ባለፈው ወር ‹‹ኢትዮጵያ እንደምን ሠለጠነች?›› በሚል ርዕስ የመሠልጠን ሂደቶችን ጅማሮ ማጠናከር እንዳለብን አይተናል። ዛሬ ደግሞ እስኪ የሰለጠኑ ሀገራትን ተሞክሮ እንመልከት። ወዲህ ደግሞ ባለፉት ሳምንታት ሲንጋፖር እንዴት እንደሠለጠነች የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች በዓይናቸው ያስተዋሉትን፣ በጆሯቸው የሰሙትን የሲንጋፖርን ተሞክሮ ሲናገሩ ነበር።
ፈጣን ሥልጣኔ፣ ፈጣን ዕድገት፣ ያልተጠበቀ ለውጥ፣ ከከፍተኛ ድህነትና ኋላቀርነት ወደ የዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪነት በመለወጥ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ሀገራት አንዷ ጃፓን ናት። ለመሆኑ ጃፓን እንደምን ሠለጠነች?
ደራሲ ከበደ ሚካኤል ከ20 ዓመታት በፊት የጻፏት ‹‹ጃፓን እንደምን ሠለጠነች?›› የምትል 120 ገጽ አነስተኛ መጽሐፍ አለች። ከበደ ሚካኤል ያቺን መጽሐፍ የጻፏት ኢትዮጵያም መለወጥ እንዳለባት ተሞክሮ ለማሳየት ነበር፤ ችግሩ ግን በተቆርቋሪነት ወደ ለውጥ መንገድ አልተሄደም ነበር። ለማንኛውም ከመጽሐፉ እና ከሌሎች ሰነዶች ባገኘነው መረጃ የጃፓንን የቀድሞ ታሪክ በጥቂቱ እናስታውስ፡፡
ጃፓን በጣም ድሃ እና እጅግ ኋላቀር የሆነ ልማድ የነበራት ሀገር ነበረች። ለውጥ ለማምጣት ያደረገቻቸው ጥረቶች በኢትዮጵያ ታሪክ ሆነዋል ሲባል ያልተሰሙ ናቸው። አንዱን ብቻ ልጥቀስ። ግራ ግብት ቢላት፤ መላ መስሏት፣ የሕዝብን ቁጥር በመቀነስ ችግሩ የሚቀረፍ መስሏት ማንኛውም ሰው ከሁለት ልጆች በላይ እንዳይወልድ ገደብ አደረገች። ይህን ክልከላ ተላልፋ ሦስተኛ ልጅ የወለደች እናት አንዱን መርጣ እንዲገደል ትሰጣለች። አስቡት! አንዲት እናት ከሦስት ልጆቿ ‹‹ይሄኛው ይገደል›› ብላ ስትሰጥ! ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ በየትኛውም ዘመን ያልተደረገ ነው፤ ማድረግ ቀርቶ ያልታሰበ ነው። ዛሬ የዓለም ልዕለ ኃያል የሚባሉት እንደ ጃፓን ያሉ ሀገራት ግን እንዲህ አይነት ኋላቀርና ዘግናኝ ልማድ የነበራቸው ናቸው።
ታዲያ የሥልጣኔ አስጀማሪ፣ የሃይማኖትና የሞራል ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ለምን ይህን ያህል ጊዜ ድሃ ሆነች? ለምን ለዓይን ማራኪ የሆኑ ነገሮች የሏትም? ብለን ከጠየቅን ቆራጥ መሪ አልነበሯትም ማለት ነው። እነ ጃፓን አሁን የደረሱበት ላይ የደረሱት በአንድ ቆራጥ ንጉሥ እንደሆነ ታሪካቸው ያሳያል። ይህ ሰው ሙትሱሂቶ (ሜይጂ) ይባላል። ሙትሱሂቶ በጃፓን መሠልጠን ውስጥ፣ በጃፓን ማደግ ውስጥ፣ ለጃፓን እዚህ መድረስ፣ በአጠቃላይ ለዛሬዋ ጃፓን መነሻ ነጥብ ነው ብለው ያምናሉ።
በነገራችን ላይ የሙትሱሂቶን ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ስናመጣው ሙትሱሂቶ ሥልጣን የያዘው በ1860 ዓ.ም ልክ የኢትዮጵያው ንጉሥ አጼ ቴዎድሮስ የሞቱበት ዓመት ማለት ነው። አጼ ቴዎድሮስ ከጃፓኑ ንጉሥ በፊት የአውሮፓን ሥልጣኔ ለማምጣት ጥረት ያደርጉ እንደነበር የታሪክ ጸሐፊዎች ጽፈዋል፤ ተናግረዋል። ኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ መንደር ለማድረግ አውሮፓውያንን ለመጠቀም ጥረት ያደርጉ ነበር። የእንግሊዝ ባለሙያዎችን ‹‹ሥሩልን›› እያሉ ይጠይቁ ነበር። ሴባስቶፖልን ያስጀመሩትም ለዚሁ ነበር።
አጼ ቴዎድሮስ ልክ እንደ ጃፓን ሃይማኖት ላይ ገደብ ጥለው ነበር። በቤተክርስቲያን ስም ብዙ ቦታ መባከን የለበትም፤ በቄስ ስም ይህ ሁሉ የሰው ኃይል ሥራ መፍታት የለበትም የሚል ዘመቻ ነበራቸው። አጼ ቴዎድሮስ ይህን ማድረጋቸው ‹‹ትክክል ነው! ትክክል አይደለም!›› አይደለም ጉዳዩ! ግን በሀገራቸው ለውጥ ለማምጣት ጥረት አድርገው ነበር ። የአውሮፓን ሥልጣኔ ለመኮረጅ ሀገራቸውን ልክ እንደ አውሮፓ ለማድረግ ጥረት አድርገው ነበር ነው። በዘመኑ ይጠቅማል ያሉትን ጥረት አድርገው ነበር፤ ችግሩ ግን የአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ ጎልቶ የሚነገረው ሽጉጥ መጠጣታቸው ነው። የጀግንነት ምሳሌ የሚደረገውም ይሄው ሆነ።
ይህ የአጼ ቴዎድሮስ ጅምር አልቀጠለም። የኢትዮጵያ የውስጥም የውጭም ጣጣ እየባሰበት ሄደ። ለሥልጣን ሽኩቻ የሚደረጉ ጦርነቶች ሀገሪቱን ወደኋላ እየጎተቷት ሄዱ። እነሆ ይህ ችግር ዛሬ ድረስ ቀጥሎ ወደ ሥልጣኔ የሚወስድ ቆራጥ ውሳኔ ላይ አልደረስንም።
አሁን ኢትዮጵያ የሲንጋፖርን ተሞክሮ ለመውሰድ እየሠራች ነው። አዲስ አበባም በከፍተኛ መታደስ ላይ ናት። አራት ኪሎና ፒያሳን ያየ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን ይረሳል። አዲስ አበባ ለዚያውም አራት ኪሎ ተወልዶ አድጎ፤ በሥራ አጋጣሚ ከ6 ወር በፊት ከአዲስ አበባ ውጪ የነበረ ሰው ዛሬ ድንገት አራት ኪሎ ቢጥሉት ሊጠፋ ሁሉ ይችላል። የሆነ አውሮፓ ሀገር ውስጥ ያለ ሊመስለው ይችላል። ይህ የሆነው በ6 ወር ውስጥ ነው። አሁን የተጀማመሩት ሲያልቁ ደግሞ በጣም ዘገየ ከተባለ ከ6 ወር በኋላ ብዙ ለውጦች ይታያሉ። በአጠቃላይ አዲስ አበባ በአንድ ዓመት ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ታሳያለች ማለት ነው። ለአንድ ዓመት ያህል ከኢትዮጵያ ውጪ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ከአዲስ አበባ ውጪ ቆይቶ የሚመጣ ሰው ‹‹ አዲስ አበባ ይቺ ናት እንዴ?›› ሊል ይችላል። አፍንጫውን ይዞ ያልፍባቸው የነበሩት እነ ራስ መኮንን ድልድይ ቆሞ እንዲፈዝ ያደርጉታል።
ይህ የሥልጣኔ ጅማሮ ‹‹እንዴትና በማን መጣ?›› ነው ጥያቄው።
ኢትዮጵያ አሁን እየሠራችው ያለውን ነገር ለማስፈጸም ብዙ ቆራጥ ውሳኔዎች ተደርገው ነው። ብዙ ልማዳዊ ነገሮችን እና መሰናክሎችን በመቋቋም ነው። ለሺህ ዘመናት ሥር ሰደው የኖሩ አሳሪ ልማዶችን በመጋፈጥ ነው። እነ ጃፓን ከ150 ዓመታት በፊት ከነበሩበት እየተነሳች ነው ማለት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህን ቆራጥ ውሳኔ ሲወስዱ የጃፓኑ ሙትሱሂቶ ወይም የኢትዮጵያው አጼ ቴዎድሮስ ያጋጠማቸውን ማህበረሰባዊና ልማዳዊ ጣጣ ተቋቁመው ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሆነው የ19ኛውን ክፍለ ዘመን ልማድ እየተጋፈጡ ነው። የሀገርን ጉዳይ እና የፓርቲን ጉዳይ መለየት የማይችለውን የፖለቲካ ልማዳችንን ተቋቁመው ነው።
ስለዚህ ይህ ትውልድ ‹‹ኢትዮጵያ እንደምን ሠለጠነች?›› የሚለው ትርክት አካል ለመሆን ቆራጥ መሆን አለበት። ፖለቲካ እና ልማትን መለየት አለብን። ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መንግሥትን መቃወም መብት ነው፤ መብት ስለሆነ ብቻም ሳይሆን መንግሥት ፖለቲካዊ ስህተት ሲሠራ መናገር ሥልጣኔ ነው። ዳሩ ግን ለሠሪው ባለሥልጣን ሳይሆን ለሀገር የሚሆኑ ነገሮችን መቃወም የጤና አይደለም፤ የሀገር ፍቅር መገለጫም አይደለም። ንጉሥ ላሊበላ ዛሬ በሕይወት የለም። ዳሩ ግን የላሊበላ ፍልፍል ዛሬ የኢትዮጵያ ሀብት ነው። እነሆ ከ900 ዓመት በኋላ ያለው ትውልድ እየኮራበት ነው። አክሱምን የሠራው ትውልድ ዛሬ የለም፤ ዳሩ ግን እነሆ የሥልጣኔ ምልክት አስቀምጦ ኢትዮጵያን በዓለም እንድትታወቅ አድርጓል።
ስለዚህ ከዓመታት በኋላ ‹‹ኢትዮጵያ እንደምን ሠለጠነች?›› እንዲባል ዛሬ እንሥራ!
ሚሊዮን ሺበሺ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም