በየትኛውም ቦታ ከሳተላይት ኢንተርኔት የምትስብ አነስተኛ ቁስ ተሠራች

የዓለማችን ቀዳሚ ባለጸጋ የሆነው ኢለን መስክ ስታር ሊንክ የተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ያለው ሲሆን ይህ ተቋም ሳተላይቶችን ወደ ህዋ በማምጠቅ በበርካታ ዓለማችን ሀገራት የኢንተርኔት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

አሁን ደግሞ ስታር ሊንክ ሚኒ የተሰኘች አነስተኛ የኢንተርኔት ኔትወርክ መሳቢያ ቁስ ለገበያ ማቅረቡን አስታውቋል።

የድርጅቱ መስራች ኢለን መስክ በኤክስ አካውንቱ እንዳለው በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ሰዎች በቀላሉ ኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙ የምታስችል ቁስ ሰርተናል ብሏል።

ይህች ቁስ የላፕቶፕ ኮምፒውተር ያክል ክብደት አላት የተባለ ሲሆን ፤በአምስት ደቂቃ ውስጥ ማብራት እና ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግም እንደሚቻል ተገልጿል።

በተለይም በጉዞ ላይ ያሉ መንገደኞች፣ ባህረኞች እና ከከተሞች ርቀው በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ዋነኛ ምርጫ ትሆናለች ተብሏል።

በቻርጅ ትሰራለች የተባለችው ይህች አነስተኛ ቁስ በአውሮፕላን ላይ ረጅም በረራ የሚያደርጉ መንገደኞች ይህችን ቁስ በማብራት አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉም ተገልጿል።

ይህች የኢንተርኔት ኔትወርክ መፈለጊያ ቁስ በአንድ ጊዜ ቻርጅ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ትሰጣለች የተባለች ሲሆን፤ በሰከንድ 100 ሜጋ ባይት ኢንተርኔት አገልግሎት እንደምትሰጥ ኢለን መስክ አስታውቋል።

አዲሷ የስታርሊንክ ተንቀሳቃሽ የኢንተርኔት አገልግሎት ቁስ በ600 ዶላር ለገበያ ቀርባለች ተብሏል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2016

 

Recommended For You