ደማቅ ተስፋ – ከአበቦች መሐል

የልጅነት ሕልም…

እሷ ዕቅድ ውጥኗ ብዙ ነው:: ሁሌም አርቃ ታልማለች:: ጠልቃ ታስባለች:: ይህ ልምዷ መዳረሻው ብዙ ነው:: ከትምህርት ጓዳ አስምጦ ያወጣታል:: ከዕውቀት መንደር አክርሞ ይመልሳታል:: ምኞቷን በየቀኑ ትኖረዋለች:: በየደቂቃው ታሰላዋለች:: ይህ እውነት የዓላማዋ ግብ፣ የማንነቷ ስር ሆኖ ዘልቋል::

ኩኩ በየነ እስካሁን የኖረችውን አይነት ሕይወት መድገም አትሻም:: የሁሌው ምኞቷ ካለችበት ደረጃ ከፍ ብሎ ማለፍ ነው:: ምንግዜም ለዚህ ሕልሟ እውንነት ትተጋለች:: በመማር፣ ጠንክሮ በማጥናት፣ ካሰቡት እንደሚደረስ አይጠፋትም:: ልጅነቷ ደግሞ ከትልሟ አላፋታትም:: ትምህርቷን ስታስብ ከሕልሟ ጥግ ደርሳ መመለስ ልምዷ ሆኗል::

ትንሽዋ ኩኩ የገበሬ ልጅ ናት:: ትውልድ ዕድገቷ ከገጠር፣ ትምህርት ዕውቀቷ ከቀዬው ተጠንስሷል:: የዕወቀት ሀሁን ከጀመረች አንስቶ ውስጠቷ በአንድ እቅድ ጠብቆ የታሰረ ነው:: መማር ለውጥ እንዳለው ታውቃለች:: በዕድሜ ከፍ ማለት ስትይዝ ደግሞ ከዕውቀት የሚገኘው ጥቅም ይበልጥ ጎልቶ ታያት:: በዚህ መስመር ያለፉ ብዙዎች የሙያ፣ የዕውቀት ባለቤቶች ናቸው:: ትምህርት በቸራቸው ድል ምሑራን ተብለው ሀገር ይመራሉ:: ወገን ይጠቅማሉ::

በአካባቢዋ በትምህርት ተለውጠው፣ በዕውቀት የበለጡ መኖራቸውን ሰምታለች:: እሷም ብትሆን የምታውቃቸው በርካቶች ከሕሊናዋ አይጠፉም:: እያንዳንዳቸው በያዙት ሙያ ስም አላቸው:: ባሉበት ሥራ ይከበራሉ:: በተማሩበት መስክ ይገኛሉ::

ኩኩ ስለሁሉም ክብር አላት:: እነሱ ነገዋን አሳይተው ዛሬን አቁመዋታል:: በማንነታቸው ጥላ ጥንካሬን ለብሳለች:: ሁሌም ትምህርት ይሉትን ፈቅዳ እንድትቀጥል ምክንያቷ ናቸው:: ከሁሉም ግን ልቧ ለአንዱ ሙያ ያደላል:: በእሷ ዕምነት ይህ ሙያ ስታድግ መዳረሻዋ ነው:: ከልጅነቷ ምኞት ሕልሟ ሆኖ አብሯት ዘልቋል::

ለእሷ ዶክተርነት የማይለቅ ንቅሳት፣ የማይፈዝ አሻራ ነው:: ከሙያዎች በላይ ሙያ አድርጋ አጥብቃ ይዛዋለች:: ለዚህ ደግሞ ምክንያቷ በብዙ መልክ ይገለጻል:: በእሷ ዕድሜ ያየች የሰማችው ችግር ጥቂት አይደለም:: በርካቶች በሕክምና እጦት መሞት፣ መቸገራቸውን ታውቃለች:: ሁሌም ታዲያ በአዕምሮዋ ለሚመጣው ጥያቄ መልስ ትሻ ነበር::

ቆይታ ግን ለምን እንዴት ለማለቷ መፍትሔው ከእሷ እንደሆነ ገባት:: አሁን የወደፊት ሕልሟ በሕክምናው ዓለም ‹‹ዶክተር›› ሆና ሀገሯን መጥቀም፣ ወገኗን ማገልገል ነው:: ለዚህ ሕልሟ መንገዷን ከጀመረች ቆይታለች::

ኑሮ ከወንድም ጋር …

ኩኩ ምንጃር አረርቲን ትታ ሞጆ ከዘለቀች ቆየች:: በዚህ ከተማ ታላቅ ወንድሟ ይኖራል:: ከነበረችበት ወጥታ ከእሱ ዘንድ መማር እንደምትሻ ስታዋየው አልተቃወመም:: አብረው እየኖሩ ትምህርቷን እንድትቀጥል ፈቀደላት:: ጓዟን ጠቅላላ ሞጆ ላይ ከተመች:: ኑሮና ትምህርት፣ በአንድ መጓዝ ያዙ:: እህትና ወንድም የአንድ ጣራን ሕይወት ለመዱት:: እስከዛሬ ለሆድ አስበው አያወቁም:: ከቤቱ ጎተራ እህል ይጫንላቸዋል፣ ቀለብ ይሰፈርላቸዋል::

ኩኩ ከአንደኛ ደረጃ አንስቶ በጥሩ ውጤት የተሻገረች ብርቱ ተማሪ ነች:: እንዲህ ትሆን ዘንድ ዓላማ አላትና መዘናጋትን አትወድም:: ፈተና ለማለፍ ሳይሆን ዕወቀት ለመጨብጥ ትጥራለች:: ግዜው ደርሶ ሕልሟን እስክታገኝ ዕንቅልፍ የላትም::

እሷ ከጥረት ልፋቷ ማግስት ያሰበችው እንደሚሳካ ሲገባት መጪው ዘመን ይናፍቃታል:: ሞጆ ላይ ከስምንተኛ ክፍል በጀመረችው ትምህርት ሰኬታማ ሆናለች:: ሁሌም ጊዜ ሰጥታ ማጥናቷን አልተወችም:: በትምህርቷ ቀልድ አታውቅም:: በዚህ ዓላማዋ የጸና፣ ሀሳቧ የጠነከረ ነው::

አሁን ብርቱዋ ተማሪ ለአስራ ሁለተኛ ክፍል የምትዘጋጅበት ግዜ ላይ ደርሳለች:: ይህ ወቅት ለእሷ የሞት ሽረት ትግል ነው:: ከማንነቷ ለመድረስ የምትፈጥንበት፣ ካሰበችው ጥግ ለመሮጥ የምትተጋበት ፈታኝ ግዜ:: ኩኩ እንዲህ ይሆን ዘንድ ጥረት ትግሏን ይዛለች:: ጠዋት ማታ የማትተወው ደብተር መጽሐፍ መለያዋ ነው:: ዛሬን ተሻግራ ነገን ድል ለመንሳት ከዕንቅልፍ ተኳርፋ ከእረፍት ተጣልታለች::

የምንጃር መንገድ…

ኩኩ የወላጆቿን ናፍቆት የቀዬ ሰፈሯን ትዝታ አትረሳም:: አንዳንዴ ከትምህርት መልስ ሀገሯ ደረስ ብላ ትመለሳለች:: ምንጃር ሸንኮራ ከዓመት እስከ ዓመት ነጭ ከጥቁር፣ ማኛ ከሠርገኛ ያመርታል:: የዚህ ምድር በረከት ለብዙኃን የተረፈ ነው:: የምንጃር ነጭ ጤፍ እውቅናው ከሁሉም ይለያል:: ይህን የሚያውቁ ብዙዎች ስለዝናው ሲዘፍኑለት፣ ሲያዜሙለት ኖረዋል::

የሀገሬው ወግ ባሕል ጭፈራ ጨዋታው በአካባቢው ልማድ እንደጸና ነው:: ዛሬም ድረስ ባሕሉ እንዳማረ፣ ወጉ እንደጠበቀ ቀጥሏል:: ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን ይህ ቦታ እንደቀድሞ የሆነ አይመስልም:: በየአጋጣሚው ተኩስ ይሰማበታል:: በየሰበቡ ሕይወት ይጠፋበታል:: የግጭቱ ትኩሳት በባሰ ቁጥር የሚፈተኑ፣ የሚጨነቁ ነፍሶች ብዙ ናቸው::

ግጭት ሲኖር ሠላም ይናፍቃል፣ ዕንቅልፍ ይሉት ይጠፋል:: ቤቶች ይዘጋሉ፣ ገበያው ይነጥፋል:: እንደቀድሞው ልጆች ከሜዳው፣ ከብቶች ከመስኩ አይታዩም:: ማንም በነፃነት ተራምዶ፣ ካሰበው አይደርስም:: ሁሉ ነገር እንዳልነበረ ይሆናል:: እንዲህ በሆነ ግዜ ሀሳብ ዕቅድ ተለውጦ ከሌላ ጥግ መገኘት ግድ ነው:: የትናንቱ ገጽታ ዛሬን እንደመልኩ ላይቆይ ሁኔታዎች ይቀየራሉ፣ መንገዶች ይለወጣሉ::

ሀገር ቤት ደርሶ መልስ…

ተማሪዋ ኩኩ ዘንድሮ አስራ ሁለተኛ ክፍልን ትፈተናለች:: ለውጤቷ መሳካት ያለእረፍት ስትለፋ፣ ስትደክም ነበር:: ሁሌም ከፈተናዋ ማግስት የምታስበው ዓላማ ዛሬም ከእሷ ጋር ነው:: ኩኩ ከፈተናዋ አስቀድሞ ወላጆቿን ልታይ ከሞጆ ወጥታለች:: ሁሌም እንደሚሆነው ቤተሰቦቿን አግኝታ ጥቂት ቀናትን አሳልፋ ልትመጣ ነው:: ምንአልባትም ከእናት አባቷ ፊት ዳግም የምትቆመው ከመልካም ውጤት በኋላ፣ ከፈተናዋ ድል ማግስት ይሆናል:: ኩኩ እንዲህ ይሆን ዘንድ እየተመኘች ነው:: ውሎ አዳር ያሳለፈችው ተማሪ ከቀናት በኋላ ሞጆ ተመልሳ ከፈተናዋ ትቀመጣለች::

ድንገቴው አጋጣሚ..

ተፈታኟ ተማሪ ክፉኛ ተጨንቃለች:: እሷ ብቻ ሳትሆን ቤተሰቦቿ ጭንቀቷን እየተጋሩ በሀሳብ እየናወዙ ነው:: ወደ ሞጆ ልትመለስ ጓዟን ያነሳችው ኩኩ ከቀናት በኋላ ስለምትወስደው ፈተና ማለሟን አልተወችም:: ድንጋጤ ከፍርሀት የዋጣት ልጅ አሁንም የሆነውን እያመነች አይደለም:: እስካሁን ስለትምህርቷ ዋጋ ከፍላለች፣ ለፈተናዋ ስትዘጋጅ የመጨረሻዋን ወሳኝ ቀን እያሰበች ነበር::

አሁን ግን ይህን ማድረግ የቻለች አይመስልም:: የአካባቢው ሠላም ዕጦት ካሰበችው ጥግ ሳያደርስ ከዕቅዷ መልሷታል:: ኩኩና አብሯት የኖረው ውጥኗ ላይገናኙ ተራርቀዋል:: አሁን ትምህርት ይሉት እውነት ፈተና ይባል ሂደት የለም:: ኩኩ ለዓመታት የለፋችበት ዝግጅት ከግቡ አልደረሰም :: ዘንድሮ ልትወስደው የነበረ ፈተና አለመሳካቱ ገብቷታል::

ሰሞኑን በታጣቂዎች መሐል የተቀሰቀሰው ግጭት ዙሪያ ገባው እንዲዘጋ መኪኖች እንዳይንቀሳቀሱ አስገድዷል:: አሁን ማንም የወጣ አይገባም፣ የገባም አይወጣም:: የመንገዱ መዘጋት ችግር ለእሷ ብቻ ባይመጣም ተስፈኛዋ ተማሪ ውስጧ ተሰብሯል:: እንደዕቅዷ ባለመጓዟ ትካዜ ገብቷታል::

ለቀናት የቆየው ችግር ሳይፈታ ጊዜያት ተቆጠሩ:: ኩኩ ለፈተና የምትመዘገብበት ቀን እያለፈ ነው:: አሁንም ተስፋ ሳትቆርጥ መጠበቅ ይዛለች:: ቀኑ ከመሮጥ አልታቀበም:: ምኞት ፣ተስፋና ሀሳብ በአንድ ወግነው ይፈትኗት ይዘዋል::

ጨለማው አልፏል:: እነሆ! ሌላ ቀን ነግቷል አካባቢው የሠላም አየር እየዞረው ነው:: ኩኩ ወደመጣችበት ሞጆ ልትመለስ ተነስታለች:: ውሎዋን መንገድ ቢይዛትም ደርሳ የልቧን ሀሳብ መጠየቋ አልቀረም:: ከሚመለከታቸው የሰማችው ምላሽ የሚጠበቅ ቢሆንም በፍጥነት ኃዘኗን አላስረሳም::

እንደገና ጽናት

እሷ አሁን እንደሌሎች ተማሪዎች ለመፈተን የሚያስችል ዝግጅት የላትም:: እናም የዘንድሮውን የመልቀቂያ ፈተና መውሰድ አይቻላትም:: ኩኩ እውነታውን ካረጋገጠች በኋላ ቀጣዩን እውነት ለመቀበል ራሷን አዘጋጀች:: አሁን ጥንካሬዋ በወጉ ተመልሷል:: ነገም ሌላ ቀን መሆኑን አምና ተቀብላለች::

ከወንድሟ ጋር የጀመረችው ኑሮ እንደትናንቱ ቀጥሏል:: እህትና ወንድም ልክ እንደቀድሞው ቀለባቸው ከእጃቸው ነው:: ከእናት አባት የሚቸራቸው በረከት ቤታቸውን አላጎደለም:: እሱ ራሱንና እህቱን ለማስተዳደር የሚያስችል እንጀራ አለው:: ማለዳ ከቤት ሲወጣ ግዴታውን አሳምሮ ያውቃል:: ተቀጥሮ በሚሠራበት የሥጋ ቦርድ የከብቶችን ብልት ሲያወጣ፣ በመልክ በዓይነቱ ሲለይ ይውላል:: ይህ ተግባሩ ለእሱ የወር ደሞዙ ነው::

ዓመታት የዘለቀበት የከብቶች እርድ ገቢ ለቤት ኪራይና ለሌሎች ወጪዎች የሚውል ነው:: ኩኩ ትምህርቷ ተቋርጦ ቤት መዋል ከጀመረች አንስቶ ብዙ ታስባለች:: አንዳንዴ ቤተሰቦቿ ይናፍቋታል፣ ቀዬ መንደሯ ውል ይላታል:: ተመልሳ መሄድ ታስብና መልሳ ትተወዋለች::

እሷ በተማረችበት ሞጆ የነገ ተስፋዋ ቁልጭ ብሎ ይታያታል:: ውሎ አድሮ ግን ከቤት ተቀምጦ መዋሉ አላስደሰታትም:: እሷም እንደወንድሟ በጉልበቷ አድራ ጎኑን ልትደግፍ ልታግዘው ማሰብ ያዘች:: ይህ ሀሳቧ በውጥን ብቻ አልቀረም:: የውስጥ ምኞቷን ለሌሎች አካፈለች:: ሥራ፣ እንጀራ፣ ደመወዝ ይሉትን ነገር ተመኘች::

ያሰበችውን ጉዳይ ጆሮ ሰጥተው ከሰሙት መሐል የአንደኛዋ ምክር የኩኩን ልቦና ገዛ:: ወደትምህርቷ እስክትመለስ በጉልበቷ የምታድርበት፣ ገንዘብ ይዛ የምትቆጥረበት አማራጭ ስለመኖሩ ነገረቻት:: ኩኩ ቦታውንና የሥራውን አይነት ጠየቀች:: ሙሉ መረጃው እስከሚከፈላት የደሞዝ መጠን ተዘርዝሮ ተነገራት:: አላወላወለችም:: ደስ እያላት በሥራው ልትገኝ ራሷን አዘጋጀች::

በአበባው እርሻ ውስጥ…

አሁን በተማሪዋ እጅ እርሳስ ደብተር የለም:: እንደትናንቱ መጽሐፍ ገልጣ የምታነብበት፣ ከጥናት የምትታገልበት ጊዜ ላይ አልቆመችም:: ዛሬ ኩኩ ውሎዋ ከአበቦች ጋር ሆኗል:: ቅጠሎቹን የሚያወሯት ይመስላታል:: ለእያንዳንዶቹ ስስቷ ልዩ ነው:: ጤናቸው እንዳይጓደል፣ በተባይ እንዳይጠቁ፣ እክል በሽታ እንዳያገኛቸው ሁሌም ከእነሱ ጋር ናት::

አበቦቹ የእሷ ተምሳሌት ናቸው:: በሠላም ውለው ካደሩ የነገ ጸሐይ ከእነሱ ጋር ነች:: ችግር ፈተና ካልቆረጣቸው:: ተስፋቸው፣ የበዛ መፈለጋቸው የላቀ ነው:: በሀገር ምድሩ በቅለው ባሕር ማዶ ለመሻገር በማንነታቸው እሴት ለመፍጠር የሚያህላቸው የለም:: የአበቦቹ ተስፋ ይለመልም ዘንድ የእሷ መልካም እጆች ወሳኝ ናቸው::

ኩኩ ስለእንጀራዋ ከሞጆ ተነስታ ቆቃ ላይ ትውላለች:: አሁን የአበባው እርሻ ልማት ተቀጣሪ ከሆነች ሰነባብታለች:: አበቦቹ የእሷ ተስፋ ናቸው:: በእነሱ መኖር የእሷ ሕይወት ቀጥሏል:: በእነሱ ማበብ ማንነቷ ተመልሷል:: ትናንት ዕቅድ ሀሳቧ ሌላ ነበር:: ዛሬ ደግሞ ሕይወት በራሱ ዓላማ እየዘወራት ነው:: እንዲህ በመሆኑ አልከፋትም:: አሁንም የነገ ተስፋዋ ከእሷ ውሎ ያድራል::

ኩኩ የሦስት ሺህ ብር ደሞዝተኛ ናት:: የምታገኘው ገንዘብ የወንድሟን ድካም እያቀለለ ነው:: እስከዛሬ እሱ ብቻውን ሲወጣው የነበረውን ኑሮ ከጎኑ ሆና ማገዝ ጀምራለች:: የቤት ወጪው ከእሷ እጅ አያልፍም:: የጎደለውን ሞልታ፣ ቤቱን ማስተዳደር፣ እያወቀችበት ነው::

ሕይወት ከትምህርት ጋር ብዙ ያስተማራት ይመስላል:: ስለነገ ያላት ዓላማ ደግሞ የተለየ ነው:: ከባልንጀሮቿ ጋር የወር ዕቁብ ገብታለች:: ገንዘብ አታባክንም፣ ትቆጥባለች:: ሥራ ውላ ስትገባ የሴትነት ድርሻዋን አትዘነጋም:: እንጀራ መጋገር ካለባት ማዕድ ቤት ትገባለች:: ወንድሟ በዝምታ አያያትም:: ወጥ በመሥራት፣ እቃ በማቀራረብ ያግዛታል::

እህትና ወንድም ተዋደው፣ ተከባብረው ያድራሉ:: እሱ ስለነገው ማንነቷ ይጨነቃል:: እሷም ብትሆን የትናንቱን ውጥኗን አትረሳም:: ከእርሻ ልማቱ የሚከፈላትን ደሞዝ ለነገ መጽሐፍ መግዣ ፣ለትምህርቷ ማገዣ ለማዋል ታስቀምጣለች:: በየቀኑ ከምትውልበት ሥራ ብዙ ተምራለች:: በተግባሯ ድርሻዋን አትዘነጋም:: አበቦቹን ስትወድ ስትንከባከብ የራሷ ሕይወት ትዝ ይላታል::

እሷ ማለት እንደቀንበጦቹ ቅጠል ናት:: ከደገፏት ፣‹‹አለንልሽ›› ካሏት ታብባለች:: የእሷ የዕለት ምግብ ዘወትር የሚኖራት፣ የሚከተላት ተስፋዋ ነው:: ይህ ተስፋ ዛሬን ያውላታል፣ ነገን ያሻግራታል:: በአጋጣሚዎች ትናንት የሆነባትን ባትረሳም ያለፈውን እያሰበች ስታለቅስ አትውልም:: ከተጋች፣ ከለፋች ያለፋትን ዕድል ልታገኘው ብትፈልገው አታጣውም:: ይህ ይሆን ዘንድ ጉልበቷ ብርቱ ነው::

በአበቦች መሐል መዋሏ ነገዋን አፍክቶ፣ አድምቆ ያሳያታል:: ስለ ኑሮ፣ ስለሕይወት ብዙ ብትሄድ አይደክማትም ዛሬን እንዲህ መኖር ይዛለች፤ ነገን በእጇ ለማዋል ትሮጣለች፣ ትደክማለች:: ጠንካራዋ ወጣት ኩኩ በየነ::

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን  ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You