ክረምት’ ስርወ ቃሉ ከርም፤ ከረመ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ወርሐ ዝናም፣ ወርሐ ነጎድጓድ፣ ዘመነ ባሕር፣ ዘመነ አፍላግ፣ ዘመነ ጠል፣ ዘመነ ደመና፣ ዘመነ መብረቅ ማለት ነው። የክረምት ወቅት ከሰኔ 26 ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም 25 ቀን ድረስ መሆኑን ክረምትን የሚያትቱ መዝገበ ቃላት ያስረዳሉ።
በዘመነ ክረምት ውሃ ይሠለጥናል፣ ውኃ አፈርን ያጥባል፣ እሳትን ያጠፋል። ሆኖም ግን በብሩህነቱ ከእሳት፤ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፤ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ከሦስቱ ባሕርያት ጋር ይኖራል። ይህ ዘመን ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት ዘመን ስለሆነ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይና የሚያሳውቅ ዘመን ነው።
ዘመነ ክረምት፡- የዝናም፣ የዘርና የአረም ወቅት በመሆኑ ምድር በጠል ዝናም ትረካለች። ዕፅዋት አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር አረንጓዴ ለብሳ በሥነ ጽጌያት የምታሸበርቅበት፣ ወቅት ነው። በመሆኑም በሀገራችን ብዙው የግብርና ሥራ የሚካሄደው በዚህ ጊዜ ነው።
በተለይም በክረምቱ መግቢያ ወር በሰኔ ገበሬው ወገቡን ጠበቅ አድሮ፤ ሞፈርና ቀንበሩን አበጃጅቶና ጥንድ በሬዎቹን አጀግኖ ለሥራ ይነሳል። የሰኔ የመጨረሻዎቹ ቀናት በዚህ ወቅት ዝናምና ደመና ምድርን የሚያለመልሙበት፣ ዘር የሚዘራበት፣ የተዘራው የሚበቅልበት በፀሐይ ሐሩር የደረቁ ዛፎች ሁሉ የሚያቆጠቁጡበት ወቅት ነው።
አርሶ አደሩ ድካምና እንቅልፍን አሸንፎ ከእርሻው መሬት ጋር ይወዳጃል። በውሃ የራሰውን መሬት እየተረተረ ለእርሻ ዝግጁ እንዲሆን ያደርገዋል። በጨቀየው መሬትና ከላይ እንደጉድ በሚወርደው ዶፍ ዝናብ ሳይበገር በሬዎቹን ጠምዶ ያርሳል፤ ቀጥሎም ዘር በማሳው ላይ ይበትናል። የተዘራው ዘርም መሬትን አሸንፎ ሲወጣ ተግቶ በማረም ጥሩ ምርት ለማፈስ ቀን ከሌት ይታትራል።
ይህ ተግባር ክረምት በመጣ ቁጥር በገበሬው ዘንድ ሰርክ የሚፈጸም ሥራ ነው። ብርቱው ገበሬ የክረምትን ጨለማ አሸንፎ፤ ብርድና ውርጩን ተቋቁሞ፤ ጭቃና ዶፉን ተጋፍጦ ከራሱ አልፎ ለሀገር የሚተርፍ ምርት ያገኛል። ከራሱ አልፎም ለሌሎች መድኅን ይሆናል።
ወደ ከተሜው ስንመጣ ክረምትን የስንፍና እና የእረፍት ጊዜ ተደርጎ የሚወሰድ ነበር። ትምህርት ቤቶች ይዘጋሉ፤ አብዛኞቹ ሥራ እንቅስቃሴዎች ይቀዛቀዛሉ፤ ሁሉም ብርድና ዝናቡን ሽሽት በያለበት መሸጎጥን ይመርጣል። ስለዚህም የክረምት ሦስት ወራት ለአርሶ አደሩ የጥንካሬና የተስፋ ወራት ለከተሜው ደግሞ የእንቅልፍ ጊዜያት ሆነው ኖረዋል።
ዛሬ ግን ሁኔታዎች ተቀይረዋል። ክረምት ግም ሲል ለከተሜውም ተስፋ ይዞ መምጣት ጀምሯል። በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ክረምት ሲመጣ ምድሪቷን በአረንጓዴ ማልበስ፤ የተለያዩ የበጎ ፍቃድ ሥራዎችን ማከናወንና ነዋሪዎችን ከጎርፍ አደጋ መታደግ የመሳሰሉት ተግባራት የሚከናወኑበት ወቅት ሆኗል።
ከአምስት ዓመታት በፊት ወደ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ወደ ሥልጣን ከመጡበት ቅጽበት ጀምሮ አረንጓዴ ዐሻራን አንዱ መለያቸው አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት በአረንጓዴ ዐሻራ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ይፋ ሲያደርጉ ከልቡ የተቀበለው ጥቂቱ ነበር፤ ለመዘባበት የሚሞክሩም ብዙ ነበሩ። ሆኖም በመጀመሪያ ዓመት ብቻ ከ4 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል እንዲሁም በአንድ ጀንበር ከ569 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ዓለም አቀፍ ታሪክ መጻፍ ተችሏል።
በተወካዮች ምክር ቤት አባላትና በገለልተኛ አካላት በተደረገ ጥናትም በመንግሥት የሚደገፈው የአረንጓዴ ዐሻራ እንቅስቃሴ የቴክኒክ ኮሚቴ እንደሚለው በአውሮፓውያኑ 2019 ከተተከሉት ውስጥ 83.4 በመቶው እንዲሁም በ2020 ከተተከሉት ውስጥ ደግሞ 79 በመቶው ችግኞች ጸድቀዋል:: አምና ከተተከሉት ውስጥ ደግሞ 90 በመቶው እንደፀደቁ ይፋ ተደርጓል።
ሀገሪቱ እያከናወነችው ያለው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ሀገሪቱን በአረንጓዴ ከማልበስ በሻገር የችግኝ ተከላን ከግብርና ጋር በማቀናጀት ማካሄድ እና አቮካዶን እንዲሁም ፓፓያን የመሳሳሉ ፍራፍሬዎችን ጨምሮ የተለያዩ ችግኞች እንዲተከሉ ያስቻለ ነው። ይህ ደግሞ ሊኖረው የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። ባለፉት አምስት ዓመታት በየዓመቱ የክረምት ወራት ከ20 ሚሊዮን በላይ ሕዝቧን በማንቀሳቀስ ከ32ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋኗን ትርጉም ባለው መልኩ መለወጥ ችላለች።
የክረምቱን መግባት ተከትሎ ዘንድሮም ኢትዮጵያውያን ምድሪቱን አረንጓዴ ለማልበስ ከወዲሁ ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው። የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ቅድመ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ከቀናት በፊት ሲካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሀገሪቱ የደን ሽፋን በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ አሁን ላይ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠርም በ2030 የደን ሽፋኗን ወደ 30 በመቶ ለማድረስ አቅዳ እየሠራች ትገኛለች። በዘርፉ የተገኘው ውጤት ከሁሉም በላይ የጠንካራ አመራር ውጤት እንደሆነ ይታመናል። ሕዝብን አሳምኖ በማንቀሳቀስ የተገኘ ውጤት ነው።
ከአረንጓዴ ዐሻራ ጎን ለጎንም የክረምት ትሩፋት ከሆኑት እና እየኮራንባቸው ካሉ እሴቶቻችን መካከል የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ተጠቃሾች ናቸው። ኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ በርካታ አኩሪ እሴቶች አሏቸው። ከእነዚህ ውስጥ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶቻችን በዋነኝነት ተጠቃሾች ናቸው። ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲያጋጥሙ መሰናክሎችን በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን ከማዳበራቸውም በላይ ለተበደሉት መሸሸጊያ፤ ለተሰደዱት መጠለያ ሆነው ዘልቀዋል።
ኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲያጋጥማቸው በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን የተላበሱ ሕዝቦች ናቸው። በረሃብም ሆነ በድርቅ፤ በግጭትም ሆነ በጦርነት ወቅት በመረዳዳት አስከፊ ጊዜያቶችን አሳልፈዋል። የእምነት ልዩነት ሳይበግራቸው ደስታንም ሆነ ኅዘንን በጋራ ያሳልፋሉ። የሀገራቸውንም ዳር ድንበር ይጠብቃሉ፤ ወራሪን በጋራ ድል ይመታሉ፤ በልማት ይሳተፋሉ። ይህ አንድነታቸውን አብሮነታቸውም በበርካታ የዓለም ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ክብርና ግርማ ሞገስ አጎናጽፏቸዋል። በአርዓያነትም እንዲወሰዱ አድርጓቸዋል።
ኢትዮጵያውያን ዘር፤ ቀለምና ሃይማኖት ሳይለዩ የተቸገረን መርዳት፤ የተራበን ማብላት፤ የተጠማን ማጠጣትና የታረዘን ማልበስ ያውቁበታል። እንኳን እርስ በእራሳቸው ይቅርና ባሕር አቋርጦ፤ ድንበር ተሻግሮ ለመጣ ስደተኛ ጭምር በራቸውን ክፍት አድርገው፤ ያላቸውን አካፍለውና ፍቅር ለግሰው ማኖር የሚችሉ ሕዝቦች መሆናቸውን በርካታ የታሪክ መዛግብት የሚያወሱት ሐቅ ነው።
ይህ የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በተለይም አቅመ ደካማ ለሆኑ ዜጎች ማዕድ ማጋራትና የድሃ ቤት እድሳት በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው። በዝቅተኛ ኑሮ ሕይወታቸውን ሲገፉ የቆዩ ነዋሪዎችን ቤት በማደስ ዜጎች በተለይም በኋለኛ ዘመናቸው በተሻለ መጠለያ ውስጥ እንዲኖሩ የሚደረጉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ዛሬ የእኛነታችን መገለጫዎች እየሆኑ ነው።
በየዓመቱም ክረምት በመጣ ቁጥር የበርካታ አቅም ደካማ ዜጎች ቤቶች እየታደሱ ዜጎችን ከዝናብና ከብርድ የመታደጉ ተግባር በመንግሥት፤ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በነዋሪው ተሳትፎ እውን እየሆነ ነው። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በስፋት ከሚታይባቸውና ውጤት እየታየባቸው ካሉ አካባቢዎች ግንባር ቀደሟ አዲስ አበባ ስትሆን በየዓመቱ እስከ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በቀጥታ ተሳትፎ በማድረግ የከተማዋን ነዋሪ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያቃልሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
በ2016 ዓ.ም የበጋ ወቅት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ3 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ወገኖች በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ተነግሯል። በዚህም 11 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚገመት የልማት ሥራ በማከናወን የመንግሥትን ከፍተኛ ወጪ ማዳን እንደሚቻልም ከበጎ ፈቃድ ማስከበሪያ ቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል። አረንጓዴ ዐሻራን ጨምሮ የአረጋውያንና አቅመ ደካማ ዜጎች ቤት እድሳትና ሌሎች የልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑና በዚሁ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብርም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች በቀጥታ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ኮሚሽኑ ጠቁሟል።
በሌላም በኩል በአቅም ማነስ ምክንያት በቀን አንድ ግዜ እንኳን እራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በጋራ ማዕድ እንዲቆርሱ በማድረግ ረገድ የተጀመሩት በጎ ተግባራት የኢትዮጵያውያንን በጎ እሴቶች ማስቀጠያዎች እየሆኑ ነው። በበጎ ፈቃድ ወጣቶች ጭምር የሚከናወኑ የማዕድ ማጋራት በጎ ሥራዎችን ለተመለከተ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን መተሳሰብና መረዳዳት የሚያመላክት ነው።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ከመረዳዳትና ከመደጋገፍ ውጪ መገለጫም የላቸውም። ኢትዮጵያም ቆማ መቀጠል የቻለችው ዜጎቿ በሚከውኗቸው መልካም ተግባራት ነው። እነዚህን በጎ እሴቶች በማጠናከር ኢትዮጵያን የማጽናቱ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ክረምት ደግሞ ለዚህ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ነው።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2016 ዓ.ም