ወደ ውጭ በሚላኩ የግብርና ምርቶች ላይ ዘመናዊ የቁጥጥርና ደህንነት ሥርዓት እየተገነባ ነው

አዲስ አበባ፡- ወደ ውጭ በሚላኩ የግብርና ምርቶች ላይ ዘመናዊ የቁጥጥርና ደህንነት ሥርዓት እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራችና ላኪዎች ማህበር እና በኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የተዘጋጀው የግብርና ውጤቶች ቁጥጥርና ደህንነት ላይ ያተኮረ ጉባኤ ትናንት ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ ባለስልጣኑ ወደ ውጪ የሚላኩና ከውጭ ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ የግብርና ምርቶችን የደህንነትና ቁጥጥር አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

እስካሁን የነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ በአብዛኛው ወረቀት ላይ የተመሰረተ እንደሆነና አሁን ላይ አገልግሎቱን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለመቀየር ከአውሮፓ ኅብረትና ከትሬድ ማርክ አፍሪካ ጋር እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከ80 በመቶ በላይ ወደ ውጭ የምትልከው በአብዛኛው ግብርና ምርት ነው ያሉት አምባሳደር ዲሪባ፣ አብዛኛው የውጭ ምንዛሪ ገቢም ከግብርና ምርቶች እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

እንደ አምባሳደር ድሪባ ገለጻ፣ የግብርና ምርቶች ጤናቸውንና ጥራታቸውን የሚቆጣጠረው ባለስልጣኑ ነው፡፡ ምርቶቹ ደህንነታቸውና ጥራታቸው የተጠበቀ እንዲሁም የተቀባይ ሀገራትን መስፈርት ያሟሉ መሆናቸውም ይረጋገጣል።

ይህንን ለማሳካት በወረቀት ሰርቲፊኬት የሚሰጠው ማረጋገጫ በብዙ ሀገራት ተቀባይነት እያጣ ስለመጣና አገልግሎት ላይም ጫና በመፍጠሩ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሮኒክስ የመቀየር ሥራ እየተሠራ እንዳለ አስታውቀዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአየር ለውጥ ምክንያት እጽዋትን የሚያጠፉ በርካታ ተባዮች፣ በሽታዎችና ባክቴሪያዎች፣ እየተፈጠሩ እንዳሉ፤ በዚህም ምክንያት የአውሮፓ ኅብረትና ሌሎችም የኢትዮጵያን ምርት የሚቀበሉ ሀገራት የቁጥጥር ሥርዓታቸውን በየጊዜው እየቀየሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

ከቁጥጥር ሥርዓቱ መጥበቅ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያም እነዚህ አካላት ከሚያወጡት የቁጥጥር ሥርዓት ጋር የሚመጣጠን ሥርዓት መገንባት ካልቻለች ምርቶች ላይ አሉታዊ ጫና ስለሚፈጥር የዘመነ የምርት የቁጥጥርና ደህንነት ሥርዓት እየተገነባ እንዳለ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዳለ ሀብታሙ በበኩላቸው፤ ጠንካራ ሀገራዊ የዕፅዋት ንፅህና አጠባበቅ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። የሥርዓቱን ስኬትና ቀጣይነት ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

አቶ ወንዳለ አክለውም፤ የዕፅዋት ሀብቶችን በመጠበቅ ረገድ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር፤ በዚህም የገበያ ተደራሽነትን ለመጠበቅና ለማስፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወጡትን መስፈርቶች ማክበር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አበባ ተክልና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ፤ ዓለም አቀፍ የእጽዋት ጤና ደረጃዎችን ለማስጠበቅ ከተቆጣጣሪ አካላት፣ ከግሉ ሴክተርና ከተለያዩ አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You