ሀገራት የኢንቨስትመንት ዘርፋቸውን በማሳደግ ጥቅል አገራዊ እድገታቸውን ዘላቂ ለማድረግ ከሚተገብሯቸው አሰራሮች መካከል አንዱ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን (Special Economic Zones) ማቋቋም ነው። ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች የሚፈጥሩትን የስራ እድል፤ ለአገር በቀል የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪው መስፋፋት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርንና የባለሙያዎችንና የሠራተኞችን ክህሎት ለማሳደግ እና የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የሚኖራቸውን ወሳኝ ሚና እንዲሁም የወጪና ገቢ ንግድን ለማቀላጠፍ ያላቸውን አበርክቶ በአጠቃላይ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት መሻሻል የሚኖራቸውን ጉልህ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት አገራት ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን ያቋቁማሉ፣ ያስፋፋሉ።
የምጣኔ ሃብት ሳይንስ ጥናቶች እንደሚያስረዱት፤ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለምርት አቅርቦት እና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ። የእነዚህ ቀጣናዎች ዋና ዋና ዓላማዎች የስራ እድል ፈጠራን እና ምርትንና ምርታማነትን መጨመር፣ የወጪ ንግድን ማስፋትና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እንዲሁም ካፒታልና ቴክኖሎጂን መሳብ ናቸው። ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች የራሳቸው የምርት ስፍራ/ወሰን፣ የአስተዳደር ስርዓት፣ የታክስ ሕግጋት እና የጉምሩክ ስርዓት አላቸው። ቀጣናዎቹ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በጥሬ እቃ አቅርቦት እንዲሁም በምርት አቅርቦትና ግብይት ተግባራት ላይ የሚሰማሩ አካላትን ቁጥር ይጨምራሉ። ይህም የልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ልማት ከኢንቨስትመንት እድገት ጋር ቀጥተኛ ትስስር እንዳለው ማሳያ ነው።
ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች የግል (Private) እና የመንግሥት (Public) ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታት የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲያድግ ያስችላሉ። ቀጣናዎቹ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን (Foreign Direct Investment) በመሳብ የግል ባለሃብቶች በስፋት በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ያደርጋሉ። በሌላ በኩል ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ሰፊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን የሚፈልጉ በመሆናቸው መንግሥት በመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት (Infrastructural Investment) ላይ እንዲሰማራ በማድረግ የመንግሥት ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ እድል ይፈጥራሉ። በአጠቃላይ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ለባለሃብቶች ምቹ እድሎችን የሚፈጥሩ በመሆናቸው ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ተነሳሽነት ይኖራቸዋል።
በልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ውስጥ የሚተገበሩ ሕጋዊ አሰራሮች ቀለል ያሉና ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረዶችን የሚቀንሱ በመሆናቸው ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሰማራት የሚያደርጉትን ጥረት በአንፃራዊነት ቀላል ያደርጉላቸዋል። በነፃ የንግድ ቀጣናው ውስጥ ገብተው የሚሠሩ ባለሀብቶች፣ አስመጪና ላኪዎችም ሆኑ ድርጅቶች የልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እንዲሁም መሬትን ጨምሮ ሌሎች እምቅ ሀብቶች ያላት ኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን በማቋቋም ረገድ በመዘግየቷ ከእነዚህ ቀጣናዎች ልማት ማግኘት የሚገባትን ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም ማጣቷ ተደጋግሞ ሲገለፅ ቆይቷል። የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ እግር ከወርች አስረው የያዙት አንዳንዶቹ መሰናክሎች ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች በሚያስገኟቸው ጥቅሞች የሚፈቱ ናቸው። ስለሆነም ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን በማቋቋም የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ለማልማት የሚያስችሉ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች ልማት በሕጋዊ ማዕቀፍ የተደገፈ እንዲሆን የሚያስችሉ ብሔራዊ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ፖሊሲ እና የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ (1322/2016) ተዘጋጅተው ወደ ስራ ተገብቷል። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነሐሴ 27 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ በብሄራዊ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ረቀቂ ፖሊሲ ሰነድ ላይ ውይይት በማድረግ፣ ፖሊሲው በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል። ምክር ቤቱ ፖሊሲው በስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ ያሳለፈው ኢትዮጵያ ለአገራዊ የኢኮኖሚ እድገት የጎላ አስተዋፅዖ ባለውና ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየተስፋፋና እየጎለበተ በመጣው ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ የንግድ ትስስር ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንድትሆን አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ነው።
ፖሊሲው የአገሪቱን የወጪ ንግድ ስርዓት ለማሻሻል፣ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበትን ለማሳደግ፣ የወጪ ንግድ አቅምን ለማጎልበት፣ ሰፊ የስራ እድሎችን ለመፍጠር እንዲሁም በአገሪቱ ዋና ዋና የንግድ ኮሪደሮች የደረቅ ወደቦችን ለማስፋፋትና የሎጂስቲክ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ ስርዓቶችን እውን ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ስብሰባው የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅን አፅድቋል። የውጭ ኢንቨስትመንትን በቀላሉ ለመሳብ፣ ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ የአምራች ዘርፉን ለማበረታታት፣ የምጣኔ ሀብት ትስስርን ለማጠናከር፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳለጥ እንዲሁም ተግባራዊ የተደረገውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስርዓት ዲዛይንና ትግበራ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ስርዓት በማሳደግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።
ነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ተመርቆ ስራ የጀመረው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና (Dire Dawa Free Trade Zone)፣ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገነባው ‹‹አዲስ ቱሞሮው›› ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እና ግንባታው በኦሮሚያ ክልል የሚከናወነው ‹‹ገዳ›› ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑት የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች ግንባታ አካል ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ግንቦት ሁለት ቀን 2016 ዓ.ም ግንባታውን ያስጀመሩት ‹‹ገዳ›› ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በግዙፍነቱም ሆነ በአዋጭነቱ ከሌሎቹ የላቀ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ነው። ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ በ24ሺ ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባና በአራት ምዕራፎች የሚለማ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ በ3114 ሄክታር መሬት ላይ ለመጀመር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። ‹‹ገዳ›› ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ለኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችለውን የአልሚነት ስምምነት ሰሞኑን ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ተፈራርሟል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ዘለቀ ተመስገን፣ የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ ሚና እንዳለው ይገልፃሉ። እሳቸው እንደሚሉት፣ የልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ወደ ትግበራ መግባት መቻል የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማጎልበትና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል። ለኢንዱስትሪያላይዜሽን መስፋፋት፣ ለቴክኖሎጂና ለእውቀትና ሽግግር እንዲሁም ለስራ እድል ፈጠራ አጋዥ ይሆናል። ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች አዳዲስ የኢንቨስትመንት እድሎችን ይፈጥራል። ኢትዮጵያም በቀጣናውም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ተፈላጊና ምቹ ሀገር ሆና እንድትቀጥል ትልቅ አስተዋፅዖ ያደርጋል።
‹‹በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን መካከል የተፈረመውን የአልሚነት ስምምነት ተከትሎ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ለንዑስ አልሚዎች፣ ለድርጅቶች፣ በአጠቃላይ ለባለሃብቱ ምቹ መደላድል መፍጠር ይጠበቅበታል። በተለይም ለባለሃብቶች አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት፣ ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል አካላት ጋር በመሆን ሌሎች አገልግሎቶች በተገቢ ሁኔታ እንዲሟሉ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ከማደራጀት ጀምሮ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጁ ላይ የተቀመጡትን ሌሎች ድጋፎችን ለገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሚያደርግ ይሆናል። የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ለማሸጋገር አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት ላይ ይገኛል›› ይላሉ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲጠናከር የውጭ ባለሃብቶችን በመሳብና በመመልመል፣ የተመለመሉትን ወደ ተግባር በማሸጋገር፣ ወደ ተግባር ለተሸጋገሩት ደግሞ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ለሀገራዊ የምጣኔ ሃብት እድገት ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሚገኝ የሚናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ የ‹‹ገዳ›› ልዩ የኢኮኖሚ ዞን መቋቋምም የዚሁ ማሳያ እንደሆነ ያስረዳሉ።
የ‹‹ገዳ›› ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞቱማ ተመስገን በበኩላቸው፣ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ በአፍሪካ ትልቅ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የመገንባት ራዕይ ያለው የምጣኔ ሀብት ቀጣና እንደሆነ ይገልፃሉ። ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚያስረዱት፣ ተልዕኮውም መሰረተ ልማቶችን በማቅረብና ኢንቨስተሮችን በመቀበል፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ዞን ማዕከልን መገንባትን ማዕከል ያደረገ ነው። የስራ እድሎችን የመፍጠር፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን የመሳብ፣ የውጭ ምንዛሬ የማስገኘትና የምጣኔ ሀብት እድገትን የማፋጠን ዓላማዎች ያሉት ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ፣ በ24ሺ ሄክታር መሬት ላይ የተቋቋመና በአራት ምዕራፎች የሚለማ ይሆናል።
‹‹የኢኮኖሚ ዞኑን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ባለብዙ ዘርፍ ዞን መሆኑ ነው። በውስጡ ለኢንዱስትሪ ብቻ የሚሆን 5000 ሄክታር መሬት አለው። የገበያ ፈጠራን መሰረት ያደረገ፣ ሰፊ መሬት ላይ ያረፈ፣ በከፍተኛ የአዋጭነት ጥናት ላይ የተመሰረተ፣ ብዙ መሰረተ ልማቶች ባሉበት አካባቢ የሚገነባ (ፈጣን መንገዶች የሚገናኙበት፣ የሀገሪቱ የሎጂስቲክስ ማዕከል በሚባለው ከሞጆ ደረቅ ወደብ አካባቢ የሚገኝ፣ ከባቡር መስመር ጋር የተገናኘ) የኢኮኖሚ ማዕከል ነው›› ይላሉ።
እንደ አቶ ሞቱማ ገለፃ፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የተደረገው የአልሚነት ስምምነት ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን እንዲጠቀሙ፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲቋቋም እንዲሁም የግብይትና የፕሮሞሽን ስራዎችን በጋራ ለመስራት የሚያስችል ነው።
ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ከሚሰጠው ከልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና ስርዓት ርቃ መቆየቷ ብዙ ጥቅሞችን አሳጥቷታል። የእነዚህ ጥቅሞችና እድሎች መታጣት ደግሞ በአጠቃላይ አገራዊ እድገቷ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረባት አይካድም። ስለሆነም ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን ለማቋቋም የተጀመሩትን ጥረቶች በማጠናከር አገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገቱ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያስመዘግብ ማድረግ ይገባል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም