ለበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ይበልጥ መጎልበት

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቅን ልብ ያላቸው፣ በጎ አሳቢ ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት የሚፈጸሙት መልካም ተግባር ነው፤ ለሚፈጸሙት በጎ ተግባር ምንም አይነት ክፍያ ሳይጠይቁ ባደረጉት በጎ ተግባር ብቻ የሚደሰቱና፤ የሕሊና እርካታም የሚያገኙ ነው፡፡ በጎ ተግባር በሁሉም የእድሜ ክልል፣ በሁሉም የሕይወት መስክ፣ ወዘተ ያሉ ዜጎች ያለምንም ገደብ የሚሳተፉበትና ሰው በመሆናቸው ብቻ የሚፈጸሙት ተግባር መሆኑም ይታወቃል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሌሎች አገልግሎቶች ይለያል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ሰዎች ማንም ሳያስገድዳቸውና ሳያነሳሳቸው በራሳቸው ፈቃድ፣ በሕሊናቸው መሪነት፣ ከውስጣቸው በሚመነጭ መልካም ስሜት ተነሳስተው ጊዜና ሁኔታዎች ሳይገድባቸው ለማኅበረሰቡ ይጠቅማሉ የሚሏቸውን ተግባራት የሚከወኑበት በመሆኑ ነው፡፡ በበጎነት መንገድ የሚጓዙ ሰዎች ሁልጊዜም ለጊዜያቸው፣ ለጉልበታቸውና ለገንዘባቸው ምንም ሳይሰስቱ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡

ሀገራችን ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆኑም፣ በራሳቸው ተነሳሽነት ወገኖቻቸውን ለማገዝና ለመረዳት በመፈለግ ለትውልድ የሚተርፍ የበጎ ፈቃድ ሥራ ሠርተው ያለፉና እየሠሩ የሚገኙ በተምሳሌትነት የሚጠቀሱ በጎ አድራጊዎች እንዳሏት ይታወቃል፡፡ በእነዚህ በጎ አድራጊዎች የተጀመሩ ሥራዎች በትውልድ ቅብብሎሽ እያደር እየሰፉና እያደጉ ድጋፍ ለሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ እየሆኑ መምጣታቸው እንዳለ ሆኖም፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው በጎ ፈቃደኛ ዜጎች ለእነዚህ በጎ ፈቃደኞች ድጋፍ በማድረግም ይሁን በራሳቸው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኅብረተሰቡን በቀጥታ ለመድረስ አስተዋፅዖ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

በዚህ በጎ ተግባር ወጣቶች፣ ባለሀብቶች፣ ተቋማት፣ በስፋት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ወጣቶች በየሰፈራቸው በማኅበር በመደራጀት፣ በትምህርት ተቋማት አስተባባሪነት የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስልቶችን በመጠቀም በቀያቸውና በአካባቢያቸው ላሉ ደጋፊና ረዳት ላጡ አቅም ደካማዎች፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችና አካል ጉዳተኞች በራሳቸውም አቅማቸው በፈቀደ መጠን፣ ሌሎችንም በማስተባበር የምግብና የልብስ ድጋፎችን ለአገልግሎቱ ፈላጊዎች ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡

ወጣቶቹ በአቅራቢያቸው የተቸገሩ ወገኖቻቸውን አይተው እጃቸውን ከመዘርጋት ወደኋላ እንደማይሉ ሁሉ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተካሄዱ ጦርነቶች ተፈናቅለው ለነበሩና በድርቅ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖቻቸው አለን በማለት ከጎናቸው በመቆም ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ደም በመለገስ፣ አልባሳትንና የምግብ ሸቀጦችን በማቅረብ አለኝታነታቸውን አሳይተዋል፡፡ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እያከናወነ ባለው በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ በአካባቢ ፅዳት፣ ተማሪዎችን በማስጠናትና በመሰል የበጎ ተግባራት አገልግሎቶች ላይ በመሳተፍ ወገኖቻቸውን በማገልገል ለወገንና ለአገር አለኝታነታቸውን ሲያሳዩ ቆይተዋል፡፡

ይህን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለይ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ሰፋ ባለ መልኩ ለማስኬድ የተሞከረበት ሁኔታ እንዳለም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህም የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል በመሄድ ይሰጥ የነበረበት ሁኔታ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ በወቅቱም በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ አንድ ሺህ ተመራቂ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

አገልግሎቱ ዜጎች ያለማንም አስገዳጅነት ለሚኖሩበት ማኅበረሰብ ልማትና ለአካባቢ ደኅንነት የራሳቸውን አስተዋፅዖ የሚያደርጉበት ስለሆነ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዚህ መልካም ተግባር የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

ይህ ተግባር ከለውጡ በኋላም በበለጠ ሁኔታ እየተስፋፋና እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ ሥራው ከዓመት ወደ ዓመት መሻሻሎች እየታዩበት እያደገና እየሰፋ መጥቶ አሁን ላይ በርካታ ዜጎች የሚሳተፉበትና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችም ተጠቃሚ እየሆኑበት የሚገኝ መሆን ችሏል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ አገልግሎቱ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎም ሥራው በኮሚሽን ደረጃ አደረጃጀት ተሠርቶለት እየተተገበረ ይገኛል፡፡ በኦሮሚያ ክልልም በዜግነት አገልግሎት በኩል እየተሠራበት ነው፡፡

ይህ የበጎ አድራጎት ተግባር ባለፉት ዓመታት ደግሞ ከወጣቶቹም ባለፈ በባለሀብቶች፣ በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ይበልጥ በተጠናከረ መልኩ በበዓል ወቅቶች በማዕድ ማጋራት፣ በአቅመ ደካሞች ቤቶች እድሳት ይበልጥ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ሥራው እየሰፋና በተደራጀ አግባብ እየተመራ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ በኮሚሽን ደረጃ እየተመራ ያለበት ሁኔታም ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል፡፡

ይህን የበጎ አገልግሎት ተግባር በሀገር ደረጃ ለማስፋትም እየተሠራ ነው፡፡ በሠላም ሚኒስቴር፣ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ትምህርት ሚኒስቴር በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ እየተሠራ ስለመሆኑ በቅርቡ ተቋማቱ በጋራ ከሰጡት መግለጫ መረዳት ይቻላል፡፡ ዘንድሮም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በሀገር ደረጃ ጭምር በሁሉም ቦታዎችና አካባቢዎች ላይ እንዲካሄድ እንደሚደረግም ተቋማቱ አስታውቀዋል፡፡

አገልግሎቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያሳተፍ እንደመሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ እየተሳተፉም ይገኛሉ፡፡ በተለይ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ብዙ ዜጎች እየተሳተፉበት ሲሆን፣ አገልግሎቱን በበጋ መስጠት የተጀመረበት ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡

የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሸረሸረ የመጣውን የኢትዮጵያውን የአብሮነት እሴት ለማደስ አይነተኛ ሚና ያለው በመሆኑ እንደ ሀገር አገልግሎቱ እንዲያንሰራራ ለማድረግና ለማስፋት በመንግሥት በኩል እየተሠራ ነው፡፡ በዚህ በኩል በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ባለፉት ዓመታት በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በአገልግሎቱ የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤት በማደስ በርካታ ዜጎችን ከደሳሳ ቤት ማውጣት ተችሏል፤ ይህን ሥራ በማስፋትም ባለሀብቶችን በማስተባበር ከእድሳትም ባሻገር በአዲስ የመገንባት እንዲሁም በርካታ ወለል ያላቸውን መኖሪያ ቤቶች በመገንባት ለአቅመ ደካሞችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች እየተላለፉ ናቸው፡፡

ዘንድሮም በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰፋፊ ሥራዎችን ለመሥራት ታቅዷል፡፡ የዚህ መልካም ተግባር ባለቤት ሆነው ዓመታትን በዘለቁት ወጣቶች የሚከናወኑት ማኅበረሰብ ተኮር የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› እንዲሉ አበው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሳተፉ ወጣቶችም የአቅመ ደካሞችን ቤት ከመጠገን መልሶ እስከ መገንባት የዘለቀ ተግባርን ጨምሮ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች በመሰማራት ማኅበረሰቡን የሚያገለግሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሠላም ሚኒስቴርና ትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተመለከተው፤ በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሀገር ደረጃ 40 ሚሊዮን የሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች ይሳተፋሉ፡፡ “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው ይህ የክረምት በጎ አገልግሎት 50 ሚሊዮን የማኅበረሰብ አካላትን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተመላክቷል፡፡

በአገልግሎቱ ወጣቶች አሁን የሚያከናውኑት ማኅበረሰብ ተኮር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሀገራቸው ያላቸው ቀና አስተሳሰብ፣ ፍቅር እና ክብር መገለጫ ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ‹‹ሀገሬ ለእኔ ምን ሠራችልኝ›› የሚለውን ቢሂል ትተው ‹‹እኔስ ለሀገሬ ምን ሠራሁላት፤ ምን መሥራት እችላለሁ›› እያሉ ራሳቸውን እየጠየቁ ለነገ የሀገራቸው ብልጽግና የሚታተሩ፣ ለነገው ትውልድም አሻራ የሚያስቀምጡ ናቸው፡፡

እነዚህ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የተሰማሩ የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ከሚሰጡት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተጨማሪ በሀገሪቱ እየመጣ ያለውን ለውጥ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ ወደ ብልጽግና የሚደረገው ጉዞ ግቡን እንዲመታ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ይጠበቃል፡፡ ወጣቶቹ ይህን በጎ ተግባራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉና ሥራውም ዘላቂነት ያለው ሆኖ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ መንግሥትን ጨምሮ የተቀረው ማኅበረሰብ በሙሉ ወጣቶቹን ማበረታታትና ከጎናቸው መሰለፍ ይኖርበታል ባይ ነኝ፡፡

ትንሳኤ አበራ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You