መንግሥት የዋጋ ግሽበቱንና እሱን ተከትሎ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲውን በማስተካከል፤ ነዳጅንና ማዳበሪያን በመደጎም፣ የምግብ ዘይትና መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች በፍራንኮ ቫሉታ እንዲገቡ በማመቻቸት፣ አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ ለማገናኘት የገበያ ማዕከልና የሽያጭ ቦታ በመስጠት፤ ደላላውን ሙሉ በሙሉ ባይሆን ከግብይት ሥርዓቱ በማስወጣት የተሻለ አፈጻጸም ሒደት ላይ ነው።
የቤት ኪራይ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ በማውጣት፣ የጅምላና የችርቻሮ ንግዱን ለውጭ ዜጎች በመክፈት፤ ለሸማች ሕብረት ማህበራት ተዘዋዋሪ ፈንድ በመፍቀድ አቅማቸውን በማጎልበት እያደረገ ካለው ጥረት ጎን ለጎን ፍላጎቱንና አቅርቦቱን ለማቀራረብ የበጋ፣ የኩታ ገጠምና የሜካናዝድ ግብርናን በማስፋፋት፤ አረንጓዴ ዐሻራን በመተግበር፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ነው።
ይህም ሆኖ ፤ የግብይት ሥርዓቱን ከማዘመንና እሴት ከማይጨምሩ ተዋናዮች ነጻ ከማድረግ፤ ሕገ ወጥ ኬላዎችን ከማስነሳት እና ጊዜያቸውን ያልጠበቁ የታሪፍ ማሻሻያዎች እንዲቆዩ ከማድረግ፤ ብልሹ አሠራሮችንና ሙስናን ከመከላከልና ከመቀነስ፤ ግሽበቱን ታሳቢ ያደረገ የደመወዝ ማሻሻያ ከማድረግ፤ ከሁሉም በላይ በሀገሪቱ ሰላምንና መረጋጋትን ከማስፈን አንጻር የሚስተዋሉ ክፍተቶች ከላይ የተዘረዘሩና ሌሎች ጥረቶቹን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ እያደረጉት ይገኛሉ። ሁኔታው መንግሥትንም አመድ አፋሽ እያደረገውም ይገኛል።
የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየተደራደርን ባለበት፤ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ስምምነትን ወደ ሥራ ለማስገባት እየጣርን ባለበት፤ ባንኩን፣ ንግዱን፣ ቴሌኮሙን እየከፋፈትን ባለበት፤ ለዛውም በ21ኛው ክፍለ ዘመን / በ2016 ዓ.ም በየ 10 ኪ/ሜትሩ ስለ ተዘረጉ የገመድ ሕገ ወጥ ኬላዎች መስማት ያሳፍራል። ሌላውን እናቆየውና በሸቀጦችና ምርቶች ዝውውር ወይም ሎጂስቲክ ላይ የሚፈጥሩትን ተጽዕኖ እንመልከት።
ምርት ወይም ሸቀጥ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በየኬላው እንዲቆሙ ሲደረግ ቢያንስ በሌላ የውጭ ምንዛሬ የተሸመተ ነዳጅ ይባክናል። በሚፈለጉበት ሰዓት እንዳይደርሱ ስለሚያደርጉ የመጓጓዣ ዋጋቸው ይጨምራል። ይህ አልበቃ ብሎ በየኬላው ሲቀረጡ ሌላ ተጨማሪ ወጭ ስለሚያስወጣቸው በእነዚህ መስመሮች ለማጓጓዝ ፈቃደኛ አይሆኑም። ግድ ሆኖባቸው ቢሄዱ እንኳ በዚህ መስመር የሚባክንባቸውን ጊዜ፣ ነዳጅ፣ እንግልትና ለቀረጥ የሚያወጡትን ወጪ አስልተው ስለሚጭኑ የጭነት ዋጋ በእጅጉ ያሻቅባል።
አምራቹ ምርቱን ለማስጫን ከፍተኛ ዋጋ ስለሚጠየቅ በርካሽ ለመሸጥ ይገደዳል። ነጋዴውም በበኩሉ በውድ ስለሚረከብ ሸማቹ ላይ ዋጋ ይቆልላል። ሸማቹ ለባሰ የኑሮ ውድነት ይዳረጋል። በዚህ የተነሳ የባሰ ኑሮውንም መንግሥትንም ያማርራል። ይሄን ምሬት ይዞ ደግሞ ጥሩ አገልጋይ ሊሆን አይችልም። መንግሥት ዋጋን ለማረጋጋት የሚያደርገው ጥረትም እንዲህ ባሉ ሕገ ወጥ ተግባራት ይጨናገፋሉ።
ይህንን አሁን ላይ የሚስተዋል ችግር ለመሻገር የጉምሩክ ኮሚሽን ከሚቆጣጠራቸው ኬላዎች ውጪ ያሉ ሕገ ወጥ ኬላዎች ነገ ዛሬ ሳይሉ ሊነሱ ይገባል። ምርቶችና ሸቀጦች በነጻነት መዘዋወር ካልቻሉ ዋጋን ለማረጋጋት የሚደረጉ ጥረቶች ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም።
ከዚህ ጎን ለጎን ሸማቹ፣ ሻጩም ሆነ መላ ሕዝቡ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የሚያደርገውን ጥረት ሊያግዝ ይገባል። የቤት ኪራይ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ የታለመለትን ግብ እንዳይመታ በአንዳንድ ደላላዎች አከራዮችና ተከራዮች የኪራይ ዋጋን አጋኖ የመዋዋል ጥረት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋን ይበልጥ እንዳያንረውና አዋጁን ከመንገድ እንዳያስቀረው ተሠግቷል። የዋጋ ግሽበቱንና የዜጎችን የመክፈል አቅም ያገናዘበ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ታሪፍ በአስቸኳይ ሊወጣና አጠቃላይ የኑሮ ውድነቱን የማረጋጋት ሥራ በበለጠ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሊሠራ ይገባል።
መንግሥት የሸማቹን ወገብ ያጎበጡ ሸክሞችን የሚያቀሉ ርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ነው። የችርቻሮ ንግድን ለውጭ ኩባንያዎች ለመክፈት መወሰኑ በችርቻሮ ገበያው ላይ ማርሽ ቀያሪ ነው። ሸማቹ ዋጋ አወዳድሮ፣ጥራት አማርጦ እንዲሸምት ከማስቻሉ ባሻገር አቅርቦቱን ፍጹም ያሻሽለዋል ተብሎ ይጠበቃል። በአቦሰጥ የሚመራውን የችርቻሮ ንግድም ያዘምነዋል ተብሎ ይጠበቃል።
እጥፍ ስንጥቅ ካላተረፈ የነገደ ለማይመስለው የሀገራችን ነጋዴም ትምህርት ይሆናል ተብሎ ይታመናል። ሌላው ሰሞኑን በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው ደንብ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የሕብረተሰብ ክፍል ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ የሚያደርግ ነው። ይህ በተለይ በመሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ ተጥሎ የነበረውን የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚያቀል ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አምራቹን ከሸማቹ በቀጥታ ያለ ደላላ ጣልቃ ገብነት ለማገናኘት የሚያስችሉ የመሸጫ መደብሮችን በመስጠቱና የገበያ ማዕከላትን ገንብቶ በማስረከቡ የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ የተወሰነ ቅናሽ ሊያሳይ ችሏል። አሁንም ተመልሶ የማሻቀብ አዝማሚያ እያሳየ ስለሆን ቁጥጥርና ክትትል ይፈልጋል።
ደላላ ከግብይት ሥርዓቱ ተወግዶ አምራችና ሸማች በቀጥታ ሲገናኝ እንዲሁ ሁለቱም ተጠቃሚ ስለሚሆኑ አጠናክሮ መቀጠል ያሻል። በእህልና ጥራጥሬም አምራቹን ከሸማቹ በቀጥታ መገናኘት ከተቻለ ዋጋውን ማረጋጋትና መቀነስ ይቻላል። የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ባካሄደው ጥናት ምርት ሸማቹ ጋ የሚደርሰው 58 በመቶ ተጨምሮበት ነው ይላል።
የሚገርመው ይህ ጭማሬ ከአምራቹ ሳይሆን ከደላላውና ከነጋዴው ኪስ ነው የሚገባው። የግብይት ሰንሰለቱ አምራቹንም ሆነ ሸማቹን ተጠቃሚ እያደረገ አይደለም። ለዚህ ነው የሕገ ወጥ ደላላና የስግብግብ ነጋዴ ሲሳይ ነው እየተባለ የሚተቸው። ለዚህ መንግሥት አሁንም ደላላውን ከግብይት ሰንሰለቱ የሚያስወጣ ሕግ ሥራ ላይ ሊያውል ይገባል።
በዚያ ሰሞን የግብይት ሰንሰለቱ ላይ እንቅፋት በመፍጠር የዋጋ ንረት እንዲባባስ ያደረጉ 790 ደላላዎች ላይ አስተዳደራዊ ርምጃ መወሰዱን፤ በእህልና ጥራጥሬ ፣ በአትክልትና ፍራፍሬና በቁም እንስሳት ግብይት ውስጥ የነበሩ ደላላዎችን ፈቃድ በመሰረዝ ከግብይት ሒደቱ እንዲወጡ መደረጉን፤ በቀጣይ የደላላን ጣልቃ ገብነት በዘላቂነት እልባት ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገልጾ ነበር።
እኛም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን መመሪያውን ከምን አደረስኸው ስንል እንጠይቃለን። የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አርቅቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ ከተሻሻለ በኋላ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወደ አጸደቀው ከሰኔ አንድ ጀምሮ ሥራ እየዋለ ስላለው የመኖሪያ ቤት ኪራይ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ አንድምታና አፈጻጸም እንለፍ።
የአከራይ ተከራይ አዋጁ ደግሞ ጨዋታ ቀያሪና የተከራዩን ሸክም የሚያቀልና መብቱን የሚያስከብር ነው። የነጻ ገበያ ሃዋሪያና ደቀ መዝሙር በሆኑት እንግሊዝና አሜሪካ ሳይቀር ነጻ ገበያ ስድ አይለቀቅም። ፈር ሲለቅ መንግሥታት ጣልቃ በመግባት ፈር ያሲዙታል። በዩናይትድ ኪንግደም ለንደንን ጨምሮ በዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች፣ በአውሮፓ በርካታ ሀገራት፣ በላቲን አሜሪካ እንዲሁ በርካታ ሀገራት የአከራይ ተከራይ ሕግ አላቸው።
አከራይ ከመሬት ተነስቶ ዋጋ አይጨምርም፣ ተከራይ አያስለቅቅም። ከዚህ አልፈው የኪራይ ተመንና የዋጋ ጣራ አላቸው። በመንግሥት በተለምዶ የኪቤአድና የቀበሌ ቤቶች ኪራይ ዋጋ በተወሰነ ደረጃ የዋጋ ተመን ያላቸው ሲሆኑ፣ ዋጋቸውም ከግል ቤቶች ርካሽ ነው ማለት ይቻላል። በአንጻሩ የግለሰብ ቤቶች ኪራይ ግን ስድ የተለቀቀና ተከራዩን የሚያማርር ነው። በሰበብ አስባቡ ዋጋ በየጊዜው የሚጨመርበት፣ የተከራዩን መብት የማያከብር ነው።
አከራይ እንዳሻው ኪራይ የሚጨምርበት፣ ከቤት የሚያስለቅቅበት፣ ከሁሉም በላይ ደላላ ጣልቃ እየገባ ዋጋ የሚተምንበት ተከራዩን ያማረረ ነበር። ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየጎነቆለ ያለ ቁልፍ ችግር ነበር ማለት ይቻላል። አሁን ግን ምንም እንኳ የዘገየ ቢሆን ይሄን አንገብጋቢ ችግር የሚቀርፍ አዋጅ ጸድቋል።
ከሰኔ አንድ ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ቢሆንም በአዋጁ መሠረት የከተማ አስተዳደሩ የውል ምዝገባ ማካሄድ የጀመረ ሲሆን፣ ምዝገባው በአንድ ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተመላክቷል:: ይሁንና ገና ከአሁኑ ቅሬታ እየተሰማበት ነው። በርካታ አከራዮች ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የኪራይ ዋጋ መጨመር አንችልም በማለት አሁን ከፍተኛ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ እያደረጉ መሆናቸውን ቅሬታ አቅራቢዎች ይናገራሉ:: አፈጻጸሙን ከስር ከስር በመከታተል መፍትሔ ማስቀመጥ ያሻል የሚባለው ለዚህ ነው።
መንግሥት ጣልቃ ገብቶ የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋ መናርን ለማስተካከል፣ የቤት ኪራይ ውል በሕግ እንዲመራ ለማድረግ የሚያስችለውንና በአከራይና ተከራይ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን አዋጅ፣ ባለፈው መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀደቀ። አዋጁ ‹‹የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ዓላማው ግልጽና ተገማች የሆነ የመኖሪያ ቤት ኪራይ አስተዳደር፣ እንዲሁም የአከራይና ተከራይን መብት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የሚያስተናግድ ሥርዓት ለመዘርጋት ያለመ ነው።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕጎች ከሚታወቁ ሠብዓዊ መብቶች መካከል አንዱ መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ሲሆን፣ መንግሥት የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ለማሻሻል የተለያየ ጥረት ቢያደርግም ከፍላጎቱ ጋር መጣጣም እንዳልቻለ ይታወቃል።
በቤት ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት በመጠቀምም ምክንያታዊ ያልሆነ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪዎች በሀገሪቱ ከተሞች እየተስተዋሉ መምጣታቸውን፣ በዚህም ሳቢያ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች መቸገራቸውንና ተረጋግተው ኑሯቸውን እንዳይመሩ ማድረጉን፣ በተጨማሪም የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋ መናር በከተሞች የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት እያባባሱ ከሚገኙ ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ መሆኑ፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የመንግሥት አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ሆኗል:: የኪራይ ዋጋ ጭማሪን በተመለከተም በተቆጣጣሪው አካል ከሰኔ 30 ቀን ጀምሮ ለአንድ ዓመት የፀና የዋጋ ጭማሪ እንደሚደረግ ተገልጿል::
አዋጁ ከመታተሙ በፊት ከፀደቀበት ዕለት ጀምሮ የፀና እንደሚሆን፤ አንድ የውል ዘመን ከሁለት ዓመት ሊያንስ እንደማይችል ገልጸዋል:: የቤት ኪራይ ውልና ዋጋ እንደ ክልሎች ነባራዊ ሁኔታ መወሰን እንዳለበት የተደነገገ ሲሆን፣ ይህንንም የሚቆጣጠር በክልል ደረጃ የሚሰየም አካል እንዲኖር መደረጉን፤ በዚህ መሀል በሁለቱ ወገኖች መካከል አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ጉዳዩን ተቆጣጣሪው አካል እንደሚመለከተውና ወደ ፍርድ ቤት እንደማይሄድ፤ ይህም የሆነው በመደበኛ የሕግ ሒደት ላይ ጫና እንዳይፈጠር በማሰብ መሆኑ በጸደቀበት ወቅት ተብራርቷል::
አዋጁ ስለቤት ኪራይ ሲያብራራ፣ ለመኖሪያ ቤት የሚያገለግል ከአንድ ክፍል ቤት ጀምሮ መሆኑን፣ ለአጭር ጊዜ የኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ ማለትም ሆቴል፣ ሪዞርት፣ እንዲሁም አልጋ ቤቶችን እንደሚያካትት፤ አዲስ የተገነባ ወይም ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከራይ ቤት የኪራይ ዋጋ በአከራይና በተከራይ ስምምነት የተዋዋይ ውል እንዲፀና ይደረጋል::
ተከራዩ ውሉን ማቋረጥ ቢፈልግ ከሁለት ወራት በፊት ቀድሞ ማሳወቅ እንደሚኖርበት በአዋጁ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ቤቱን ተከራይቶ ሲኖር የኪራይ ክፍያውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለ15 ቀናት ካሳለፈና ለሁለተኛ ጊዜ ለሰባት ቀናት ካሳለፈ፣ አከራዩ ውሉን ማቋረጥ እንደሚችል ተደንግጓል:: ተከራይ ሊጠየቅ የሚችለው ቅድመ ክፍያም ከሁለት ወራት የቤቱ ኪራይ ዋጋ ሊበልጥ አይችልም::
አከራዩ ቤቱን ለመሸጥ ሲፈልግ ለተከራዩ የማሳወቅ ግዴታ ባይኖርበትም፣ ቤቱን የሚገዛው ግን ውሉ እንዲቀጥል ካልፈለገ ለተከራዩ የስድስት ወራት ጊዜ መስጠት እንደሚኖርበት፣ ለአዲስ ተከራይ ሲያከራይም ከዚህ በፊት ከነበረው የኪራይ ዋጋ በላይ አድርጎ ማከራየት እንደማይችል ተደንግጓል። ነገር ግን ቤቱ የሚተላለፈው በስጦታ ከሆነ የውል ዘመኑ እስኪጠናቀቅ ድረስ ውሉ ቀጣይነት ይኖረዋል::
በሌላ በኩል ቀደም ሲል ሲከራይ የነበረ የመኖሪያ ቤት ወይም ግንባታው የተጠናቀቀ አዲስ ቤት ያለ አገልግሎት ከስድስት ወራት በላይ እንዲቀመጥ ከተደረገ፣ ቢከራይ አከራዩ ሊከፍል ይችል የነበረውን የኪራይ ገቢ ግብር ተሠልቶ እንዲከፍል ይደረጋል:: የቤት ኪራይ ክፍያን በተመለከተም በባንክ ወይም በሌላ ሕጋዊ የኤሌክትሮኒክ ዘዴ ብቻ እንዲፈጸም በአዋጁ ተደንግጓል::
አዋጁ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት የነበሩ የአከራይ ተከራይ ውሎችን የሚያስቀር አለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ አዋጁ ሲወጣ የነበረ ውል እስከ ቀጣዩ ሦስት ወራት ድረስ እንዲመዘገብ ይጠበቃል:: ይህን አዋጅ የጣሰ አከራይና ተከራይ የወንጀል ቅጣት እንደማይጣልበት፣ ነገር ግን አስተዳደራዊ ቅጣት እንደሚጣልበት ተገልጿል::
አዋጁ የአከራዩንና የተከራዩን መብት በማጣጣም የሚያስከብር ስለመሆኑ፣ በሁለቱ መካከል አለመግባባት ካለ በተቆጣጣሪው አካል በሚደረግ አስተዳደራዊ ፍትሕ የሚቀረፍ መሆኑ፤ አዋጁ የመኖሪያ ቤት ችግር በስፋት በሚስተዋልባቸው ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግ ስለመሆኑና ዝርዝር አፈጻጸሙ ግን ለከተማ መስተዳድሮችና ለክልሎች እንደሚሰጥ፤ አዋጁ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞችና የከተማ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት ያጋጠማቸውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። አፈጻጸሙ በሒደት የሚታይ ነው።
ዜጎች ከሚያገኙት ገቢ ከ25 እስከ 30 በመቶ በላይ ለቤት ኪራይ ማዋል የለባቸውም። አንድ ተከራይ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ ሳይደረግበት በተከራየው ቤት ውስጥ ለሁለት ዓመታት ያህል ተረጋግቶ መኖር እንዲችል አዋጁ መብት ይሰጠዋል::
የቀረበው አዋጅ የመኖሪያ ቤቶችን ኪራይ ብቻ የሚመለከት እንደሆነ፣ የንግድ ቤቶችን የኪራይ ዋጋና ውልን በተመለከተ በሒደት እንደሚታይ መገለጹ የሚታወስ ቢሆንም በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ላይ ላለች ሀገር ለነገ ይደር የሚባል ጉዳይ መኖር የለበትም:: አዋጁ ከመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋና የኪራይ ውል ጋር የተገናኙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ሥርዓት የሚያበጅ ከመሆኑ ባሻገር፣ መንግሥት ከቤት ኪራይ ገቢ ሊያገኝ የሚገባው የኪራይ ግብር በአግባቡ እንዲከፈል በማድረግ የከተሞችን ገቢ ለማሳደግ ያስችላል ።
ሆኖም አዋጁ ዋና የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት አባባሽ የሆነውን የንግድ ሱቅና ሕንጻ ኪራይ አለማካተቱ ሙሉኡ እንዳይሆን አድርጎታልና መንግሥት እንደገና ሊያጤነው ይገባል ስንል በአክብሮት እናሳስባለን። በተረፈ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት በዘላቂነት እንዲፈታ በማዕቀፍ ማየት ይገባል።
ሰላምን ማረጋገጥ፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ብልሹ አሠራርንና ሙስናን ማስወገድ፣ ጠንካራ የፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲን በመከተል የፋይናንስ ሥርዓቱን ማረጋጋት፣ አምራቹንና ሸማቹን ይበልጥ በቀጥታ ማገናኘት እና የሕግ የበላይነትን በተለይ በግብይት ሥርዓቱ ማስፈን ይጠይቃል።
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2016 ዓ.ም