ከቅጥር ወደ ኢንቨስትመንት ያደገው የዲዛይነሯ ጉዞ

የዲዛይኒንግ ሙያ ምንነቱ እንኳን በውል ሳታውቅ ገና በጠዋቱ በለጋ እድሜዋ በውስጧ ሲብሰለሰል ቆይቷል:: ልጅ ሳለች ጀምሮ ሀሳቧን በተግባር ለመተርጎም ዲዛይኖችን በመፍጠር የተለያዩ ልብሶች በመሥራት እጆቿን ታፍታታ ነበር:: በወቅቱ ታድያ ሕልሟን እውን ለማድረግ የራሴ የምትላቸውን ልብሶች በቤት ውስጥ ለመሥራት አላመነታችም:: ቀድሞም ቢሆን ለሙያው የተሰጠች ነበረችና ሙያውን ለመቀላቀልና በሙያዋ ታዋቂነትን ለማትረፍ በብዙ ጥራለች:: ጥረቷም ተሳክቶ በውስጧ የሚንቀለቀለውን የዲዛይኒንግ ሙያ የተማረችው የዕለቱ እንግዳችን ዲዛይነር ማርስዓለም ሁሴን ትባላለች::

ዲዛይነር ማርስዓለም ተወልዳ ያደገችው በመዲናችን አዲስ አበባ ነው:: የወላጆቿ ሙያውን መሞከር ወደ ሙያ እንድትሳብና እንድትገባ መልካም ዕድል ፈጥሮላታል:: በሙያው በመመሰጧም የተለያዩ ሥራዎች በቤት ውስጥ በመሥራት የዲዛይኒንግ ሙያ አሃዱ ብላ ጀምራለች:: በአሁን ወቅትም ቢኤም ኤፍ ባሕላዊና ዘመናዊ አልባሳት ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን (ማርስ ዲዛይን) አቋቁማለች::

ዲዛይነሯ ሙያውን ከጀመረች ጀምሮ በቤት ውስጥ የተለያዩ ዲዛይን ያላቸው ልብሶች እየሠራች በነበረችበት ወቅት ሥራዋን ያዩና የተመለከቱ ሰዎች በልምድ የምትሠራውን ሥራ በትምህርት በመደገፍ እንድታሳድግ ይመክሯት ነበር። ታዲያ አንድ አጋጣሚ የሙያው ባለቤት እንድትሆን የሚያስችል መንገድ ከፋች የሆነ ዕድል ተፈጠረላት:: ዕድሉን በመጠቀም በሙያው ተቀጥራ መሥራት ቻለች።

ነገሩ እንዲህ ነው። ሥራዎቿን ያዩና የወደዱ ለጋብቻ ዝግጅት እያደረጉ ያሉ ጥንዶች ቤት ውስጥ እየሠራች ሳለ ወደ እርሷ መጥተው የምትሠራቸው ልብሶች በጣም ስለሚወደዱ የሠርጋቸውን ልብስ እንድትሠራላቸው ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ ቀኑ ደርሶ የተሠራላቸውን ልብስ ሲመለከቱ በጣም ይደሰታሉ። ዲዛይነሯ ልብሱን የሠራችላቸው የዲዛይኒንግ ትምህርት ሳትማር በራሷ ውስጣዊ ፍላጎትና ባላት ተነሳሽነት መሆኑን ሲስሙ ደግሞ የበለጠ በመገረም በልምድ የምትሠራውን ሥራ በሙያ ቢታገዝ የበለጠ ሥራ መሥራት እንደምትችል በማመን ከዲዛይነር ጋር እንድትገናኝ መንገዱን አመቻቹላት:: ጥንዶቹ በሙያ ብቁ ከሆነች ዲዛይነር ጋር አገናኟት:: ዲዛይነሯም ‹‹ሥራዬን ስታይ ስለወደደችው እሷ ዘንድ ተቀጥሬ እንድሠራ አደረገች›› ብላለች::

ዲዛይነር ማርስዓለም፤ ሙያው ለማሳደግና ከሌሎች ልምድ ለመቅሰም በማሰብ ለ10 ዓመታት ያህል ተቀጥራ በመሥራቷ ብዙ ልምዶቹ እንዳገኘችበት ትገልጻለች:: ተቀጥራ ትሠራበት የነበረችበት ‹‹የጂጂ ዲዛይን›› ባለቤትና መሥራች ከሆነችው ዲዛይነር ገነት ዘንድ ሲሆን ከሷ በብዙ መልኩ ለሙያው መሠረት የሚሆን ብዙ ልምዶችና ተሞክሮዎች ያገኘበትና ሙያ በሚገባ የተማረችበት እንደሆነ ትመሰክራለች:: ይህም ለዛሬ ውጤታማነቷ መሠረት እንደሆናት ትገልጻለች::

በዚህ ያላበቃው ማርስዓለም ሙያውን በጥልቀት የማወቅ ጉጉት ቀጥሎ ሙያውን በይበልጥ በትምህርት በመደገፍ በማሰብ ከሥራዋን ጎን ለጎን በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት በማቅናት የዲዛይን ትምህርቷን ተከታትላለች::

ዲዛይነር ማርስዓለም ልምድ ልትቀስም የገባችበት ትምህርት ቤት ልምዱን ብቻ ቀስማ የወጣች አልነበረም:: የዛሬ ውሃ አጣጭ የሆነ የትዳር አጋሯ ያገኘችበት አጋጣሚ ጭምር የፈጠራላት ነው:: ባለቤቷ ዲዛይነር ደጀኔ ሙሉነህ ይባላል ። ታዲያ ባለቤቷም ዲዛይነር በመሆኑን ሙያው የጋራቸው አድርገውታል:: እንደሷው ሁሉ የትዳር አጋሯም ለሙያው የተሰጠ በመሆኑን፤ የሁለቱ ባለትዳሮች ለሙያ መሰጠት ለስኬት እንዳበቃቸው አልሸሸገችም::

ሁለቱም የአንድ ሙያ ባለቤት መሆናቸው ሥራውን በፍቅር፣ በመመካከር፣ በመተጋገዝና በትጋት እንደሚሠሩት ያስቻላቸው መሆኑን የምትገልጸው ዲዛይነር ማርስዓለም፤ ከዚህም ባሻገር ሙያው ከፍ ወደሚል ደረጃ እንዲደርስ የሚያደርጉትን ጥረት ላይ እገዛ ማድረጉን ትናገራለች:: ‹‹ባለቤቷ የሙያ ባለቤት መሆኑ ጥሩ ሥራዎችን እንድንሠራና ውጤታማ እንድትሆን አስችሏታል፤ ሁለታችንም የጎደለበት ቦታ በመገኘት ክፍተቶች እንዳይኖሩ በእጅጉ ተጋግዘን እንድንሠራ ረድቶናል:: ሁለታችንም ሥራውን በባለቤትና የኔ ነው በሚል ስሜት እንድንሠራም አስችሎናል:: በሥራችንን ውጤታማ እንድንሆን አድርጎናል›› ትላለች::

ዲዛይነሯ፣ ሙያውን ከጀመረች 23 ዓመታት ያስቆጠረች ሲሆን፤ የራሷን “ቢኤም ኤፍ ባሕላዊና ዘመናዊ አልባሳት ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (ማርስ ዲዛይን)” የተሰኘ ድርጅት መሥርታ ሥራ ከጀመረች 13 ዓመታት ተቆጥሯል:: ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከመንግሥት በተደረገላት ድጋፍ የማምረቻ ቦታ (ሼድ) ተሰጥቷት ሥራዎችን እየሠራች ትገኛለች::

“ቢኤም ኤፍ ባሕላዊና ዘመናዊ አልባሳት ማምረቻ ፒኤልስ (ማርስ ዲዛይን)” ባሕላዊና ዘመናዊ የሆኑ የአዋቂዎች፣ ወጣቶችና የሕጻናት እንዲሁም ለሁሉም ሰው የሚሆኑ የሽመና ልብሶች የሚያመርት ድርጅት ነው:: ከዚህም በተጨማሪ ቦርሳ፣ መጋረጃ፣ አልጋ ልብስ፣ የጠረጴዛ አልባሳት እና ለመሰል አገልግሎት የሚውል ልብሶችን ያመርታል::

አሁን ላይ ገላን ከተማ አካባቢ በሚገኘው የማምረቻ ቦታዋ አልባሳት እያመረተች ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ገበያ እያቀረበች ትገኛለች:: የምታመርታቸውን ዘመናዊና ባሕላዊ አልባሳት ቦሌ በሚገኘው መሸጫ ሱቅ ለገበያ እያቀረበች ሲሆን፤ የተለያዩ እንደቴሌግራም፣ ፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ቲውተር እና የመሳሰሉ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም በዓለም ገበያ ላይ ምርቶቹን እያስተዋወቀች ትገኛለች::

አሁን ላይ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት በርካታ ደንበኞች እንዳሏት የምትናገረው ዲዛይነር ማርስዓለም፤ የውጭ ሀገር ደንበኞችን ለማፍራት የቻለችው ዲኤች ኤልና መሰል የገበያ አማራጮችን በመጠቀም ምርቶቿን ለውጭ ገበያ በማቅረብ እንደሆነ ትናገራለች:: በዚህም ወደ ውጭ ከሚላከው (ኤክስፖርት) የሚደረገው ልብሶች የማይተናነስ ገበያ እንዳላት ትገልጻለች::

ዲዛይነሯ፤ አብዛኛው ሥራዎቿ በየዓመቱ በሚዘጋጅ የፋሽን ሳምንት ላይ እና በተለያዩ የፋሽን ትርዒቶች ላይ የማስተዋወቅ አጋጣሚ አግኝታ እንደነበር ታስታወሳለች:: ይህም መልካም አጋጣሚ ሆኖላት ከበርካታ ታዋቂ ሰዎች፣ ባለሥልጣናት፣ አርቲስቶች፣ አትሌቶች ጋር እንድትገናኝና እንድትተዋወቅ ዕድል ፈጥሮላታል:: በተፈጠረላት ዕድልም ተጠቅማም በብዙ ሰዎች ዘንድ የተወደዱ በየጊዜው በማኅበራዊ ሚዲያ ሳይቀር ደጋገመው የሚታዩ ልብሶች ለአትሌቶች፣ ለመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ለአርቲስቶች እና ለበርካታ ታዊቂ ሰዎች ለመሥራት ችላለች ::

ፋሽን ዲዛይነሮች ማኅበር አባል ስትሆን፤ ማኅበሩ 78 ዲዛይነር አባላት ያሉት ሲሆን፤ የተለያዩ የፋሽን ዲዛይን ሥራዎችን በቅንጅት በመሥራት እንደሚያሳዩም ትገልጻለች:: በየዓመቱ በባሕል ሚኒስቴር የሚዘጋጀው የፋሽን ሳምንት ዝግጅት እንዳለ ሆነ ማኅበሩም በራሱ የተለያዩ የፋሽን ትርዒቶች ስለሚያዘጋጅ እዚያ ላይ የራሷ አስተዋፅዖ እንደምታደርግ ትገልጻለች::

በተለይ ማኅበራዊ ኃላፊነት ከመወጣት አንጻር በሙያዋ የሚጠበቅባቸው ለመወጣት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራች ትገኛለች:: ከማኅበሩ አባላት ጋር በአንድነት ለልብ ሕሙማን፣ የአካል ጉዳተኞች፣ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ለማገዝ በማሰብ በተዘጋጁ የፋሽን ትርዒት መድረኮች ላይ በመሳተፍ እነዚህ ወገኖች ለማገዝ ባለመ የገቢ ማሰባሰቢያ ላይ ተሳታፊ እንደሆነች ትገልጻለች::

በድርጅቷም በርካታ ሰዎች በሥራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን ሸማኔዎች፣ ጠላፊዎች፣ የስፌት ሥራ የሚሠሩ፣ የቁጭት ሥራ የሚሠሩ፣ ጥጥ ፈታዮች ጨምሮ በአሁን ላይ 45 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥራለች:: ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ሴቶች ናቸው:: በድርጅቱ የሚሠሩ ሠራተኞች ለሥራ የደረሱ ልጆች ካላቸው ድርጅቱ በተለያየ ሥራ ዘርፍ ላይ ቀጥሮ የማሠራት ልምድ እንዳለም ገልጻለች::

ዲዛይነሯ እንደምትለው፤ በመንግሥት በኩል ማምረቻ ቦታ (ሼድ) በመስጠት የተደረገው ድጋፍ ቀላል የሚባል አይደለም:: የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም በተለያዩ ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች ላይ እንድንሳተፍ በማድረግ ትልቅ እገዛ እያደረጉልን ነው:: በተለያዩ ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች መሳተፋችን ብዙ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩልን አግዞናል:: ይህም ሥራችን ውጤታማ እንዲሆን አስችሏል::

የምታመርታቸው ምርቶች ጥራት ላይ በእጅጉ እንደምትጨነቅ የምትገልጸው ዲዛይነሯ፤ ምርቶቿ የጥራት ደረጃቸው የጠበቁ ናቸው:: ደንበኞቿ ልብሶቿን በጥራታቸው እንደሚለዩአቸውና እንደሚወዷቸው ትገልጻለች:: አሥር ሸማኔዎች ቀጥራ በምትፈልገው ዲዛይን መሠረት ልብሶቹን ስለምታሠራና የምትጠቀማቸውን ማቴሪያሎችም ጥራታቸው የጠበቁ በመሆናቸው ምርቶቿ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ በጥንቃቄ የተሠሩ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል::

የሀገራችንን የሸማ ልብሶች ለባሹ በሚመቸው መልኩ አድርጎ እንዲለብሱ ተደርገው ይሠራሉ:: በጉርድ፣ በሱሪ፣ ጋዎን፣ እና ወጥ የሆነ ልብሶች በመሥራት ቀላል ብለው ዘወትር እንዲለበሱ ተደርገው ይሠራሉ:: ለዚህም ልብሶቹ ሲለበሱ የሚያምሩ ከመሆናቸው በላይ ከለበሷቸው ሰዎች በራሳቸው ላይ ከማማር አልፈው ሀገራቸውን እንዲያስተዋወቁ የሚያደርጉ ናቸው::

በተለይ በባሕላዊም ሆነ በዘመናዊ የሚሠሩት አልባሳት የደንበኞቻቸውን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ሆነ በተለያዩ በዓላትና ዝግጅቶች ላይ የሚለበሱ እንዲሁም በአዘቦት ቀን እንደልብ የሚለበሱት ያካተቱ ናቸው::

ዲዛይነሯ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባሕላዊ ልብሶችን በመሥራት ለሀገር ውስጥም ለውጭ ገበያም እያቀረበች ሲሆን፤ ባሕላዊ ልብሶች ስትሠራ ጥናት በማድረግ በጥንቃቄ በትክክል የወከለውን ብሔር እንዲገልጽ አድርጋ ታዘጋጃለች:: የምትሠራቸው ባሕላዊ አልባሳት ሀገር በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያደርጉ ትናገራለች::

በተጨማሪም የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚለበሷቸውን እንደሂጃብ አይነት አልባሳትን በማካተት ለየት ባለመልኩ ዲዛይን የተደረጉ ልብሶችን እንደምትሠራ ትገልጻለች:: የምትሠራቸው አልባሳት ለሁሉም በሚሆን መልኩ የሚዘጋጁ ናቸው:: በተለይ ቀሚሱን ከሂጃቡ ጋር እንዲመሳሰል ተደርጎ ለባሹ ሳይጨናነቁ ዘና ብለው እንዲለብሱ የሚያደርግ ልብስ እንደምትሠራ ትገልጻለች::

የሀገር ውስጥ አልባሳት በዋጋ ደረጃ ከፍተኛ እንዲሆን የሚያደርገው የጥሬ እቃ አቅርቦትና የማቴሪያል እጥረት መኖሩ ነው የምትለው ማርስዓለም፤ እነዚህ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ማምረት ቢቻል በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ማቅረብ እንደሚቻልም ትገልጻለች:: አሁን ላይ ቀጭን ጥለት ካለው ልብስ ሰፋፊ ጥለት ያለው እየተመረጠ መሆኑን ገልጻ፤ ሥራው በእጅ የሚሠራ እንደመሆኑን መጠን የሚወስደው ጊዜ እና ጉልበት በጣም ቀላል ስላልሆነ የልብሱ ዋጋ እንዲጨምር ያደርገዋል ትላለች ::

በቀጣይ የጥራት ደረጃቸው የጠበቁ አልባሳትን በማምረት ኤክስፖርት የማድረግ ሀገሯን ለማስተዋወቅ ጭምር እንደምትሠራ ትገልጻለች:: የኢትዮጵያን ያልተነኩ ቱባ ባሕል ያላት አገር በመሆኗ ይህ ዓለም ላይ እንዲተዋወቁ ጠንክራ እንደምትሠራ ገልጻ፤ የኢትዮጵያ አልባሳት በዓለም ገበያ ላይ ተፎካካሪና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማስቻል ታዋቂ ብራንድ ለመፍጠር ጭምር እንደምትሠራ አስታውቃለች::

ማርስዓለም ሥራ ስትጀምር የነበራት በአንድ የልብስ ስፌት ማሽን ነበር:: ቀስ በቀስ ሁለት ሦስት እያለ የልብስ ስፌት ማሽኑን ቁጥሮች እየጨመረች አሁን 80 ያህል የልብስ ስፌት ማሽን በማስገጠም ሥራዋን በጋርመንት ደረጃ ለመጀመር ዝግጅት እያጠናቀቀች ትገኛለች::

በ15 ሺብር ካፒታል የተጀመረ ሥራ አድጎ ሞዴል ኢንተርፕራይዝ ሆኖ አሁን ላይ ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገር ችሏል:: ማርስዓለም በኢንቨስትመንት ደረጃ ሥራዎችን ለመጀመር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ 10 ሚሊዮን ብድር እየተመቻቸላቸው መሆኑን ትገልጻለች:: በቀጣይ ድርጅቱ ኢንቨስትመንት ደረጃ አልባሳትን በማምረት ኤክስፖርት እንደሚያደርጉ ገልጻ፤ በኢንቨስትመንት ሥራ ሲጀመሩ ከ140 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚችሉ ትገልጻለች::

ዲዛይነሯ ‹‹መጀመሪያ ላይ የነበረኝ ከፍተኛ ፍላጎቱ እንጂ ለዚህ ያደረሰኝ የተነሳሁበት በጣም ትንሽ ነገር ነው:: የተነሳሁት ከትንሽ ነገር መሆኑ ብዙ ነገሮችን እንዳይ ስላደረገኝ ከዚህ በኋላ ብዙ ነገር እንደሚቻልና ምን ነገር ሊከብደኝ እንደማይችል ተረድቻለሁ›› ትላለች:: የሰዎች የሚያሰቡትን ሀሳብ ወደ ተግባራዊ ለመቀየርና የፈለጉበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችና መሰናክሎች ሊያጋጡሙት ይችላል:: እነዚህ በትዕግስት ማለፍ ከቻሉ ያሰበበት መድረስ የማይቀር ነው:: ለዚህ የሚያስፈልገው የሚያደርጉትን ጥረት ያለመታከትና ያለመሰልቸት ማከናወን ያስፈልጋል›› ብላለች::

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You