ሩሲያና ሰሜን ኮሪያ አንዳቸው ለሌላኛቸው ሁሉንም አይነት ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደረሱ

ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ ከሁለቱ በአንደኛቸው ላይ ወታደራዊ ጥቃት በሚቃጣበት ወቅት ወታደራዊ ድጋፍ ለማቅረብ የሀገራቱ መሪዎች ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ይህ ስምምነት የተደረሰው የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከ24 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰሜን ኮሪያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው።

ስምምነቱ ሁለቱ የቀዝቃዛው ጦርነት አጋሮች በፈረንጆች 1961 ተፈራርመውት የነበረው እና ሶቭየት ህብረት ከደቡብ ኮሪያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስትጀምር ተሰርዞ የነበረውን ወታደራዊ ትብብር የሚያድስ ነው ተብሏል።

“ኮምፕርሄንሲቭ ስትራቴጂክ ፓርትነርሺፕ” ለማድረግ በሩሲያው ፕሬዚዳንት ፑቲን እና በሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን መካከል ከትናንት በስቲያ የተደረሰው ስምምነት ሞስኮ በዓመታት ውስጥ በእስያ አህጉር ያደረገችው ትልቅ እርምጃ ነው።

“ከሁለቱ በአንደኛቸው ላይ ጦርነት የሚታወጅ ከሆነ ወይም በጦርነት ውስጥ ካለ፣ በተመድ ቻርተር አንቀጽ 54 መሰረት ሌላኛው ሁሉንም አይነት ወታደራዊ እና ሌሎች ድጋፎችን ወዲያውኑ ያቀርባል” ይላል የስምምነቱ አንቀጽ አራት።

የተመድ ቻርተር አንቀጽ 51 አባል ሀገራት ወረራ ሲፈጸምባቸው በተናጠል ወይም በቡድን ራሳቸውን መከላከል እንደሚችሉ ያስቀምጣል።

ስምምነቱ ሩሲያ በዚህ ምዕተ ዓመት የኑክሌር ጦር መሳሪያ የሞከረችውን ሰሜን ኮሪያን ምን ያህል ልትረዳት ትችላለች የሚል ምዕራባውያንን ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል።

ኪም የበላይነት እና ኢምፔሪያሊዝምን ለማስቀጠል የሚጥረውን የምዕራባውያን ፖሊሲ እንዋጋለን የሚለውን የፑቲን መግለጫ አስተጋብተዋል።

ሁለቱ ሀገራት አንዳቸው የሌላኛቸውን ጥቅም የሚጻረር ስምምነት ከሦስተኛ ሀገር ጋር እንዳይፈራረሙ እና ግዛታቸውንም ደህንነት እና ሉአላዊነት ለሚጎዳ ሌላ ሀገር ላለማስጠቀምም ተስማምተዋል ተብሏል።

በተጨማሪም የቀጣናውን ብሎም ዓለምአቀፍ ሰላምን ለማስፈን ወታደራዊ አቅማቸውን ለማጠናከር የሚያስችሉ ርምጃዎችን ይወስዳሉ።

ፕሬዚዳንት ፑቲን፣ ሩሲያ በዩክሬን ለምታካሂደው ወታደራዊ ዘመቻ ሙሉ ድጋፍ የሰጠችውን ሰሜን ኮሪያን አመስግነዋል።

ጃፓን ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላት ትብብር እንደሚያሰጋት ገልጻለች።

ከሰሜን ኮሪያ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚ ዋና ተጠቃሚ የሆነችው ቻይና በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ጉዳይ ምንም ማለት አልፈለገችም።

ዋሽንግተን እና ሴኡል ግን እየጠነከረ የመጣው የሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ግንኙነት ስጋት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።

ምዕራባውያን ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ በዩክሬን ለምታደርገው ጦርነት ጥቅም ላይ የሚውል የጦር መሳሪያ ታቀርባለች ሲሉ ይከሷታል። ሰሜን ኮሪያ ግን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ነው ስትል አስተባብላለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You