ቴክኒክና ሙያ የጀርመን ትንሳኤ እስትንፋስ

የመላው ዓለም ዓይን ጀርመን ላይ ነው። ከዋክብቶች ባሉበት የዓለም ዓይን ይከተላል። የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ የጣሊያን ሴሪያ፣ የስፔን ላሊጋ፣ የጀርመን ቡንደስሊጋ ከዋክብት በታደሙበት የዓለም ዓይን በዛ አለ። ከአበበ ግደይ እስከ መሰለ መንግሥቱ፤ ከቢቢሲ እስከ እስካይ ኒውስ፤ ከአይቲቪ እስከ ዲኤስቲቪ፤ ከደይሊ ቴሌግራፍ እስከ ጋርዲያን የወሬ ማሟሻቸው በጀርመን እየተካሄደ ስላለው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ነው።

በናዚ፣ በአዶልፍ ሒትለር በስድስት ሚሊዮን አይሁዶች ጭፍጨፋ ክፉኛ የጠለሸውን ገጽታዋን ላለፉት 80 ዓመታት ብታጥበውም ገና ይቀረዋል። ይሄን ውድድር ያስተናገደችው ገጽታዋን የማደስ ፕሮጀክቷ አካል ስለሆነ ነው። ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማግኘትና የቱሪዝም ኢንዱስትሪዋን ይበልጥ ማነቃቃት ሁለተኛው ምክንያት ነው። ለዚህ ነው ዛሬም የዓለምን ቀልብና ትኩረት የሚስቡ ሁነቶችን የምታዘጋጀው።

ካለፈው ሰኔ 7 እስከ ሀምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ለአንድ ወር በሚቆየው የእግር ኳስ ውድድር በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎችና የኳስ አፍቃሪዎች በጀርመን ተገኝተው ጨዋታውን ይከታተላሉ። በቢሊየኖች የሚቆጠሩ የኳስ ወዳጆች ደግሞ በቴሌቪዥን መስኮት ይሰየማሉ። ጀርመንም አጋጣሚውን ተጠቅማ ራሷን ታስተዋውቃለች። በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ታሪኳን ባህሏንና የእድገት ደረጃዋን ለሕዝበ አዳም አቅርባለች።

የየሀገራቱ ቡድኖች ጨዋታቸውን ወደሚያካሂዱባቸው ስታዲየሞች ሲያመሩ ከአረፉበት ሆቴል ጀምሮ በቀጥታ በቴሌቪዥን ይተላለፋል። ጽዱና ውብ ከተሞቿ፣ መንገዶቿ፣ የሕንጻዎቿ የኪነ ህንጻ ውበት፣ ሀውልቶቿ፣ ታሪካዊ መስህቦቿ እግረ መንገድ ይታያሉ። በአካል የተገኘው ደጋፊና ኳስ አፍቃሪ ተዘዋውሮ ይጎበኛታል። የስታዲየሞቿ ውበትና ግዝፈት በራሱ ስለጀርመን እድገት ጮኽ ብለው ይናገራሉ።

የበርሊን ኦሎምፒክ ስታዲየም፣ ሬንኢነርጂ ስታዲየም፣ አሊያንዝና ፍራክፈርት አሬናንና ሌሎችን ልብ ይሏል። እንደኔ ያለ የኳስ አፍቃሪ ደግሞ በቴሌቪዥን መስኮት ያያታል። ለመጎብኘት ይመኛታል። እንዲህ የምታጓጓው ጀርመን ከ80 ዓመት በፊት በተካሄደው 2ኛው የዓለም ጦርነት እንደ ዛሬዋ ጋዛ ወደ ፍርስራሽነት የተቀየረች ሀገር ነበረች። ዜጎቿ ጦርነቱ በፈጠረው ችጋር የሚቆራመዱ፤ የሚልሱት የሚቀምሱት ያጡ፤ የተራዙና የተራቡ ነበሩ።

በእነዛ ፍርስራሽ ከተሞች ግን ከሞትና ከጦርነቱ የተረፉ በደህናው ጊዜ በታወቁ የሀገሪቱ የቴክኒክና ሙያ ት/ቤቶች የተማሩ አናጺዎች፣ ግንበኞች፣ ኤሌክ ትሪሽያኖች፣ ቀያሾች፣ መሐንዲሶች ፣መካኒኮች፣ ቧንቧ ሠራተኞች፣ ወዘተረፈ ነበሩ። እንግዲህ እነዚህ ሙያተኞች ናቸው ጀርመንን ከፍርስራሽነት፣ ከድህነትና ከውድቀት አንስተው ለዛሬ ትንሳዔና ክብር ያበቋት። ከአሜሪካና ከቻይና ቀጥሎ የዓለማችን ሶስተኛ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያደረጓት። ዓመታዊ ጥቅል ምርቷ ወደ 6 ትሪሊዮን ዶላር ሲሰላ፤ የዜጎች የነፍ ወከፍ ገቢ ደግሞ ከ54 ሺህ ዶላር በላይ ነው።

የሚገርመው ጀርመን ዛሬም ስዊዘርላንድንና ኦስትሪያን አስከትላ ከዓለም በቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋሞቿ ከዓለም ቀዳሚ ናት። የዛሬው ኃያልነቷ ሚስጥር ይሄ ነው። በነዳጅ በአልማዝ በወርቅ ወይም በሌላ ማዕድን አይደለም እዚህ የደረሰችው በልጆቿ ወርቅ እጅ እንጂ። ዛሬ ጀርመን የሚለው ስም ራሱ የብዙ ትሪሊዮኖች ዩሮ ብራንድ ነው። መርቸዲሱን፣ ቮልስዋገኑን፣ ቢኤምደብሊውን፣ የሴሜንስ ምርቶችን፣ አዲዳስን፣ ወዘተረፈ ተውት ዛሬ የጀርመን መድሃኒት ፋርማሲ ውስጥ ማግኘት የሞት መድሃኒትን የማግኘት ያህል ነው። የጀርመን መድሃኒት የያዘ ባለፋርማሲ ከተገኘ ያመረተው ይመስል ኩራቱ የሌለ ነው።

ጀርመንን በአብነት አነሳን እንጂ ጃፓን፣ ቻይና፣ ቬትናም፣ ሕንድ፣ ማሌዥያ፣ ኢንዶኔዥያና ሌሎች በማደግ ላይ ያሉ የደቡብ ደቡብ ሀገራት በፍጥነት እያደጉ ያሉት በብቃትና በጥራት በሠለጠነ የቴክኒክና ሙያ ምሩቃን ነው። አንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትን በማምጣት የሕዝቦቿን ኑሮ ማሳደግ የምትችለው በሚኖራት የሰው ኃይል እምቅ አቅም ነው። ዛሬ በሣይንስና ቴክኖሎጂ በልጽገው በሀገራቸው ልማትን በማምጣት የሕዝባቸውን ተጠቃሚነት ያጐለበቱ ሀገሮች ልምድ የሚያሳየን ይህንኑ ሐቅ ነው።

በተለይ በቅርብ ዓመታት ከነበሩበት የድህነት አረንቋ ወጥተው ከፍተኛ የሣይንስና ቴክኖሎጂ እድገት ላይ የደረሱ እነዚህን ሀገራት ተሞክሮን እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ሀገሮች ለትምህርትና ሥልጠና በሰጡት ትኩረት የሰው ኃይል ሀብታቸውን በከፍተኛ ደረጃ በማልማት ከፍተኛ እድገት በማስመዝገብ የሕዝባቸውን ኑሮ ማሻሻል ችለዋል። ከዚህ የምንረዳው ትምህርትና ሥልጠና ብቁና በቂ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ነው።

ወደ ሀገራችን ስንመለስ እንደ ተግባረ ዕድ ያሉ ማሠልጠኛዎች የነበሩን ቢሆንም በነበራቸውን ብቃት አልቀጠሉም። አልበዙም። አለሙም። ይባስ ብለን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደግሞ ከ10ኛ እና ከ12ኛ የወደቁ ተማሪዎች መጣያ ከመሆኑ ባሻገር ሥልጠናው በንድፈ ሃሳብ እንጂ በተግባር ያልተደገፈ ስለነበር ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል። ከለውጡ በኋላ ግን ጅምር መሻሻሎችን እያየን ነው። ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ሳይመጣላቸው ሲቀር ወደተለያዩ ቦታዎች ያማትራሉ።

ብዙዎችም የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋምን እንደ አንድ አማራጭ አድርገው ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። 10ኛ ክፍል ላይ ሲወድቁ አልያም 12ኛ ክፍል ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባት ሳይችሉ ሲቀሩ ወደ ቴክኒክ ኮሌጅ በመግባት ተቋሙን እንደ አማራጭ አድርገው ይገቡበታል እንጂ ጥሩ ወጤት አስመዝግበው ሙያውን ለመቅሰም ብለው የሚገቡ ተማሪዎች እስከዚህም አይደሉም። ለችግሩ መፈጠር ደግሞ ብዙ ዓይነት ምክንያቶች ይቀርባሉ።

ለአማርኛው ሪፖርተር፣ ‹‹ችግሩ የትውልዱ አይደለም እኛም የመራንበት ጉድለት ነው ብለን እናምናለን›› ያሉት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሥልጠና ዘርፍ የሀገር ውስጥ አማካሪ አዝመራ ከበደ (ዶ/ር) ናቸው። የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተማሪ 10ኛ ክፍል ሲወድቅ የሚገባበት ተደርጎ እየተሳለ ነው የመጣው፣ ይህንንም ለማስቀረት በአዲሱ የሥልጠና ፖሊሲ ላይ ለውጥ ተደርጎበታል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በነበረው የትምህርት ፖሊሲ ለሙያው የተሰጠው ትኩረት አናሳ እንደነበር በአሁኑ ወቅት በተለይ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ ተማሪዎች ችሎታቸውን እየለዩ፣ እየተለማመዱና እያወቁ እንዲመጡ ለማስቻል የትምህርት ፍኖተ ካርታው አንዱ አካል ተደርጎ እየተሠራ ነው።

በቀጣይ ምናልባት የዝግጅት ሥራው ካለቀ ተማሪዎች 12ኛ ክፍል ሲደርሱ በመረጡት ሙያ ሠልጥነው ወደሚፈልጉት እንዲሄዱ ይደረጋል። ከዚህ በኋላ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ምራጭ ሳይሆን መርጠውት የሚመጡበት ዘርፍ እንዲሆን የሚያስችል አዲስ ፖሊሲ የተዘጋጀ ስለሆነና ተማሪዎች ይኼንን አውቀው ዕድሉን ለመጠቀም ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ አዝመራ (ዶ/ር) አሳስበዋል።

ባለፉት ዓመታት የትምህርት ዘርፉ የመጣበትን ሁኔታ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በትምህርትና ሥልጠና ዘርፉ ያሉ ድክመቶችና ፈተናዎች ምንድ ናቸው? ቀጣይስ ችግሮች እንዴት መፈታት አለባቸው? በሚል ጥናት አቅርበው እንደነበርና ከጥናቱ በመነሳትም የትምህርትና ሥልጠና ዘርፉ ሊመራ የሚገባበትን ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተው ማቅረባቸውን የተናገሩት አዝመራ (ዶ/ር)፣ ከዚሁ ፍኖተ ካርታ በመነሳት አዲስ ፖሊሲ ተቀርፆ ወደ ሥራ ከገባ ከዓመት በላይ እንዳስቆጠረ አክለዋል።

በዋናነት ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የትምህርት አግባብነትና የጥራት ችግር አለበት ተብሎ መወሰዱን፣ ችግሩን በሀገር ደረጃ ባለው አቅም ብቻ መፍታት እንደማይቻል፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችንና ልምዶችን መጠቀም ስለሚያስፈልግ ከተለያዩ ሀገሮች ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል። ከጀርመንና ከቻይና መንግሥታት ጋር የተደረጉ ትብብሮችን ያስታውሷል።

የቀድሞ የናሳ ሳይንቲስት ቅጣው እጅጉ (ዶ/ር) የባህር ዳር ፖሊቴክኒክ ምሩቅ እንደሆኑ በአንድ አጋጣሚ ራሳቸው ሲናገሩ ተደምጠው ያውቃሉ። ከአንጋፋው ተግባረ ዕድና ከሌሎችም የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ማዕከላት እጅግ ታላላቅ ባለ ብሩህ አዕምሮ ምሁራን መውጣታቸውን፣ ብሩክ ከድር (ዶ/ር) የዘርፉን ታሪክ በዳሰሰ ጥናታቸው አመልክተዋል።

ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው በለውጡ ማግስት በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ላይ የአሠራርም የአደረጃጀት ለውጥ እየተደረገ ነው። በአብነት የኢፌዴሪ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ቀደም ሲል ለተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ተጠሪ ነበር። በዋናነት ለትምህርት ሚኒስቴር፣ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም ተጠሪ ነበር። አሁን ግን ተልዕኮውን የበለጠ ሊያሳካ በሚችል መንገድ ለኢፌዴሪ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠሪ ነው። ተቋሙ በዋናነት የሚከተሉት ተልዕኮዎች ናቸው የተሰጡት።

የመጀመሪያው ተልዕኮው ኢትዮጵያ ውስጥ የቴክኒክና ሙያ መምህራንን፣ አሠልጣኞችንና ቴክኒሻኖችን ማፍራት ነው። በዚህ ረገድ ደግሞ በሀገራችን ብቸኛው ነው። ሌላ እንደዚህ ዓይነት ቅርጽ ያለው ተቋም በኢትዮጵያ ውስጥ የለም። በሌሎች አፍሪካ ሀገሮች ውስጥም ቢሆን የቴክኒክና ሙያ አሠልጣኞችን ለማፍራት ተብሎ የተዋቀረ ተቋም የለም። ሁለተኛው ተልዕኮ ደግሞ የዘርፉ የፖሊሲ ክንፍ ሆኖ ማገልገል ነው።

ሦስተኛ ተልዕኮ ደግሞ የኢንዱስትሪ ትስስር መፍጠር ነው። ከኢንዱስትሪዎች ጋር በመተባበር በአጫጭርና በረዥም ርቀት ሥልጠናዎች የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ማከናወን ይገኝበታል። የሰው ኃይል ከማዘጋጀት በተጨማሪ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችንም ያከናውናል። ከሶስት ዓመት ወዲህ ኢትዮጵያ የክህሎት ልማት ሥራን የምትመራበት ሚኒስቴር አደራጅታለች። አሁን የክህሎት ልማት የራሱ ባለቤት አለው። በሚኒስቴሩ የቅርብ ድጋፍና ክትትል እየተደረገለት ነው።

የክህሎት ልማት ሥራ የሚመራው በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሥር መሆኑ ሌላው ማሻሻያ ነው። የኢፌዴሪ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ተጠሪነቱ ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሆነው ለዚህ ነው። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደ አካባቢው የኢኮኖሚ ኮሪዶር ፍላጎትና ተጨባጭ ሁኔታ የጥናት፣ የአፕላይድ ሳይንስ፣ እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ባህሪ ያላቸው ተብሎ በተልዕኮ የተደራጁበት ሁኔታ አለ።

እንዲሁም ቴክኒክና ሙያ የራሱ የሆነ ባህሪያት ያሉት ነው። አንደኛ ብዙ ሚሊዮኖች ሕይወታቸው የሚቀየርበት ዘርፍ ነው። በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዜጋ የሚሠለጥንበት በክህሎት ልማት ማለትም በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ነው። አሠለጣጠኑ ደግሞ በደረጃ (ሌቭል) የተቀመጠ ሲሆን፣ በአዲሱ ፖሊሲ መሠረትም ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ ስምንት የሥልጠና መርሐ ግብሮች ያሉት ነው።

ከአንድ እስከ አምስት ያሉትን በየክልሉና በየከተማ መስተዳድሮቹ ያሉ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኮሌጆች ናቸው የሚያዘጋጁት። ሌቭል ስድስት፣ ሰባትና ስምንትን ግን የሚዘጋጀው በኢንስቲትዩቱ ነው። ከሌቭል ስድስት ጀምሮ ያለውን አሠልጣኝ የሚያፈራው ይኸው ኢንስቲትዩት ሲሆን፤ ሌቭል ስድስት የመጀመሪያ ዲግሪ ሲሆን፣ ሌቭል ሰባት ደግሞ የሁለተኛ ዲግሪ (ማስተርስ) ሥልጠና ነው።

ሌቭል ስምንት ደግሞ ሦስተኛ ዲግሪ (ፒኤችዲ) ነው ማለት ነው። ከሌቭል ስድስት ጀምሮ ያለው ሥልጠና የቴክኒክና ሙያ አሠልጣኞችን ለማፍራት ያለመ ነው ማለት ነው። ከደረጃ ስድስት በላይ ያሉ ሠልጣኞች ግን በዘርፉ አዳዲስ የሰው ኃይል የሚያፈሩ መምህራን እንዲሆኑ፣ ወይም ወደ ኢንዱስትሪው ተቀላቅለው ኢንዱስትሪዎችን የሚመሩ ቁልፍ ቴክኒሺያኖች እንዲሆኑ ታሳቢ በማድረግ ነው።

ሌላው የብቃት ምዘና ጉዳይ ነው። በቴክኒክና ሙያም ብቃት ይመዘናል፣ ይህ ደግሞ በፖሊሲውም ተቀምጧል። በፖሊሲው መሠረት 70 በመቶ የተግባር 30 በመቶ ደግሞ የቀለም ትምህርት መስጠት ተብሎ ነው የተቀመጠው። እጁን በደንብ ያፍታታ፣ ከማሽነሪዎች ጋር በደንብ የሚተዋወቅ፣ ሙያ ለምዶ የሚወጣ፣ ፋብሪካዎች ውስጥ ገብቶ የሚያገለግል፣ በኢንዱስትሪውም ሆነ በኢኮኖሚው ውስጥ አቅም የሚፈጥር ሙያተኛን ነው ለማፍራት ጥረት እየተደረገ ያለው።

በፖሊሲው በተቀመጠው መሠረት ያንን ሥልጠና አግኝቶ ወጥቷል ወይ በሚል ይመዘናል። ብቁ ሥልጠና አግኝቷል ወይ የሚለው ይመዘናል። ሲኦሲ እንደሚታወቀው እስከ ሌቭል አምስት ድረስ ያሉ ሠልጣኞች የሚመዘኑበት ነው። በየአካባቢው ያሉ የምዘና ማዕከላት ይህን ሥራ ይሠራሉ ማለት ነው። በከፍተኛ ትምህርት እሳቤ መሠረት አንድ ሠልጣኝ ከመመረቁ በፊት የመውጫ ፈተና እንዲወስድ ከ2015 ዓ.ም. ዓ.ም. ጀምሮ የተቀመጠው አሠራር እየተተገበረ ነው።

የኢፌዴሪ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ይዘት ያለው በመሆኑ ይህንኑ የመውጫ ፈተና (ኤግዚት ኤግዛም) አሠራርን ተግባራዊ አድርጓል። በሌላ በኩል የቴክኒክና ሙያን በተመለከተ የቆየው የተዛባ የማኅበረሰብ አመለካከት መቀረፍ አለበት። ቴክኒክና ሙያ አማራጭ ያጡ ሰዎች የሚሰባሰቡበት ነው ብሎ የማሰብ ጉዳይ መቀየር አለበት። ዜጎች ሕይወታቸውን የሚቀይሩበት የተከበረ ዘርፍ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You