ቦይንግ ኩባንያ 25 ቢሊዮን ዶላር እንዲቀጣ የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦች ጠየቁ

የቦይንግ ኩባንያ 25 ቢሊዮን ዶላር እንዲቀጣ የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦች መጠየቃቸው ተገለጸ።

በሁለት የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ሰለባዎች ቤተሰቦች በአሜሪካ ታሪክ ከባድ ለተባለው ኮርፖሬት ክራይም” 24 ነጥብ 8 ቢሊዮን ቅጣት እንዲጣል እና ክስ እንዲመሰረት መጠየቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ቦይንግ በፈጸመው ወንጀል የደረሰው የሞት መጠን ከባድ በመሆኑ መጠኑ “ምክንያታዊ እና ተገቢ ነው” ብሏል የቤተሰቦቹ ጠበቃ ፓውል ካሴል።

ቢቢሲ እንደገለጸው፤ ካሴል ባቀረበው ባለ 32 ገጽ ደብዳቤ በ2018 እና በ2019 በደረሱ ሁለት የመከስከስ አደጋዎች 346 ሰዎች በሞቱበት ወቅት ኩባንያውን ሲመሩ የነበሩ ሰዎች መከሰስ አለባቸው ብሏል።

ይህ ደብዳቤ የቦይንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴቭ ካልሆን ባለፈው ማክሰኞ እለት በኮንግረስ ፊት ቀርበው ይቅርታ መጠየቃቸውን ጠቅሷል።

“ላደረስነው ጉዳት ይቅርታ እጠይቃለሁ” ሲሉ የሰለባዎቹ ቤተሰቦች በጩኸት ንግግራቸውን አቋርጠዋቸዋል ተብሏል።

ሁለቱ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ የደረሰባቸው በተለያየ ጊዜ ቢሆንም የአደጋው መንሰኤ ግን ተመሳሳይ ነበር።

በፈረንጆቹ ጥር 2018 ንብረትነቱ የላዮን ኤየር ፍላይት የሆነ አውሮፕላን ከኢንዶኔዥያ ዋና ከተማ ጃከርታ ከተነሳ ከ13 ደቂቃ በኋላ ባጋጠመው የመከስከስ አደጋ ተሳፍረው የነበሩ 189 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

በመጋቢት 2019 ደግሞ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየርመንገድ የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከተነሳ ከስድስት ደቂቃ በኋላ ሲከሰከስ አሳፍሯቸው የነበሩት 157 ሰዎች ሞተዋል። በሁለቱም አደጋዎች በሕይወት የተረፈ ሰው የለም።

ሁለቱም አደጋዎች በበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ብልሽት ምክንያት ነበር የተከሰቱት።

ኮልሆን ኮንግረስ በቀረቡበት ወቅት ኩባንያው ስህተት መሥራቱን አምነው እና ከስተቱ ተምሯል ብለዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቦይንግን ምስጢር በማያወጡ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መውሰዱን ገልጾ የሠራተኞቹን ስጋት ግን እንደሚያዳምጥ ተናግረዋል።

የአሜሪካ የፍትህ ክፍል ወይም ጀስቲስ ዲፓርትመንት ከሁለት የመከስከስ አደጋዎች ጋር በተያያዘ በቦይንግ ላይ በፈረንጆች 2021 ጀምሮ የነበረውን የወንጀል ክስ እንደገና ለመጀመር እያጤነው ነው።

ክስ የቆመው ኩባንያው የአየር ተቆጣጣሪዎችን ማሳሳቱን ካመነ እና ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች የሚቆጣጠር አዲስ ኮምፒሊያንስ ሥርዓት ለመዘርጋት ቃል መግባቱን ተከትሎ ነበር።

ባለፈው ወር በረራ ላይ የነበረ 737 ማክስ አውሮፕላን በሩ ከተገነጠለ በኋላ አቃቤ ሕግ ቦይንግ ስምምነቱን ጥሷል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።

ጀስቲስ ዲፓርትመንት እስከ ፈረንጆቹ ሐምሌ ሰባት ድረስ ክሱ እንደገና ይጀመር ወይስ አይጀመር በሚለው ጉዳይ ውሳኔ ይሰጣል።

ካሴል ደንበኞቻቸው ወይም የአደጋ ሰለባ ቤተሰቦች በቦይንግ ላይ ወደፊት ከሚጣለው ቅጣት ላይ የተወሰነው የኩባንያውን ደህንነት እና የጥንቃቄ አሠራሮች የሚቆጣጠር ነጻ ተቆጣጣሪ ለማቋቋም እንዲውል ሃሳብ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You