አሜሪካ እና አጋሮቿ በሊባኖስ እና እስራኤል መካከል የ21 ቀናት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሁለቱ አካላት ግጭቱን ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ መፍታት የሚችሉበትን ሁኔታ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር እንደሚያመቻች ተገልጿል።
ሀገራቱ ከሊባኖስ በተጨማሪ የጋዛው ጦርነት ላይ ተኩስ አቁም ተግባራዊ እንዲደረግ እና ወደ ግጭት ማቆም ምክክሮች እንዲገባ ነው ጥሪ ያቀረቡት።
ከ79ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን ባደረጉት ውይይት የተኩስ አቁም እንዲደረግ የጠየቁት ሀገራት አረብ ኤሜሬትስ፣ አውስትራሊያ፣ ሳኡዲአረቢያ፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ናቸው፡፡
በነጩ ቤተ መንግሥት ይፋ በተደረገው የሀገራቱ የጋራ አቋም መግለጫ ላይ በቀጣናው እያደገ የመጣው ሁሉን አቀፍ ጦርነት በአካባቢ ተጨማሪ የደህንነት ስጋት ማንገሡን ገልጾ በውጥረት ውስጥ የሚገኙ አካላት ከዚህ ድርጊት እንዲታቀቡ ጠይቋል፡፡
ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በሊባኖስ መጠኑ ከፍ ያለ የአየር ጥቃት እየፈጸመች የምትገኘው እስራኤል ከትናንት በስቲያም አጠናክራ በቀጠለችው ጥቃት 72 ሰዎች ሲገደሉ 223 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ሮይተርስ የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የእስራኤል ወታደራዊ አዛዥ በሊባኖስ የምድር ላይ ጥቃት ሊከፈት እንደሚችል ተናግረዋል። ይህም ሲፈራ የነበረውን ሁሉን አቀፍ ጦርነት የሚያስከትል ውሳኔ ሊሆን ስለሚችል ይህ ከመሆኑ በፊት ውጥረቱን ለማርገብ ነው አሜሪካ እና አጋሮቿ የተኩስ አቁም ጥሪውን ያቀረቡት፡፡
በመንግሥታቱ ድርጅት የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን ሀገራቸው ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን ለመመለክት ፈቃደኛ እንደሆነች ተናግረው በቀጣናው ሰላማዊ ድርድር እንዳይሳካ የምታበላሸው “የአካባቢው በጥባጭ” ኢራን ነች ሲሉ ከሰዋል፡፡
የኢራኑ አምባሳደር አባስ ርካቺ በበኩላቸው ኢራን በቀጣናው የሚገኘው ውጥረት ከዚህ የበለጠ እንዲሰፋ ባትፈልግም በሄዝቦላ እና እእራኤል መካከል ጦርነት ከተጀመረ ግን ቴሄራን ሄዝቦላህን እንደምትደግፍ አስረግጠው ተናግረዋል።
አሜሪካ እና አራት አጋሮቿ ያቀረቡትን የሊባኖስ ተኩስ አቁም ስምምነት ጥሪ ከመሪዎቹ ጋር እንደሚመክሩበት ይጠበቃሉ፡፡
ቴልአቪቭ ከሰኞ አንስቶ በሊባኖስ የተለያዩ አካባቢዎች እየፈጸመችው በምትገኘው የአየር ጥቃት እስካሁን ከ550 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም