ብሄራዊ ምክክር እንደብሄራዊ ድል

ብሄራዊ ምክክር የኢትዮጵያውያን የእርቅና የዳግም መወለድ ትንሳኤ ከመሆኑ እኩል እንደ ብሄራዊ ድል ሊወሰድ የሚገባው የውይይትና የተግባቦት መድረክ ነው። በተለይም በፖለቲካ ሽኩቻ እየደበዘዘ የመጣውን አብሮነት መልክ በመስጠት ረገድ የማይናቅ ሚና ያለው ነው። እንደሀገር ከብሄራዊ ድል ጋር አንድምታ ያለው፣ እንደትውልድ ደግሞ ነገን አርቆ በሚያይ ብዙሃነት የተቃኘ የሰላም ጉባዔ ነው።

ያለፉትን ዓመታት በብዙ ተግዳሮት ውስጥ አልፎ ፍሬውን በከተማ አቀፍ አጀንዳ ልየታ መድረክ በኩል አስተዋውቋል። በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሮ የተጠናቀቀው የአጀንዳ ልየታ መርሀ ግብር በርካቶችን ባሳተፈና ከበርካቶች ሃሳብ በመቀበል ረገድ የተሳካለት እንደነበር ተገልጿል። ሰላምንና ሀገራዊ አንድነትን መነሻና መድረሻው ያደረገው ሀገራዊ ምክክር በበላጭ ሃሳብ በላጭ ዋጋ ያላቸውን የእርቅና የማህበራዊ ትስስር እሴቶችን በማጎልበት የአብሮነት ድልድይ የሚሠራ መድረክ ነው።

በዓድዋ መታሰቢያ መነሻውን ያደረገው ከተማ አቀፉ የምክክር መድረክ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሶስቱ የመንግሥት አካላት (ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ)፣ የተቋማትና የማህበራት ተወካዮች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በመያዝ ስለመጻኢ እድላችን በጎ ባለው ነገር ላይ ሁሉ መክሯል። እርቅና ይቅርታን ታሳቢ ያደረገው የምክክር መድረኩ ስላለፈውና ስላለው ሀገራዊ ሁኔታ መጪውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተስፋ ሰጪ ውይይት አድርጓል።

መላውን ኢትዮጵያ ባደረሰና ሀገር አቀፍ በሆነ መልኩ በቀጣይ እንቅስቃሴውን የሚጀምረው ኮሚሽኑ ኢትዮጵያን በሃሳብ ለመፍጠር ሙሉ ዝግጅቱን በመጨረስ አትራፊ ርምጃ በማድረግ ላይ ይገኛል። ከማንም ሳይሆን ከሕዝብ በተዋጣ ሃሳብና ምክረ መፍትሄ የነበረውን በይቅርታ፣ ያለውን በእርቅ፣ የሚኖረውን ደግሞ በውይይት ለማረቅ ሀገር መር መርህ ይዞ በራፋችንን እያንኳኳ ይገኛል። ይሄ እድል በደርግና በኢህአዴግ ዘመን ተጀምሮ የቆመ በእኛ ዘመን ግን ለትግበራ የበቃ ሀገር የማዳኛ ወሳኝ አጋጣሚ ነው።

ሃሳብ ያልዳበረባቸውን ትላንትናዎች በሃሳብ ለማከም፣ ሃይለኝነት የነገሰባቸውን ወቅታዊ ሁኔታዎች በእርጋታና በስክነት ተመልክቶ እልባት ለመስጠት በገለልተኛና፣ በአሳታፊ፣ በተደራሽነትና በተአማኒነት እንደፋና ወጊ በመሆን ከፊት የተሰለፈ የውይይት መድረክ በመሆን ሚናውን እየተወጣ ይገኛል። አንዳንድ አጋጣሚዎች የተፈለገላቸውን ዓላማ ለመምታት ረጅም ዓመታት የሚወስዱ ናቸው እንደዛም ሆኖ የማይሳኩ ብዙ አሉ።

ብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን ግን የበዙ ተግዳሮቶችን በማለፍ ስለሰላም ዋጋ በመክፈል የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ በመቆም ሕዝብ እያወያየ ይገኛል። እድሉን በመጠቀም፣ በእድሉ በማትረፍ፣ ባለእድል በመሆን እድለኛ ትውልድ መፍጠር የእኛ ድርሻ ይሆናል። ሜዳውም ፈረሱም ተዘጋጅቶልናል ፈረሱን መጋለብ የእኛ ፈንታ ነው። ሜዳው የምክክር መድረኩ ነው ፈረሱ ደግሞ የምናንሸራሽረው ሃሳብ ነው።

ባልተገራ ፈረስና ባልሠለጠነ ባልደራስ እድላችንን ማምከን ድጋሚ የማይመጣን ከመጣም ብዙ ዋጋ የሚፈልግን መልካም አጋጣሚ ከማባከን ጋር አንድ ነው። ያልተገራው ፈረስ እርቅና ተግባቦት የሌለው ሃሳብ ነው። ያልሠለጠነው ባልደራስ ደግሞ ከእልህና ከሃይል ያልወጣው እኛነታችን ነው።

ምክክር መነሻው የሃሳብ የበላይነት፣ ግዙፍ ሆደ ሰፊነት ነው። መድረሻው ሀገርና ሕዝብ ቢሆንም ከፍጻሜው ለመድረስ መጀመሪያው ማማር አለበት። በሃሳብ ዳብረን፣ በሆደ ሰፊነት ገዝፈን ስለሀገራችንና ስለወገናችን ስንል እርቅን እንደመጨረሻ አማራጫችን ልንቀበል ይገባል። እንቢ ባይነትንና አልሸነፍ ባይነትን ይዞ እርቅና ምክክር የለም። እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን በማለት እና በእልኸኝነትን እየተመሩ የጋራ ትርክት የማይታሰብ ነው። መድረሻችን ሀገርና ሕዝብ ከሆኑ መነሻችን ሰላማዊ ውይይትና አብሮነት መር ምክክር ሊሆኑ ግድ ይላል።

ሀገር በሃሳብ ስትፈጠርና በጦርነት ስትፈጠር የተለያየች ናት። በሃሳብ የተፈጠረች ሀገር፣ በሃሳብ የተፈጠረ ማህበረሰብ፣ በሃሳብ የተራመደ ትውልድ ጦርነትን ይሽራል እንጂ ለእርስ በርስ ግፊያ ጠመንጃ አይወለውልም። ማረፊያው ሰላም፣ መጽናኛው አብሮነት ነው። ማረፊያችን ጦርነት ሆኖ ለብዙሃን የጉስቁልና ምክንያት የሆነው በሃሳብ ስላልበለጸግን ነው። በሃሳብ መበልጸግ ተነጋግሮ በመግባባት ልዩነትን ማጥበብ፣ ሰላምን ማምጣት ነው። በሃሳብ መበልጸግ ወንድማማችነትም ማጽናት፣ አብሮነትን ማወጅ ነው። ካልሆነ ልዩነቶች ወደ ጦርነት ሲወስዱን፣ በብዙ ዋጋ መክፈል ውስጥ ስንገዳገድ ቆመን የምንመለከት እንሆናለን።

በሃሳብ ያልበለጸገ ፖለቲካና ፖለቲከኛ፣ በውይይት ያልዳበረ ትውልድና ማህበረሰብ ድንጋይ በማቀበልና ድንጋይ በመወርወር ተወዳዳሪ የለውም። በሀሰት ትርክት ሀገር ለማፍረስ እና አብሮነትን ለመሻር ፊተኛ ነው። በጋራ ታሪክና በጋራ ሀገር ላይ ግፊያ የያዝነው ለምን ሆነና? ከአንድ መንጭተን በአንድ እየፈሰስን፣ እንደዓባይና ጣና መልካችን ተወራርሶ የምንባላው ለምን ሆነና? በሃሳብ ስላልበለጸግን ነው። ተነጋግሮ መግባባት ስላልቻልን ነው።

ብሄራዊ ምክክር ከዛ ወደዚህ የምንሻገርበት፣ አሻፈረኝ ስንል ገሎ በመሞት ሃይላችንን ለማሳየት የሄድንበትን የእንቢተኝነት ፖለቲካ በፍቅርና በይቅርታ ለመግለጥ የመጣ በጎ አጋጣሚአችን ነው። ከሰሞኑ በተካሄደው ከተማ አቀፍ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገራዊ ምክክር ሁሉንም ወገን አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑን በመግለጽ በእድሉ ተጠቃሚ በመሆን አትራፊ እንድንሆን የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሀገራዊ ምክክሩ ዋና ኮሚሽን ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ‹ከጠመንጃ ወደሃሳብ መንጃነት በመሸጋገር፣ እርቅና አብሮነትን ባቀፈ የጋራ ማዕቀፍ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ምቹ አጋጣሚ ፊት እንዳለን ገልጸው ፣ ሁሉም የእድሉ ተሳታፊ በመሆን ሀገሩን ነጻ እንዲያወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ሀገራዊ ምክክሩን በሚመለከትና ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ በማንሳት ያጋሩት መልዕክት ነበር ‹ጦርነትና አብዮት የተሟላ መፍትሄ የማያመጡት አሸናፊና ተሸናፊ ጎራዎችን ስለሚያስከትሉ ነው። ቢዘገይም የተሸነፈው ለማሸነፍ ይታገላል ያሸነፈውም ድሉን ለማስጠበቅ ይዋጋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ሀገር ዋጋ ትከፍላለች፣ ሕዝብ ብዙ ነገሩን ያጣል። ምክክር ግን ሁሉም እኩል አሸናፊ የሚሆኑበት መድረክ ነው። ከተሸነፍንም ሁላችንም ለሀገራችን ብለን ነው የምንሸነፈው› ሲሉ አጋርተዋል።

‹ጦርነትን ኖረንበታል፣ የተወሰኑ ችግሮቻችንን ፈተንበታል። አብዮትን ደጋግመነዋል፣ የተወሰኑ እንከኖችንም ተሻግረንበታል። በሁለቱነም ያልተፈቱትን ችግሮች ለመፍታት የቀረን አማራጭ ምክክር ብቻ ነው። ምክክርን ግን አልተጠቀምንበትም› ሲሉ ተደምጠዋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምክክር ካለው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች መሀል በዋናነት ሶስቱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሁሉንም ባይሆን ዋና ዋና ችግሮችን እንደሚፈታ፣ ከጦርነት ይልቅ ውይይት ባህል እንዲሆን እንደሚያግዝ፣ በተቃራኒ ሃይሎች መካከል መቀራረብና መግባባት እንደሚፈጥር በማንሳት የአስፈላጊነቱን መጠን አውግተዋል።

የመጨረሻ መልዕክታቸው በመሆን የተገለጸው ‹በምክክሩ ተቀራርበን፣ ተወያይተንና ሃሳብ ተቀባብለን ወደፊትም በችግሮቻችን ላይ እየተወያየን እንድንቀጥል እድል የሚሰጠን በመሆኑ የተከፈተውን የአብሮነት መድረክ በመጠቀም ወደ ድል እንሸጋገር ሲሉ በመጠየቅ ነው። ከዚህ የማህበራዊ ትስስር መልዕክት ውስጥ አሸናፊና ተሸናፊ የሚሉትን ቃላት መዘን ብንነጋገር በዚም ሆነ በዛኛው ወገን ጦርነት በጎ ገጽ እንደሌለው እንረዳለን። አሸናፊው ድሉን ለማስጠበቅ ሲታትር ተሸናፊውም ጊዜ ጠብቆ ለበቀል ሲሰናዳ በዚህ መሀል በሀገርና ሕዝብ ላይ ብዙ ጉዳት ይደርሳል። እንዳው ተለማምደንው ሞትና የአካል መጉደል ተራ ነገሮች ሆኑ እንጂ በዚህ ዓለም ላይ እንደሰው ልጅ ሞት የመጨረሻ ክስረት አልነበረም።

ጦርነት ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። በሰሜኑ ጦርነት ስለጠፋው የሰው ሕይወት፣ ስለጎደለው አካል፣ ስለወደመው ንብረት፣ ስለተፈናቀሉ ዜጎች፣ ስለወደሙ ሆስፒታሎች፣ ባንኮች፣ መሠረተ ልማቶች፣ የጤና ጣቢያዎች ሰምተናል። እኚህ ለአንዲት ድሃ ሀገር አይደለም በኢኮኖሚያቸው ለዳበሩትም ቢሆን እጅግ አክሳሪዎች ናቸው። የታሪካችን መሀል በጦርነት፣ በእርስ በርስ ግጭት መጠራቱ ያሳዝነኛል። በዘመነውና እጅግ በተራቀቀው፣ የሰው ልጅ የምድር ኑሮ በቃኝ ብሎ ቤቱን ጨረቃ ላይ በማገረበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰላምን በጦርነት ለማምጣት መሞከር፣ በደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ግጭት ዋጋ መክፈል አሳፋሪ ድርጊት ነው።

በመጽሀፍ ቅዱስ ላይ ‹ወንድሞች በህብረት ቢቀመጡ መልካም ነው እንሆም ያማረ ነው ›። ይላል። ወንድማማችነት ትርጉሙ ህብረት፣ አብሮነት ነው። አንዱ ላንዱ አለኝታና መከታነት እንጂ በፖለቲካ ቁርሾ የሚደማሙበት፣ የሚዛዛቱበት አይደለም። ትንቅንቃችን ማንንም ፊተኛ ማንንም ባለክብር አያደርግም። ተያይዘን ከመውደቅ ባለፈ የሚሰጠን ጋት ብኩርና የለም። የሰላም ጀግና ያስፈልገናል። ከጦርነት ጀግንነት ወጥተን ስለሰላም ዋጋ የምንከፍልበት፣ ስለአብሮነት የምንዳክርበት የውይይት መድረክ ያስፈልገናል።

አክሳሪና አዋራጅ በሆነ ጦርነት ለበስ መንገድ ላይ ብዙ ዋጋ ከፍለናል። ደም ተቃብተን ትውልዱ እንዲፈራራ ወንድማማችነቱን አሳጥተነዋል። ብልህ ከሌሎች የሚማር ቢሆንም እኛ ግን ከራሳችን ለዛውም ከቅርብ ጊዜ ታሪካችን መማር አቅቶን አሁንም በተመሳሳይ ጉስቁልና ውስጥ ነን። ሞትና ጉስቋሌ ተራ ነገሮች ሆነው በየቤታችን ገብተዋል። ዓላማችን ምንድነው? ዓላማችን ጫፍ ካለው ያ ጫፍ እንዴት ገሎ በመሞት ይደረሳል? ከሰላም ውጪ ዓላማ መዳረሻ አለው?

ድሃና ኋላ ቀር ሕዝቦች ነን። በውጭ ሀገራት ርዳታ እና ድጎማ የመጣን ነን። መሠረታዊ ፍላጎቱን ተነጥቆ በተስፋ መጪውን መልካም ለማድረግ በሚታትር ትውልድ ጥላ ስር ነን። ባልሞላና ባልደላ ሕይወትና ወጥቶ መግባት ውስጥ ነን። እንዲስተካከሉልን የምንፈልጋቸው ብዙ ነገሮች አሉን። ርሃብና ርዛት ሌላው ታሪካችን ነው። በእነዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ጦርነትና ጥላቻ፣ ዘረኝነትና የእርስ በርስ ግጭቶች ምን ያክል ዋጋ አስከፋዮች እንደሆኑ መረዳት አይከብድም። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ማለት ይሄ ነው። ጆሮ ደግፍ ተጨምሮብን አይደለም እንቅርቱን ብቻ አልቻልነውም።

ሰላም በተራበና ሰላም በሚሻ ማህበረሰብ መሃል ነን። ዝምታና ኩርፊያችንን፣ እልህና ቂማችንን ትተን በመመካከር ለአዲሷ ኢትዮጵያ ዋጋ መክፈል ይኖርብናል። እንደጲላጦስ እጅን ታጥቦ ከደሙ ንጹህ ነኝ ማለት ለማንም አይበጅም። ስቀለው፣ ስቀለው በዚህ ሕዝብ መሀል ትርጉም የለውም። በሰከነና በረጋ መንፈስ ለችግሮቻችን መፍትሄ መስጠት ነው አርነት የሚያወጣን። ለዚህ ምቹ ሆኖ የተዘጋጀው ደግሞ ሀገራዊ የውይይት መድረክ ነው። ካሉብን ነባርና ወቅታዊ የፖለቲካና የጦርነት እንዲሁም የሰላም ርሃብ ለመሻር እንደመጨረሻ አማራጭ የሚቀመጠው ሀገራዊ ውይይት ነው።

ኢትዮጵያን ስንል፣ ትውልዱን ስንል፣ ስለሕዝብ ስንል ብዙዎች ዓላማ ይዘው በተሰለፉበት የእርቅና የይቅርታ መድረክ ላይ ተሳታፊ በመሆን ዐሻራችንን ማሳረፍ ይጠበቅብናል። ሀገር የምትድነው በእኔና በሌላው ሰው የሃሳብ ፍጭት እንጂ የጦርነት ግጭት አይደለም። የነውር ሰንኮፋችንን አውልቀን የሰላም ዘውዳችንን መድፋት የከእንግዲህ ሃላፊነታችን እንዲሆን በጋራ መጣር ከውለታችን አንዱን ነው።

መዳፎቻችን ከመድፍ ወጥተው እርፍ እንዲጨብጡ፣ ከንዶቻችን ከጠብመንጃ ወደ ወደሃሳብ መንጃነት እንዲለወጡ፣ አንደበታችን ከእርግማን ወደምርቃት እንዲሸጋገር ጊዜው አሁን ነው። ባለፈ ክረምት ቤት እንደማይሠራ ባለፈ ቁርሾዎች ዛሬን መሞት ሊበቃን ይገባል። በሰላም ስለሰላም፣ በአንድነት ስለአንድነት ማውጋትና መመካከር ታሪካችንን የምናድስበት፣ ቤታችንን የምንቀልስበት የኢትዮጵያዊነት ቀለም ነው። ቸር ሰንብቱ።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2016

 

 

Recommended For You