ሙስናን እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመሻገር …

ጠንካራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመፍጠር ከሚያስፈልጉት ቁልፍ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚ ሊባል የሚችልው መልካም አስተዳደር እንደሆነ የማኅበረሰብ ሳይንስ ምሑራን ይስማማሉ። በእነዚህ ምሑራን ምልከታ፤ መልካም አስተዳደር በአንድ ሀገር አስተዳደር ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና ቀዳሚው ነው። በመንግሥትና ሕዝብ መካከል በመተማመንና በመተጋገዝ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ሊፈጠር የሚችለው የመንግሥት ሥርዓቱ አስተማማኝ የመልካም አስተዳደር ሁኔታን መገንባት ሲችል ብቻ ነው ፡፡

የመንግሥት ጥንካሬና ውጤታማነት ከሚለካባቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው በምርጫ ወቅት በተገባው ቃል መሠረት የሕዝብን ጥያቄና ፍላጎት በቅንነትና በታማኝነት መመለስ መቻሉ ነው። ይህ ደግሞ ሕዝብ በመንግሥት ላይ የሚኖረው ዕምነት ከፍ እንዲል ከማድረጉ በዘለለ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል የተሻለ መቀራረብና የሰመረ ግንኙነት ይፈጥራል። በተቃራኒው በሕዝብ ፈቃድ ወደ ሥልጣን የመጡ ተመራጮች ለሕዝብ የገቡትን ቃል ችላ ካሉ ውጤቱ ሌላ መልክ ይሆናል፡፡ ይህ ሁኔታ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ዕምነት እንዲያጣ ብሎም ድጋፍ እንዲነፈገው ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል እንደ አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል ።

ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ሥርዓቶች ገዥዎቹ ውግንናቸው ለሕዝብ ጥቅም ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ማደላደል ላይ ዋነኛ ትኩረታቸው አድርገው ሲሠሩ መቆየታቸው ይታወሳል። ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዘው ያሉ ችግሮች መንግሥትና ሕዝብን ሆድና ጀርባ ሲያደርጉ ታዝበናል። በ2010 ዓ.ም. ሀገራዊ ለውጥ እንዲመጣ ነዳጅ ሆነው ካገለገሉ አጀንዳዎች መካከል የሕዝብን ልብ ያደማ የመልካም አስተዳደር እጦት በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል። በሀገራዊ ለውጡ ወደ ሥልጣን የመጣው አዲሱ አመራር በኅብረተሰቡ ሲቀርቡ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታትና በሕዝቡ ዘንድ ያለውን መጥፎ ስሜት ለመቀየር የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን ሲያከናውን ታይቷል ።

የልማትና የመልካም አስተዳደር ሕዝባዊ ጥያቄዎችን መፍታት የሚችሉ ሥራዎችን በማከናወን መንግስት ከሕዝብ ጎን መቆሙን አረጋግጧል። ሕገ መንግሥቱ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ ለሙሉ መከበር እንዳለባቸው ይደነግጋል። የመልካም አስተዳደር ግድፈት ማለት በተዘዋዋሪ የሰብዓዊና ሕጋዊ መብቶች ጥሰት ነው:: ሰብዓዊ መብት፤ ከሀገሪቱ ሕገ መንግሥት አልፎም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስጠይቅ ነው:: ሁለቱም ድርጊቶች፤ ወንጀል ስለመሆናቸው በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተደነገጉ ናቸው። መንግሥትም ይህንን ድንጋጌ ተግባራዊ ለማድረግ ሠርቷል።

በሀገሪቱም በርካታ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚያጎለብቱና የሚያፋጥኑ ተግባራት አከናውኗል። በዚህም ሕዝቡ በየደረጃው የልማት ተጠቃሚ ቢሆንም አሁንም ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ረገድ ያልተፈቱና ሕዝቡን እያማረሩ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ።

የመልካም አስተዳደር ችግር ትልቁ እልፍኝ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ናቸው:: የመልካም አስተዳደር ችግሩ በግልም ሆነ በየትኛውም ቦታና ጊዜ ሊፈጠር የሚችል ቢሆንም በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግን ይብሳል:: በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚታዩ የሙስናና ኢ-ፍትሐዊ አካሄዶች ሕዝብን ለከፍተኛ ቅሬታ የሚዳርጉ ተግባራት በስፋት ይስተዋላል፡፡

በተለይ በአንዳንድ አካባቢ በአፍ ብቻ፣ በሌላ አካባቢ ደግሞ በእጅ መገፍተርም ጀምሯል፡፡ በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ የገዘፉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ይዞ የልማት ዕቅዶችን ማሳካት እንደማይቻል ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሕዝብ በልማት ውጤት ተጠቃሚ ካልሆነ ችግሮች መፈጠራቸው አይቀርም። ይህ ደግሞ በመንግሥት ላይ ከሚፈጥረው ራስ ምታት ባሻገር፤ የመንግሥትን ተዓማኒነት የሚያሳጣ እንደሚሆን አያጠራጥርም።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንዲሁም ተከታታይነትና ወጥነት ያለው የተጠያቂነት ሥርዓትን መዘርጋት ይኖርበታል። ይህ አሠራር በጥልቀትና በስፋት በማስቀጠል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት መሥራት ያስችላል። እንዲያም ሆኖ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለመግታት በመሯሯጥ ላይ የሚገኙ የሀገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች አሉ ።

እነዚህ ኃይሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ደፋ ቀና ማለታቸው እንደማይቀር መጠርጠሩ አይከፋም። የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና የማይሹ የሀገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች ዓላማ የተጀመሩ የለውጥ ጉዞን በማደናቀፍ እንዲሁም የማያባራ ሁከትና ግጭትን በማቀጣጠል ሥርዓት አልበኝነትን ማስፈን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህን ተልዕኳቸውንም ለማሳካት የሚሞክሩት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩ ኃይሎችንና በችግሩ የሚማረሩ ወገኖችን በመሣሪያነት በመጠቀም ነው።

የመልካም አስተዳደር ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በተጨባጭ ለመፍታት በመንግሥት ደረጃ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። በየትኛውም መስክ ለጥፋት የሚሆን ምቹ ምሕዳርን ማሳጣት ይገባል። የተሰጣቸውን ሕዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ ኃይሎችን በፅናት መታገል ያስፈልጋል።

ተቋማት በመልካም አስተዳደር አፈጻጸማቸው የሚገመግሙበት እና የሚመዘኑበት አሠራር ሊኖር ይገባዋል። በዚህ ረገድ በቅርቡ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋማትን በመልካም አስተዳደር የመመዘን ሥራ መጀመሩ ይታወቃል። የሕዝብ እንባ ጠባቂ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ መልካም የሕዝብ አስተዳደር እንዲሰፍን፣ የተጠያቂነት አሠራሮችን ለማዳበርና የሕዝቡን ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት እና ተሳትፎ ለማረጋገጥ የራሱን ዐሻራ በማሳረፍ ላይ የሚገኝ ተቋም ነው።

በተቋሙ አማካኝነት የተካሄደው ምዘና ለመልካም አስተዳደር መሻሻል ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም ይታመናል። ይህ እንደ ጥሩ ጅምር ሊታይ ይገባል። እንደ ሀገር የተሻለውን ከደከመው መለየት ባለመቻላችን ጠንካራ ተቋማትን መፍጠር ካለመቻሉ ባሻገር፤ ሁሉንም ተቋማት በጅምላ የመፈረጅ ትልቅ ችግር አለብን። በተቋሙ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው ምዘናም ይህንን ችግራችንን መቅረፍ እንደሚያስችል ይታመናል።

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ ሌሎችንም ተቋማት በመልካም አስተዳደር አፈጻጸማቸው የመመዘኑ ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ይህም ከመልካም አስተዳደር አኳያ ሕዝቡ በማናቸውም ሕጋዊ የሙያና የብዙኃን ማኅበራት በመደራጀት መብትና ጥቅሙን እንዲያስ ከብር ያደርገዋል። በለውጡ የተጀመሩ ወሳኝ የልማት ሥራዎችን በማቀላጠፍ የሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲጠናከር ያግዛል።

በአጠቃላይ መንግሥት ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመከላከል የጀመረው ጥረት የሚበረታታ እና የሚደገፍ ቢሆንም ችግሩ ካለበት ሀገራዊ ደረጃ አንጻር ግን ገና ብዙ መሥራት የሚጠይቅ ነው። ለዚህም እንደ ሀገር የተጀመሩ ተቋማዊ ሪፎርሞችን በማጠናከር፤ የመልካም አስተዳደር መርሆዎችን በመተግበር፤ የተናበበና ተገልጋይ ተኮር ለውጥ አምጪ ተግባራትን መፈጸም ይገባል።

ቀጣይነትና ወጥነት ባለው መልኩ የተቋማትን አሠራር ፈትሾ የክህሎት፣ የአቅርቦት፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ማነቆዎችን ነቅሶ ማውጣት ያስፈልጋል። በየደረጃው ያሉ የመንግስት ኃላፊዎች መንግሥት የጀመረውን ሙስናናን የመታገል፤ መልካም አስተዳደር የማስፈን ሀገራዊ ትግል አቅም መሆናቸውንን በአግባቡ መፈተሽ ተገቢ ነው።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You