በዓለማችን ከሦስት ሕፃናት አንዱ ‘አርቆ የማየት ችግር’ እንዳለባቸው አንድ ጥናት ይፋ አደረገ

በዓለማችን ከሦስት ሕፃናት አንዱ ቅርባቸው ያለ ነገር እንጂ አርቀው ማየት እንደማይችሉ አንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሠራ ጥናት ይፋ አደረገ። አጥኚዎቹ እንደሚሉት የኮቪድ ወረርሽኝ በሕፃናት ዕይታ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሮ ያለፈ ሲሆን ሕፃናት ወጣ ብለው ከመጫወት ይልቅ ስክሪን ላይ ብዙ ሰዓት ማሳለፋቸው ጎድቷቸዋል።

ራቅ ያለ የማየት ችግር አሊያም በሳይንሳዊ አጠራሩ ማዮፒያ ዓለማችንን የሚያሰጋት ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2050 በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ይህ ችግር ሊከሰትባቸው ይችላል ሲል ጥናቱ ያስጠነቅቃል። በጃፓን ካሉ ሕፃናት መካከል 85 በመቶ፣ በደቡብ ኮሪያ 73 በመቶው እንዲሁም በቻይና እና ሩሲያ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት ማዮፒያ እንዳለባቸው ጥናቱ ይጠቁማል።

ፓራጓይ እና ዑጋንዳ አንድ በመቶ ብቻ ሕፃናት የማዮፒያ ተጠቂ ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አየርላንድ እና ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ 15 በመቶ ላይ ተቀምጠዋል። ብሪቲሽ ጆርናል ኦፍ ኦፕታልሞሎጂ የተሰኘው የሕክምና ሕትመት ላይ የወጣው ሐተታ ከስድስቱም አኅጉራት ከተውጣጡ 50 ሀገራት ያሉ ከ5 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትን በጥናቱ ዳሷል።

ከአውሮፓውያኑ 1990 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ማዮፒያ በሦስት እጥፍ መጨመሩን ቁጥሮች ያሳዩ ሲሆን ይህ የእይታ እክል ባለፉት 33 ዓመታት 36 በመቶ ጨምሯል። አጥኚዎቹ እንደሚሉት ይህ ቁጥር መጨመሩ በግልፅ መታየት የጀመረው ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ ነው።

ማዮፒያ ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው ሕፃናት ትምህርት መቅሰም ሲጀምሩ ሲሆን በተለይ የዓይን ዕድገት በሚያቆምበት 20ኛው ዕድሜ አካባቢ መባባስ ሊያሳይ ይችላል። በምሥራቅ እስያ ያሉ በርካታ ሰዎች በማዮፒያ ተጠቂ ናቸው። ለዚህ አንደኛው ምክንያቱ በዘረ-መል ሊተላለፍ የሚችል በመሆኑ ሕፃናት ከወላጆቻቸው ስለሚወስዱት ነው።

እንደ ሲንጋፖር እና ሆንግ ኮንግ ባሉ ሀገራት ደግሞ ሕፃናት ገና በልጅነታቸው መጽሐፍት አሊያም ስክሪን ላይ ስለሚያፈጡ የዓይናቸው ጡንቻ መጨማደዱ ለማዮፒያ ሊያጋልጥ እንደሚችል ጥናቱ ያመላክታል። ሕፃናት ከስድስት እስከ ስምንት ዓመት ዕድሜያቸው ትምህርት በሚጀምሩበት አሕጉረ አፍሪካ ማዮፒያ ከእስያ ሲነፃፀር ሰባት እጥፍ ዝቅ ያለ ነው።

ጥናቱ እንደሚገምተው በአውሮፓውያኑ 2050 በዓለማችን ከሚኖሩ ታዳጊዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ማዮፒያ ሊኖርባቸው ይችላል። ታዳጊ እና ወጣት ሴቶች ከታዳጊ እና ወጣት ወንዶች የበለጠ ለማዮፒያ ሊጋለጡ ይችላሉ፤ ምክንያቱም ወደ ውጭ ወጥቶ የመጫወት ዕድላቸው የጠበበ ነው ይላል ጥናቱ።

ምንም እንኳ በ2050 እስያ በማዮፒያ ከሌሎች አህጉራት በ69 በመቶ ልትበልጥ ብትችልም እያደጉ ናቸው የሚባሉ አሕጉራትም 40 በመቶ ሊደርሱ ይችላሉ ይላል። ሕፃናት በተለይ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ7-9 በሚደርስበት ወቅት በየቀኑ ቢያንስ ለሁለት ሰዓታት ወጣ ብለው ቢጫወቱ በማዮፒያ የመያዝ ዕድላቸው ይጠባል ይላሉ የዩኬ ባለሙያዎች።

ነገር ግን ልዩነት የሚፈጥረው የተፈጥሮ የፀሐይ ብርሃን ይሁን አሊያም ሕፃናት ራቅ ያለ ቁስ ለማየት የሚጠቀሙት የትኩረት መጠን ገና አልታወቀም። “ያም ሆነ ይህ ሕፃናት ወጣ ብለው መጫወታቸው ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው” ይላሉ የዩኬ ኦፕቶሜትሪስትስ ኮሌጅ ክሊኒካል አማካሪ ዳንኤል ሀርዲማን ማካርትኒ።

እንዲሁም ምንም እንኳ ቀድመው ቢመረመሩም ዕድሜያቸው ከ7-10 ያሉ ሕፃናት የዓይን ምርመራ ማድረጋቸው ተገቢ ነው ሲሉ ይመክራሉ። ቤተሰብ መርሳት የሌለበት ነገር ማዮፒያ የሚተላለፍ መሆኑን ነው። እናት ወይም አባት ማዮፒያ ካለባቸው ሕፃናት የማዮፒያ ተጠቂ የመሆን ዕድላቸው በሦስት እጥፍ ይጨምራል።

ምንም እንኳ ማዮፒያ ሕክምና ባይኖረውም በመነፅር አሊያም በኮታክት ሌንስ ሊስተካከል ይችላል። ማዮፒያ ያለባቸው ሰዎችን ዕይታ የሚያስተካክል ልዩ ሌንስ ቢኖርም ዋጋው ከፍተኛ ነው። ራቅ ያሉ ጽሑፎችን ለማንበብ መቸገር ለምሳሌ መማሪያ ክፍል ውስጥ ሰሌዳ ለማየት መቸገር፤ የኮምፒውተር ስክሪን አሊያም ተንቀሳቃሽ ስልክ በጣም ቀረብ አድርጎ መመልከት፤ ራስ ምታት እና ዓይንን ቶሎ ቶሎ ማሸት የማዮፒያ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You