በዘመናት የተገነባ የኦሊምፒክ ወርቃማ ታሪክ እንዳይጎድፍ

ተጠባቂው የፓሪስ ኦሊምፒክ ሊካሄድ የአንድ ወር የጊዜ ርዝማኔ ብቻ ይቀረዋል። በመሆኑም በመድረኩ ሀገራትን የሚወክሉ ብሔራዊ ቡድኖች ዝግጅታቸውን ከምን ጊዜውም በላይ አጠናክረው መቀጠላቸውን መታዘብ ይቻላል። በአትሌቲክስ ስፖርት ይበልጥ ተስፋ የተጣለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በተመሳሳይ ሁኔታ ፓሪስ ላይ ለመንገስ በሚያስችለው ዝግጅት ላይ ነው። ይህ በእንዲህ ባለበት በዚህ ወቅት ኦሊምፒክን ተከትሎ በኢትዮጵያ ስፖርት የተለመደው ውዝግብ መስተዋሉ ግን አልቀረም። ኢትዮጵያን ያላስቀደመው ይህ እንቅስቃሴም ከአራት ዓመት በፊት የታየው ዓይነት አስከፊ ሁኔታ እንዳይፈጠር ያሰጋል።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ የሚመዘዘው ከኦሊምፒክ ነው። ሜልቦርን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ የሚለውን መለያ የያዘው ብሔራዊ ቡድን ተሳትፎ ተከትሎ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ውድድር ድምቀት ልትሆን ችላለች። ሻምበል አበበ ቢቂላ ባዶ እግሩን ሮጦ ዓለምን ያሸነፈበት፣ ምሩጽ ይፍጠር የአውሮፓውያንን የበላይነት ታሪክ የቀየረበት፣ ማሞ ወልዴ የማራቶን ስኬትን ያስቀጠለበት፣ ደራርቱ ቱሉ እና ፋጡማ ሮባ ለአፍሪካዊያን ሴት አትሌቶች ፈር የቀደዱበት፣ እነ ኃይሌ ገብረስላሴ ሀገርን ከክብር ማማ ላይ ያስቀመጡበት፣ ወጣቶቹ እነ ሰለሞን ባረጋ ደግሞ ለድል የሚተጉለት፣… ኦሊምፒክ መሆኑ እውን ነው።

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለአፍሪካም የኦሊምፒክ ብርሃን የሆነች ሀገር እንደመሆኗ ከኦሎምፒክ ጋር ያላት ቁርኝት ከዚህም የጠበቀ ስለመሆኑ አያጠያይቅም። ለአህጉሪቱ ተምሳሌት ከመሆን አልፋ ተጨማሪ ውጤት በምታገኝበት የኦሊምፒክ መድረክ ፓን አፍሪካኒዝምን በማቀንቀን ተሳትፎዋን ገድባ ስለጥቁር ሕዝቦች መብት ተሟግታለች። እንደ ተከበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ እና የተከበሩ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ባሉ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ብርታትም የኦሊምፒክና የአፍሪካ ስፖርት ጎዳና መቀየሱም አይካድም።

ኢትዮጵያ ረጅም ጊዜ ባስቆጠረው የኦሊምፒክ ታሪክ ተሳትፎዋ በሰበሰበቻቸው የሜዳሊያ ቁጥር ከቀዳሚዎቹ የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗም ይታወቃል። በመሆኑም የኢትዮጵያን የኦሊምፒክ ታሪክ ማጉደፍ አህጉር አቀፉንም የሚጨምር እንደሆነ መገንዘብ ያሻል።

ኢትዮጵያ ስሟ በተደጋጋሚ በተነሳበት የአትሌቲክስ ስፖርት በበርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ስኬትን ብትጎናጸፍም፤ ከሁሉ የደመቀው ታሪኳ የሚቀዳው ግን በየአራት ዓመቱ አንዴ ከሚካሄደው ታላቁ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች መድረክ ነው። ነገር ግን ኦሊምፒክ በመጣ ቁጥር ስፖርቱን ማዕከል ያላደረጉ እሰጣ ገባዎችና ውዝግቦች ከሥራ አስፈጻሚ አልፎ የቡድን ስሜትን እንዳይሸረሽሩ ያሰጋል።

በእርግጥም ከዚህ ቀደም የታዩ ክስተቶች ውጤት ላይ ተጽእኖ ያላቸው መሆኑን አስመስክረዋል፤ ሌላው ዓለም ገጽታውን ለመገንባት በሚጣጣርበት መድረክ ኢትዮጵያ ግን የተፍረከረከ ቡድንን ይዛ መቅረቧ የስፖርት ቤተሰቡን ያስቆጣ ነበር። ከዚያ ሁኔታ አለመማር ደግሞ አሁንም ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ግልጽ ነው።

እንደሚታወሰው ከአራት ዓመት በፊት ቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ ኢትዮጵያን የወከለው ቡድን ለሁለት የተከፈለ ነበር። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መካከል በተከሰተው አለመግባባት ስፖርት ወዳዱን ሕዝብ ያሳዘነ፣ የኢትዮጵያን መልካም የኦሊምፒክ ታሪክም ያጎደፈ ተግባር ታይቷል። አለመግባባቱ ሲካረርም ሕገወጥና አንገት የሚያስደፉ ተግባራት አንቱ የተባሉ ሰዎችን ጭምር ለትዝብት ዳርጓል።

የሁለቱ አካላት አለመግባባት የሃገሪቷን የስፖርት መዋቅርና አደረጃጀት ሽንቁር ቁልጭ አድርጎ ያሳየም ሲሆን፤ መንግሥታዊ አካላትም እጃቸውን ለማስገባት መገደዳቸው ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለቱ አካላት ‹‹ታርቀናል›› ብለው ቀረቡ፤ በእርግጥ እርቅ መልካም ነገር ነው። ነገር ግን ሕዝብን ባሳተፈው ተቃርኖ የተነሱ ችግሮች መፈታታቸው ባልታወቀበት ሁኔታ ስምምነት መፈጠሩ በራሱ አጠያያቂ ሆኖ ነበር።

ከአራት ዓመት በኋላ ታሪክ ራሱን ደግሞ ኦሊምፒክ ኮሚቴው የሀገሪቷን ስፖርት ከሚመራው የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ጋር የጎሪጥ መተያየታቸው ሌላኛውን ውዝግብ በማስተናገድ ላይ ይገኛል። የፓሪስ ኦሊምፒክን ቅድመ ዝግጅት በሚመለከት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሚኒስቴሩን ያገለለ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ከወራት በፊት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገልጾ ነበር።

ኮሚቴው ቅድመ ዝግጅቱን ከዓመት በፊት የጀመረ ቢሆንም እያከናወነ ያለውን ተግባር የኢትዮጵያን ስፖርት የበላይ የሆነው የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን እንደማያውቀው ነበር ያስታወቀው። ቅድመ ዝግጅትን በሚመለከት ኮሚቴው እቅዱን እንዲያቀርብ ቢጠየቅም በቂ ምላሽ ካለመስጠቱም በላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ክልሎችን ብቻ ነጥሎ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን በማግለል ከአዲስ አበባ እስከ ፓሪስ የሚል እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ነቅፎ ነበር።

ይህንን በተመለከተ ምላሽ የሰጠው ኮሚቴው መንግሥትን ያገለለ ሥራ አለመሥራቱንና ከሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር እየሠራ መሆኑን ነበር ያመላከተው። ይኸውም በቀጥታ የሥራ ግንኙነት ያለውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያካተተ አለመሆኑን አመላካች ነው። ይህ ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠሉን ኮሚቴው ስለ ሥራ እንቅስቃሴው በተለያየ ጊዜ በሚሰጠው መግለጫ ወቅት ሚኒስቴሩን ባለማካተት አሳይቷል።

ውድድሩ እጅግ በተቃረበበት በዚህ ወቅትም ልዩነቱ እየተካረረ መሆኑን የሚያመላክቱ ሁኔታዎች በግልጽ እየታዩ ናቸው። ኮሚቴው የሥራ ማሻሻያዎችን ሲያደርግም ሆነ የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ባከናወነበት ወቅት በታዛቢነት አለመገኘትን ጨምሮ ኦሊምፒክን የሚመለከት ሀገራዊ አቅጣጫ አለመሰጠቱም ይህንኑ ያጠናክራል።

ከዚህ ጋር በተገናኘ የተነሳው የሰሞኑ እሰጣ አገባም የቡድኑን ስሜት እንዳይበታተን የሚያሰጋ ነው። አትሌቶች ውጤታማ እንዲሆኑ፤ ከሚያደርጉት ዝግጅት ባለፈ የተረጋጋ አካባቢና ሁኔታ ማግኘት አለባቸው። የኢትዮጵያን ባንዲራ በክብር ለማውለብለብ እየተጉ ሌላው ደግሞ ግላዊ ጥቅምን ያስቀደመ ተግባር ላይ ማተኮሩ እንደ ዜጋ ስሜታቸውን እንደሚጎዳ አስረጂ አያስፈልገውም።

ሀገር አደጋ ሲደቀንባት ሕይወቱን ለመስጠት የማይሰስት ዜጋ፤ በሰላማዊው የፉክክር መድረክ ኢትዮጵያን አለማስቀደሙ አጠያያቂ ቢሆንም፤ ካለፈው መማርና የቀደሙትን የኦሊምፒክ ባለውለታዎች ፈር በመከተል በመልካም የሚነገር ታሪክን ማጻፍ ያስፈልጋል። ሀገር የምትመራው በሕግ እንደመሆኑ ሕግን ያከበረና እርስ በእርስ መከባበር የሰፈነበት አካሄድ መከተልም ተገቢ ነው።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You