የወላጆችና ሴት ልጆች ግንኙነት

አንድ ማለዳ ነበር። ከቤት ወደ ሥራ ለመሄድ በያዝኩት ትራንስፖርት ውስጥ ስለ ወላጆችና ስለ ሴት ልጆች ግንኙነት እንዳስብ ያደረገኝን ታሪክ ያደመጥኩት። አንዲት እናት ስለልጇ በስልክ የምታወራው ነገር ትኩረቴን ስቦት ሙሉ ለሙሉ አደመጥኳት።

እናቲቱ እንደምትናገረው ልጇ የክፍል ጓደኞቿ ብር ሰርቃ እንድታመጣ እያስገደዷት መቆየታቸውን፤ በዚህም የተነሳ ከቤት በተለያዩ ጊዜያት ሳንቲም እየሰረቀች ስትወስድ መቆየቷን ታወራለች። በስልክ የምታወራለት ሰው ለሚጠይቃት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ የምትሰጠው ይህች ሴት ያን እለት ግን የሚሰረቅ ነገር በማጣቷ ባዶ እጇን ክፍል እንዳትገባ ፈርታ እናቴ ታማብኝ ነው እያለች ስትለምን በፖሊሶች ቁጥጥር ስር መዋሏን ታብራራለች።

ፖሊሶች ልጅቷ በእድሜ ትንሽ መሆኗንና ሁኔታዋን አይተው በቁጥጥር ስር ካዋሏት በኋላ ለወላጅ ደወለው ስለተፈጠረው ነገር በስልክ ለወዳጇ የምታወራውን እናት ንግግር ሳደምጥ ነበር ይህች ልጅ ምን ያህል ከወላጆቿ ብትርቅ ነው ተጨንቃ ጎዳና ወጥታ እስከ መለመን የሚደርስ ፍርሃት ውስጥ የገባችው የሚል ጠያቂ ልቤ ውስጥ ተፈጥሯል። የአስራ ሶስት ዓመት ታዳጊ የሆነችው ይህች ልጅ በዚህ ልክ ተፅእኖ እስኪፈጠርባት ድረስ ወላጆቿ የት ነበሩ እያልኩ ሳሰላስል መውረጃዬ ደርሶ ከታክሲው ወረድኩ።

ስለዚህ ጉዳይ የህክምና ባለሙያ የሆኑ፤ ልጆቻቸውን አሣድገው ለቁምነገር ያበቁ ነዋሪነታቸው በአሜሪካን ሀገር ሲሆን፤ ለወገኖቼ የተወሰነ ነገር ከልምዴ ባካፍል ብለው በማህበራዊ ድረ-ገፆች መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ስልጆች አስተዳደግ መፅሃፍ የፃፉትን ወይዘሮ ሣራ ዘመኑን አነጋግረናል።

እንደ ወይዘሮ ሳራ ገለፃ ከዚህ መሠረታዊ በወላጆችና በልጆች መካከል የሚኖር መልካም ግንኙነትና ግልጽነት ለልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት መሠረት ነው። ልጆች ምን እንደሚፈልጉ፣ ምን እንደሚያስደስታቸው ማወቅ ከወላጆች ይጠበቃል። ስሜቶቻቸውንና ፍላጎቶቻቸውን በግልጽ እንዲናገሩም ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ልጆቻቸውን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ሊቀርጿቸው ይገባል። ሆኖም ልማድ፣ አመለካከትና ኑሮን ለማሸነፍ የሚደረግ ትግል በሚፈጥረው ተፅዕኖ ሳቢያ ልጆች ከትምህርት ሲስተጓጎሉ፣ ለሱስና ለወሲብ ጥቃት ሲጋለጡ፣ ጉዳያቸውን ሁሉ ሚስጥር አድርገው የሚደርሱባቸውን ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጥቃት ሲያስተናግዱ ይስተዋላሉ።

ከቤተሰባቸው ጋር ጥሩ ግንኙነትና ግልጽነት ኖሯቸውም ቤተሰባቸውን በመፍራትና በማፈር ጉዳያቸውን በተለይ ከፆታ ግንኙነት ጋር ያለውን ግልጥልጥ አድርገው ለቤተሰቦቻቸው መንገርን የማይደፍሩ፣ በአንፃሩ ደግሞ የጓደኛ ያህል ተቀራርበው የሚወያዩ ቤተሰቦችም አሉ።

ወይዘሮዋ እንደሚሉት በአንድ ወቅት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረችው የጓደኛቸው ልጅ ከወንድ ጋር ስላላት የፆታ ግንኙነት ለእናቷ የነገረችበትን ሁኔታ ሁሌም እንደምታስታውሰው ትናገራለች። ‹‹ዩኒቨርሲቲ ስማር አይቼው የወደድኩት ልጅ ነበር። ደስ ስለሚለኝ ለክፌውም አውቃለሁ። ›› ብላ ለእናቷ ተናግራለች። በወቅቱ እናቲቱ ስለጉዳዩ መስማቷ ልጇ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለማቅለል ምቹ እንዳደረገላት ትናገራለች።

እናቷ ከልጅነቷ ጀምሮ የዘረጋችላት ነገሮችን በግልጽ የመነጋገር ሥርዓት፣ ለሕይወቷ መቃናት ወሳኝ እንደነበር በመግለጽም፣ ወላጆች ልጆቻቸው በተለይ አፈቀርን፣ ተፈቀርን ወይም በፍቅር ጥያቄ የሚያስቸግረን ሰው አለ ብለው ለወላጅ ሲናገሩ ከልማድና ካለመረዳት በመነጨ ስሜት ከመቆጣት፣ እንደነውር አድርገውም ልጆቻቸውን ከማስደንገጥ ቢቆጠቡ መልካም ነው ትላለች።

ወላጆች የተቻላቸውን ያህል ግልጽ ሆነውም ልጆች ጉዳያቸውን ድብቅ የሚያደርጉበት ጊዜ ይከሰታል። አንዳንዴም ይህ ድብቅነት በአጭሩ ሊቀጭ የሚችል ችግርን ችላ አስብሎ እስከሞት ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል።

ከዚህ ቀደም የሰሙትን ታሪክ የሚያነሱት ወይዘሮ ሳራ 16 ዓመቷን ጥቅምት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ጓደኞቿና ቤተሰቦቿ በተሰበሰቡበት ያከበረችው ኖሃሚን ጥላሁን የአሥረኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን ለመፈተን የወራት ጊዜ ያህል ሲቀራት ነበር የካቲት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀኑ አሥር ሰዓት ገደማ ሜክሲኮ አካባቢ በስለት ተወግታ ሕይወቷ ያለፈው ብለዋል።

የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ሕፃን ሳለች አባቷ መሞቱንና ሕይወቷ እስካለፈበት ድረስ በብቸኝነት እንዳሳደገቻት የምትናገረው የኖሃሚን እናት ወይዘሮ ወይንሸት ወዳጆ፣ ‹‹ልጄ ደረሰች። አሁን ቀና ብያለሁ ስል ልጄ ባልጠበቅኩት ሁኔታ በሞት ተነጥቃለች፤›› ብለው እንደነበር ታስታውሳለች።

የሟች እናት እንደምትለው ኖሃሚን ረጋ ያለች ዝምተኛ ልጅ ነበረች። በመሆኑም በተለይ ዕድሜዋ ከፍ ሲል የወንድ ጓደኛ እንዳላት፣ የምትቸገረው ነገር እንዳለ በማለት ብዙ ጊዜ ትጠይቃት ነበር። ሆኖም ልጇ ‘ምን ይኖራል ብለሽ ነው?’ ከማለት ውጭ ይደርስባት የነበረ ተፅዕኖ ካለ እንኳን ነግራት እንደማታውቅ መናገሯን በማሰታወስ ወይዘሮ ሳራ ይናገራሉ።

ብዙ ጊዜ ሴቶች ጥቃት ሲደርስባቸው ስለጥቃቱ ተወርቶ ለዚህ ጥቃት ምክንያት ስለሆኑ ነገሮች ሲነሳ ብዙዎች ምክንያት የሚያነሱትን ሲያወግዙ ይሰማሉ። በተለይ ሞት ተከስቶ ከሆነ ገዳይ ፍርዱን እንዲያገኝ ከመረባረብ ውጭ ሴቶች ለጥቃት እንዳይጋለጡ ምን እንሥራ? የወላጆችና የልጆች ግንኙነት ምን መሆን አለበት? ልጆች በትምህርት ቤት ባላቸው ቆይታ ስለሚገጥሟቸው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ጉዳዮች እንዴት ግንዛቤ እንፍጠር? በትምህርት ቤት ውስጥ መደበኛውን ትምህርት ከመማር ባለፈ ስለሕይወት ክህሎት እንዴት እናስርፅ የሚሉት እምብዛም ሲወሱ አይሰማም። በመሆኑም ታዳጊ ሕፃናትም ሆኑ ወጣቶች ከልጅነታቸው ጀምሮ ኃላፊነት ሊሰማቸው ሲገባ ለሱስ፣ ላልተፈለገ የወሲብ ጥቃት ሲጋለጡ ከትምህርታቸው ሲስተጓጎሉ ብሎም በእከሌ ተገደሉ ሲባል ይሰማል።

‹‹ለልጆቻችን የተቃና ሕይወት መሠረት ለመጣል እኛ ያለፍንበት የበዛ ፍርሃትና ድብብቆሽ ወይም ጓዳ መደበቅ ጊዜ አልፎበታል›› የሚሉት ሌላው ያነጋገርናቸው አባት አቶ ይትባረክ ሃይሌ ናቸው። እኚህ አባት ጥሩ አዳማጭ ሆነው ከልጆቻቸው ጋር በግልጽ እንደሚወያዩ ይናገራሉ።

በቤተሰብና በልጆች መካከል ያለው ግንኙነት እየቀነሰ፣ መደበኛውን ትምህርት የሚወስደው ጊዜ እየበዛ፣ ወላጆችም የቤተሰብ ፍላጎት ለመሙላት እየተሯሯጡ ባሉበት ጊዜ፣ ልጆች ከወላጅ ይልቅ ጓደኞቻቸውንና ውጭ የሚያዩትን እንደሚመስሉ በማስታወስ፣ በራሳቸው በኩል ልጆቻቸውን እንደ ጓደኛ በማድረግ ከትምህርት ባለፈ ስለፆታ ግንኙነትና በአፍላ ዕድሜ ስለሚከሰቱ ባህሪያት በግልጽ እንደሚወያዩ ይገልጻሉ።

‹‹የልጆች ባህሪ ድንገት ይለወጣል። ትላናት ጥያቄ ስትጠይቂው የነበረው ልጅሽ ዛሬ ላይ ሊቆጣሽ ይችላል። በመሆኑም ቁጣውን ምን አመጣው? ቤት ውስጥ ምን ተፈጥሮ ነበር? ትምህርት ቤትስ? የዕድሜው ጉዳይ ነው ወይስ ሌላ? ብሎ ወላጅ የልጁን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መከታተል አለበት›› ሲሉም ይመክራሉ።

ቤት ውስጥ ቁጣ የሚበዛባቸው ልጆች ፈሪና ድብቅ እንደሚሆኑ በማስታወስም ወላጆች በተለይም ልጆቻቸው ለአቅመ ሔዋን ሲደርሱ የሚያሳዩዋቸውን ባህሪዎች በመከታተል በግልጽና በትዕግሥት ሊያዳምጧቸውና ሊረዷቸው ይገባል ይላሉ።

ወላጆች በሕይወት ዘመናቸው ክፉውንም ሆነ ደጉን ብሎም የማኅበረሰብ ተፅዕኖን አልፈው ልጆች ለመውለድና ለማሳደግ እስከበቁ ድረስ፣ ልጆቻቸው በአካልም ሆነ በአዕምሮ እንዲበለፅጉ ከልምዳቸው እያካፈሉ ሊያድኗቸው ይገባል ሲሉም ያክላሉ።

በሥነ ልቦና ፍልስፍና፣ በልጆች አስተዳደግ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ስምንት ዓመታት ወሳኝ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። እንደ መረጃው ባህሪና አመለካከት ተቀርፆ የሚያልቀውም በእነዚህ ዕድሜ ውስጥ ነው። ከዚህ በኋላ ያለው የማሰማመርና የመቀባባት ያህል ነው።

ልጆች እስከ ስምንት ዓመታቸው በባህሪ ሳይታነጹ ቀርተው፣ ከጎረመሱ በኋላ የሚያሳዩትን ባህሪ በምን መልኩ ማረቅ ይቻላል የሚለው ሊነሳ ይችላል። ወላጆች በጉርምስና ጊዜ ሳይሆን እስከ ስምንት ዓመት ባለው ዕድሜ ውስጥ ሥራቸውን መሥራት እንደሚገባቸው ይመክራሉ። ሆኖም ወላጆች እዚህ ላይ ያላቸው ግንዛቤ በቂ ስላልሆነ ይህንን አያደርጉትም።

ልጆችና ወላጆች አብረው የሚቀመጡበት ሳይሆን የሚለያዩበት ጊዜ ይበልጣል። ሆኖም በቤት ውስጥ ቢያንስ ለእራት አብሮ መቀመጥ ያስፈልጋል። ይህም ከልጆች ጋር ስለውሏቸው ለማውራት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል። ሆኖም በእንደዚህ ዓይነት መድረክ ልጆች ስለማፍቀርና መፈቀር ሲያነሱ እንደነውር ቆጥረው የሚያስደነግጡ ቤተሰቦች አሉ።

ከአሥር ዓመት ጀምሮ በሴቶች የጡት ማጎጥጎጥ፣ በመራቢያ አካላት ስፍራ ፀጉር ማብቀል የዳሌ መስፋት ሲጀምሩ፣ በወንዶች ደግሞ የድምፅ መጎርነን፣ ጡንቻ የማውጣትና በሰውነት ላይ ፀጉር መታየት ይጀምራል። እነዚህ ክስተቶች የሆርሞን ለውጥ ስለሚያመጡ የተለየ አስተሳሰብና አመለካከት ይመጣል። ይህ ሴቶች ወደ ወንዶች ወንዶችም ወደ ሴቶች እንዲመለከቱ ያደርጋል። ማፍቀርና መፈቀርም ይፈጠራል።

ልጆች ስለነዚህ ክስተቶች አውቀውና ዝግጁ ሆነው ቢያድጉ ቢያፈቅሩም፣ ቢፈቀሩም የፍቅር ጥያቄ ቢቀርብላቸውም አይደነግጡም። እንዴት መወጣት እንደሚችሉም ያውቃሉ። ከልጅነታቸው ያልተቀረፁት ደግሞ ወዳልተፈለገ ዕርምጃ ይገባሉ። ስለሆነም ወላጆች ልጆቻቸው ተፈጥሯዊ ክስተቶች ሲያጋጥሟቸው ከመጮህና ከመቆጣት ይልቅ ሊመክሯቸው ይገባል። ይህ ካልሆነ ልጆች ችግራቸውን ይደብቃሉ ያፍናሉ። ይህ የተዳፈነ ስሜትም በምክር ሊፈታ የሚችል ጉዳይን ወደ መጥፎ ይለውጠዋል።

ልጆችን በግልጽ አወያይቶና ኃላፊነት እንዳለባቸው ነግሮ የማሳደጉን ሰፊ ድርሻ ወላጆች ቢወስዱም በትምህርት ቤት ውስጥ የሚኖረው ሁኔታም ወሳኝ ነው። በመሆኑም ከወላጆች ኃላፊነት ጎን ለጎን የሥርዓተ ፆታ ትምህርት በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ራሱን ችሎ መካተት አለበት ይላሉ። የውጭ ሀገሮች ተማሪዎችም የሥርዓተ ጾታ ትምህርትን በሥርዓተ ትምህርቱ ተካቶላቸውና የራሱ ፕሮግራም ተበጅቶለት ይማሩታል።

ይህ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን በመራዳት የሥርዓተ ፆታ ትምህርት በአብዛኛው በሥነ ሕይወት ትምህርት ውስጥ ተካቶ ለተማሪዎች የሚቀርብ ቢሆንም፣ በመደበኛው ትምህርት ፈተና ለማለፍ ካልሆነ በስተቀር የሕይወት ክህሎት የሚያስጨብጥ አይደለም። ስለሆነም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

በየትምህርት ቤቶች ያሉ የሥነ ልቦና አማካሪዎች በምን መልኩ ይሠራሉ? አሉስ ወይ? ምን ያህልስ ወደ ተማሪዎች ይቀርባሉ? የሚለውም ሌላው መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ትውልድ መቅረፅ የሁሉም ሃላፊነት በመሆኑ ወላጅ ማህበረሰብ ትምህርት ቤት በአንድነት የተቀናጀ ሥራ ሲሠሩ ራሷን የምታውቅ በጥንካሬ የሚታድግ ሴት ልጅ እንድትኖረን ይሆናል።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2016

Recommended For You