
አዲስ አበባ– ሀገሪቷ ባለፉት አምስት ዓመታት በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና ልማት ላይ የሠራችው ሥራ የግብርናውን ዘርፍ በዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት መደገፍ አስችሏል ሲል የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢትዮጵያን እናልብስ ተብሎ በተከናወኑ ተግባራት ኢትዮጵያ የፍራፍሬ ምርትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ቀዳሚ ስፍራ ላይ እንድትገኝ ያስቻለ ሲሆን በተለይም የአቮካዶ ምርትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከኬንያ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓል ሲል ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ እንደገለጹት ሀገሪቷ ያላትን ለም መሬት፣ የውሃ እና የሰው ሀብት አስተባብራ ማልማት ስላልቻለች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ሳትችል ቆይታለች። ይህም የግብርናው ዘርፍ ኢኮኖሚውን ከመደገፍ እና ከማሳደግ አንፃር በሚፈለገው ደረጃ ሳያድግ እንዲቆይ አድርጓል።
በተለይም ባለፉት 10 እና 15 ዓመታት ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተዳምሮ እያደጉ በመልማት ላይ ያሉ ሀገራት ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።
በሀገሪቷ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ መንግሥት በወሰደው ቁርጠኛ አቋም የተፈጥሮ ሃብቶች እንዲለሙ፣ የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ፣ የተጨፈጨፉ ደኖች እንዲመለሱ፣ የአፈርና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በጥራት እና በፍጥነት እንዲሠራ አድርጓል። ይህም የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ግብርናውን በዘላቂነት እንዲደግፍ እና ከግብርና ዘርፍ የሚገኙ ውጤቶች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ በማስቻል ላይ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር “ኢትዮጵያን እናልብስ” ፕሮግራም ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት 32 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች እንድትተክል ማድረጉን አስታውሰው ከእነዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት ችግኞች በአርሶ አደር ጓሮ ለምግብነት እንዲያገለግሉ ተደርገው የተተከሉ ናቸው ብለዋል።
በዚህም የተተከሉት ችግኞች ደርሰው እና ፍሬ አፍርተው ኢትዮጵያ የፍራፍሬ ምርትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ስፍራ እንዲኖራት አድርጓቷል። በተለይም የአቦካዶ ምርትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከኬንያ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች ሲሉም ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የተተከሉት 35 በመቶ የሚሆኑት ችግኞች ደግሞ ጎርፍን ለመከላከል፣ የተራቆቱ ተራሮችን አረንጓዴ ለማድረግ፣ የተመናመነውን የደን ሽፋን ለመመለስ፣ የአፈርን መሸርሸር ለመከላከል እንዲሆኑ ተደርገው የተተከሉ መሆኑን ተናግረው ይህም ሀገሪቱ የግብርና ዘርፍ በዘላቂነት የአየር ንብረት ለውጥን ተቋቁሞ ዘላቂ ኢኮኖሚ ለመገንባት እያገዘ ነው በማለት አብራርተዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተዘጋጁት ችግኞች ውስጥ 5 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከተማዎችን ለማሳመር እና ለማስዋብ የተተከሉ ሲሆን ይህም የአየር ንብረት ለውጥን በገጠር ብቻ ሳይሆን በከተማም ለመከላከል ያለመ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በዘንድሮ ዓመትም በሀገር አቀፍ ደረጃ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን በመተግበር ኢትዮጵያን በአረንጓዴ የማልበስ ሥራ ለማከናወን እንዲቻል በ123 ሺህ የችግኝ ጣቢያዎች ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል። በዚህም የበልግ አብቃይ የሆኑ የሀገሪቱ ክፍሎች የችግኝ ተከላ የጀመሩ ሲሆን ሌሎች አካባቢዎች ደግሞ በጥር እና በየካቲት በሚሠሩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች አማካኝነት ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ብለዋል።
በዚህም ለችግኝ መትከያ የሚሆኑ ቦታዎች ተለይተዋል፣ የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ እየተከናወኑ ይገኛል፣ የተፋሰስ ሥራም ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር ተቀናጅቶ እንዲሠራ አስችሏል። በዚህም ሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠቀም ዘላቂ የግብርና ሥራ እንዲኖራት አስችሏል ሲሉ ተናግረዋል።
ኤፍሬም አንዳርጋቸው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም