‹‹በምኞት ነው የምንሳፈፈው፣ እኔ በጣም ብዙ ፍላጎት አለኝ፣ ብዙ ነገር እፈልጋለሁ ተግባሬ ግን ዜሮ ነው፣ የመቶ ሺ ብር ምኞት አለኝ ነገር ግን ልፋቴ የአምስት ብር ነው፣ መዋኘት እፈልጋለሁ መርጠብ ግን አልፈልግም፣ ብዙ ስኬት እፈልጋለሁ ግን ወደ ተግባር አልገባሁም፤ የተግባር ሰው አይደለሁም፣ የቀን ሕልመኛ ሆኛለሁ›› ለምትሉ ሁሉ የተግባር ሰዎች ምን አይነት ፀባይ እንዳላቸው በቅጡ መረዳት አለባችሁ:: ጥሩ ነው ማለም:: መልካም ነው መመኘት!
እንደውም አንድ ሽማግሌ ለልጃቸው ‹‹ልጄ መመኘትህ ጥሩ ነው:: የምኞትህን ፎቅ አየር ላይ መሥራትህ መልካም ነው:: ልክ ነህ ፎቅ አየር ላይ ነው የሚሠራው:: ግን መሠረቱን መሬት ላይ ማቆም አለብህ›› አሉት:: እናንተም መሠረቱን መሬት ላይ የምታቆሙት የተግባር ሰው ከሆናችሁ ብቻ ነው:: እነሆ የተግባር ሰው የሚያደርጉ ሰባት ፀባዮች…
1ኛ. እቅዳቸውን አያጋንኑም
አንዳንድ ግዜ የሚያነቃቃ ነገር ታዩና ‹‹በቃ ሁሉም ነገር እኮ ይቻላል:: ምን አለበት ምኞቴን አሳካለሁ›› ትሉና የማይሆን ነገር ታቅዳላችሁ:: ግን በዚህ ዓለም ላይ የማይቻሉ ነገሮች እንዳሉም ማወቅ አለብን:: ወይም ደግሞ የእኛን ትእግስት፣ የግዜ ሁኔታ የሚጠይቁ ነገሮች አሉ:: ለምሳሌ አንድ የአርባ ዓመት ሰው ድንገት ከመሬት ተነስቶ ‹‹እኔ ትልቅ የቅርጫት ኳስ ኮከብ ተጫዋች መሆን እፈልጋለሁ›› ቢል የሚሳካለት ይመስላችኋል? የቅርጫት ኳስ ኮከብ ተጫዋች ለመሆን ቢያንስ በአስር ዓመቱ ወይ በልጅነቱ ቅርጫት ኳስ እየተጫወተ ማደግ አለበት:: ያ ነው ኮከብ የሚያደርገው:: አርባ ዓመቱ ላይ ቢጀምር ግን አይሆንም::
ስለዚህ የማይሆኑና የማይቻሉ ነገሮች አሉ:: ስለተነቃቃንና ስላሰብን ብቻ የማናሳካቸው ነገሮች አሉ:: ምን አልባት የአርባ ዓመት ሰው የቅርጫት ኳስ አሠልጣኝ ሊሆን ይችላል:: ከዚህ አንፃር የሚመስል እቅድ ያስፈልገናል:: ከሁኔታው ጋር የሚጣበቅና አብሮ ሊሄድ የሚችል እቅድ ያስፈልገናል:: መጋነን የለበትም:: በተለይ እቅድ የማድረግ ልምድ ከሌለን እቅዳችንን ቀነስ ማድረግ አለብን:: የሚመስል ማድረግ አለብን::
አንደኛ ክፍል ተማሪዎች አይታችሁ ከሆነ የመጀመሪያው ዓመት ላይ ከእነሱ የሚጠበቀው ማንበብ ወይ ቁጥር መደመር ነው:: መቀነስ እንኳን እንዲማሩ ላይፈለግ ይችላል:: ማካፈልና ማባዛትማ ቆይ ከፍ ሲሉ ይባላል:: ለምን? ከአቅማቸው በላይ ነው:: እኛም አንዳንዴ ግዜ ቁጭ ብለን ስናስባቸው የሚቻሉ ይመስለናል:: ግን አሁን ላለንበት ሁኔታ ከአቅማችን በላይ ነው ስለዚህ የአቅማችንን ያህል ማቀድ፤ ያኔ እምነት እናዳብራለን:: እምነት ሲኖረንና ስንጠነክር ምንስ ብንመኝ የምናሳካበት ልምድ አለና! ነገ ዩኒቨርስቲ ሲገባ የሚፈልገውን ቁጥር ማባዛትና ማካፈል የፈለገውን የረቀቀ ቁጥር መሥራት ይችላል:: አሁን ግን መደመር ላይ ማተኮር አለብን:: እኛም በሕይወታችን የሚቀራረብና ያልተጋነነ እቅድ ያስፈልገናል::
2ኛ.ሳያሳኩ አያርፉም
የተግባር ሰዎች ሳያሳኩ አያርፉም:: መጀመሪያ የሚያቅዱት የሚችሉትን ነው:: ስለዚህ የሚችሉትን ሳያሳኩ አያቆሙም:: አያችሁ! እንዳንዴ እቅድ ስታወጡ ስሜታዊ መሆን የለባችሁም:: ምክንያታዊ ነው መሆን ያለባችሁ:: አንድ ሰው ካለበት ሁኔታ አንፃር ውፍረት ልቀንስ ቢል በአንድ ወር ስንት ኪሎ ግራም መቀነስ እንዳለበት ማወቅ አለበት:: አንድ ኪሎ ግራም ከሆነ ጥሩ ነው:: አንድ ኪሎግራም ለመቀነስ በቀን ምን ያህል ደቂቃ፣ በሳምንት ለምን ያህል ቀን ስፖርት መሥራት እንዳለበት፣ ምን መመገብ እንዳለበት ሊያውቅና ሊያቅድ ይገባል:: ‹‹ይህንንም ሳላሳካ ማረፍ የለብኝም›› ማለት አለበት::
አያችሁ! የተግባር ሰው የምትሆኑት መጀመሪያ እቅዳችሁ የሚመስል ከሆነ ነው:: ከዛ ደግሞ እሱን ሳላሳካ አላርፍም ማለት አለባችሁ:: መጽሐፍ አንብቦ መጨረስ የሚፈልግ ሰው በቀን አስር ወይም አምስት ገፅ ወይ አንድ ገፅ አነባለሁ ካለ እሱን ነው ማንበብ ያለበት:: አንዷን ገፅ ሳልጨርስ አላርፍም ማለት አለበት:: የምንችለው ከሆነ ለምን ጥግ ድረስ አንሄድም?
3ኛ.ሽልማቱ አያጓጓቸውም፤ ትችት አያደናቅፋቸውም
ልጁ በጣም ጎበዝ ተማሪ ነው:: አባቱ ግን በጉብዝናው አይደሰትበትም:: ለምን ሁለት ኤክስ ይገባብሃል? ይለዋል:: አንደኛ ወጥቶ ሁለት ኤክስ ቢገባበት እንኳን ለምን ይለዋል አባቱ:: ስለዚህ ሁልጊዜ ልጁ አባቴን ማስደሰት የምችለው ሙሉ በሙሉ ፈተናውን ከደፈንኩት ነው ይላል:: ልጁ ካምፓስ ገባ:: ካምፓስ ገብቶ እንደውም በደምብ ቁጭ ብሎ አጥንቶ በሚችለው አቅም ሁሉ ጥረት አድርጎ አራት ነጥብ አመጣ:: ሙሉ በሙሉ ‹‹ኤ›› አመጣ:: ደስ አለው:: ተመረቀ:: አባቱ ጋር ሄደ::
‹‹አባዬ ተመረኩ እኮ! ያውም አራት ነጥብ አምጥቼ›› ብሎ አሳያው:: አባት ‹‹አይ ጥሩ በቃ!›› ብሎ ዞር እንኳን ብሎ ሳያየው ሄደ:: ልጅ ተናደደ:: ስሜቱ ተነካ:: ‹‹አባቴ የሚደሰተው ምንም ኤክስ ካልገባብኝ ኤ በኤ ከደረደርኩ ነው ብሎኝ ነበር›› አለ:: አባቱ ግን ግድ የለሽ ሆነበት:: ‹‹ስለዚህ መማሬ ምንድን ነው ትርጉሙ፤ ሕይወቴን መቀየሬ ምንድን ነው ትርጉሙ›› አለ:: መማሩን ጠላው:: ራሱን ጠላ:: ወደ ሱስ ገባ:: ሕይወቱን አበላሸ:: ሱሰኛ ሆነ:: በቃ! ሕይወቱ ተበላሸ:: መጨረሻ ላይ ሊሞት ደረሰ:: ሆስፒታል አባቱ ተሯሩጦ ሄደ:: ልጅ እየቃተተ ነው:: መናገር ግን አልቻለም:: በዛው አሸለበ ሞተ:: አባቱ ምን ያህል እንደሚቆጨው አስቡት::
ከዚህ ታሪክ ሁለት ነገር እንማራለን:: የመጀመሪያው ከሰው ሽልማት የምንጠብቅ ከሆነ የሆነ ቀን እንሰበራለን:: ሲያደንቁን ደስ ሊለን ይችላል:: ካላደነቁን እንከፋለን:: ስለዚህ አንድ ቀን እንሰበራለን:: ልጁን የሰበረውና እንዲሞት ያደረገው ‹‹አባቴ ያደንቀኛል›› ብሎ መጠበቁ ነው:: ለልፋቱ ውጤት ሽልማት ሲጠብቅ ነበር:: ሁለተኛው ግን አባቱ ምንም ነገር አለማለቱ ነው:: አንዳንዴ ሰዎች አጠገባችን ሆነው ሲለፉ ጥረታቸውን ማድነቅ አለብን:: እውነት ነው ይህች ዓለም ውጤትን እንጂ ጥረትን አትሸልምም:: ግን እኛ ለራሳችን መንገር ያለብን ሰዎች ቢያደንቁኝም እቀጥላለሁ፤ ቢተቹኝም የማስተካክለውን አስተካክዬ እቀጥላለሁ ነው ማለት ያለብን:: አንዳንዴ እኮ ምንም ሳንጀምር ተግባር ውስጥ ሳንገባ ሰው ምን ይለናል ብለን ሳንጀምር እናቆማለን:: ይህ የብዙዎች ሕይወት ነው:: ገና ሳንጀምር ሰዎች ምን ይሉኛል፤ ሽልማቱን ወይ ትችቱን ፈርተን እናቆማለን:: ስለዚህ ሥራው ራሱ ለኔ ሽልማት ነው ማለት ያለብን::
4ኛ.ምን እንደሚያስቀድሙ ያውቃሉ
አንዳንዴ የምትፈልገውን ብቻ አይደለም ማወቅ ያለብህ የማትፈልገውንም ማወቅ አለብህ:: ምክንያቱም ‹‹አይ! ይሄ ነገር ይቅርብኝ ይሄ ነው የኔ ትኩረት›› እንድትል ነው:: ሰዎች የነገሩህ ሁሉ ያዋጣል ያሉህ ላይ ሁሉ የምትሞክር ከሆነ ሕይወትህን አትቀይረውም:: የተግባር ሰው አትሆንም:: ብዙ ነገር መሞከር አሪፍነት አይደለም:: ተንሳፋፊ ነው የሚያደርግህ:: ለምን? ሁለት እግር አለኝ ብለህ ሁለት ዛፍ ላይ አትወጣም:: ስለዚህ እስከ ጥግ ድረስ መሞከር ያለብህ ያመንክበት ነገር ላይ ነው:: ብዙ ነገር ላይ አይደለም:: ስለዚህ የተግባር ሰው ለመሆን የምትፈልግ ከሆነ ምን እንደምታስቀድም እወቅ::
5ኛ.የግል ፍላጎታቸውን ወደ ጎን ይተዋሉ
የተግባር ሰዎች ለጊዜያዊ ጥቅማቸው ሲሉ የነገውን ትልቁን ስኬታቸውን አያባክኑም:: ዛሬን ትንሽ ልጨነቅና ነገሮችን ላሳካ፤ በጥሩ መንገድ ላስኪድ ይላሉ:: እንደውም ታዋቂው ቦክሰኛ መሐመድ አሊ ‹‹ዛሬን ተጨነቅና ነገን በደስታ ኑር!›› ይላል:: በአንድ አጋጣሚ ደግሞ መሐመድ አሊ ዝናው ጫፍ በደረሰበት ግዜ ሲልቨስተር ስታሎን የተሰኘው የሆሊውድ አክተር አብሮት ጂም ሊሠራ ሄደ:: አብረው ጂም መሥራት ጀመሩ:: ሲልቨስተር ስታሎን ትንሽ እንደሠራ ደከመው:: መሐመድ አሊ ግን አሁንም ጠንክሮ እየሠራ ነው:: ሲልቨስተር ስታሎን ስፖርቱን ሠርቶ ጨርሶ ሻወር ወስዶ ሲመለስ መሐመድ አሊ አሁንም ስፖርቱን እየሠራ ነው:: ሲልቬስተር በጣም ገረመው:: ‹‹ምን ያህል ፑሽና ሲት አፕ ነው ዛሬ የሠራኸው?›› ብሎ ጠየቀው:: ‹‹አይ አልቆጥረውም›› አለው:: ‹‹እንዴት?›› ሲለው ‹‹መቁጠር የምጀምረው ሲደክመኝ ነው›› አለው::
አያችሁ! ስንቶቻችን ነን ገና ትንሽ ነገር እንደለፋን ‹‹አረ ልፋቴ በዛ፣ ይህን አድርጌ፣ ይሄን ሠርቼ›› ብለን በቃ አሁን ፈታ ልበል፤ ለምን ፊልም አላይም ራሴን ለምን ኣላዝናናም እንላለን:: ትንሽ ልፋታችንን እንትልቅ እንቆጥራለን:: መሐመድ አሊ ግን ገና ሲደክመው ነው መቁጠር የሚጀምረው:: ስለዚህ አንዳንድ ግዜ ለትልቁ ዓላማችን ስንል ወደ ጎን የምንተዋቸው ነገሮች መኖር አለባቸው:: የተግባር ሰው መሆን ካለብህ እንደዛ ነው ማድረግ ያለብህ::
6ኛ.ከቀላሉ ሥራ ጀምር
እስኪ ከማጥናትህ፣ ከማንበብህ ወይም የሆነ ሥራ ከመሥራትህ በፊት አካባቢህ ላይ ያሉትን ነገሮች ንፁሕ አድርጋቸው:: በቃ እስኪ ቤትህ ወይ ቢሮህ አንብብ! አንብብ! ሥራ! ሥራ! የሚያስብል ይሁን:: ያኔ በጥሩ ሙድ ትጀምራለህ:: ቀለል ይልሃል:: ለምሳሌ ጠረጴዛውን ብታስተካክለው እስኪ ለምን ቀስ ብዬ አላነብም፤ አልፅፍም ትላለህ:: ንፁሕ ነገር ስታይ ደስ ይልሃል:: እስፖርት መሥራት ከፈለግ እስኪ ከቻልክ ብድግ በልና ቱታ ነገር ልበስ፤ ጫማውን አድርግ ከመሥራትህ በፊት ከቀላሉ ጀምር:: ከቀላሉ ስትጀምርና ስትዘጋጅ ጥሩ ሙድ ውስጥ ትገባለህ:: እንደውም የሚያነቃቃ ነገር አትጠብቅ:: እስኪ ስነቃቃ እሠራዋለሁ አትበል:: ትንሹን ቀላሉን ነገር ስትጀምረው ሥራው ራሱ ያነቃቃሃል:: ስለዚህ ከቀላሉ ጀምር:: የተግባር ሰው ትሆናለህ:: ብዙ ግዜ ከባዱን እጀምራለሁ፤ ከባዱን እሠራለሁ ስትል አንዱንም አትሠራውም:: ከቀላሉ ጀምር ወዳጄ!
7ኛ.እውነታውን ይቀበላሉ
የተግባር ሰዎች እውነታው መራር ቢሆን እንኳን ይውጡታል:: አይቸኩሉም:: ለምሳሌ ጓደኞቻቸውና በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ቶሎ ሲቀየሩ፤ ሲያልፍላቸው ያዩና ‹‹ለምን እኔስ ቶሎ አያልፍልኝም›› ብለው የአስር አመት ስኬት በአንድ ዓመት ካልተወጣሁት አይሉም:: ጊዜን ካልቀደምኩት አይሉም:: ጊዜን ግን ከጎናቸው ያሰልፋሉ፤ ይታገሳሉ:: የታገሰ ከሚስቱ ይወልዳል አይደል የሚባለው:: ይታገሳሉ:: ትልቅ ነገር የሚፈልግ ሰው እኮ ትልቅ መስዋዕትነት መክፈል አለበት::
በጣም ንፁሕና የጠራ ውሃ የሚፈልግ ሰው ከጥልቅ ጉድጓድ ወይም ምንጭ መቅዳት አለበት:: ልፋትህም እንደጉድጓዱ ጥልቅ መሆን አለበት:: ስለዚህ ግዜን ልቅደመው ማለት የለብህም:: ከእውነታው ጋር ታረቅ:: የአስር ዓመት ሕልሜን በአንድ ዓመት ካልተወጣሁት አትበል:: ግን ከእውነታው ጋር ታረቅ:: እውነታው መራር ቢሆንም ዋጠው:: ያኔ የተግባር ሰው ትሆናለህ:: ያኔ ሕልምህን ለማሳካት የሚጠበቅብህን ሁሉ ነገር ታደርጋለህ:: ግዜ ቀደመኝ፣ ሰዎች ጥለውኝ ሄዱ አትልም:: መቼም አይረፍድብህም:: የተግባር ሰው ከሆንክ እንደውም ግዜን ትቀድመዋለህ:: ግዜን ከጎንህ ታሰልፈዋለህ:: አሁን ምን ላድርግ፣ አሁን ላይ ከኔ የሚጠበቀው ነገር ምንድን ነው በል!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም