የኪነ-ጥበብና ሥነ-ጥበብ ፈጠራን በመጠቀም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ማጎልበት ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፡- የኪነ-ጥበብና ሥነ-ጥበብ ፈጠራ ሥራን በመጠቀም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ማጎልበት ያስፈልጋል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ገለጹ፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር “የባህል ጥበባት ለማህበረሰብ ትስስርና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የኪነጥበብና ሥነጥበብ ፈጠራ ውድድር ፌስቲቫል አካሂዷል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የጥበብ ሥራን በማበረታታት፣ ጥበብና ጥበበኞችን በማገናኘት የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ማጎልበትና ሀገረ መንግሥትን መገንባት ያስፈልጋል።

ውድድሩ የማህበረሰብን ግንኙነትና ትስስር ከማጠናከር ባሻገር ፈጠራን ለማበረታታት፣ ተወዳዳሪዎች የበለጠ እንዲሠሩና አዳዲስ ከህሎቶችን እንዲያዳብሩ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የጥበብ ሥራዎች በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች የተወጠረ አዕምሮን አለዝቦ ሥነልቦናዊ ህክምናን በመስጠት፣ ለጠነከረና ለጎለበተ ሀገራዊ ስሜት፣ ለሀገራዊ አንድነትና የወል ትርክትን ለማጽናት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡

ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረ ብዝሃ ባህላዊ የኪነ-ጥበብና የሥነ-ጥበብ ባለቤት መሆኗን ገልጸው፤ በውድድሩ የጥበቡ መሠረት የሆነውን የጥበብ ማህበረሰብ ለማሳተፍና ተደራሽ ለማድረግ ተከታታይነት ያለው ሥራ በአሳታፊነት መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

በቀጣይ ሀገር አቀፍ የኪነ ጥበብና ሥነጥበብ ውድድሮችን በክልሎች፣ በዞኖች፣ በትምህርት ቤቶችና በክበባት አደረጃጀቶች እንደሚሠራ አመላክተዋል።

ጥበብን በሁሉም ዘንድ አልምቶ ሀገራዊ ጥቅሞችን ለማግኘት እንዲያስችል በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በወጥነት እንደሚሠራ አቶ ቀጀላ ገልጸዋል።

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነጥበብ፣ ሥነጥበብና ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማኻዲ በበኩላቸው፤ ባህልን ከትውልድ ወደ ትውልድ በጥበብ ማስተላለፍ እንደሚገባ ገልጸው ለዚህም ምቹ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህ የኪነ-ጥበብ ፈጠራ ወድድር እና ትዕይንት መድረክ በሀገር አቀፍ ደረጃ መዘጋጀቱ ዘርፉን ለማነቃቃት፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳውን አጉልቶ ለማውጣት እንደሚረዳ ወይዘሮ ነፊሳ ጠቁመዋል።

ብዝሃ ባህሎችን በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ በስፋት እንዲንፀባረቁ በማድረግ የሀገር ገፅታን መገንባት የፌስቲቫሉ ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል።

በፌስቲቫሉ የሙዚቃ፣ የስዕልና የባህል አልባሳት ፋሽን ሾውና የዕደ ጥበብ ውጤቶች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን ለሶስት ቀናት እንደሚቆይ ተመላክቷል።

በፌስቲቫሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳን ጨምሮ የክልል ባህልና ስፖርት ቢሮ ሃላፊዎች፣ አባት አርበኞች፣ የሃይማኖት አባቶች አባ ገዳዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን  ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You