ሩሲያ በምዕራባውያን ኮንቬንሽናል ሚሳኤሎች ጥቃት ከደረሰባት የኒዩክሌር መሣሪያዎቿን ለመጠቀም እንደምትገደድ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስታወቁ።
ሞስኮ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የኒዩክሌር መሣሪያዎቿን መቼና እንዴት መጠቀም እንዳለባት የሚወስነውን ሕጓን በማሻሻል ላይ መሆኗንም ነው ፕሬዚዳንቱ ያነሱት።
ፑቲን የሀገሪቱ የደህንነት ምክር ቤት ስብሰባን ሲከፍቱ የኒዩክሌር ሕጉን ማሻሻል ያስፈለገው ሞስኮ ለተደቀነባት አደጋ ምላሽ ለመስጠት ነው ብለዋል።
ማሻሻያው ኒዩክሌር ያልታጠቁ ሀገራት ከታጠቁት ጋር በመተባበር በሩሲያ ላይ ጥቃት ካደረሱ በሞስኮ ላይ “የጋራ ጥቃት” እንደከፈቱ ይቆጠራል የሚል ሃሳብ ማካተቱንም ተናግረዋል።
ሩሲያ የኒዩክሌር መሣሪያዎቿን መቼ መጠቀም እንዳለባት በግልጽ መስፈሩን በማንሳትም ከፍተኛ ድንበር አቋራጭ የሚሳኤል፣ የአየር እና ድሮን ጥቃት ከተፈጸመ ሀገራቸው አውዳሚዎቹን መሣሪያዎች መጠቀም እንደምትጀምር አብራርተዋል።
ሞስኮ አጋሯ ቤላሩስ ከተወረረች እና በኮንቬንሽናል መሣሪያዎች ጥቃት ከደረሰባት የኒዩክሌር መሣሪያዎቿን ልትጠቀም እንደምትችል መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ሩሲያ በ2020 በይፋ ያወጣችውን የኒዩክሌር ሕግ እያሻሻለች መሆኑን ያስታወቀችው አሜሪካ እና ብሪታኒያ ለዩክሬን የላኳቸው ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ለማሳሰብ ነው ተብሏል።
በአሜሪካ የሚገኙት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ረጅም ርቀት የሚጓዙትን ሚሳኤሎች በመጠቀም ሩሲያን እንድትመታ ፈቃድ እንዲሰጧቸው ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጋር ይነጋገራሉ ተብሏል።
ኬቭ ከዋሽንግተንም ሆነ ለንደን ፈቃድ ካገኘችና ሚሳኤሎችን ወደ ሞስኮ መተኮስ ከጀመረች ሶስተኛውና የኒዩክሌር ጦርነት ሊጀመር ይችላል የሚሉ ተንታኞች፥ የኬቭ አጋሮች ይህን አደገኛ ውሳኔ ያሳልፋሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ ይናገራሉ።
የዩክሬን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ አንድሪ ያምራክ ግን “ሩሲያ ዓለምን በኒዩክሌር ከማስፈራራት ውጭ አማራጭ የላትም” ሲሉ ለፑቲን ዛቻ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሩሲያ በኒዩክሌር ጦር መሣሪያ አቅም የዓለማችን ቀዳሚዋ ሀገር ናት። በዓለም ላይ ከተመረቱ የኒዩክሌር አረሮች 88 በመቶው በሩሲያ እና አሜሪካ ነው የሚገኙት።
“ኒዩክሌር የዜጎቻችን ደህንነት ለማስጠበቅም ሆነ የዓለም ሥርዓት ሚዛንን ለማስተካከል ዋነኛው አማራጭ ነው” ያሉት ፕሬዚዳንት ፑቲን፥ ምዕራባውያን ሀገራት “በእሳት እንዳይጫወቱ” አሳስበዋል ተብሏል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም