ተስፋ ሰጪው በምግብ እህል ራስን የመቻል ጉዞ

በዓለም ላይ ግብርና ትልቁና ዋነኛው የሀገራት ኢኮኖሚ መሰረት ነው። ጠንካራ አቅም የገነቡ ሀገራት ለግብርና ምርትና ምርታማነት የሰጡት ትኩረት ውለታው ይከፍላቸዋል። የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸው ማጠንጠኛ ግብርና እና ግብርና የሚል ነው። መርሀቸው ከፍጆታ ወደ ሸመታ የሚቀርብ፣ በምግብ ራስን የመቻል እሴትን ጨምሮ በግዙፍ የማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እድገትን ማሳለጥ ነው።

በዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት /ፋኦ/ ትርጓሜ መሰረት የምግብ ዋስትና ተረጋገጠ የሚባለው በአንድ ሀገር ያሉ ሁሉም ዜጎች ሁልጊዜ ንቁና ጤናማ ሆነው ለመቆየት የሚያስችላቸውን በቂ፣ ንፁህና የተመጣጠነ የምግብ አማራጭ ለማግኘት የሚችሉበት የኢኮኖሚ አቅምና አቅርቦት ሲኖራቸው ነው።

የምግብ ዋስትና አንድምታው የራስን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የውስጥን ፍጆታን ከመሙላት የዘለለ ነው። የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ማለት የምግብ ምርትን በማሳደግ የምርት መውደቅና የዓለም አቀፍ ገበያ አሉታዊ ተፅዕኖ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳ ለዜጎች በቂ የምግብ ምርት ሳይስተጓጎል የሚያቀርብ፣ የምርት፣ የግብይትና የመጠባበቂያ ክምችት መዘርጋት ነው።

‹‹በምግብ ራስን መቻል ከማምረት በላይ›› በሚል የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ዓመታት በተለይ በስንዴ ምርትና ምርታማነት አስደናቂ ውጤትን እያስመዘገበ ይገኛል። ለእርዳታ እጇን ትዘረጋ የነበረች ሀገርም የተሻለ ምርት አምራች የሚል ስም ተለጥፎላት እውቅና ማግኘቷ ይበል የሚያሰኝ ነው።

ባለንበት ዘመን በምግብ ራስን መቻል ከሉአላዊነት ጋርም በቀጥታ የሚያስተሳስሩት በርካቶች ናቸው። ለዚህ በእርዳታ ሰበብ ፖለቲካቸውን የሚያቀብሉ ሀገራት መብዛታቸው ራስን መቻል ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ያስረዳል።

ዛምቢያዊቷ ኢኮኖሚስት ዳምቢሳ ሞዮ ‹‹Dead aid: Why aid is not working and how there is a better way for Africa›› የሚል ርዕስ በሰጠችው ቆየት ያለ መፅሀፏ በዕርዳታ ሰበብ አፍሪካን የተጣቧትን የምዕራባዊያን ሴራ ተንትና አቅርባለች። በመፅሀፉ የሚጎላው ሀሳብ ከዕርዳታ ያልተላቀቀ ማኅበረሰብ መፍጠር የተረጂነት ስነልቡናን ማንገስ፤ ራስን መቻል ብርቅ እስከሚሆን ድረስ በማሳየት ይህንን ትርክት እንደመርፌ መውጋት ነው።

በምግብ እህል ራሷን የቻለች ሀገር ኢኮኖሚዋ እንዳደገ ጭምር የምትቆጠር ነች። እናም ግብርና በምግብ እህል ራስን ለመቻል ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚውም ሆነ ለሌላው ነገር መሰረት ለሆኑባት ኢትዮጵያ ደግሞ ትልቅ ትርጉም ይሰጠዋል።

በሀገራችን ግብርና ዋነኛው የኢኮኖሚ መሰረት ሆኗል፤ አሁንም ነው። በዓለም ግብርና ከአስር ሺህ ዓመታት የተሻገረ ታሪክ እንዳለው ይነገርልታል። ስንዴ ደግሞ ዋናው ሰብል ነው። ይሁን እንጂ የፖለቲካ ሰብል በመባል የሚታወቀው ስንዴ፣ በምግብ ጥያቄ የዓለም መሳሪያ በሆነው ስንዴ ራሳችንን ባለመቻላችን ረሀብተኛ ከሚለው ስያሜያችን ጀምሮ ዓለማቀፍ ጫናዎችን ስንሸከም ቆይተናል።

ኢትዮጵያ ከፍጆታዋ ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ዓመታዊ የስንዴ ፍላጎቷን ለማሟላት ለዓመታት በየዓመቱ ከ700 ሚሊዮን ዶላር እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለስንዴ ግዢ ስታወጣ ቆይታለች። ታሪክ ተቀየረና በኢትዮጵያ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በማስፋፋት ስንዴ በየዓመቱ የሚመረትበት ወቅትን በመጨመር በ2014 የስንዴ ፍጆታዋን ሙሉ በሙሉ ሸፍና በየካቲት 2015 ዓ.ም ደግሞ ስንዴ ወደ ውጪ መላክ ጀመረች።

ይህ ጥረት የኢትዮጵያን ገፅታን የሚለውጥ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ሆነ። ዓለምም ይህን ጥረትና የተገኘውን ፍሬ አደነቀ። ይህ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዓለማቀፍ አካላት ጭምር ዕውቅናን ማግኘት ጀምሯል። ሀገሪቱ በጀመረችው አስደናቂ የስንዴ ምርት ልማት ከተገኙ ውጤቶች መካከልም በ2010 በስንዴ ምርት ይሸፈን የነበረው 50 ሺህ ሄክታር የስንዴ እርሻ በ2013 ወደ 167 ሺህ ሄክታር አድጓል።

በ2014 መጀመሪያ ላይ ደግሞ ወደ 650 ሺህ ሄክታር ማደጉን መረጃዎች ያሳያሉ። በ2015 ደግሞ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መድረስ ችሏል። ከዚህም 47 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ መሰብሰብ ተችሏል። ዘንድሮ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለመሸፈን በዕቅድ ተይዞ እንደነበር ተገልጧል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ምርትና ምርታማነት ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተገኘ እንደሆነ እየተመለከትን ነው። በበጋ መስኖ ልማት በርካታ ክልሎች ካለፉት ዓመታት አንፃር የተሻለ ምርት እያመረቱ ይገኛሉ። ለግብርናው ዘርፍ ቅድሚያ በመስጠት በስንዴና በሩዝ ምርት ስኬታማ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛል። የሜካናይዝድ እርሻም እየተስፋፋ መጥቷል።

በሰው ኃይል ጉልበትና ልፋት ላይ የቆየው የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ እምብዛም ለውጥ ሳታይበት ዘመናት አልፈዋል። ለዚህም ነው መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን በማድረግ ወደ ስራ ተገብቶ የሚጨበጥ ለውጥ ማምጣት የተቻለው ይላሉ የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ። ከሞፈርና ቀንበር ወደ ማሽን በማሸጋገር ሰፊ ስራ ተሰርቷል። በቅርብ ዓመታት ብቻ ከ5 መቶ በላይ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተደርጓል።

እንዲህ መደረጉን ገበሬዎቹም ያምናሉ። ቀደም ባሉ ዓመታት በበሬ ያርሳሉ በበሬ ይሰበስባሉ። አሁን ከዘር እስከ ምርት መሰብሰቢያ ጊዜ ዘመናዊ መሳሪያዎችን መጠቀማቸው በምርት ግኝትም የተሻለ፣ በኑሯቸውም ለውጥ ያመጣ መሆኑን ይናገራሉ።

ቀደም ባሉ ዓመታት የቅንጦት እቃዎች ከውጭ እንዲገቡ ቅድሚያ ይሰጥ ነበር። አሁን ግብርናውን በማዘመን በመካናይዜሽን መሳሪያዎች አቅርቦት የተሰራው ተግባር የሚታይ ሆኗል። ይህ ምርትን በማሳደግ ረገድ ያለው ሚና ከፍ ያለ ነው። ነገር ግን አሁንም የተሻለና የበለጠ ስራን ይጠይቃል።

በእርግጥም ከዚህ በፊት ባለሀብቶች መኪናዎችን ለማስገባት ከቀረጥ ነፃ እድል ያገኙ ነበር። ይህንን መሰል እድል አርሶ አደሩ አግኝቶ አያውቅም። የግብርና ዘርፉ ወደ ሜካናይዜሽን እንዲገባ የማበረታታት ተግባራት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተጀመረ ተግባር ነው። ይህ ቀጣይነት ኖሮት ግብርናውን የመደገፍና የማበረታታት ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ከሆነ ተስፋ ሰጪ ጅምር እየታየ ነው።

በሀገራችን ምጣኔ ሀብት ለውጥ እንዲመጣ ከተሰራው መዋቅራዊ ማሻሻያና በተግባር የታየው በግብርናው ረገድ ከፍ ያለ ነው። ምርትን ለማሳደግ የተሰራው በስንዴ፣ በሩዝና በሌሎች ምርቶችም ውጤት ማየት ተችሏል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ግብርና ከፍተኛ እመርታ አምጥቷል ማለት ያስደፍራል። ይህ አምናም ዘንድሮም በተግባር ታይቶ የተመሰከረለት ነው። የሀገሪቱን ዕድገት ተሸካሚ ሆኗል ማለት ያስችላል። ለስንዴ ሀገሪቱ በየዓመቱ 7 መቶ እና 8 መቶ የአሜሪካ ዶላር ታወጣ ነበር። ከአምና ጀምሮ ሀገሪቱ ለስንዴ አንድ ብር እንደማታወጣ መንግስት አሳውቋል።

ባለፉት 50 ዓመታት ስንዴ ከውጭ ስናስገባ ነበር። 2011 በመኸር የሚታረሰው የስንዴ መሬት 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ብቻ ነበር። ይህ ማለት በዝናብ ብቻ ነበር የምናርሰው ማለት ነው። ኢትዮጵያ ታገኝ የነበረው 48 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ነበር። በ2016 ዓ.ም የካቲት ላይ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንደሚሸፈን ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ አሳውቆ ነበር።

ለውጡና እድገቱ በዚህ መልኩ የሚገለፅ ሆኗል። ምርታማነቱ ከ5 ዓመታት በፊት 27 ኩንታል በሄክታር የነበረው ስንዴ በ2015 ዓ.ም በነበረ መረጃ ወደ 39 ኩንታል በሄክታር ማግኘት ተችሏል።

ግብርናችን የሚታወቀው በተበጣጠሰና በአነስተኛ ማሳ ላይ የሚከወን ነው። ይህንን በመቀየር በአሁኑ ሰዓት 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታገጠም የገበያ እሳቤ አርሶና አርብቶ አደሮቻችን በልቶ ለማደር ሳይሆን ለገበያ፤ ለኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ እንዲያመርቱ ተደርጓል። ከ 9 ሚሊዮን ባላይ አርሶና አርብቶ አደር ተደራጅተው እየሰሩ ይገኛሉ።

ከተናጠል ይልቅ በኩታ ገጠም እንዲታረስ በማድረግም ምርታማነት እንዲጨምር፣ የአርሶ አደሩ ኑሮ እንዲሻሻል የተወሰደ ሌላ እርምጃ ነው። ኑሮን ማሻሻል ተገቢ ተደርጎ ገበያ ተኮር ምርትና የእርሻ ስራ ማከናወን ተመራጭም ተደርጓል።

በግብርናው ዘርፍ በተሰራው ስራ ውጤት ቢኖርም ፈተናዎች ነበሩበት። የግብአት አቅርቦት በዋናነት የሚነሳ ነው። ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ መሰል ችግሮችን በማስወገድ፣ ቅርብ ክትትል በማድረግ ምርትን ማሳደግ ዋና መፍትሄ ነው።

ከእኛ አልፎ ለውጪ ገበያ የቀረበ ስንዴ በሀገር ውስጥ ገበያ ዋጋው አልቀመስ ብሎ የዳቦ ዋጋ ከምንግዜውም በላይ ተወዶ ኢትዮጵያውያን ችግር ውስጥ መገኘታችን እሙን ነው። ስንዴን ከሀገሯ ፍጆታ ተሻግራ ለውጭ ገበያ ያቀረበች ሀገር ዜጎቿን ዳቦ በአግባቡ አለመመገብ ተቃርኖ በብዙ የግብይት ሰንሰለት ችግሮች የተተበተበ መሆኑን ያመላክታል።

ይህን ችግር መፍታትና የስንዴን የሀገር ውስጥ ዋጋ ማረጋጋት ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል። ደግሞም በቀጣይ ኢትዮጵያ ለስንዴ ምርት የሚሆን የውሃ፣ የመሬትና የሰው ኃይል አቅም ያላት ሀገር በመሆኗ ይህንን ሀብት በሙሉ አቅም በመጠቀም ከተገኘው ውጤት በላይ ጠንካራ ስራ መስራት ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ ከብሄራዊ ሉአላዊነት ጋር ያስተሳሰረችው ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። በስንዴ የታየው ስኬትም በሌሎች ሰብሎችም መድገም፣ የገበያ ሰንሰለቱን ማዘመን ደግሞ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋትም መፍትሄ ይዞ የሚመጣ ይሆናል። አርሶ አደሩም ለእርሻ ስራው በቂ ግብአት በወቅቱና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲደርሰው ማድረግም ከሁሉም ይጠበቃል።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You