በአማራ ክልል በሠላም ጉዳይ የተካሄደው ኮንፈረንስ ያወጣው ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ

ኢትዮጵያ ሀገራችን ረጅም ታሪክ ያላት ሀገር፣ የበርካታ ባሕል እና ቋንቋ ባለቤት፣ የነፃነትና የአንድነት ተምሳሌት፣ በገፀ ምድርና በከርሰ ምድር ሀብት የበለፀገች፣ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛና ድንቅ የባሕል እሴቶች ባለቤት መሆኗ እንደተጠበቀ ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ ሀገራችን በተለያዩ ጊዜያቶች በርካታ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲፈትኗት ቆይተዋል:: ይሁን እንጂ እነዚህን በየጊዜው የገጠሟትን ፈተናዎች በሕዝቦቿ ትብብርና አንድነት በከፍተኛ የድል አድራጊነት መንፈስ በመታገል እየተሻገረች እዚህ የደረሰች ሃገር መሆኗ ግልፅ ነው::

የአማራ ሕዝብ፣ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችን ጨምሮ ይህን የኢትዮጵያዊነት እሴት የተላበሱ ናቸው:: በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደትም ከሌሎች ወንድምና እህት ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን የራሱን አስተዋፅዖ ያበረከተ እና በርካታ ዋጋ የከፈለ ሕዝብ ነው:: ስለሆነም የሕዝቦችን የአብሮነትና የአንድነት ገመድ ለመበጣጠስ የተለያዩ ግጭቶች በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች እያጋጠሙ ቆይተዋል::

በአማራ ክልልም ገጥሞን የቆየው ችግር ለበርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ምስቅልቅሎች ዳርጎን ቆይቷል:: ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች አንፃራዊ ሠላምና መረጋጋት የተፈጠረ ቢሆንም ወደ ቀድሞ ሠላሙና ወደ ዘላቂ ልማት ለመመለስ እንዲሁም ሕዝቡ የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ በማድረግ ረገድ በርካታ ቀሪ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉን ይታወቃል::

በመሆኑም ክልሉ ሠላማዊና የተረጋጋ፣ እንደቀድሞ ታሪኩ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገትና አንድነት የድርሻውን እንድወጣ ለማስቻል ይህን የሠላም ኮንፍረንስ ያደረግን ሲሆን በውይይታችንም የተገኙ ግብዓቶች ሕዝቡ በሠላም ለመኖር ያለውን መሻት በጉልህ የተረዳንበት እንዲሁም አሉን የምንላቸውን ጥያቄዎች በግልፅ ያቀረብንበት ነው:: ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን የክልሉን ሠላም ወደነበረበት ለመመለስ ሲከፍል ለቆየው መስዋዕትነት በአማራ ሕዝብ ስም ታላቅ ክብር እየሰጠን የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ጄኔራል መኮነኖች ለነበራቸው የመሪነት ሚና ከፍተኛ ምስጋና እያቀረብን ለመላው የሀገር መከታ እና አለኝታ ለሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ያለንን አክብሮትና አድናቆት ለመግለፅ እንወዳለን::

ከሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ለተከታታይ ሁለት ቀናት በባሕር ዳር ከተማ ያደረግነውን ክልላዊ የሠላም ኮንፍረንስ አስመልክቶ ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት የጋራ ማድረጋችንን እናረጋግጣለን::

1. በሠላምና በፀጥታ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በማንነትና በራስ አስተዳደር ጉዳይ እንዲሁም ሕገመንግሥትን ስለማሻሻል አስመልክቶ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች በየፈርጃቸው ለፌደራል መንግሥትና ለክልሉ መንግሥት እንዲቀርብልን ስምምነት ላይ ደርሰናል:: ሁሉም ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ እንደማይመለሱ ስለምናምን መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት እንዲሁም በፍጥነት መመለስ ያለባቸውን ለመፍታት የሚኖረውን ዝግጁነት በጋራ እያየን እንዲሁም በሠላማዊ መንገድ እየተወያየን ጥያቄዎቹ እንዲፈቱልን መጠየቃችንን እንቀጥላለን::

2. በክልሉ ውስጥ በርካታ የልማት ጥያቄዎች መኖራቸው ይታወቃል:: እነዚህ የልማት ጥያቄዎች ያለ ሠላም ሊታሰቡ ስለማይችሉ ቅድሚያ በክልላችን ውስጥ ማንኛውም ጥያቄ በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት በውይይታችን የተስማማን መሆኑን እናሳውቃለን::

3. ለሚዲያ ተቋማትና ሙያተኞች እንዲሁም ለማኅበረሰብ አንቂዎች የክልሉ ሕዝብ በርካታ ሁለንተናዊ ችግሮች ተጋርጠውበት ቆይተዋል:: በርካታ ምስቅልቅሎችም ደርሰውበታል:: ስለሆነም ይህን ዘርፈ ብዙ ችግር ተገንዝባችሁ ሕዝቡን ወደ ሠላም የሚመልስና የክልሉ ሕዝብ ከሌሎች ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በጋራ የገነባናት ሀገር ተከባብሮና በነፃነት ተዘዋውሮ እንዲሠራባት ለማስቻል የሚዲያውን አየር በሠላም እንድትሞሉልን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን::

4. የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሑራን፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች፣ እንዲሁም መላ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፤ በክልላችን ከተፈጠረው ቀውስ በመውጣት አስተማማኝና ዘላቂ ሠላም ለመገንባት በምናደርገው ጥረት ለክልላችን ሠላም ስትሉ ሁሉንም አይነት የሠላም ድጋፍ እንድታደርጉ፣ ከመገፋፋትና ከመጠላለፍ በመውጣት ለክልሉ ሕዝብ ሠላማዊ እንቅስቃሴ በጋራ እንድትቆሙ እንጠይቃችኋለን::

5. ታጥቃችሁ ጫካ የገባችሁ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንታገልለታለን የምትሉት ሕዝብ ያለበትን ችግርና የክልሉ ሕዝብ ሕልውና እንዴት እንደተፈተነ በግልፅ ታውቃላችሁ:: ስለሆነም ጥያቄያችሁን በሠላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር እንድታቀርቡ እንዲሁም የወገናችሁን ስቃይ ለመቀነስ እንዲቻል መገዳደል ይብቃን ብላችሁ ወደ ወገኖቻችሁ እንድትቀላቀሉ የሠላም ኮንፈረንሳችን ተሳታፊ በሙሉ ወገናዊ ጥሪ እያስተላለፍን መንግሥትም ሆደ ሰፊ በመሆን እነዚህ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በመወያየት እና በመደራደር ለሕዝባችን ሠላም ሲባል በይቅርታና በክብር እንዲቀበላቸው ጥሪያችንን እናቀርባለን::

6. የክልል መንግሥታት፣ እንዲሁም የዞንና የከተማ አስተዳደሮች በምታገለግሉት ሕዝብ ውስጥ የክልላችን ተወላጆች እናንተን የመንግሥት አስተዳደሮችን እና አብሮ ለዘመናት የኖረውን ወገኖቹን አምኖ እየኖረ መሆኑን በመገንዘብ ሕዝባችን ባይተዋርነትና ብቸኝነት እንዳይሰማው፣ ጥቃት እንዳይደርስበት፤ በክልላችን ለሚኖረው ሕዝብ የጥያቄ ምንጭ እንዳይሆን እንዲሁም የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደታችንን በአስተማማኝ ሁኔታ መሠረት እንዲኖረው በጋራ እንዲንቀሳቀስ በሠላም ኮንፈረንሳችን ጥሪያችንን እያሰተላለፍን በአማራ ክልል ማንኛውም ዜጋ በብሔሩ ወይም በእምነቱ ወይም በሌሎች ምክንያቶች የማይገለልበት ክልል እንዲሆን እኛም እንደቀደመው ሁሉ እንደምንሠራ ቃል እንገባለን::

7. በክልላችን ውስጥ የምትንቀሳቀሱ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎች በማንም ይጠንሰስ ማንም ይጀምረው በክልላችን ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር ወንድም ወንድሙን እየገደለና ሕዝባችን የከፋ ችግር እየደረሰበት በመሆኑ ነው:: በመሆኑም የጀመርነው የሠላም ጥረት እንዲሳካ የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉና ከጫካ የሚመጡ ወንድሞቻችሁ ወንድም መሆናቸውን አውቃችሁ በፍፁም ሙያዊ ዲሲፕሊንና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት አቀባበል ታደርጉላቸው ዘንድ የከበረ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን::

8. በጫካ የሚገኙ ወንድሞቻችን በሠላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር ወደ ማኅበረሰቡ ከተቀላቀሉ በኋላ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ችግር በዘላቂነት ይፈታል ተብሎ በታሰበውና ተስፋ በተጣለበት የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ ያላቸውን ጥያቄ በሠላማዊ መንገድ አቅርበው የሕዝቡን ችግር በትክክለኛው መንገድ እንዲፈታ በማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሁሉም አካል የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን::

9. በክልሉ ውስጥ ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ ተጠርጥረው በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች ማለትም ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሑራን፣ እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ዜጎች በክልሉ ውስጥ ለምንገነባው ዘላቂ ሠላም የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማስቻል መንግሥት በይቅርታና በምሕረት ነፃ እንዲወጡ በማድረግ ሚናቸውንና ድርሻቸውን እንዲወጡ እንጠይቃለን::

10. በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተደረገውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሠላማዊ መንገድ ለመቋጨት መንግሥት በሆደ ሰፊነት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል:: የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የፌደራል መንግሥትና የክልላችን መንግሥት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ በሚገኙበት በዚህ ወቅት በሕወሓት በኩል ገና ከጅምሩ ጀምሮ ስምምነቱን እንደ ጊዜ መግዣ በመጠቀም የማንነት እና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ባለባቸው አካባቢዎች ወረራ በመፈፀም ላይ ይገኛል::

በመሆኑም መንግሥት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊና ተፈፃሚ እንዲሆን በማድረግ ወራሪ ኃይሎች ከወረሩበት ቦታ በፍጥነት እንዲወጡ እንዲሁም ጥያቄዎች በሠላማዊና በሕጋዊ መንገድ እልባት እንዲሰጣቸው ስንል የሠላም ኮንፈረንሳችን ይጠይቃል:: ሠላም ለኢትዮጵያ፣

ሠላም ለክልላችን

ሰኔ 18/2016 ዓ.ም

ባሕር ዳር

አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2016 ዓ.ም

Recommended For You