ሙያ ተኮር የክህሎት ማበልጸጊያ ተቋማት- ለሀገር እድገት

አንድ ሀገር እውቀትን ከሙያና ከሥነ-ምግባር ጋር አቻችላ ወደፊት ለመጓዝ ሙያ ተኮር የክህሎት ማበልጸጊያ ተቋማት በብዛትና በጥራት እንደሚያስፈልጓት እሙን ነው። የነዚህ ተቋማት ሚና የእውቀት ትስስርና ሽግግርን በመፍጠር ቴክኖሎጂንና ፈጠራን በማበረታታት ለውጥና እድገት ከማምጣት አንጻር የማይተካ ሚና ይኖራቸዋል። ሀገራችን ኢትዮጵያም የሙያ ተቋማትን መሠረት ባደረገ መልኩ ለጀመረችው የለውጥና የተሐድሶ እንቅስቃሴ እንዲህ ያሉ ተቋማት እጅግ አስፈላጊ ናቸው።

ሙያ ተኮር የክህሎት ማበልጸጊያ ተቋማት ትውልድን በመቅረጽ ረገድ ላቅ ያለ ሚና ያላቸው ሲሆን በተለይም እውቀትን ወደተግባር በመለወጥ እና ችግር ፈቺ የሆኑ ፈጠራዎችን በማመንጨት በኩል የማይተካ ጠቀሜታ አላቸው።

ሀሳብ ወደተግባር ካልተለወጠ ብቻውን ትርጉም ላይኖረው ይችላል። አንድ ሀገር የቱንም ያህል የተማረ ዜጋ ቢኖራት እንደቴክኒክና ሙያ ያሉ የክህሎት ማበልጸጊያ ተቋማት በአይነትና በጥራት ከሌሏት የእውቀት መኖር ብቻውን ትርጉም አይሰጥም።

የእውቀት ሽግግር ተቋማት በእውቀት ዳብረው፣ በሙያ በልጽገው፣ አዕምሮን በማንቃት ትውልዱን ከጠባቂነት ወደሥራ ፈጣሪነት፣ ከተቀጣሪነት ወደቀጣሪነት፣ ከተቀባይነት ወደሰጪነት የሚያሻግሩ የዕድልና ድል መፍለቂያዎች ናቸው። እነኚህ የዕድልና ድል ማዕከላት ከግለሰብ እስከ ሀገር በሚደርስ ከዛም አልፎ ዓለም አቀፋዊነትን በከለለ መልኩ ስኬትን የሚያቀዳጁ የተሐድሶ ማዕከላት ናቸው።

የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ብንመለከት መነሻቸው ቴክኒክና ሙያ እንደሆነ እንረዳለን። ኃያላን ሀገራት በቴክኖሎጂና በዘመናዊነት ነቅተውና በቅተው ጎልተውም የሚታዩት እውቀትን ወደተግባር በቀየረ የእውቀት ሽግግር ነው። ሙያ ተኮር የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል በእውቀት መር በሆነ እሳቤ ቴክኖሎጂ የሚባለውን የሥልጣኔ መሠረት ተንተርሶ እየተንቀሳቀሰ ያለ ዓለም አቀፍ ጽንሰ ሀሳብ ነው። በእንዲህ ያለው እሳቤ ታቅፈንና ዳብረን በፈጠራና በሙያ በክህሎትም አዲስ አስተሳሰብን ካልቀደድን በመጣንበት ነባር አቅጣጫ ተጉዘን ፍሬ ማፍራት የማይታሰብ ነው።

በፈጠራና ቴክኖሎጂው ዘርፍ እንደሀገር ከሚነሱብን ችግሮች መሐል አንዱ እውቀትን ወደመሬት የሚያወርድ የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል አለመኖሩ ነው። ቢኖር እንኳን ትውልዱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም አስተሳሰብ ተላቆ ፊቱን ወደቴክኒክና ሙያ እንዲሁም ወደ ተግባረ-ዕድ አለማዞሩ ነው። እነኚህ ማኅበራዊ ልምምዶች የተሐድሶ አቅጣጫን ሳይሰጡን በአድሮ ቃሪያ ፈሊጥ ለአንድ አይነት ክዋኔ ዳርገውን ሰንብተዋል። ለለውጥና ለእድገት በምናደርገው ጉዞ ላይ እውቀትና ሙያ በአንድ ቦታ ለፈጠራ የሚውሉበት የልህቀት ማዕከላት ያስፈልጉናል።

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከዩኒቨርስቲና ከከፍተኛ የትምህርት ማዕከላት በተሻለ መልኩ የልህቀት ማዕከላት ናቸው። እውቀትን ከሥነ-ምግባርና ከተፅዕኖ ፈጣሪነት ጋር አጋምደው ወደማኅበረሰብ የሚያንጸባርቁ የብርሃን ቀንዲሎች ናቸው። የብዙዎቻችን እውቀት ወደሀገርና ሕዝብ ሳይንጸባረቅ በጊዜ ሂደት የአገልግሎት ዘመኑ ያበቃ ነው። ልክ የጋን ውስጥ መብራት እንደሚባለው ርቀን ሳናበራ በእውቀትና በሙያችን ሌሎችን ሳናገለግል አንድ ቦታ በርተን የከሰምን ነን። እንዲህ አይነቱ ቆሞ ቀርነት ሙያን ከክህሎትና ከተራማጅ አስተሳሰብ ጋር ያለማቆራኘት፣ በሙያ ማበልጸጊያ ማዕከላት ሠልጥኖ ያለመውጣት መንስዔ የፈጠረው ነው።

ተምረን ወደመሬት ወርደን ሳንሠራና በክህሎት ዳብረን አዲስ ነገር ለሕዝባችን ሳንሰጥ ምንም ያህል ብንማር ዋጋ አናወጣም። እውቀት ዋጋ ያለው የሚሆነው በተግባር ሲገለጥ፣ ሀገርና ሕዝብን ስናገለግልበት ነው። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ትውልዱ ራሱን ከዩኒቨርሲቲ ጋር አስተሳስሮ የሙያ ማዕከላትን ችላ ያለበት ሁኔታ ነበር። ስንማር ዩኒቨርሲቲን እያሰብን፣ ተመርቀን ከወጣን በኋላም ሥራን ፈጥሮ ከመሥራት ይልቅ መንግሥት ሥራ እንዲያስቀጥረን የምንጠብቅ ነን። በዚህ ሥነልቦና ውስጥ በቴክኖሎጂና በችግር ፈቺ ፈጠራ ራሷን የቻለች ሀገር መፍጠር አልቻልንም።

በአሁኑ ሰዓት መንግሥት በጀመረው የቴክኒክና ሙያ የክህሎት ማበልጸጊያ ንቅናቄ አዲስ አሠራርን እየተለማመድን እንገኛለን። ይሄ ልምምድ ትውልዱን ከክህሎትና ከሥራ ፈጣሪነት ጋር የሚያስተዋውቅ ወደ ዩኒቨርስቲ ብቻ ይመለከት የነበረውን ማኅበረሰብ ወደሙያ ማዕከላት እንዲያይና ሠልጥኖ እንዲወጣ፣ የጋን ስር መብራት የሆነውን ብዙኃነ እውቀት ሰፊና ግዙፍ በማድረግ ወደሌሎች እንዲንጸባረቅ የሚረዳ እንቅስቃሴ ነው።

እንቅስቃሴው በመርሕና በመሪ ቃል ታጅቦ፣ በውይይትና በከፍተኛ አትኩሮት እየተመራ ያለ ነው። በጀት ተመድቦለት፣ ፖሊሲዎች ረቀውለት፣ ለክህሎት ምቹ በሆነ አካባቢ፣ በተሟላ የሙያ ማሠልጠኛ ማዕከል አሳቢ የሆነ አዲስ ትውልድ ለመፍጠር ብርቱ ትጋት እየተደረገ ይገኛል። የመጣንበትን የመማር ማስተማር አቅጣጫ የሚቀይር፣ ዲግሪ ከመያዝ በላይ እውቀትን ለሕዝብ እንዲጠቅም በክህሎት የማረቅ እንቅስቃሴ ከተልዕኮው አንዱን ነው።

ለአንድ ሀገር የለውጥ ዋስትና ከሆኑ የትውልድ ንቃት ውስጥ የመጀመሪያው እውቀትን ወደተግባር መቀየር ነው። በእኛ ሀገር እንዲህ አይነቱ ነገር እምብዛም አልነበረም። ለምን ካልን ታሪኮቻችን ከዩኒቨርስቲ ጋር ብቻ የተቆራኙ ስለነበር ነው። የለውጥ ዋስትና የሆኑ የትውልድ ንቃት በክህሎትና በቴክኒክና ሙያ ተቋም በኩል የሚገለጡ ናቸው። አዕምሮ የተረዳውን በተግባር የሚተረጉምበት፣ ለፈጠራና ለአዲስ እይታ የምንተጋበት የልህቀት ስፍራ ነው።

የክህሎት ማበልጸጊያ ተቋማት በትውልዱ ላይ የተለያዩ መገለጫዎች አሏቸው። ከነዚህ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ከፈላጊነት ወደሰጪነት፣ ከጠባቂነት ወደሥራ ፈጣሪነት፣ ከተገልጋይነት ወደአገልጋይነት የሚደረግ የለውጥና የተሐድሶ ጉዞ ነው። እነኚህ ገጸበረከቶች ከግለሰብ ወደቤተሰብ፣ ከቤተሰብ ወደማኅበረሰብ ላቅ ሲልም በዓለም አቀፍ ደረጃ የምንጠራበትን ዕድል የሚፈጥሩልን አጋጣሚዎቻችን ናቸው። እጆቻችን ለሥራ፣ አዕምሯችን ለለውጥ ካልተጋ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ነን። እውቀት ኃይል ነው ስንል ችግር ፈቺና አገልጋይ ሲሆን ነው።

እንደሚታወቀው ሀገራችን በሁሉም ዘርፍ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ በጠባቂነት ውስጥ ናት። ይሄ ትውልድ በእውቀት ዳብሮና በክህሎት በልፅጎ ከጠባቂነት ካላወጣት ሊታደጋት የሚችል ሌላ ኃይል የለም። ሁላችንም ኃላፊነት አለብን። መንግሥት ሁኔታዎችን በማስተካከልና ምቹ ከባቢን በመፍጠር እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለሀገርና ሕዝብ ዋጋ ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል። ቀሪው ማኅበረሰብ ለሙያ ተቋማት በጎ አመለካከትን በመፍጠር፣ ትውልዱ ለክህሎትና ለእጅ ሙያዎች ልዩ ፍቅር በመስጠት አዲስ ለውጥን ማምጣት ይቻላል።

ማር በማይሰጥ ቀፎ ብዙ ዓመታትን ደክመናል። ቀፎን መቀየር ሳይሆን አበቦች ወዳሉበት ሥፍራ መስቀል ለውጥ ያመጣል። ይሄ ማለት ትውልዱ አበባ በሌለበት ስፍራ ነበር እየዳከረ ያለው ማለት ነው። ለዛም ነው ድህነትን ማሸነፍ አቅቶን በተረጂነትና በጠባቂነት ስንማቅቅ የቆየነው። የክህሎት ተቋማት ደግሞ ራሳችንን የምንለውጥበት፣ ሕዝባችንን የምናገለግልበትን እድል የሚፈጥሩልን የብስለትና የብልህነት ማዕከላት ናቸው።

አሁን ስለምናወራው ጉዳይ የሚያትት በመረጃ ላይ የተደገፈ በፈረንጆቹ 2022 ላይ የወጣ አንድ ጥናት አንብቤ ነበር። የጥናቱ መነሻ ሀሳብ ኢትዮጵያውያን ለምን ድሀ ሆኑ? የሚል አንድምታ ያለው በጥያቄ የሚጀምር ሀሳብ ነው። እዛ ጥናት ላይ ለድህነታችን ዐበይት ምክንያት ሆነው ከተነሱት ውስጥ በቀዳሚነት የተጠቀሰው የሥራ ፈጠራ ክህሎት ውስንነት ነው። ሌሎቹን እንተዋቸውና በዚህ ጉዳይ ላይ ብንነጋገር እንኳን ብዙ ሀሳቦችን መለዋወጥ እንችላለን። ጥናቱ እንደምክንያት ያነሳው የክህሎት መበልጸጊያ ተቋማት አለመኖራቸው፤ ቢኖሩም በተገቢው መንገድ አለመጠቀማችን፣ እንደቴክኒክና ዕደ-ጥበብ ያሉ የሙያ ዘርፎች ቦታ ማጣታቸው፣ እውቀትን ወደተግባር አውርዶ አለመጠቀም የመሳሰሉትን ጠቅሷል።

እንደአጋጣሚ ሆኖ የጥናቱ ውጤት አሁን እኛ እንደችግር ካነሳነው እውነታ ጋር የተመሳሰለ ሆኗል። መንግሥትም ቀድሞ በመንቃት እስከ ተወካዮች ምክር ቤት በደረሰ ርቀት በአሁኑ ሰዓት ልዩ አትኩሮት በመስጠት እንቅስቃሴ እያደረገበት ይገኛል። ለውጥ ከመንግሥት ወደሕዝብ፣ ከሕዝብ ወደመንግሥት ነው። የሙያ ማዕከላት ግን ከማንም ወደማንም አይደሉም። ዓለም ራሷን የቀየረችበት፣ ኃያላኑ ከድህነት የወጡበት ስለሆነ ያለማንም አስገዳጅነት ልንጠቀምበት የሚገባ ነገር ነው።

የጀርመንና የቻይና ሥልጣኔ መነሻውን ያደረገው ቴክኒክና ሙያን ነው። የነዚህ ሀገር የቴክኖሎጂና የኃያልነት ሚዛን በክህሎትና በሥራ ፈጣሪነት ላይ የተመሠረተ ነው። የዛሬ ስልሳ ዓመት ገደማ ቻይና ከወደቀችበት ስትነሳ እንደምርኩዝ የተደገፈችው የክህሎት መርሆችን ነው። ለዚህም ትውልዱ ሙያ ማዕከላት ውስጥ ገብቶ እውቀት እንዲቀስም፣ ሙያ እንዲለምድ፣ ከችግር ፈጣሪነት ወደችግር ፈቺነት እንዲሸጋገር ንቅናቄ ጀመረች። ያ ንቅናቄ ፍሬ አፍርቶ ቻይናን በዓለም ላይ ካሉ በሁሉም ነገር ከተሳካላቸው ሀገራት አንዷ እንድትሆን አደረጋት።

የጀርመንም የለውጥና የተሐድሶ ተሞክሮ ከዚህ የሚነሳ ነው። እንደነበረ የሚቀጥል ምንም ነገር የለም። የዓለም መልክ ወደሥራ ፈጣሪነት ተቀይሯል። እኛም ከስንፍና ወደትጋት፣ ከስልቹነት ወደታታሪነት በመቀየር እንደጀርመንና ቻይና ታሪካችንን ማደስ ይኖርብናል። ሀገራችን የምትታማበት አንዱና ዋነኛው ጉዳይ እውቀትን ወደተጨባጭ እውነታ የሚቀይር የሙያ ተቋማት አለመኖራቸው ቢኖሩም ንድፈ ሀሳብን ወደተጨባጭ እውነታ በመቀየርና የዕደ-ጥበብ ባለሙያዎችን ማብቃት አለመቻል እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ የሆነ እውነት ነው። ከፊተኞቻችን ተምረን ራሳችንን ለለውጥ ማዘጋጀት የዚህ ትውልድ ተግባር መሆን አለበት።

ሰባና ሰማኒያ ከመቶው ወጣት በሚኖርባት ሀገር ላይ ሩቅ በማይወስድ መንገድ ላይ መፍገምገም አጉል ነው። ወጣቱ እጆቹን አፍታቶ ተዐምር እንዲሠራና አዕምሮውን ተጠቅሞ ለሀገር የሚበጅ ቁም ነገር እንዲያደርግ የክህሎት ማበልጸጊያ ተቋማት በእጅጉ ያስፈልጉናል። ጊዜያችንን ከኃይላችን ጋር አጣጥመን በክህሎት በልጽገን ሩቅ ለመሄድ ሙያ የምንቀስምባቸው የአእምሮ መበልጸጊያ ስፍራዎች ሊኖሩን ግድ ይላል።

ትኩስ ኃይል አለን። ለለውጥና ለእድገት የተሰናዳን ነን። እኚህ ፍላጎቶቻችን ሁነኛ ቦታ ካላገኙ ባክነው ነው የሚቀሩት። የሕዝብ ቁጥር ብቻውን አንድን ሀገር ከድህነት አይታደጋትም። በክህሎት ካልተገራ የወጣት መብዛት ብቻውን ለውጥ አያመጣም። ለውጥና እድገት ያለው ለአእምሮ ምቹ ስፍራን በማዘጋጀትና እውቀትን ወደተግባር በሚቀይር ተቋም በኩል ነው። እንደሀገር የጀመርንው እንቅስቃሴ ፍሬ አፍርቶ በሙያና በክህሎት የበሰለ ትውልድ እንደሚፈጠር እናምናለን።

ሩቅ የማይወስዱ መንገዶች ትርፋቸው ድካም ነው። አቅጣጫችንን ቀይረን ትርፍ ባለውና እሴት በሚጨምር የሙያ ዘርፍ ላይ በመሰማራት ራሳችንንና ሀገራችንን ነፃ ማውጣት እንችላለን። የመማር ማስተማሩ የስምሪት አቅጣጫ ወደ ዩኒቨርስቲ ብቻ ነበር። የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች ተማሪ አጥተው ተዘግቶባቸው ከርመዋል። አዋጪና ለዋጪ ባልሆነ የእውቀት ስም ተምረን ጥቅም ሳንሰጥ እንዲሁ የቀረን አለን።

አዲስ እይታ ያስፈልገናል። ጊዜን ከእውቀት ጋር፣ ሙያን ከክህሎት እና ከሥነምግባር እንዲሁም ከፈጣሪነት ጋር ያቆራኘ የመማር ማስተማር ሥርዓት የነበረውን በመሻር በትውልዱ ላይ ንቃትን የሚፈጥር ነው። ሀሳብ አመንጪነትን ከትጋትና ከታታሪነት ጋር አጣጥመው የሚሄዱ፣ ተምሮ ሥራ ለመፈለግ ሳይሆን ተምሮ ለማስተማር፣ ሠልጥኖ ለማሠልጠን፣ አውቆ ለማሳወቅና ሙያውን ለሌሎች ለማጋራት የበረታ የክህሎት ማዕከላት የዚህ ዘመን የትውልዱ ስጦታዎች እንዲሆኑ በመመኘት ላብቃ ቸር ሰንብቱ።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You