እውቀትን በእውነት፣ ለእውነት

ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ መልዕክቱ ምዕራፍ 9 ቁጥር 6 ላይ ‹አላዋቂነትን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ፣ በማስተዋልም መንገድ ሂዱ› ይለናል:: ከዚህ ኃይለ ቃል በመነሳት አንዳንድ ነገሮችን እንመልከት:: አላዋቂነት ምንድነው? የማስተዋልስ መንገድ የትኛው ነው? ስል በጥያቄ ልጀምር::

አላዋቂነት መልከ ብዙ ቢሆንም ርዕሳችን ሀገር ስለሆነች እውነት የሌለበት፣ ከብዙኃነት ኩሬ ውስጥ ያልመነጨ፣ ትውልድ መር ያልሆነ እንደሆነ ሁላችንንም ያስማማናል:: ከዚህ በተቃራኒ የማስተዋል መንገድ እውነትን የለበሰ፣ ምንጩም በውል የሚታወቅ ከየት? ብሎ ለሚጠይቅ ማን? ላለ ለምንና መቼ እንዴትስ? ብሎ ለሚጨነቅ መልስ የሚሰጥ እንደሆነም ይታመናል::

‹አላዋቂነታችሁን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ‹ በሚለው ሐረግ ውስጥ ሕይወት ከእውቀት ጋር ተቧድኖ እናገኛለን:: አላዋቂነት ምንድነው? አላዋቂነት እውነት ያልገባበት፣ በብስለትና በብልህነት ያልተዋጀ እውቀት ማለት ነው:: በሕይወት ለመኖር እውነት ለበስ እውቀት፣ በመረጃና ማስረጃ የተደገፈ ምንጩ የሚታወቅ ሐቅ አስፈላጊ እንደሆነ መተማመን ላይ ያደርሰናል::

እውነት የሌለው እውቀት ገዳይ፣ መርዛማ፣ ሀገርን ወደብዥታ፣ ትውልዱን ወደዝቅታ የሚወስድ እንደሆነ ለመረዳት ቀላል ነው:: የኃይለ ቃሉ ማብቂያ ‹በማስተዋል መንገድ› ሂዱ የሚል ነው:: የማስተዋል መንገድ ሰብዓዊነት ላይ ያረፈ፣ እውነት ላይ የተመሰረተ፣ ነፃ የሚያወጣ ነው::

እውቀት ነፃ አውጪ ነው:: ነፃ የሚያወጣን ግን በእውነት ደልቦ ሲሰባ ነው:: በሕይወት የምንኖረው፣ ሠላምና እርቅ የመጪው ጊዜ ፍሬዎቻችን የሚሆኑት፣ ሀገራችንን በአዲስ አስተሳሰብ የምናራምዳት እውነት በገባበት እውቀት ነው:: ትውልዱ ፍቅርን ለብሶና አብሮነትን ወርሶ አጠገቡ ካለው ጋር በስጋት ሳይሆን በወንድማማችነት እንዲተያይ አላዋቂነታችንን መተውና ለማተዋል መሰናዳት ግድ ይለናል::

የእውቀት ቀዳማይ ጽንሰ ሀሳቦች ከሆኑት መሐል እውነት አንዱና ዋነኛው ነው:: እውቀት እውነት ከሌለው ማር እንደሌለው ቀፎ ነው:: ምን አርቀን ብንሰቅለው፣ በተዋበና ባማረ አበቦች ብንከበው ንቦች ካልሰፈሩበት በውስጡም ማር ካልያዘ ቀፎው ብቻውን ትርጉም አይኖረውም:: በውስጡ እውነት የሌለው እውቀት፣ በውስጡ ተራማጅና ሁሉን አቃፊ ያልሆነ ፖለቲካ፣ ሀገርና ሕዝብ ያልተቆራኙበት ዓለማዊና መንፈሳዊ ሥርዓቶች ማር እንደሌለው ቀፎ ትርጉም የማይሰጡ ናቸው::

እውቀት በውስጡ አስታራቂና አግባቢ፣ አስተቃቃፊና አጠጋጊ፣ አወዳሽና አሞጋሽ፣ አክባሪና አቃፊ እውነት ከሌለው አንድነትን በመሸርሸር እንዲሁም ብዙኃነትን በመናድ ወይም ደግሞ መሰል ችግሮችን በመፍጠር ትውልዱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ይወስደዋል:: የትውልዱ አቅጣጫ መሳት ደግሞ ከእውነት እንዳንገናኝ፣ በሐሰት ትርክት በተቀደደ ሰርጥ እንድንፈስ በማድረግ ለሐሰት እውቀት ሰለባ የሚያደርግ ነው::

የሀገራችን አብዛኛው ችግር ከሐሰት እውቀት የመነጨ ነው:: የሐሰት እውቀት መነሻ ስለሌለው መድረሻውን ጠብና ክርክር፣ ጥላቻና መገፋፋት በማድረግ በሀገርና ሕዝብ ላይ የከፋ ውድመትን ያስከትላል:: ታሪኩ በዚህ አያበቃም በወቅቱ ካልታከመና ምንጩን ካላደረቅነው ለምንግዜም አብሮን የሚቆይ ነው:: በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊ ትስስራችን መሐል የገቡ ጉድፎች ይሄን የሐሰት እውቀት ታከው ነፍስ የዘሩ ናቸው::

እንደምሳሌ ፖለቲካችንን ብናየው ላለፉት ስልሳ ዓመታት በተመሳሳይ ትኩሳት፣ በተመሳሳይ አስተሳሰብ ስር ነን:: ገሎ መሞትን፣ ጥሎ ማለፍን እንደመፍትሔ ተቀብለን የመጣን ነን:: ይሄን ልምምድ ለትውልዱ አውርሰን ትውልዱ በዘረኝነትና በጥላቻ ዳብሮ ከአብሮነት ይልቅ ኃይልን የመረጠበትን አሁናዊ ታሪካችንን ማስታወስ ይቻላል:: እነኚህ የሐሰት ትርክቶች ከየት መነጩ ብለን ብንጠይቅ ብዙ መነሻ ምንጮችን ነው የምናገኘው::

እንደመፍትሔ የሚወሰደው በስክነትና በእርጋታ ምንጩን የምናደርቅበትን መላ መዘየድ ነው:: ለችግሮቻችን እውቅና ከመስጠት ባለፈ የመፍትሔ ሀሳብ ስናመነጭ፣ የመፍትሔ መድረክ ስናዘጋጅ እምብዛም አንታይም:: የነበረውን እውቅና ከመስጠት ባለፈ ትርክቶችን ለመሻር የሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ እስከዚህም ነን:: በንቃትና በወኔ ከሐሰት ወደእውነት፣ ከእብለት ወደ አቃፊ ሐቅ ካልተሸጋገረን አቅም ሀገራችንን ከሐሰት እውቀት ለማሻር አቅም አይኖረንም::

የነበረውን ከማስተካከል ጀምሮ ያለውንና የሚመጣውን በሀገርኛ የጋራ እውነት ስር ለማስተዳደር ከነበርንበት ሽርፍራፊያዊ እውነት መውጣት ተቀዳሚ ግብራችን ይሆናል:: ፈር የሳቱ፣ መሠረታቸውን የለቀቁ አንዳንድ ዝንፎች እንዲህ ባለው የጋራ ውይይት ካልሆነ በሌላ የማይስተካከሉ ናቸው::

ያለው በነበረው፣ መጪው ደግሞ ባለውና በነበረው የሚቃኝ ነው:: ትላንት ወደዛሬ መጥቶ ዋጋ አስከፍሎናል:: ዛሬ ወደነገ እንዳይሄድ እና ሌላ ዋጋ እንዳያስከፍለን እውነትን ፍለጋ ላይ መሠማራት ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ነው:: ሀገር እውነት ባለበት እውቀት ካልሆነ በምንም ብትዋጅ ልክ አትመጣም:: መቆም አቅቶን የምንገዳገደው፣ መጽናት አቅቶን የምንፈልገው ምንጫቸው ባልታወቀ እውቀቶች ነው::

የሐሰት ትርክት በአንድ ሀገር ላይ እንደአውዳሚ መርዝ ነው:: መርዙ በጊዜ ካልፈረሰ ትውልድ እየነደፈ በሽተኛ ነው የሚያደርገው:: ሀገራችን በዚህ መርዝ ተመርዛ እንዳትሞትና እንዳትሽር የሆነችበትን ብዙ አጋጣሚዎችን ማውሳት ይቻላል:: ወደአዲስ በሁላችንም ላይ ብርሀን ወደሚፈነጥቅ፣ ወደሚያስተቃቅፍ፣ ወደሚያግባባ የጋራ እውቀት መመለሳችን ጥቅሙ የነበርንበትን ከማስተካከል በተጨማሪ መጪውን የሚያቀና ጭምር ነው::

ተሐድሶ ከታሪክ ዝንፈት፣ ከእውነት ሽርፈት የሚጀምር ነው:: የተዛነፉ ታሪኮች እና የተሸረፉ እውነቶች እስካልተጠገኑና እስካልተስተካከሉ ድረስ ከሐሰት ትርክት መውጫ መንገድ የለንም:: በጊዜ እልባት ያልተሰጣቸው ተደባብሰው የሚታልፉ አንዳንድ ነገሮች የባሰና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ ሚናቸው የላቀ ነው:: በውይይት እና በምክረ ሀሳብ ዳብረንና ደርጅተን ነውሮቻችንን ማጽዳት ተሐድሷችንን እውን የምናደርግበት አጋጣሚያችን ነው:: ለእንዲህ አይነቱ ለውጥ ብቸኛ ማለፊያ መንገዳችን እውነትን ፈልጎ ማግኘት ነው::

እውነት አርነት የምንወጣበት፣ ክፍተቶቻችንን የምንደፍንበት የስምምነት ሰነዳችን ነው:: በአስታራቂና በአግባቢ እውነት በኩል መጪውን ለማየት እያደረግነው ላለው ጥረት እውነት ለበስ እውቀት እጅግ አስፈላጊያችን ነው:: አብዛኞቹ መነሻዎቻችን ጋርዮሽን በተመለከተ እምብዛም አስተማማኞች አይደሉም:: ከየት ተነስተን የት እንዳለንና የታሪኮቻችን መነሻ ቦታ እውነተኛ ስፍራው ያን ያክል የሚታወቅ አይደለም:: እነዚህ አጋጣሚዎች ናቸው ለሐሰተኛ እውቀቶች በር በመክፈት እውነትን ደብቀው ለአስቸጋሪ ሕይወት የዳረጉን::

ልክ ያደለን ልክ አይደለም የሚሉና ሁነኛውን የሚቀበሉ የፍትሕ ሚዛኖች ያሹናል:: ከውሸት ጋር አብረው እውነትን የሚደብቁ እነሱ ዋጋ አስከፍለውን ከርመዋል:: እውነትን የመሻት፣ ነፃ አውጪና ሐሰተኛ እውቀቶችን በመቃወም የሚከሱ ድፍረት ለበስ ወኔዎች ወደአዲሱ እውነት መሸጋገሪያ ድልድዮቻችን ናቸው:: የታቀፍናቸውን ካለቀቅን፣ የጨበጥናቸውን ካልተውን ከሐሰት እውቀቶች መቆራረጥ ይቸግረናል:: ይሄን ለማድረግ ደግሞ መንግሥት ነቅቶ ሕዝቡን ማንቃት፣ የሃይማኖት አባቶች ተሳትፎ ሚናው የበረታ ነው::

አይጥ የማትይዝ ድመት የቻይናውያን የአዲስ አስተሳሰብ መነሻ ነው:: የዛሬ ስልሳ አመት ገደማ ቻይናውያን ለትውልዱ እርባና በሌለው እና ለሕዝብ ትርፍ በማይሰጥ በሐሰት እውቀት ውስጥ ነበሩ:: አንድ ወቅት ላይ በተቀጣጠለ አዲስ አስተሳሰብ በኩል የአሁኗን ልዕለ ኃያል ሀገር መሆን ችለዋል:: ነገሩ እንዲህ ነው.. ቻይናውያን እንደእኛ ሀገር ማደግና መሠልጠን ፈለጉ:: የነበሩበት ሁኔታ ግን ያንን ለማድረግ ዕድል የሚሰጥ አልነበረም:: በኋላም የነበሩበትን ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ አስተሳሰብ የሚሽር ‹አይጥ የማትይዝ ድመት ምን ትሠራልናለች? ወደሚል ሁሉን አቀፍ ንቅናቄ ዞሩ::

ይሄ ንቅናቄ የሐሰት እውቀቶችን በመሻር፣ ሀገርና ሕዝብን ከድህነት በማውጣት በዓለም ላይ ኃያሏን ቻይና ፈጥሯል:: አሁን ላይ ቻይና በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በትራንስፖርት ከዓለም ፊተኛ ከሆኑት መሐል ትመደባለች:: መነሻዋ የውሸት ትርክቶችን የሚቀይር ዋጋ ያለውና ትርፍ አምጪ ተሐድሶ ነው:: አይጥ የማትይዝን ድመት እያሽሞነሞኑ በርካታ የስኬት ዕድሎችን አባክነዋል::

እኛስ አይጥ የማትይዝ ድመት ምን ትሠራልናለች? ትውልዱን የማይመራ፣ ሰብዓዊነትን ማዕከል ያላደረገ፣ መነሻው የማይታወቅ የሐሰት እውቀት ምን ይበጀናል? ፍቅር የሌለበት፣ በጠብ የታጀበ፣ ወንድማማችነትን የሻረ፣ ለእድገትና ሥልጣኔ በር የሌለው የጦርነት እውቀት ምን ይሠራልናል? የማያሻግር፣ የማይመራ፣ ትርፍ የሌለው፣ ከእኔነት ያልጎደለ፣ ብዙኃነት የራቀው የሐሰት ትርክት ምን ሊበጀን? ያላስተሳሰረ፣ አብሮነትን ያጎደለ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሸረሸረ፣ ለሞትና ለጉስቁልና የበረታ እውቀት ምን ትርፍ አለው? ለሥራ የማያተጋ፣ ለለውጥና ለብልጽግና መንገድ የሌለው፣ ለፉክክር ፖለቲካ መንገድ የሚጠርግ፣ እውነት የሌለው እውቀት ምኑ ነው ክብር? የማያጠጋጋ፣ የማያስተቃቅፍ፣ አፈራርቶና አሰጋግቶ እዛና እዚህ የሚያቆም፣ አብሮነትን የሻረ፣ እኛነትን የበረዘ ትርክት ምን ሊጠቅም?

እውቀትን በእውነት እና ለእውነት የሚያስተጋባ ማኅበራዊ ንቃት አይጥ የምትይዘዋን ወርቃማዋን ድመት የምንከተልበት የለውጥ ሕጋችን ነው:: ያለንበትን ካልተጸየፍን ለምንፈልገው መንገድ አናገኝም:: ጨብጠን ይዘናቸው ዋጋ ያላወጡልንን ትተን ለአዲስ ተሐድሶ መንጠራራት ይገባል:: ለሀገር ለውጥ፣ ለትውልዱ ስኬት የሆኑ በትብብር መንፈስ የደለቡ፣ ሰብዓዊነት የሚንጸባረቅባቸው የእውቀት መንፈሶች ለአዲስ ንቃት የሚያበቁን ተስፋዎቻችን ናቸው::

አንድ ቀፎ በውስጡ ማር ካልያዘ ጥቅሙ ምንድነው? በዚህ ዓለም ላይ እውነት የሚለው ቃል ለአንድ ብርቱና ሁነኛ የሚሰጥ ስያሜ እንደሆነ የጋራ መረዳት አለን:: እውቀትን በእውነት ለእውነት መርሕ ውስጥ መጠቀም የጋራ ትርክትን ከመፍጠር አኳያ የማይተካ ሚና ያለው እንደሆነም ለብዙዎቻችን አሻሚ ጉዳይ አይደለም:: ያልበሰሉ እና ቢበስሉ እንኳን ጣዕም የሌላቸው አንድን አካባቢና አንድን ሁነት ብቻ ታከው የተመሠረቱ እውነቶች ከእውነት ይልቅ ቀልድና ቧልት ያመዘነባቸው ናቸው:: እነኚህ ሂደቶች አይጥ የማትይዘዋን ድመት እየካደምን እንድንኖር አይጥ የማትይዘዋን ደግሞ እንዳንደርስባት የሚያደርጉ ናቸው::

አንድ ነገር የቱንም ያክል ግዝፈት ቢኖረውና በብዙኃን ዘንድ ተቀባይነት ቢኖረው በውስጡ አሻጋሪና ሁሉን ማዕከል ያደረገ እውነት ከሌለው ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል:: የእኛን ሀገር ጥንታዊና አሁናዊ የፖለቲካ ሽግግርና ምሕዳር ብናየው አብዛኛው ከእውነት ባፈነገጠና መሠረት በሌለው መነሻ የመጣ እንደሆነ እንደርስበታለን:: የሚያጨቃጭቁን እና የሚያነታርኩን ብሎም ጦር የሚያማዝዙን ጉዳዮች እንኳን ከየት እንደተነሱ፣ ማን መቼና ለምን ዓላማ እንደጀመራቸው የማናውቃቸው ናቸው:: ግን ተቀያይመን ተኮራርፈንባቸዋል:: ግን ለእድገትና ለለውጥ እንቅፋቶቻችን ሆነዋል::

እውቁ ደራሲ አንቶን ቼኮሆቭ ‹እውቀት በእውነት እስካልተገለጠ ድረስ ዋጋ ቢስ ነው› ይለናል:: ሐቅ ነው እውቀት በእውነት ካልታጀበ አጥፊና አውዳሚ ትውልድን ነው የሚፈጥረው:: ማኅበረሰባችን የመጣበት መንገድ፣ ትውልዱ የተቀረጸበት ሁኔታ ያንን እውነታ የሚያንጸባርቅ ነው:: ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ‹ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቷል:: ሲል እውቀት ከማኅበረሰብ ጋር ያለውን ግዝፈት ይነግረናል::

እውቀት ኃይል ነው፣ ለየትኛውም ችግር ፍቱን መድኃኒት ሆኖ ከፊት የሚመጣ ነው:: ኃያልነቱ እና መፍትሔነቱ የሚያረጋግጠው ግን በእውነት ለእውነት ጀምሮ ሲያበቃ ነው:: አይጥ የማትይዘውን ድመት ገፍተን አይጥ የምትይዘውን ድመት ለመካደም ከሐሰት እውቀት መላቀቅ የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው:: እውቀትን በእውነት፣ ለእውነት መጠቀም ሀገር ማዳኛ፣ ትውልድ መታደጊያ ዋስትናችን ነው:: ቸር ሰንብቱ::

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You