ለውጭ ባለሀብት በር መክፈት – ለኢኮኖሚ መነቃቃት

መንግሥት ለበርካታ ዓመታት የአስመጪነቱንም ሆነ የላኪነቱን ሚና ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ትቶ መቆየቱ የሚታወስ ነው። በተለይም በፋይናንስ ዘርፉ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገር ውስጥ ቢገቡ ውድድሩ ላቅ ያለ እንደሚሆን ቢታሰብም መግቢያ በሩ ተከርችሞ ቆይቷል።

በቴክኖሎጂም ሆነ በሀብት ረገድ ብቁ ሆኖ መገኘት የግድ ስለሚልም እንዲሁም የሀገሪቱ የአገልግሎት ልሕቀት የተፈለገው ቦታ እስኪደርስ የውጭ ባለሀብቶች ሀገር ውስጥ ገብተው በፋይናንስ ዘርፉ ሚናቸውን እንዲጫወቱ ለማድረግ ብዙም አልተኬደበትም ነበር።

ነገር ግን አሁን አሁን ዓለም አንድ እየሆነች መምጣቷን ተከትሎ በር መዝጋት አዋጭ ነው ተብሎ አይታሰብም። ያለፈውን መንገድ ተከትሎ መሥራት ደግሞ ኢኮኖሚው እልፍ እንዳይል ጫና ከማድረጉ በተጨማሪ የዜጎች ሥራ ዕድልም እንዳይስፋፋ እንቅፋት እንደሚሆን ይነገራል።

በአሁኑ ወቅት ግን የውጭ ባለሀብቶች ወደሀገር ውስጥ ገብተው በፋይናንስ ዘርፍ እንዲሠማሩ የሚፍቅድ ሕግ መበጀቱም የሚታወቅ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሀብቶች በሯን መክፈቷ የሚያመጣው ፋይዳ እና ተግዳሮት ይኖር ይሆን ስንል የምጣኔ ሀብት ምሁራን አነጋግረናል።

ካነጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ምሁር አንዱ ብርሃኑ ደኑ (ዶ/ር) ናቸው። ብርሃኑ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በንግድ ሥራ ኮሌጅ የምጣኔ ሀብት መምህር ሲሆኑ፣ ማንኛውም ነገር የራሱ የሆነ ጠቃሚ ጎን እንደሚኖረው ሁሉ የራሱ የሆነ ጉዳት አሊያም ተግዳሮት ሊኖረው ይችላል ይላሉ። ይሁንና ጥቅሙን ለማግኘት ተግዳሮት ሊሆን በሚችለው ጉዳይ ላይ ጠንክሮ መሥራት ወሳኝ እንደሆነ ያመለክታሉ።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ያለችው ግሎባላይዜሽን ወይንም ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት የገነነበት ሁኔታ ውስጥ ነው። ስለሆነም ብቻችንን የምንቆምበትም ሆነ ብቻችንን የምንጓዝበት ሁኔታ የለም። ሁሉም ሀገር ሙሉ በሙሉ ራሱን ችሎና በራሱ ሀገር በሚያደርጋቸው ነገሮች ላይ ብቻ ተመርኩዞ ሕልውናውንም ሆነ የኢኮኖሚ ጉዳዩን ማስተካከልና ወደፊት መራመድ አይችልም ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ከዚህ የተነሳ እኛ አንዳንድ የሥራ መስኮች ላይ በቂ የሆነ ልምድ የማጣት ሁኔታ ይታይብናል። እሱ ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂም ሆነ በሰው ኃይልም ወደኋላ ቀረት ያለ ሁኔታ እንዳለን ይታወቃል።

እርግጥ ነው፤ አንዳንድ ጎዳዮች ላይ ከአፍሪካ ሀገሮች እንዲሆም ከሌሎች አገሮችም በተሻለ ሁኔታ የምንንቀሳቀስባቸው መስኮች አሉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከማናቸውም የአፍሪካ አየር መንገዶች በተሻለ ሁኔታ የሚሠራ፣ ትርፋማ ብሎም ታዋቂ የሆነ በብዙ መልኩም የሚደነቅ ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ስም ጥር ሆና ቀጥላለች ሲሉ ይናገራሉ።

እንዲያም ሆኖ የሚሉት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ ዋና ዋና የሆኑትን በመንግሥት እጅ የነበሩት የኢኮኖሚ ዘርፎችንና ዋና የአገልግሎት መስጫ ድርጅቶችን ከመንግሥት እጅ ወደ ወጪ የግል ባለሀብቶች ለማዘዋወር የሚደረገው ሥራ ደረጃ በደረጃ እንጂ ሁሉንም በአንድ ጊዜ አይደለም ሲሉ ያስረዳሉ።

ማዘዋወር በእነዚያ ድርጅቶች ላይ የተወዳዳሪነትን፣ የተፎካካሪነትን እንዲሁም ከውጭ ባለሀብቶች ወይም ከሚገቡ ልዩ ልዩ ድርጅቶች የተሻለ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ትግበራ ስለሚኖር ይህ ለኢኖሚው እድገት ከፍተኛ መነቃቃትን ሊያስከትል እንደሚችል ያመለክታሉ። በእነዛ ዘርፎች ላይ ትርፋማነትን ብሎም ተወዳዳሪነትን ሊያስገኝ ይችላል። ስለዚህም ማዘዋወሩ ለኢኮኖሚው ይጠቅማል በሚል የሚሠራበት ነው ይላሉ።

እንደ ብርሃኑ (ዶ/ር) ገለጻ፤ አንድ ኢኮኖሚ በመንግሥት እጅ ብቻ ቢሆን የሚጠበቀውን ያህል ተወዳዳሪ ላይሆን ይችላል። የግሉ የተሻለ ሊሆን ይችላል። የግሉ የተሻለ ሥራ እና የተሻለ ትርፋማነት፣ የተሻለ ቴክኖሎጂ፣ የተሻለ የአደጋ አቀናነስ ሁኔታ ሊኖረው ይችላል ። ነገር ግን በእኛ ሀገር ከመንግሥት ያን ያህል ሻል ያለ የግል ዘርፍ አናገኝም። ለዚህም ነው መንግሥት በአብዛኛው በኢኮኖሚው ዘርፍ በአብዛኛው ተሳትፎ እያደረገ ያለው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ መዋዕለ ንዋዩንም አትርፎ ብዙ ጉዳዮችን የሚያከናውነው በዚህ የተነሳ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

ስለዚህ የውጭ ባለሀብቶች ወደሀገር ውስጥ ገብተው ኢንቨስት እንዲያያደርጉ የተፈለገበት ምስጢር፤ የግል ባለሀብቱ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከውጭ ደግሞ የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች እዚህ መጥተው ቢሳተፉ የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ሊመጣ ይችላል በሚል ታሳቢነት ነው ይላሉ። እነዚህ ጉዳዮች ታስበውና ተጠንተው የተደረጉ ስለሆኑ ለኢኮኖሚው እድገት የሚጠቅሙ እንደሆኑም ያመለክታሉ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው የቀድሞው የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና በበኩላቸው፤ የፋይናንስ ዘርፉ ተዘግቶ ለዘላለም ሊኖር አይችልም ይላሉ። በእስካሁኑ ሒደት የኢትዮጵያ መንገግሥት የፋይናንስ ዘርፉን በጣም አባብሎ እንዲዳብር ማድረጉን ጠቅሰው፤ የውጭ ባለሀብቶች ወደሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ በመልካም ጎኑ የሚታይ መሆኑን ያስረዳሉ።

አምባሳደሩ እንደሚሉት፤ መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን እዚህ ያደረሰው በእወቀትና በመረጃ አሊያም ሌሎች ሀገሮች እንደሚያደርጉት ተወዳድሮ ሳይሆን ይህን ያህል በዚህን ያህል ተበደር፤ በዚህን ያህል ደግሞ አበድር ብሎ በፈቀደውና ባስቀመጠው መመሪያ መሠረት ነው። ያንን ተጠቅሞ ከፍተኛ ትርፍ እያገኘ የመጣ ዘርፍ ነው። ይህ ደግሞ የፋይናንስ ዘርፉን አዳብሯል፤ በእግሩም እንዲቆም ትንሽ ረድቷል።

ነገር ግን ለወደፊት ይህንን ያዳበርነውን ፋይናንስ ሴክተር እንዲሁ ክፍት አድርገን እነዚያ ብዙ ገንዘብና ብዙ እውቀት ያላቸው አካላት ገብተው ይህን የያዳበርነውን ዘርፍ እንዲጥሉ ማድረግ ደግሞ ተገቢ አለመሆኑን ይገልጻሉ። በዚህ በኩል ጥንቃቄ ማድረጉ ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ። እንዲያም ሆኖ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች መከፈቱ አግባብነት ያለው ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ ይህ በኢትዮጵያ ብቻ የተጀመረ ሳይሆን ዓለም ሁሉ የሚያደርገው ነው ይላሉ።

ነገር ግን ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሀብቶች በሯን ክፍት ማድረጓ ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል የሚሉት አምባሳደር ጥሩነህ፣ ጥንቃቄውም ያዳበርነውንና እዚህ ደረጃ ያደረስነው የፋይናንስ ዘርፋችን መውደቅም ከውጭ በሚመጡ ባለሀብቶች መዋጥም የለበትም ባይ ናቸው። የሚመጡ የውጭ ባለሀብቶች አብረው ቢዳብሩ ጥሩ ነው። ባለሀብቶቹ መምጣቸው ካፒታል ይዘው እንዲመጡ እድል ይፈጥራል። በአሁኑ ወቅት ተግዳሮት ሆኖ ሲያስቸገረን የቆየውን የውጭ ምንዛሬም ዕጥረት ለመቅረፍ እድል ይዞ ይመጣል ይላሉ።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ እነርሱ በመምጣቸው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የበለጠ ይደፋፈራሉ። እኛ ደግሞ ኢንቨስትመንትን የመሳብ አቅም አለን፡። ለምሳሌ አንድ የውጭ ባለሀብት ቀደም ብሎ በባንኩ ዘርፍ የመጣ አካል ካለ የሚያውቀው ባንክ አሊያም ከእርሱ ጋር ግንኙነት ያለው ባንክ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን ሲያውቅ እዚህ መጥቶ ኢንቨስት ለማድረግ ይደፋፈራል።

አምባሳደር ጥሩነህ፣ ልክ እንደ ብርሃኑ (ዶ/ር) ሁሉ በር መዝጋት በፍጹም አያዋጣም። ስለዚህ ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሀብቶች በሯን መዝጋት የለባትም ይላሉ። አምባሳደሩ፣ እስካሁንም በራችንን ዘግተን ቆይተናል ሲሉ ጠቅሰው፤ በእርግጥ ዘግተን የፋይናንስ ሴክተሩ እንዲዳብር አድርገናል ብለዋል። ነገር ግን ያንን ያዳበርነውን የፋይናንስ ሴክተር ዝም ብለን መጣል የለብንም።

ስለዚህ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱም እንዳይወድቅ በማድረግ መንቀሳቀሱ አዋጭ ነው ባይ ናቸው። ብዙ ነገሮች ሊደረጉ እንደሚችሉም ጠቁመው፣ ሕግ የምናወጣው እኛ ስለሆንን ማጥበቅም ማላላትም እንችላለን ብለዋል። ስለዚህም ሀገራችን በመሆኑ በእዚህ ግባ፤ በእዚያ ውጣ የሚለን ሌላ አካል የለብንም፤ ሊኖርብንም አይችልም ብለዋል።

ብርሃኑ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ የውጭ ባለሀብቶች ወደሀገር ውስጥ ሲገቡ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ጉዳይ በተወሰነውና በተግባባነው መሠረት ማለትም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የውጭ ባለሀብቶች በተቀመጠውና በሚገቡት ግዴታ መሠረት ሥራቸውን ማከናወን አለባቸው፤ ያንን ደግሞ መቆጣጠር ያስፈልጋል። ስምምነቱም ተግባራዊ መሆን ይጠበቅበታል።

ሌላው ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ያሉ ደግሞ ከመጀመሪያውኑ ማለትም ከመግባታቸው በፊት ስለእነርሱ የኋላ ታሪክና የሚሠሩትን ሥራ በተመለከተ በስፋት በአግባቡ ማጠጥናት ያስፈልጋል። በመንግሥት በኩል የተዘጋጀ ስምምነት ይኖራልና ያንን መሠረት በማድረግ ግዴታቸውን እንዲወጡ መከታተልንም ይጠይቃል። እኛም ደግሞ የሚያስፈልጉትን አገልግሎቶች እንደሚገባ ማስተካከል እና ቢሮክራቲክ የሆኑ አካሔዶች እንዳይኖሩ መከላከልን የግድ ይለናል ብለዋል። እነዚህና መሰል ነገሮች ከተስተካከሉ የውጭ ሀገር ባለሀብቶች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው ጠቃሚ ሊሆን ይችላል ሲሉ ገልጸዋል።

በተለያዩ የገበያ ሁኔታዎች የግል ባለሀብቶች እንዲገቡ ተጋብዘዋል፤ እና በማንኛውም የሥራ መስክ በአስመጪነትም ሆነ በላኪነትም ንግዶች እንዲሠማሩ ተፈቅዶላቸዋል፤ ጥሪም ቀርቧል። የተወዳዳሪነትን ጉዳይ ስናነሳ የእኛ የውስጥ ንግድ በጣም የተዛባ ነው። ዋጋ በመጨመር እንጂ ሀገር የምትጠቀምበትን ፋይዳ በመጨመር የሚሠራ አይደለምና ይህ በጣም አስቸጋሪ ነው። ከውጭ የሚገቡ ባለሀብቶች ምናልባት ተወዳዳሪነትን ሊያሰፉ ይችላሉ። በተመሳሳይ ኢኮኖሚው ቀልጣፋ እንዲሆን ሊያደርጉ ይችላሉ። በተጨማሪም ስጋት የሆነውን የሥራ አጥነትን ጉዳይ የሚቀንስ ይሆናል። ሕጉም ይህንን የሚመለከት ነው። ያንን ሕግ በትክክል ከተጠቀምንበት ጠቃሚ ነው የሚሆነው ብለዋል።

በሀገራችን ሀብት ብቻ ብዙ የምናቅዳቸውን ነገሮች መሥራት አያስችለንም። የውጭ ሀገር ባለሀብቶች መጥተው እኛንም ራሳቸውንም ጠቅመው እንድናድግ ያደርጋሉ። ስለዚህም ኢትዮጵያ ለውጭ ሀገር ባለሀብቶች በሯን ክፍት ማድረጓ ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ ብለዋል።

ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ በር ዘግቶ መቀመጥ በራሱ ጉዳት ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ እንደ አምባሳደር ጥሩነህ ሁሉ በሩን ዘግቶ ያደገ ሀገር የለም ሲሉ ተናግረዋል። እኛ በራችንን ለረጅም ጊዜ ዘግተን ቆይተናል። አሁን የምናያቸው አንዳንድ ያልተስተካከሉ የእድገት ሁኔታዎች አሉ። ድህነትም ይህን ያህል ገዝፎ የታየው በራችንን ለረጅም ጊዜ ዘግተን ስለቆየነው ነው። ሌሎች ሀገሮችም በዚህ ውስጥ ያለፉ አሉ። ብዙዎቹ ሀገሮች ቀደም ሲል በራቸውን ዘግተው የነበሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በርካታ ሀገራት ይህንን ችግር ተገንዝበው በራቸውን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረግ መጀመራቸውን ያስረዳሉ። ለአብነት የምስራቅ ኢስያ እንዲሁም ሌሎች ሀገራትም በራቸውን እየከፈቱ ነው። እነቻይና በከፍተኛ ደረጃ ሊያድጉ የቻሉት በራቸውን በሰፊው ከፍተው በተለያየ ሁኔታ በመተባበርና ውጭም ኢንቨስት በማድረግ ላይ ስለተሰማሩ ነው። ለዚህም ነው ሀብት ማፍራትና የጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆን የቻሉት ሲሉ አብራርተዋል።

አምባሳደ ጥሩነህ እንደሚያስረዱት፤ በር መክፈቱ የጥቅሙን ያህል አይሁን እንጂ መጥፎ ጎን ይኖረዋል። ለአብነትም የውጭ ባለሀብቶች ምናልባት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትንሽ ገድገድ የሚል ከመሰላቸው ሀብታቸውን በአንዴ ሊያሸሹ ይችላሉ። ሕጉ ይህንንም ጉዳይ ታሳቢ ያደረገ መሆን ይኖርበታል። የዘርፉ ተቆጣጣሪ አካልም መስኩን በአግባቡ የሚያውቅ ሊሆን ይገባል።

በጥቅሉ ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሀብቶች በር መክፈቷ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ነው። ምክንያቱም እንደዚህ ዘግተን ከዓለም ተለይተን መቀጠል አንችልም። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ያለነው ድሮ በነበርንበት ሁኔታ ውስጥ አይደለንም። እንዲህ እየተንገዳገድንም ቢሆን ሀገራት የሚመለከቱን በትልቅ ደረጃ ላይ አስቀምጠው ነው። ለምሳሌ ብሪክስን ለመቀላቀል በርካታ ሀገሮች ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወቃል። ነገር ግን የወሰዱት ኢትዮጵያን ነው። ይህች ሀገር ደግሞ በብዙ ፈተና ውስጥ ብትሆንም የራሷ ባህል ያላት በራሷ የምትተማመን መሆኗና የአፍሪካ መግቢያ በር በመሆኗ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል ሲሉ አምባሳደሩ ተናግረዋል።

የውጭ ባለሀብት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ ያስችላቸዋል ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የሰው ኃይል ማግኘት መቻላቸው ነው ያሉት አምባሳደሩ፣ ከዚህ ጎን ለጎን ገበያ መሆን የሚችል ኃይል መኖሩም የማይካድ ሐቅ ነው ብለዋል። ለምሳሌ የውጭ ኢንቨስተር በአንድ የሥራ መስክ በአንድ ጊዜ እስከ አስር ሺህ ሠራተኛ ይፈልጋል። ብዙ ሠራተኛ ያለበት እና ሥነምግባሩም የተመሰገነ ሠራተኛ እንዲሁም ጠንካራ መንግሥት ያለው ሀገር እንደመሆናችን እንዲሁም ሰላም ያለው ሀገር ለመሆን የሚያቅተን ነገር የለም ብለዋል። ያንን በማድረግ የበለጠ ኢንቨስተሮች በመሳብ ማደግ የሚቻል እንደሆነ አመልክተዋል።

የምጣኔ ሀብት ምሁራኑ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት የትኛውም ሀገር በሩን በመዝጋት አድጋለሁ ማለት አይችልም። ይልቁኑ ባለሀብቱን መሳብ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ተጠቃሚ ለመሆን መትጋት የግድ ይላል። ኢትዮጵያ ደግሞ የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ የሚያስችላት ምቹ ሁኔታ አላት። ነገር ግን በበለጠ በኢኮኖሚው ዘርፍ ተጠቃሚ መሆን እንዲያስችል ትልቁ ጉዳይ የሆነውን የሀገር ሰላም ማስጠበቅ የግድ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ደምድመዋል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2016

 

 

Recommended For You