ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት ከታደሉ ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ነች። ሁሉም አይነት የአየር ፀባይ፣ ሥነ ምህዳር፣ እፅዋት፣ የዱር እንስሳት (ብርቅዬ የሚባሉትን ጨምሮ)፣ አእዋፋት እና ልዩ ልዩ ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በውስጧ አስማምታ ይዛለች። የሥነ ምድራዊ አወቃቀርና ይዘት በራሱ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችንና ጎብኚዎችን ትኩረት የሚስብ ነው።
ኢትዮጵያውያን ከዚህ የተፈጥሮ ፀጋ ጋር ተስማምቶ የሚኖር ባህል፣ እሴት እንዲሁም ታሪክ አላቸው። በተፈጥሮ የተሰጣቸውን ሀብት የመጠበቅና በአግባቡ የመጠቀም ልምድን ለዘመናት አዳብረው እንደኖሩ የታሪክ መዛግብት ይነግሩናል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለተፈጥሮ ጥበቃ እና ልማት አመቺ የሆነ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እንዲሁም መንግሥታዊ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ይታወቃሉ። የዱር እንስሳት፣ አእዋፋት እና ለሥነ ምህዳር መጠበቅ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን ፍጥረታት ለምድራችንም ሆነ ለሰው ልጆች በእጅጉ አስፈላጊ መሆናቸውን ዛሬ ሳይሆን ከጥንትም የተረዱ ናቸው።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብትን፣ በውስጣቸው የሚኖሩ የዱር እንስሳትን እንዲሁም አእዋፋትን የሚጠብቅ፣ የሚያለማና በቱሪዝም ከጎብኚዎች ተጠቃሚ እንድትሆን የሚሠራ መንግሥታዊ አደረጃጀት ፈጥራለች። ይህ ተቋም የቱሪዝም ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማቶች መካከል አንዱ ሲሆን የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የሚል ስያሜን ይዟል። ባለፉት ዘመናትም በተለያዩ አደረጃጀቶች ፓርኮችን፣ ጥብቅ ሥፍራዎችን እንዲሁም የዱር እንስሳትን የማስተዳደር ድርሻ ወስዷል።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከሰሞኑ በሰጠው መግለጫ ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚሠራቸው ተግባራትና ሃላፊነቶች ዙሪያ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የማህበረሰብ ክፍሎች የግንዛቤ እጥረት አጋጥሞኛል›› በማለት ማብራሪያዎች ለጋዜጠኞች ሰጥቶ ነበር። በተለይ በተከለሉ ፓርኮች፣ ጥብቅ ቦታዎችና በውስጣቸው በሚኖሩ የዱር እንስሳት፣ አእዋፋትና መሰል ፍጥረታት ላይ አደጋ የሚጋርጥ ሕገ-ወጥ ተግባራት፣ የተዛቡ የመገናኛ ብዙሃን ምልከታዎች፣ ዘመናትን የተሻገሩ የተፈጥሮ ጥበቃ ባህልና አመለካከቶችን የሚጎዱ ተግባራት መስተዋላቸው በማንሳት ማብራሪያ ይሻሉ ባላቸው ጉዳዮች ምላሽ ሰጥቷል።
አቶ ኩመራ ዋቅጅራ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ዘመናዊው የተፈጥሮ ጥበቃ አስተሳሰብ የኢንዱስትሪ አብዮት መስፋፋትን ተከትሎ እአአ በ1714 አካባቢ በአውሮፓ ተዋውቋል። ዋናው ምክንያት ደግሞ የሰው ልጆች የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠን በላይ የመጠቀምና በውስጡ የሚገኙ የዱር እንስሳት፣ ፍጥረታትና ሥነ ምህዳሩ አደጋ እያስከተለ በመምጣቱ ነው። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከዚህም ቀደም ብሎ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከንጉሥ ዘርያዕቆብ ጀምሮ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የማድረግ ልማድና ባህል ነበራት። ለዚህ ምሳሌ ንጉሡ ከዛሬ 500 ዓመት ቀደም ብሎ በወጨጫ ተራራ እንዲሁም፣ ጓሳ ሳርን ለመጠበቅ በመንዝ ጓሳ የተደረጉ የጥበቃ ሥራዎች ማስረጃ ይሆናሉ።
‹‹የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እንዲሁም ፓርኮችን የማስተዳደር ተግባርን ከውጪ ተፅእኖና ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ጋር ማያያዝ ተገቢነት የለውም›› የሚሉት የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ፤ በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃንና በዲጂታል ሚዲያው የሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎች ትክክል አለመሆናቸውን ይናገራሉ። ተፈጥሮንና የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ ሃይማኖታዊም ሳይንሳዊም ድጋፍ ያለውና የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመግለፅም ባለሥልጣን መሥሪያቤቱ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚያከናውናቸው ተግባራት በማህበረሰቡ ዘንድ የተሳሳተ እሳቤ እንዲይዝ መደረጉ ፍፁም ስህተት እንደሆነ ይናገራሉ።
የብዝሃ ሕይወት መጥፋት፣ የአየር ንብረት ለውጥና ብክለት ዓለማችንን በእጅጉ እያሳሰባት መሆኑን የሚያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህ ቀጥተኛ ተጋላጭ ከሆኑት ውስጥ ኢትዮጵያና ሌሎች ታዳጊ ሀገራት እንደሚገኙበት ያብራራሉ። ይህንን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ተቋማትና የሀገራት ህብረት ልዩ ልዩ የትብብር ማእቀፎችን በማዘጋጀት እየሠሩ መሆኑን ያስረዳሉ። ከእነዚህ ስምምነቶች መካከል የ2015 የፓሪሱ ስምምነት፣ የ2022 የሞንትሪያል የብዝሃ ሕይወት ማዕቀፍ ስምምነት፣ የዘላቂ የልማት ግቦች ‹‹sustainable development goal (SDG)›› እንደሚገኙበት ይናገራሉ። ኢትዮጵያም በእነዚህ ዓለም አቀፍ ተግባሮች ላይ አባል በመሆን ስምምነቶቹን ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራች መሆኑን ያነሳሉ። ከዚህ ባሻገር በ1966 የዓለም የተፈጥሮ ጥበቃ ሀብረት አባል እንደሆነችና ያንን ቃልኪዳን እያከበረች እንደምትገኝ ያስረዳሉ።
ሁሉም ፍጥረታት ለምድራችንም ሆነ ለሁለንተናዊ (universe) አስፈላጊ መሆናቸውን የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ብዝሀ ሕይወትን ለመጠበቅ ኢትዮጵያ ከዘመናዊው የተፈጥሮ ጥበቃ አጀማመር አስቀድማ ጥብቅ ቦታዎችን በመከለል እካሁን ድረስ ማቆየት እንደቻለች ያስረዳሉ። በዚህ እሳቤ አሁንም ድረስ የተከለሉ ፓርኮች፣ ጥብቅ ደኖች፣ የዱር እንስሳትና ፍጥረታት መኖሪያዎች መኖራቸውን ይናገራሉ። በምሳሌነትም በ15ኛው ክፍለ ዘመን የሱባ ደን ጥበቃ መጀመሩ፣ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የመንዝ ጓሳ ማህበረሰብ ባህል መሠረት የጥበቃ ተግባራት እንዲሁም በ1909 ዝሆን ማደን የሚደነግግ አዋጅ መታወጁን እንደምሳሌ አንስተዋል።
ከዚያ ባሻገር በአፄ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት ንጉሡ ጎረቤት ሀገራት በመሄድ በጎበኙበት ወቅት ያገኙትን አዲስ የተፈጥሮ አጠባበቅ ልምድ በኢትዮጵያም እንዲተገበር በመወሰናቸው ምክንያት የአዋሽ፣ ማጎ፣ ኦሞና በስምጥ ሸለቆ የሚገኙ ፓርኮች መመስረታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። ንጉሡ ለዩኒስኮ በፃፉት ደብዳቤ መፃፋቸውንና የባለሙያዎች ድጋፍ ማግኘታቸውን ያስረዳሉ። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ግን በመገናኛ ብዙሃን ማህበረሰቡ ለተፈጥሮ ጥበቃ ያለው አመለካከት እንዲዛባና በሀብቱ ላይ ጉዳት እንዲደርስ አሳሳች መረጃ የሚያሰራጩ፣ ሕገወጥ እርሻን፣ ሰፈራን እንዲሁም ሌሎች አሉታዊ ተግባራትን የሚያበረታቱ አካላት መኖራቸውን ያስረዳሉ። ይህ እሳቤም ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው ያነሳሉ።
ሁሉም በምድር ላይ የሚኖሩ ፍጥረታት በምክንያት እንደተፈጠሩ የሚናገሩት አቶ ኩመራ፤ በተፈጥሮ ሚና የሌለው ትርፍ የሆነ አንዳችም ነገር እንደሌለ ይገልፃሉ። የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች ሲቋቋሙም ለቅንጦት ሳይሆን ለህልውና ጉዳይ መሆኑን ያስረዳሉ። የሥነ ምህዳር ጤና መጓደል ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደሚያስከትሉ በማንሳትም ይህንን ችግር አስቀድሞ ለመከላከል ኢትዮጵያ ከጥንትም በባህላዊና ሃይማኖታዊ መንገድ ትሠራ እንደነበር ያነሳሉ። ለዚህ እንደማሳያ የሚገልፁት የስንቅሌ ቆርኪዎችን ለመጠበቅ አባገዳዎች የሚጠቀሙትን ስልት ሲሆን። በሻሸመኔ አቅራቢያ ስንቅሌ በሚባል ቦታ ላይ የሚኖሩ ቆርኪዎችን እንደ አንድ ጎሳ በመቁጠር በአደንም ሆነ በልዩ ልዩ ምክንያት ቆርኪዎችን የገደለ ማንኛውም ነዋሪ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጣልበት ይገልፃሉ።
ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚገልፁት በዘመናዊው የተፈጥሮ ጥበቃ ኢትዮጵያ ፓርኮችን፣ ጥብቅ ቦታዎችን በመከለል፣ በማልማት የምትጠብቅ ሲሆን ከሀገሪቱ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት እስካሁን ከተከለለው ጥብቅ ሥፍራ ውስጥ የደን ሽፋን ያለበትን ጨምሮ 14 በመቶ እንደሚሆን ይናገራሉ። አማካዩ የዓለም የጥበቃ ቦታዎች ሽፋን 17 በመቶ ሲሆን እዚህ መስፈርት ላይ እንዳልተደረሰ ያስረዳሉ። ጥብቅ ቦታዎችን በመከለል የብዝሃ ሕይወት እልቂትን መታደግ የአየር ብክለትና ለውጥን መከላከል እንደሚቻል ያስረዳሉ።
እአአ በ2015 የፓሪስ ስምምነት የዓለም ሙቀት ከሁለት ዲግሪ ሴሊሺየስ እንዳይበልጥ 185 ሀገራት የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰዋል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያም የዚህ ስምምነት አካል እንደሆነች ይገልፃሉ። በተመሳሳይ በ2022 በሞንትሪያል ካናዳ ላይ የዓለም የብዝሀ ሕይወት ማእቀፍ በተመለከተ የሰው ልጅ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁንና የብዝሀ ሕይወት እልቂት እየጨመረ መምጣቱን ሀገራት በመገንዘባቸው ምክንያት ይህንን አደጋ ለመከላከል የጥበቃ ቦታ ሽፋን ማሳደግ እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በዚህም በ2030 ከ 17 በመቶ ሽፋን ወደ 30 በመቶ ለማድረስ እቅድ መኖሩን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ የልማት ግቦች ከተፈጥሮ ጥበቃ ጋር የተቆራኙ ናቸው የሚሉት አቶ ኩመራ የ 17ቱ ዘላቂ የልማት ግቦች ‹‹sustainable development goal SDG›› ውስጥ 11 እና ከዚያ በላይ የሚሆኑት ከዚህ ዓላማ ጋር እንደሚተሳሰሩ ይናገራሉ። ደህነትን ለመቀነስ፣ የታዳሽ ሃይል፣ ተፈጥሮን መሠረት ያደረጉ መፍትሄዎችን ለማምጣት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ከዚሁ ጋር እንደሚያያዝ ይናገራሉ። ኢትዮጵያም እነዚህን ግቦች ለማሳካት ዓለም አቀፍ ቃልኪዳኖችን መግባቷን ይገልፃሉ።
መንግሥት ከላይ የተነሱትን ቁልፍ ጉዳዮች ተፈፃሚ ለማድረግና የተፈጥሮ ቦታዎችን ለመጠበቅ ጥረት እያደረገ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ኩመራ፤ ይሁን እንጂ ግቡ እንዳይሳካ በርከት ያሉ ፈተናዎች መኖራቸውን ያስረዳሉ። ከእነዚህም ውስጥ በፓርኮችና የተፈጥሮ ጥብቅ ቦታዎች ላይ ሕገወጥ የሰው ሰፈራ፣ እርሻ፣ ሕገወጥ አደን፣ አሳ ማስገር፣ የደን ጭፍጨፋ እና መሰል ተግባራት መስፋፋታቸውን ይናገራሉ። ይህ የሚከሰተው ከግንዛቤ እጥረት መሆኑን አንስተውም ችግሮቹን በዘላቂነት የሚፈታ ሥራዎች እየተተገበሩ መሆኑን አንስተዋል።
ሌላው አሳሳቢው ጉዳይ ነው በማለት ዋና ዳይሬክተሩ ያነሱት በብሔራዊ ፓርኮች በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የእሳት ቃጠሎን ሲሆን ለእሳት አደጋ ተጋላጭ ለሆኑ እንደ ቃፍታ ሽራሮ፣ ሰሜንና ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮች የእሳት አደጋ ለመቀነስና መከላከል የእሳት አደጋ ብርጌድ መቋቋሙን እንዲሁም አስፈላጊ ግብዓት መሟላቱን ተናግረዋል። ወደፊትም አስቀድሞ የመከላከልና የአቅም ግንባታ ስትራቴጅ ተግባራዊ እንደሚደረግ አንስተዋል።
እንደ መውጫ
በመግቢያችን ላይ እንዳነሳነው ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብትና በብዝሀ ሕይወት ስብጥር ከሚታወቁ ሀገራት ቀዳሚዋ ነች። ከእነዚህ እፁብ ድንቅ ሀብቶች ጋር ተስማምቶ የሚኖር ማህበረሰብና ባህልም አላት። ለዚህ ማሳያ እሩቅ ሳንሄድ በያዝነው ዓመት በዩኒስኮ የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ የተመዘገበውን የጌዲዮ ባህላዊ መልከዓምድር መመልከት እንችላለን። ማህበረሰቡ ከብዝሀ ሕይወትና ከዱር እንስሳት ጋር እራሱን አዋህዶ የመኖር ጥበብም የታደለ ነው። ይህንን እሴት ከምንም ነገር በላይ መጠበቅ ቀዳሚው ሊሆን ይገባል። በሌሎች ጥብቅ ፓርኮች እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የጌዲኦን ማህበረሰብ ባህል፣ የአባ ገዳ አባቶችን ብልሃት እንዲሁም መሰል ሀገር በቀል ልምዶችን ተግባራዊ በማድረግ የብዝሀ ሕይወት ስብጥርን መጠበቅና ከእልቂት መታደግ ለነገ የሚቀመጥ የቤት ሥራ ሊሆን አይገባም።
የማህበረሰቡን ሥነ ልቦና፣ ልምድ እና እሴት የሚሸረሽሩ የተዛቡ የመገናኛ ብዙሃን መረጃዎች፣ የዲጂታል ሚዲያ አሉባልታዎችም መመከትም ይገባል። የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የሚያከናውናቸውን ተግባራት መደገፍም ይገባል። ይህ ሲሆን የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብቶች መጠበቅ፣ ማልማት እንዲሁም ማህበረሰቡን ያካተተ የተፈጥሮ ቱሪዝም አቅምን ለመገንባት ይቻላል።
ዳግም ከበደ