የክረምቱ ወሮች – የአረንጓዴ ዐሻራችን ማኖሪያ ነጭ ወረቀቶች

ባለንበት ዘመን ዓለምን እያሳሳቡ ከሚገኙ ጉዳዮች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው በደኖች መመናመን ምክንያት እየተስተዋለ የመጣው የሙቀት መጠን መጨመር (የአየር ጸባይ ለውጥ) እና ይህንን ተክትሎ የሚከሰተው ተፈጥሯዊ አደጋ ነው። የኦዞን ሌየር መሳሳት (መሸንቆር)፣ ድርቅ፣ ጎርፍ ፣ የለም አፈር መታጠብ፣ የግግር በረዶዎች መቅለጥ ፣ የዱር እንስሳት ቁጥር መቀነስ ወይም ዝርያቸው መጥፋት፣ የወባ በሽታ መስፋፋት፣ የሰዎች መፈናቀል ወይም መሰደድ፣ የምርት መጠን መቀነስ፣ ሰደድ እሳት ከብዙዎቹ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

የዓለም ሕዝብ ለእነዚህ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ መስጠት የማይችል ከሆነ በሕይወት የመቀጠል ህልውናው አደጋ የተደቀነበት እንደሆነ የሚያስረዱ ጥናቶችም በየጊዜው መውጣታቸው የተለመደ ነው። የደኖች መመናመን በሰው ልጆች ላይ እያስከተለ ያለውን አደጋ ከጥናት ውጤቶችም በላይ አይኖቻችን እያረጋገጡ ያሉት ሐቅ ነው። ከላይ የጠቃቀስናቸው አዳዲስ ክስተቶች እና ሌሎችም ተፈጥሯዊ አደጋዎች አንዱ መነሻቸው የደን ሽፋን መቀነስ ነው። ተፈጥሯዊ አደጋዎች በሰው ልጅ ላይ የሚያሳርፉት በትር እንዲህ እንደምናወራው ቀላል ሳይሆን የመኖርና ያለመኖርን ሁኔታ እስከመወሰን የሚደርስ ነው።

ዕጽዋት ከሰው ልጅ ጋር ያላቸውን ተፈጥሯዊ ትስስር እና ለሰው ልጅ ያላቸውን አስፈላጊነት እንዲህ ነው ብለን ዘርዝረን የምንጨርሰው ጉዳይ አይደለም። በጥቅሉ ያለ እጽዋት መኖር የሰው ልጅ ህለውናውን ማረጋገጥ አይችልም ብሎ መደምደም ይቻላል። እንዲህ አይነት ድማዳሜ ላይ እንድንደርስ ከሚያስችሉን ጉዳዮች አንዱ ሰው የሚተነፍሰውን አየር (ኦክሲጂንን) ከእጽዋት የሚያገኝ መሆኑ ነው። ይህን እንደ አንድ ማሳያነት ተመለከትነው እንጂ የሚጠጣውን ውሃ እና የሚመገበውን ምግብም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በዘላቂነት ማግኘት የሚችለው እጽዋት ሲኖሩ ነው።

እጽዋት ተፈጥሮና ፍጥረታት ተመሳጥረው እንዲኖሩ የሚያስችሉ፤ ቢያንስ ከምድር እስከ ምድር ከባቢ አየር ድረስ ያለውን ሰፊ ግዛት ሚዛን የማስጠበቅ ሚና ያላቸው ድንቅ የተፈጥሮ ስጦታዎች ናቸው። የእጽዋትን ሽፋን በማሳደግ ዓለምን ከተደቀነባት አደጋ ለመታደግ ሀገራት በኃላፊነት እንዲሠሩ በየጊዜው እየተመከረ ነው። ለዚህም ነው ሀገራት ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋንን እያሳደጉ በርሃማነትን እና ድርቅን የመከላከል ፤ በኢንዱስትሪ ያደጉ ሀገራትም የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ የተያዘውን ዓለም የማከም መርሀ-ግብር እንዲያግዙ ጥረቶች እየተደረጉ ያሉት።

ጉዳዩ አጽንኦት እንዲያገኝም ‹‹ዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን›› በየዓመቱ ታሳቢ እንዲሆን ተደርጓል። በዚሁ መሠረት በዘንድሮው ዓመትም በአውሮፓውያኑ ጁን 5/2024 በኢትዮጵያ ግንቦት 28/2016 ዓ.ም ‹‹የመሬት ማገገም፤ በረሃማነትንና ድርቅን ለመቋቋም›› በሚል መሪ ሃሳብ ዓለምቀፍ የአካባቢ ቀን ታስቦ ውሏል።

ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ከምታከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ-ግብር ነው። በተለይም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ-ግብር እምርታ የታየበትና እንደ አፍሪካም ተጠቃሽ የሆነ ነው። በመጀመሪያው የችግኝ ተከላ መርሀ- ግብር ማለትም ከ2011 እስከ 2014 ዓ.ም በተካሄደው ሥር ነቀል ዘመቻ ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል እንደተቻለና የጽድቀት መጠኑም 80 በመቶ እንደሆነ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላካትል።

በሁለተኛው ምዕራፍ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮም 25 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል እቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ከተገባ አንድ ዓመት አልፏል። አምና በሁለተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያ ዙር በነበረው ንቅናቄ እንደሀገር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን መትክል ተችሏል። የነዚህ ችግኞች የመጽደቅ መጠንም 90 በመቶ መሆኑ ተመላክቷል። ከዚህ የምንረዳው የመትከል ባህላችን ብቻ ሳይሆን ችግኞችን የመንከባከብ ባህላችንም እያደገ ስለመምጣቱ ነው።

በዘንድሮዎቹ የክረምት ወራትም 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞችን የመትክል እቅድ ተይዟል። በአንድ ጀምበርም 150 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ውጥን ተይዟል። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ-ግብራችን ችግኝን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ማስቀረት ከሚለውም በላይ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ነው። ለምሳሌ መንግሥት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሀ-ግብሩ በትኩረት ከሚሠራቸው ጉዳዮች አንዱ የሌማት ትሩፋት ነው።

እያንዳንዱ ሰው በየደጃፉ ላይ የሚተክላቸው ችግኞች ለምግብነትም ጭምር የሚውሉ መሆናቸው ሲታይ አረንጓዴ ዐሻራችን የምግብ ዋስትናችንንም ጭምር ለማረጋገጥ የሚያግዝ እንደሆነ መረዳት አይከብድም። መርሀ-ግብሩ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ሰዎች እንደ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ዘይቱን፣ ቴምር፣ ፓፓያ፣ ማንጎና ሌሎችንም ፍራፍሬዎች በየደጃፋቸው ላይ መትከልን እየተለማመዱ መጥተዋል።

በዘንድሮውም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ-ግብር ለፍራፍሬ፣ ለመድኃኒትነት እና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ላላቸው ዛፎች ትኩረት ተሰጥቷል። ውጥኑን ለማሳካትም ግብርና ሚኒስቴር አስቀድሞ በጉዳዩ ዙሪያ ስልጠና እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎችን ሲሠራ እንደነበር ያገኘናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ-ግብሩ ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሲወጡ ሰንብተዋል። ለአብነትም፤ የኢትዮጵያ ደን ልማት ችግኞች የሚተከሉበትን ቦታ ስለመምረጥ፣ ስለጉድጓድ አዘገጃጀት፤ ለሥነ-ምህዳሩ ተስማሚ ዝርያ ስለመለየት እና ሕዝብን አስተባብሮ ወደ ችግኝ ተከላው ፕሮግራም በማስገባቱ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ ሰንብቷል። ይህን በተመለከተም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፤ በተለይም ከችግኝ አተካከል ሥርዓት ጋር የተያያዙ ሰነዶችን በማቅረብ ውይይት እንዲደረግባቸው አድርጓል።

የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ-ግብር መረጃን ሰብስቦ ማደራጀት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ዝግጅት መጠናቀቁንም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በቅርቡ አስታውቋል። እስከአሁን ባለው ሂደትም የ3 ሺህ 900 የችግኝ ጣቢያ ማዕከላትና የ12 ሺህ የመትከያ ሥፍራዎች የጂኦ-ስፓሻል መረጃ መሰብሰቡን ይፋ አድርጓል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ-ግብር ይፋ ከተደረገ ጀምሮ በመረጃ የታገዘ የቴክኖሎጂ ሥራ ሲከናወን ቆይቷል። በዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ-ግብር ላይም በችግኞች የጽድቀት መጠን ላይ ክትትል ማድረግ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁ ተገልጿል።

በመጨረሻም በዘንድሮ አረንጓዴ ዐሻራ መርሀ-ግብር መላው ሕዝብ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጥሪውን ማስተላለፉም ታውቋል።

እኛስ እጃችን ከምን? መጪዎቹን የክረምት ወራት ምን ይዘን ልንቀበላቸው ተዘጋጅተናል? የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ-ግብር ልክ እንደታላቁ ሕዳሴ ግድባችን ዐቢይ ሀገራዊ አጀንዳችን ነው። ለዛሬይቱም ይሁን ለነገይቱ ኢትዮጵያ ሕልውና መሠረት የምንጥልበት መሆኑም የታወቀ ነው። በልምላሜ የተዋበች፣ ነፋሻና ተመራጭ የአየር ንብረት ያላት፣ ድርቅ የማይበግራት ፣ ለም አፈሯ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ የደን ሀብት ያላት ፣ በደኖቿ ውስጥ የሚንፎለፎሉ ምንጮችን ፣ አዕዋፍ እና የዱር እንስሳትን የያዘች ፣ የማይነጥፉ ወንዞች እና ያልተዛባ የአየር ጸባይ ያላት ኢትዮጵያ እንድትኖረን በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብሩ ላይ ተሳትፈን ችግኞችን በመትከል የድርሻችንን ጠጠር እንወርውር። መጪዎቹ ወራት የአረንጓዴ ዐሻራችንን ማህተም የምናሳርፍባቸው ነጭ ወረቀቶች ናቸውና ተዘጋጅተን እንጠብቃቸው፤ ሞሽረን እንሸኛቸው።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2016

 

 

Recommended For You