የሜሪ ጆይ እናት

በጎ ተግባር በአምላክም በሰውም ዘንድ የሚወደድ ነው። ጊዜ ጥሏቸው አልያም በህመም እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ብቻ እጅ አጥሯቸው የእለት ጉርሳቸውን መሸፈን የተሳናቸውን እናትና አባታቸውን በሞት ተነጥቀው ጎዳና የወጡትን ብቻ በጠቅላላው ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች ሁሉ አልሟላ ብሏቸው የቀን ጨለማ ወርሷቸው የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማገዝና መርዳት መልካም የሆነ ተግባር መሆኑ መቼም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም።

ይህንን ሥራ መሥራት ደግሞ በፈጣሪ ዘንድ የሚያስገኘው በረከት ቀላል አይደለም፤ ነገር ግን ይህንን ሥራ ለመሥራት ብዙዎች ቢመኙም የሚሳካላቸው ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ምናልባት እነዚህ ሰዎች ለዚህ ሥራ የተፈጠሩ ሆነው አልያም በልምድ በቤተሰብ የወረሱት የደግነት፣ የመስጠት፣ ለሌሎች የመኖር ልምድ ኖሯቸውም ሊሆን ይችላል።

ያም ሆነ ይህ ግን የሚሰጡ እጆች ሁሉ የተባረኩ ናቸውና የወደቀን የሚያነሱ፣ የተረሳን የሚያስታውሱ፣ የተራበን የሚያበሉ፣ የተጠማን የሚያጠጡ ፣ የታረዘን የሚያለብሱ ሁሉ ከሰማያዊ በረከታቸው በተጨማሪ በምድርም ታላቅ ናቸውና ሊከበሩ ሊወደሱ ይገባል።

እንደ ሀገርም እኛ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የመስጠት፣ አብሮ የመብላት፣ የመጠጣት ፣ በደስታ፣ በሃዘን፣ የመገናኘት፣ የመረዳዳት ብቻ የጎረቤቱ መቸገርና ማጣት የራሱ ሆኖ የሚሰማው ማህበረሰብ ውስጥ እንዳደገ ሕዝብ መረዳዳትን ባህል ማድረጉ ጠቃሚ ነው።

ከዚህ ማህበረሰብ ወጥተው ደግሞ የግል ጥረታቸውን አክለው የራሳቸውን ኑሮና ሕይወት ወደጎን አድርገው የኔ መኖር ለወገኔ ነው ብለው በርካታ በጎ ሥራዎችን የሚሠሩ ብዙ ሰዎች አሉን።

ከእነዚህ ወገኖች መካከል ደግሞ ተርፏቸው ሳይሆን ካላቸው ላይ ለማካፈል ቆርጠው በመነሳት በጀመሩት የበጎ ተግባር ሥራ ዛሬ ላይ ለብዙዎች ብርሃን የሆኑ ሰዎች በዙሪያችን አሉ። ከእነዚህ ብርቱዎች መካከል ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ አንዷ ናቸው። ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ብዙዎች በልተው ጠጥተው ለብሰው ከነበረባቸው ችግር ተላቀው ቢታመሙ ታክመው እንዲኖሩ ምክንያት የሆኑ ሴት ናቸው።

በጥቂት ገንዘብና በትንሽ ችግረኛ ሰው የተጀመረው የሲስተር ዘቢደር ሜሪጆይ የርዳታ ድርጅት ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና ተደናቂ የብዙዎች ቤት ሆኗል። እኛም በዛሬ የሕይወት ገጽታ አምዳችን ላይ የዛሬ 31 ዓመት በፊት ሥራውን የጀመረውን ሜሪጆይ የርዳታ ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴን የሕይወት ተሞክሮ ልናጋራችሁ ወደናል።

ትውልድ እና ዕድገታቸው ጋሞ ዞን ጨንቻ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በደጃዝማች ወልደማርያም ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን የትምህርት እርከን የተማሩ ሲሆን ከዛም ከጨንቻ ወጣ ብሎ በሚገኘው ጦሎላ ምሽን የዘጠነኛ ክፍል ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ የ10 ክፍል ትምህርታቸውን ጨንቻ ተምረዋል። በአርባ ምንጭ ኮምፕሪሄሲቭ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ የ11 ኛና የ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ስለማጠናቀቃቸው ይናገራሉ።

“…በትምህርቴ በጣም ጎበዝ ነበርኩ፤ ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ እህቶቼ ከፍ ያለ ማበረታታት ያደርጉልኝ ስለነበር ነው፤ ለዩኒቨርሲቲም የምጠበቅ ነበርኩ። የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ላጠናቅቅ ስጠጋ እናቴ በጣም በመታመሟ ምክንያት ጭንቀት ውስጥ ገባሁ፤ ምንም እንኳን የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን በአንደኝነት ያጠናቀቅሁ ብሆንም መልቀቂያ ፈተናው ላይ ግን ውጤቴ የሚጠበቀውን ያህል ሳይሆን ቀረ” ይላሉ።

ይህ ሁኔታ ግን ሲስተር ዘቢደርን ከትምህርት አላስቀራቸውም ይልቁንም መምህራኖቻቸው የትምህርት አቀባበላቸውን እና ጉብዝናቸውን ስለሚያውቁት ነጥባቸው ባስገባቸው ቦታ ላይ ገብተው መማር እንዳለባቸው ስለገፋፏቸው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነርስነትን ለመማር መግባታቸውን ይናገራሉ። ትምህርት ቤቱ ሲገቡም የቀረበላቸውን የመግቢያ ፈተና በአንደኝነት ስለማጠናቀቃቸውም ያብራራሉ።

“…ገጠር መማር በራሱ አድማስን ያጠባል። በትምህርት ላቅ ያለ ደረጃ የደረሰን ሰው ስለማናይ ምናልባት ሳድግ እሆናለሁ ብለን ልንመኝ የምንችለው በቤታችን አልያም በጎረቤታችን ትንሽ ትምህርት ተምረው ሥራ የያዙ ሰዎችን ነው፤ እኔም የማየው ለምሳሌ እህቴ የስልክ ኦፕሬተር ነበረች። እንደሷ መሆን እፈልግ ነበር ፣ አስተማሪ መሆንም አስብ ነበር፤ ምክንያቱም ከጨንቻ ከፍ ካለም ከአርባ ምንጭ ወጥቼ አላውቅም፤ አዲስ አበባ ለትምህርት ስመጣ ነው የተማሩ ሰዎችን ማየት የጀመርኩት። ሴት የመኪና አሽከርካሪ እንኳን እንዳለ ያወቅሁት ያን ጊዜ ነው ” በማለት ይናገራሉ።

ሲስተር ዘቢደር አዲስ አበባ ከተማ ገብተው የነርስነት ትምህርታቸውን ሲማሩ ከትምህርቱ ባሻገር ሕይወት በራሱ አዲስ ሆነባቸው። የማያውቋቸውን ብዙ ነገሮች አወቁ። አዲስ አበባም ለእሳቸው እንግዳ በመሆኗ ከአስፋልቱ ጀምሮ መኪናው አኗኗሩ ብቻ ሁሉም ነገር አስገረማቸው። ከመገረምም አልፈው ግን እኔም እራሴን መለወጥ እንደ ከተማ ሰዎች መሆን አለብኝ ብለው ራሳቸውንም እንደገና የሠሩበት ወቅት መሆኑን ያብራራሉ።

“…እኔ ለቤተሰቤ አስረኛ ልጅ ነኝ። በእኔ ሁሉም እምነት ነበራቸው። ትልቅ ደረጃ ላይ እንድደርስም ከፍ ያለ ሥራ ነው ሲሠራብኝ የነበረው፤ እናም አዲስ አበባ መጥቼ መማሬ ሁሉም ላይ ከፍ ያለ ደስታን ከመፍጠሩም በላይ በማበረታታትም ሆነ የሚያስፈልገኝን ነገር አሟልተው እንድማር በማድረጉ በኩል እህቶቼ እንዲሁም መላ ቤተሰቤ ሚናው በቀላሉ የሚታይ አልነበረም” ይላሉ።

ስራ በጋሞ ጎፋ

ሲስተር ዘቢደር የነርስነት ትምህርትቸውን እንዳጠናቀቁ አርባምንጭ ሴቻ ላይ ነው የመጀመሪያ ሥራቸውን የጀመሩት። በዛም ትንሽ እንደሠሩ ትምህርቴን ማሻሻል ራሴንም መቀየር አለብኝ በማለት ፊታቸውን የኖርዌጃን ሚሽን ሆስፒታል አዞሩ፤ የሆስፒታሉን ማናጀር በማናገርም ወደ አዲስ አበባ የሚገቡበትን መንገድ ማፈላለግ ጀመሩ።

“…የሆስፒታሉ ማናጀር ባናገርኩት መሠረት ወደ አዲስ አበባ የምቀየርበትን መንገድ በተለያዩ ሁኔታዎች አድርገው አመቻቹልኝ፤ በዚህም አርባ ምንጭ ላይ ሁለት ዓመት ካገለገልኩ በኋላ በሶስተኛው ዓመት አዲስ አበባ የካቲት 12 ሆስፒታል መጣሁ”።

በ301 ብር የወር ደመወዝ ሥራቸውን የጀመሩት ሲስተር ዘቢደር ኑሮ ግን እንዳሰቡት ቀላል አልነበረም፤ ከሚያገኙት ገንዘብ ላይ ቤት ኪራይ ከፍለው ለምግብና ለተለያዩ ወጪዎች አውጥተው ከዛም ቤተሰቦቻቸውን መደገፍ የማይሆን ሆነባቸው።

ስለዚህ ሌላ አማራጭ ማየት እንዳለባቸው አሰቡ፤ በተፈጥሯቸው ተግባቢና ቅን ሴት ስለሆኑ ሰዎችን በሚያማክሩበት ወቅት ለምን ብለሽ ትቸገሪያለሽ ጳውሎስ ሆስፒታል ብትሄጂ ለነርሶች ቤት ስለሚሰጥ አትቸገሪም ባሏቸው መሠረት ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል አመሩ። በዛም እንደተባሉት ቤት አገኙ ሥራቸውንም በአግባቡ መሥራት ቀጠሉ። ይህም ቢሆን ግን የሚያገኙት ነገር በቂ ስላልነበር ወደ ኖርዌደጂያን ህጻናት አድን ድርጅት በመቀጠር የሥራ አካባቢያቸውን ከአዲስ አበባ ወደ ሊሙገነት አደረጉ።

“…አሁን የወር ደመወዜ ከ 347 ብር ወደ 1 ሺ 200 ብር ገባ፤ በዚህ ላይ የምኖርበት አካባቢ ገጠር በመሆኑ ወጪ የለብኝም ፤ በዚህም በማገኘው ገንዘብ እናትና አባቴ በደንብ እያገዝኩ እኔም በጥሩ ሁኔታ ሕይወቴን መምራት ቻልኩ፤ ነገር ግን ያ ፕሮጀክት የስራ ጊዜውን አጠናቆ ሲዘጋ አዲስ አበባ ላይ የሴቭ ዘ ችልድረን የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ስለነበር እዛ ለመሥራት አዲስ አበባ ገባሁ” በማለት የሥራ ቆይታቸውን ይናገራሉ።

የሜሪጆይ ውልደት

ሲስተር ዘቢደር ለሩብ ክፍለ ዘመን በዘለቀ የሰብዓዊነት አገልግሎት ዛሬ ላይ ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ህፃናትና ወጣቶች እናት ሆነው እየኖሩ ይገኛሉ።

ሲስተር ዘቢደር ከሜሪጆይ ምስረታ በፊት የሕዝቡን የጤና ችግር ለመቅረፍ በማሰብ በወቅቱ ብዙም ያልተስፋፋ የነበረውን የግል ክሊኒክ አነስተኛ ቤት በመከራየት ለመክፈት ችለው ነበር። ይህም ክሊኒክ በሚሰጠው አገልግሎት ዝናው ከፍ ያለ ነበር።

“…እናቴ ደግነትን አስተምራ ነው ያሳደገችኝ፤የሠራችን እናታችንን ናት ማለት ይቻላል፤ አባታችንም የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲኖረን አድርጎ አሳድጎናል፤ ይህ እናታችን የቀረጸችብን ደግነት በተለይም ሊሙ ገነት ስሠራ እየወጣ መጣ፤ የአርሶ አደር ልጆች ነው የማስተምረው። በዚህም ቤተሰቦቻቸው ለእኔ በጣም መልካምና ቅርብ ናቸው፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ውስጤ ያለውን ደግነት እንዳወጣ የረዳኝ ይመስለኛል ” በማለት የሜሪጆይን የመጠንሰስ ምክንያት ይናገራሉ።

በዚህን ወቅት ነበር ሲስተር ዘቢደር ያላሰቡት የሕይወት ትልቅ ገጠመኝ የተከሰተባቸው። በአፍንጫቸው ውስጥ እጢ መሰል ነገር በመውጣቱ የሚሰጡትን አገልግሎት ለማቆም ተገደዱ ።

ሲስተር ዘቢደር ከህመማቸው ለመፈወስ ብዙ ጥረቶችን አደረጉ ፤ሁኔታው ግን ከበድ ያለ ስለነበር ለመዳን ጊዜያትን ወሰደባቸው። ነገር ግን አምላክ ለትልቅ አገልግሎት ያጫቸው ነበሩና አጋሮ ውስጥ የምትገኘውን የጌራ ኪዳነምህረት ጸበል መጠቀም ጀመሩ። እሳቸውም ከህመሜ ከዳንኩ ብለው ወደ አምላካቸው ስለትን ተሳሉ። ልመናቸው ተሰምቶ ነበርና በስድስት ወራት ውስጥ ከህመማቸው ዳኑ። በተሳሉት መሠረትም ቀደም ሲል ከፍተውት የነበሩትን ክሊኒክ በመዝጋት የአምላክ ጥበብ የሚታይበትን ሥራ ለመሥራት ወሰኑ።

ከብዙ ውጣውረዶች በኋላ ከህመማቸው የዳኑት ሲስተር ዘቢደር ቀደም ሲል አስኮ ገብርኤል በማለት ከፍተውት የነበረውን ክሊኒክ በመዝጋት በ 1984 ዓ.ም ተጠንስሶ በ1986ዓ.ም ሜሪ ጆይ (ማርያም ደስታ ናት) የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ተወለደ።

“…ሜሪጆይን ስመሠርት ከህመም ያገገምኩበት ጊዜ ነው ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ እናታችን አስር ልጆችን ወልዳ አምስቱን ስለቀበረች ስድስተኛ እኔ እንዳልሞትባትና እንዳታዝን አብዝቼ እጨነቅ ነበር። ሰውነቴ በወሰድኳቸው መድሃኒቶች ተጎድቷል። እኔ የገጠር ተማሪ ነኝ እንደልቤ እንግሊዝኛ ተናግሬ ለጋሽ አካላትን ማሳመንና ድጋፍ ማግኘት ይከብደኛል፤ ነገር ግን በወቅቱ የሚያበረታቱኝ የሚረዱኝ ፕሮጀክት ፕሮፖዛል በመጻፍ ብቻ በሁሉም ነገር ከጎኔ የሆኑ ሰዎች ነበሩ፤ ግን ደግሞ አምላክ ዓላማ ስለነበረው ሁሉንም ነገር እኔ ካሰብኩት በላይ አመቻቸልኝ ” በማለት የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።

በሌላም በኩል ህብረተሰቡ እንደዚህ ዓይነት ተቋማት ላይ እምነት ጥሎ ያለውን መስጠት ይፈራል። ከዛ ይልቅ ቤተክርስቲያን ሄዶ ለሚለምነው መስጠትን ነው የሚመርጠው። በዚህም የመስጠት ባህል የሌለን ሕዝቦች መሆናችን በራሱ ለሲስተር ዘቢደር ፈታኝ ነበር።

“…ይህንን መሰል ወገን የሚጠቀምበትን ሥራ ለመሥራት ሀብት ንብረት አይደለም መሠረታዊው ነገር ዋናው ልብ ነው። መጀመሪያ ውስጥን ማሳመን ነው። እኔ በወቅቱ በጣም ወጣትና በ20ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ያለሁኝ ነኝ እናትና አባቴ ደካማና ታማሚ ናቸው። ይህ ሁሉ ነገር ብዙ ፈተናዎች ነበሩት። ሁኔታውም ለብዙ ሰዎች አስገራሚ ነበር። ነገር ግን በአምላክ ሁሉም ተችሏል”።

መልካም ሥራ ራሱ ይከፍከላል የሚባል ከአባባል በላይ የሆነ ነው። ሲስተር ዘቢደር በነርስነት ዲፕሎማቸው ላይ እንዳሉ ነው ለሌሎች ልኑር ብለው የራሳቸውን ነገር ሁሉ ትተው ወደ ግብረ ሰናይ ተግባር የገቡት። ይህንን ሥራቸውን የተመለከቱ ደግሞ እሳቸው ያስፈልጋቸዋል ያሉትን ነገር ያሟሉላቸው ጀመር።

ከእነዚህ መካከል የኖርዌጂያን የህጻናት አድን ድርጅት የመንግሥት ተወካይና የሂሳብ ክፍሉ ሃላፊ አንዱ ሲሆኑ እሳቸውም “…በስራሽ ተደስቻለሁ” በማለት አሜሪካን ሀገር በክረምት የትምህርት መርሃ ግብር ለስድስት ዓመት የዲግሪ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አደረጉ። በዚህ አላበቃም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን (ማስተርሳቸውን) ደግሞ ሆላንድ ያለ የኮርዴም ኢንተርናሽናል ድርጅት እዛው አሜሪካን ፒሪስተን ዩኒቨርሲቲ ላይ እንዲማሩ አመቻቸላቸው። ይኸው ትምህርት ቤት ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍኖ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሊያስተምራቸውም ወረቀት ሰጥቷቸዋል።

መቶ ሰዎችን በመርዳት ሥራውን በይፋ የጀመረው ሜሪ ጆይ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በርካታ መሠናክሎችን እንዳለፈ የሚገልጹት ሲስተር ዘቢደር እርሳቸውም በግላቸው በሜሪ ጆይ የተነሳ በርካታ ፈተናዎችን አሳልፈዋል።

ሜሪ ጆይ በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ በአምስት ክልሎች ላይ በሚገኙ 105 ወረዳዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማም ከ ስድስት ሺ 500 በላይ ሰዎችን በቀጥታ ተጠቃሚ በማድረግ ከ 10 ሺ በላይ ደግሞ የተለያዩ ድጋፎችን የሚያገኙ ሰዎች አሉት።

በዚህም ከ 36ሺ በላይ ታዳጊዎች፤ ከ10 ሺ በላይ ወጣቶች፤ ከ አምስት ሺህ በላይ አረጋውያን እንዲሁም ከስምንት ሺህ በላይ ጨቅላ ህፃናት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል። በሃዋሣ የህጻናት እና አረጋውያን ማዕከል የከፈተው ተቋሙ አሁን ደግሞ በአርባ ምንጭ ከተማ ተመሳሳይ አይነት ማዕከል ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ሜሪ ጆይ ዛሬ ላይ ከ አራት ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኞች ያሉት ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ታዋቂ ግለሰቦች፣ አርቲስቶች፣ የጤና ባለሙያዎች እና የተለያዩ ባለሀብቶች ይገኙበታል። የዚህ ታላቅ ድርጅት መሥራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር መሉ እድሜያቸውንና ጊዜያቸውን በሚባል ሁኔታ ለዚህ ድርጅት የሰጡ ሲሆን ለዚህም አስተዋጾዋቸው በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በርካታ ሽልማቶች እና የእውቅና ሰርተፍኬቶችን ለማግኘት ችለዋል።

“…ሜሪ ጆይ የተነሳበትንን አሁን ያለበትን ደረጃ ሳየው በጣም እገረማለሁ። አምላክ ሙሉ ክብሩን ይውሰድ፤ ይህ ታላቅ ሥራ በእኔ አቅም የሚሠራ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ በመገናኛ ብዙሃን ስለ ሥራዎቹ ስሰማ ፣ ሪፖርቶችን ሳይ የሌላ ሰው ድርጅት ሁሉ የሚመስለኝ ጊዜ አለ” በማለት ይናገራሉ።

የሰዎች እገዛ

ሜሪጆይ እዚህ እንዲደርስ በጣም ብዙ ሰዎች ሌት ተቀን ይሠራሉ ማለት ይቻላል። በዚህም ባለሀብቶች ታዋቂ ሰዎች አርቲስቶች ይሳተፋሉ። ሥራ አመራር ቦርዱ በጣም ጠንካራ ነው። ሠራተኞቹ ደግሞ ለበረከት ብለው የሚሠሩ ናቸው። በጣም ምስጋና ይገባቸዋል። ማኔጅመንቱ ሜሪጆይ ከፍ እንዲል ብዙ ይለፋል። በጠቅላላው ሜሪጆይ የሰው ሀብታም ነው ቢባል ይሻላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ሰዎች ድጋፋቸው ከጊዜው ጋር የሚሄድ ነወይ? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ ገና ነው ይሆናል። ምክንያቱም ድሮ መለመን በጣም አስነዋሪ ከመሆኑም በላይ እሳት የሆነው የሰው ፊት ላይ የሚቆመው ሰው በጣም የባሰ ችግር ውስጥ የገባ ብቻ ነበር። የምንሰጠውም ደግሞ ካለን ላይ ነበር። ዛሬ ላይ ግን የሕዝብ ቁጥራችን ጨምሯል ። አሁን ላይ ወደልመና የሚወጣው የተቸገረ ብቻ ሳይሆን ያለውም ነው። ሰጪውም ላይ የኑሮ ወድነት ተጭኗል። ነገር ግን እንደ እኛ በየሃይማኖቱ ሁሉም አማኝ ነው። ግን ካለን ላይ የማካፈሉ ሂደት ገና እየተለማመድነው ነው በማለት የመስጠት ባህላችን ገና እንደሚቀረው ይናገራሉ።

ገጠመኞች

ማንኛውም ሰው በመኖር ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙት መጥፎም ጥሩም አጋጣሚዎች አሉ። እንደ ሲስተር ዘቢደር ደግሞ ከብዙ የተቸገሩ ሰዎች ጋር የሚውል ሰው አስደሳችም አሳዛኝም አጋጣሚ አያጣምና ጥያቄዬን የማንሳቴ ምክንያት እርሱ ነው።

“…በጣም የተደሰትኩት የሃዋሳው የአረጋውያን ማዕከል አንድም የነጭ እጅ ሳይገባበት ኢትዮጵያውያን ተረባርበው ሠርተው የተመረቀ እለት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ከእኛ ጋር አብሮ ተባብሮ ለመሥራት በመወሰን የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገልን መሆኑ ሲሆን ይህም ባለፈው የሲዳማ ክልል 5 ሚሊዮን ብር ሰጥቶናል፤ በቅርቡ ደግሞ የደቡብ ክልል 10 ሚሊዮን ብር ሰጥቶናል፤ ይህ በጣም አስደሳች ከመሆኑም በላይ ሁለታችንም ለማህበረሰቡ የምንሠራውን ሥራ ፍሬያማ እንዲሆን ያደርገዋል” ይላሉ።

የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት ጉዳይ መፍትሔ አልባ መሆኑ ደግሞ ከሁሉም ነገር በላይ ልቤን ይነካኛል የሚሉት ሲስተር ዘቢደር እሳቸው ቀርበው ባዩት ልክ ሲናገሩም ልጆቹ በጣም ያሳዝናሉ። ህጻናቱ ከ9 ዓመት ጀምሮ ይደፈራሉ። በዚህም የማህጸን በሽተኛ ሆነዋል። ወንዶቹም ከችግሩ አላመለጡም። የትምህርት እድል ባለማግኘታቸው መጻፍና ማንበብ እንኳን አይችሉም። ይህ ሁኔታ ደግሞ በጣም እንቅልፍ የሚነሳ ነገር በመሆኑ መንግሥት ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል።

ሜሪጆይም በዚህ ዙሪያ ለመሥራት ገዳም ሰፈር ላይ ከበጎ ፈቃደኛ ቤት አግኝቶ ሥራውን ጀምሯል። ሁለተኛውንም የአዋጭ ብድርና ቁጠባ ተቋም መሥራችና ባለቤት አስኮ ላይ ማዕከል ስለሠሩልን በዛም ሥራውን ለመሥራት እየተንቀሳቀስን ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት የቀን ማቆያ (Day care ) አገልግሎት እየተሰጠንም እንገኛለን ይላሉ።

የቤተሰብ ሁኔታ

ብዙ ጊዜ በርዳታ ድርጅት ሥራ ላይ ያለን ሰዎች ሞልቶን ተርፎን የምንሰጥ የራሳችን ሕይወት የሌለን ቤተሰብ የማንመሠርት ልጆች የማንወልድ የሚመስለው ብዙ ሰው አለ የሚሉት ሲስተር ዘቢደር በመሠረቱ እሳቸውም መጀመሪያ ላይ ለማግባት ፍላጎት አልነበራቸውም። ምክንያቱ ደግሞ ለሥራቸው ሙሉ ትኩረት ለመስጠት በማሰብ ነበር። ነገር ግን ይህንን የሥራቸውን ባህርይ የተረዱና የሚደግፏቸውን ሰው በማግኘታቸው ትዳር መስርተው የአንድ ወንድና የአንዲት ሴት ልጅ እናት ስለመሆናቸው ይናገራሉ።

“…እኔ ከዓላማዬ ወይም ከሥራዬ ትዳርም ሆነ ልጆች አላስቀሩኝም ፤ባለቤቴም ሥራዬን ይረዳል። ልጆቼም ህጻንም ሆነው ከአባታቸው ጀምሮ አያቶቻቸው አክስቶቻቸው ስለነበሩ ምንም አልተቸገርኩም፤ ይልቁንም እነሱም እኔ የምሠራውን ሥራ እያወቁና እያዩ በማደጋቸው ዛሬ ላይ የመጀመሪያ ልጄ የከፍተኛ ትምህርቱን አጠናቆ ተመርቆ ሥራ ይዞ በሚያገኘው ደመወዝ አንድ ልጅ እያሳደገ ነው፤ ሴቷም ትምህረቴን እንዳጠናቀቅሁ ህጻናትን አሳድጋለሁ ብላ እየጠበቀች ነው” ይላሉ።

መልዕክት

“…እንረዳዳ እንተሳሰብ ቀና አእምሮ ይኑረን፤ ሁላችንም በጎ ፈቃደኛ በመሆን ከሜሪጆይ ጎን እንቁም፤ የግድ ገንዝብ አያስፈልግም። ለልጆች ጊዜን ፍቅርን መስጠት ፤ወደማዕከሉ በመምጣት በጎ ፍቃደኛ መሆን፤አልባሳትና ቁሳቁስ ማምጣት ለድርጅቱ ትልቅ ድጋፍ ከመሆኑም በላይ ለሚያደርገው ሰውም በረከት የሚያስገኝለት መልካም ተግባር ነው።

ከዛም አለፍ ሲል በወር ስድስት መቶ ብር ብቻ በማውጣት አንድ ልጅ ማሳደግ ወይም አንድ አረጋዊ መጦር ይቻላል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You