በሳሙና መታጠብና ራስን ለቅንጥቦቹ ደህንነት በወጉ ማዘጋጀት ግድ ይላል:: ወደ ውስጥ ማለፍ የሚቻለው ሞባይል ስልኮችን ጨምሮ በእጅ የሚገኙ ንብረቶች በአልኮል ታጥበውና ተጠርገው ከስጋት ነጻ መሆናቸው ሲረጋገጥ ብቻ ነው:: ይህ ልምድ በየቀኑ በሠራተኞቹ ጭምር የሚተገበር አይቀሬ ግዴታ ነው::

ምርቱ ለሽያጭ ከመድረሱ አስቀድሞ የሚያልፍባቸው የራሱ ሂደቶች አሉ:: እያንዳንዱ መስመርም ቅንጥቦቹን ከበሽታ በመከላከል፣ ንጽህናን መርህ ባደረገ ርምጃ መሀል ይጓዛል:: ሁሉም ጎብኚ በተነገረው መመሪያ መሠረት ግዴታውን በአግባቡ እየተወጣ ወደ አረንጓዴው ግዙፍ ቤት ማምራቱን ይዟል::

የጉብኝቱ ቀዳሚ እይታ የጀመረው የቅንጥቦቹ የመጀመሪያ መሠረት ወደሚጣልበት ሰፊ ማሳ ላይ ነው:: በዚህ ቦታ ቅንጥቡ ተቆርጦ በተለየ ዝግጅት ዘር ሆኖ እስከሚያወጣበት ደረጃ ያለው ሂደት ይታያል::

ቅንጥቡ ለአራት ሳምንታት ከቆየና ዘር መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ምርታማነቱ ከሚጠበቅበት የዳበረ ሥፍራ በመትከል ሊያመጣ የሚችለውን ተጠባቂ ለውጥ በባለሙያዎች መከታተል ግድ ነው:: ቅንጥቡ በቀጣዩ ሶስት ወራት በራሱ ሙሉ ሆኖና አካሉን ገንብቶ እንዲታይ ልዩ ክትትልና ቁጥጥር ይደረግለታል::

ቅንጥቡ ወደታሰበው ቁመና እንዲደርስ የተለያዩ ግብዓቶች ሊሟላለት ያስፈልጋል:: የአየር ፀባዩ ልኬታ፣ የውሃ አጠቃቀሙ ሂደት ፣ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት፣ የጸረ ቅንጣት ነፍሳት መከላከልና ሌሎችም ጥንቃቄዎች በአግባቡ ይተገበራሉ:: በየሳምንቱ በሚኖረው ክትትልም በተክሉ ላይ የሚኖሩ የአበባ ቅንጣቶች በወጉ ተስተካክለውና አምረው ዕድገታቸው ጤናማ ሆነው መታየት ይኖርባቸዋል::

ቅንጥቦቹ ለዓለም ገበያው ፍላጎትና ለደንበኞች እይታ ከነወዘናቸው ይቀርቡ ዘንድ በወጉ እየተቆረጡ ባሉበት የጥራት ደረጃ ወደ ውጭ ሀገራት ገበያ የሚላኩበት ሁኔታ ይመቻቻል:: ቅንጥቦቹ አንደ አይነትና ባህሪያቸው በተለያየ የሰው ሃይል ቁጥር የሚመረቱ ናቸው:: የምርት ሂደታቸው የሚከወነውም በተለመደው አይነት በአፈር ላይ ተክሎ በማብቀል አይደለም::

ለእያንዳንዳቸው በተዘጋጀ ልዩ የመትከያ ዕቃ፣ ያለምንም የመሬት ንክኪ በአሸዋ ላይ ቆይተው ዕድገታቸውን ይጨርሳሉ:: እንዲህ መሆኑ በተለምዶ ምርቱ በአፈር ላይ የከፋ ጉዳት ያስከትላል፣ የሚባለውን ስጋት ለመታደግ አስችሏል::

የአበባ ቅንጥቡ በምርት ደረጃ ሂደቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደውጭ ገበያ እንዲደርስ በተገቢው ሥፍራ ሊያልፍ ግድ ይለዋል:: ይህ ቦታ በሃይለኛ ድምጽ የታጀበና ልብን ሰቅዞ በሚይዝ ከባድ ቅዝቃዜ የተሞላ ነው:: በዚህ ክፍል ታሽጎ ሲዘጋጅም እያንዳንዱ ቅንጥብ የተመረተበት ጊዜ፣ ግራሙና ስያሜው ከሙሉ መረጃ ጋር በደማቅ ጽሁፍ ታትሞበት ይሆናል::

ሬድ ፎክስ ኢትዮጵያ ማህበራዊ ሃላፊነትን ለመወጣት በቆቃና አካባቢው በተለያዩ ገጽታዎች ይንቀሳቃሰል:: ለማህበረሰቡ የአጸደ ህፃናትን ጨምሮ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤቶችን በማስገንባት ተደራሽነቱን እያሳየ ነው:: በራሱ ክሊኒኮችም ትኩረቱን ኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ በማድረግ ይሠራል::

ወላጅ አልባ ለሆኑ ልጆች ከሌሎች ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርገው፤ ሬድ ፎክስ ለአካባቢ ጥበቃ ባለው ተሞክሮ ሰፊ ቦታን የሚሸፍን የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን እያለማ ቀጥሏል:: ለቀድሞ ሠራተኞቹ ድጋፍ በማድረግና ጡረታ ወጥተው መኖሪያ ለተቸገሩ ቤት በመሥራትም አርአያነቱን አስመስክሯል::

በኩባንያው የሬድ ፎክስ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ ዮርዳኖስ ጀማል እንደሚያረጋግጡት በአካካባቢው ለሚያስፈልጉ ማንኛውም የልማት ግብአቶች ድርጅቱ እስከ ሃያ ሚሊዮን ብር ወጪ በመሸፈን ማህበራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት ላይ ነው::

የጋዜጠኞቹ ቡድን የጀመረው የመስክ ጉብኝት አልተጠናቀቀም:: የቆቃው ሬድ ፎክስ ቆይታ እንዳበቃ ቀጣዩ ጉዞ ቢሸፍቱ ወደሚገኘው ‹‹ጆይ ቴክ›› ኩባንያ ጊቢ አምርቷል::

ጆይ ቴክ መገኛውን ቢሾፍቱና ለገዳዲ ላይ አድርጎ የሚሠራ ኩባንያ ነው:: በዋንኛነት ሳይንሳዊ ዘዴን ተግባራዊ በማድረግ የቲሹ ካልቸር ምርት ማባዛት ላይ ያተኩራል:: ልክ እንደ ሬድ ፎክስ ሁሉ ይህ ኩባንያም ቀድሞ በውጭ ሀገር ዜጎች ሲመራ ቆይቷል::

ወደ ኩባንያው የማምረቻ ሥፍራ ለማለፍ አሁንም የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ ግድ ነው:: ማንም ወደ ውስጥ ባለፈ ጊዜ ነጭ ካፖርት፣ መልበስ፤ ጸጉርን መሸፈንና እጆቹን በአልኮል ማጽዳት ይጠበቅበታል:: ይህን አልፈው ወደ ውስጥ ሲዘልቁ አፍንጫን በልዩ መአዛ የሚያውደው የቅጠላቅጠል ውህድ ውስጠትን ይቆጣጠራል::

ሠራተኞቹ እረፍት የለሽ ናቸው:: ቅጠሎቹን እየቀነጠሱ፣ እየከተፉ፣ እያሸጉ፣ ይጣደፋሉ:: ምርቶቹ በተለያዩ ሂደቶች አልፈው ለገበያ እስኪቀርቡ በየደረጃው አሠራራቸው ይለያያል:: ከፍተኛ በሚባል የቅዝቃዜ ቆይታም ያልፋሉ::

የጆይ ቴክ ኩባንያ ቺፍ አፊሰር ብስራት ሃይለስላሴ እንደሚሉት በአበባ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሲንቀሳቀስ የቆየው ይህ ኩባንያ በአሁኑ ጊዜ በ100 ሄክታር መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማምረት ለውጭ ሀገራት ገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል:: ጆይ ቴክ ምርቶቹን ከአውሮፓ ገበያ በዘለለ በእስካንዲቪኒያና መካከለኛ ምስራቅ ሀገራት ተደራሽ በማድረግ ኢኮኖሚውን እየደገፈ ነው::

በኩባንያው ተመርተው የሚላኩትና በተለምዶ ‹‹እፀ-ጣዕም›› ተብለው የሚታወቁት እንደ ድንብላል፣ በሶብላ፣ ጦስኝ ፣ናና ሮዝመሪኖ፣ ባሮ፣ ፐርስሊና ሌሎች ሀገር በቀል ምርቶች ባደጉት ሀገራት ገበያ በእጅጉ ተፈላጊ ሆነዋል:: ምርቶቹ የሚበቅሉት በውሃ ላይ በመሆኑ ምርታማ፣ ለምለምና ፈጣን ናቸው::

እንደ አቶ ብስራት ገለጻም እነዚህ ምርቶች በሀገራችን እንደዋንኛ ምግብ የማይቆጠሩ ናቸው:: ባደጉት ሀገራት ግን ከምግብነት ባለፈ ለማጣፈጫነትና ለመድሃኒትነት ጭምር ተፈላጊነታቸው ከፍተኛ እየሆነ ነው:: ይህ እውነታም ለውጭ ምንዛሪውና ለኢንቨስትመንቱ ድርሻ ታላቅ አበርክቶ በማድረግ ላይ ይገኛል:: በዓመትም እስከ 12 ሚሊዮን ዩሮ ማስገኘት ተችሏል::

የቲሹ ካልቸር ምርትን በማባዛት ለምግብ ዋስትናው መረጋገጥ ከፍተኛውን ሚና እየተወጣ ያለው ጆይ ቴክ አምራች አርሶደሮችን በማበረታታት ጭምር ይታወቃል:: ከ 1400 በላይ ሠራተኞችን ቀጥሮ በማሠራትም የሥራ ዕድል ፈጥሯል::

አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ የኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬዎች አምራች ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ናቸው:: የሚዲያ ባለሙያዎቹ የመስክ ጉብኝት የግብርናውን የልማት እንቅቃሴ በማረጋገጥ፣ ቴክኖሎጂንና መረጃን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ ይናገራሉ::

ከዛሬ ሃያ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ከዘርፉ ታገኘው የነበረው ገቢ ከ24 ሚሊዮን ዶላር የበለጠ አልነበረም:: በአሁኑ ጊዜ ግን ገቢው በእጥፍ በማደጉ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛውን ገቢ ማስመዝገብ ተችሏል::

መንግሥት 25 ቢሊዮን ብር በማውጣት አራት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብቷል:: ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ባለፉት አስራ አንድ ወራት በአበባ ምርት ብቻ 494 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል:: ኢትዮጵያ ካላት ዕምቅ ሀብት አኳያ ግን ይህ ገቢ በቂ ነው የማይባል በመሆኑ ኢንዱስትሪውን በማስፋት አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ይናገራሉ::

በጉብኝቱ ወቅት የጋዜጠኞችን ቡድን የተቀላቀሉት የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በዕለቱ በሰጡት ማጠቃለያ የመስክ ምልከታው አስፈላጊነት ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት በመጠቆም በጥረትና ተሳትፎ እየታየ በሀገራችን ያለውን ለውጥ ለማመላከት ነው::

እንደ ወይዘሮ ሰላማዊት ገለጻ ባለፈው ዓመት ከሆልቲካልቸር ዘርፍ ከአንድ መቶ 22 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ተችሏል:: በዘንድሮ ዓመት ለማግኘት የተቃደው 318 ሚሊዮን ኩንታል ቢሆንም በክንውኑ ግን ወደ 344 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል::

እንደ ሚኒስትር ዲኤታዋ ይህ የተሻለ አፈጻጻም ሊገኝ የቻለው በመንግሥት በኩል በተደረገው ተለየ ትኩረትና ድጋፍ ነው:: መንግሥት የግል ኢንቨስትመንቱን በማበረታታት አስተዋጽኦው ከፍ ያለ ነው:: ሚኒስትሯ ቀደም ሲል ከግል ባለሀብቶች የሚነሱ የመሬት፣ የግብዓትና የውጭ ምንዛሪ ጥያቄዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል::

እነዚህን ጨምሮ ለዘርፉ አስፈላጊ የሚባሉ ቀዝቃዛ የማጓጓዣ ግብዓቶችና ማከማቻዎች፣ የመሠረተ ልማትና የሃይል አቅርቦቶች አስፈላጊ መሆናቸውን መንግሥት እንዲገነዘብ ለማድረግ የመስክ ጉብኝቱን ወሳኝነት አጽንኦት ሰጥተውታል::

በግል ኢንቨስትመንቱ የአምራችነት ዘርፍ የሀገርን ኢኮኖሚ በአጋርነት የሚመራ ሃይል ነው:: ዘርፉ ከመንግሥት ተገቢውን ድጋፍና ይሁንታ ባገኘ ቁጥር የዓለም ገበያውን ለመምራትና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ ዕድሉ የሰፋ ይሆናል:: እንዲህ በሆነ ጊዜ ሀገራችን ለማደግ መንገዷ ይቀናል:: የመንግሥትን የድካም ትከሻ በመጋራትም የኢኮኖሚው ቀኝ እጅ ሆኖ ለመቀጠል ያግዛል::

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2016 ዓ.ም

Recommended For You