የንግድ ሥራ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብዙ ዘመናትን ያስቆጠረ የኢኮኖሚ ማዕከል ነው። ያም ቢሆን ታዲያ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የንግድ ስርዓትን በአግባቡ የሚመራ ወጥ የሆነ የንግድ ፖሊሲ አልነበረም። በመሆኑም በፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አፈፃጸም እና በንግድ ዘርፉ ላይ ያሉ የንግድ እድሎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች እና ስታንዳርዶች በተመለከተ የአሰራር ወጥነት ችግሮች ሲስተዋሉ ቆይተዋል። በአገሪቱ ሕገወጥ ንግድ መስፋፋቱም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
በአገሪቱ ያለው የንግድ ስርዓት ጤናማ፣ ዘመናዊ፣ የተቀላጠፈና ሕግና ስርዓትን የተከተለ፤ ሸማቹን፣ ነጋዴውን፣ መንግሥትንና አጠቃላይ የንግዱን ማኅብረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግም መንግሥት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱ አይዘነጋም። ከሚደረጉ ጥረቶች መካከልም በአሁን ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ እየገባ ያለው አዲስ የንግድ መመሪያ አንዱ ነው። መመሪያው በከተማዋ ጤናማ የሆነ የንግድ ስርዓትን በማስፈን ሸማቹን፣ ነጋዴውንና አጠቃላይ የንግዱን ዘርፍ ካላስፈላጊ ወከባና እንግልት የሚታደግ እንደሆነ ታምኗል፡፡
አዲሱና ወደ ሥራ የገባው መመሪያ ‹‹በመንደር የንግድ ቁጥጥር የአሰራር ስርዓት መመሪያ ቁጥር 159/2016 ዓ.ም›› ሲሆን፤ ቢሮው ከሰሞኑ በመመሪያው አተገባበር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። የመመሪያው ዋና ዓላማ ከተማዋን ወደ ዘመናዊ የንግድ ስርዓት ውስጥ በማስገባት የተሻለ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር ማድረግ የሚል እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢንያም ምክሩ ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ የተሰጠውን ኃላፊነት እየተወጣ ሲሆን፤ አንደኛ ፍትሃዊ የሆነ የንግድ ስርዓት በከተማዋ ለማስፈን፤ በየአካባቢው ያለውን የንግዱ ማኅበረሰብ የንግድ ሥራውን በሚሰራበት ጊዜ በተረጋጋና ከወከባ ነጻ በሆነ መንገድ ሥራውን በአግባቡ ማከናወን እንዲችል፣ እንዲሁም መንግሥት ያስቀመጠውን የንግድ ስርዓት የሚተላለፉ ነጋዴዎችን ወደ ስርዓት ማስገባት በመሆኑ ይህን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል መመሪያ አዘጋጅቷል፡፡
መመሪያው ‹‹በመንደር የንግድ ቁጥጥር የአሰራር ስርዓት መመሪያ ቁጥር 159/2016 ዓ.ም›› ሲሆን መመሪያውን ወደ ሥራ ከመግባቱ አስቀድሞ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በመሆኑም አሁን ላይ መመሪያው ወደ ተግባር እየገባ ይገኛል። ያም ቢሆን ታድያ አሁንም የግንዛቤ የማስጨበጫ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት በመሆኑ በቢሮው፣ በክፍለከተሞችና በወረዳዎች አማካኝነት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል በማለት አስረድተዋል፡፡
በተለይም በንግድ ቢሮ፣ በክፍለከተማና በወረዳ ደረጃ መሰራት ያለበት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠልና ጤናማ የሆነ የንግድ ስርዓት በከተማዋ መስፈን እንዳለበት ነው። በዋናነት ሕግና ስርዓትን አክብረው የሚሰሩ ነጋዴዎች መብትና ግዴታቸው ምን እንደሆነና እንዲሁም ሕግና ስርዓትን ሳይጠብቁና ያለ ንግድ ፈቃድ የሚሰሩ ነጋዴዎች ደግሞ ምን አይነት እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችል ግልጽ መረጃ በመያዝ ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር ማድረግና ወደ ንግድ ስርዓቱ እንዲገቡ መሥራት ከአመራሩ ይጠበቃል። በተለይም የወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች ጥብቅ ቁጥጥር አድርገው የሚሠሩ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 በጀት ዓመት 230 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ያቀደ መሆኑን ያነሱት አቶ ቢንያም፤ ይህን ዕቅድ ለማሳካት ከንግዱ ዘርፍ ብዙ የሚጠበቅና የተሰጠው ኃላፊነትም ትልቅ እንደሆነ ነው ያስረዱት። እሳቸው እንዳሉት ወደ ንግድ ስርዓቱ ያልገቡ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ይህን ኃላፊነት መወጣት ይቻላል፡፡
ስለዚህ በከተማዋ በየትኛውም መንደርና ወረዳ ላይ ያለንግድ ፈቃድ የሚሰራ አንድም ነጋዴ እንዳይኖር የማድረግ ኃላፊነት የወረዳው መዋቅር በመሆኑ ወረዳው እዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ያለንግድ ፈቃድ ሲሰሩ የነበሩ ነጋዴዎች በሚገኙበት ጊዜ ንግድ ፈቃድ እንዲያወጡ የማድረግ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ቢንያም፣ ከዚህ በኋላ ግን ተደጋጋሚ የማስገንዘብ ሥራ ሲሰራ የቆየ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት ማንኛውም ነጋዴ ያለንግድ ፈቃድ ሲሰራ ለቆየባቸው ጊዜ ሁሉ አስፈላጊውን ቅጣት ይቀጣል ነው ያሉት።
አያይዘውም ቢሮው በነቃ ጊዜ በሕጋዊ መንገድ የሚነግድና ባልተደረሰበት ጊዜ ደግሞ በሕገወጥ መንገድ የሚነግድ ነጋዴ በየትኛውም አካባቢ መኖር የለበትም ብለዋል። ስለሆነም ሁሉም ነጋዴ እስከሰራ ድረስ የመንግሥትን ሕግ አክብሮ ንግድ ፈቃድ አውጥቶ ለመንግሥት የሚገባውን ግብር እየገበረ መነገድ እንደሚገባው ማስገንዘብ ተገቢና የግድ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም የወረዳ መዋቅር አንዱና ትልቁን ኃላፊነት የሚወስድ አካል በመሆኑ እዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ አሳስበዋል።
ሌላው በንግድ ስርዓት ውስጥ ገብተው ንግድ ፈቃድ አውጥተው ለሚሰሩ ነጋዴዎችም እንዲሁ ወቅታዊ መረጃ የሚሰጥ ሲሆን፤ በተለይም ወቅቱን ጠብቀው ንግድ ፈቃድ የማያድሱ ነጋዴዎች በወቅቱ ንግድ ፈቃዳቸውን እንዲያድሱ የማድረግ ኃላፊነት ይወጣል። ከእነዚህ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ውጭ ያሉ የተለያዩ ጥፋቶችን ነጋዴው ሲፈጽም ለሚቀጥለው ዕርከን መረጃዎችን በማቅረብ በከተማ ደረጃ እርምጃዎቹ የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡
በከተማዋ በተደረገው ጥናት መሰረት በርካታ ነጋዴዎች ንግድ ፈቃድ ሳያወጡ በየወረዳው የንግድ ሥራ እንደሚሰሩ የጠቀሱት አቶ ቢንያም፤ ወረዳው በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት ትኩረት አድርጎ ከሠራ የንግድ ሥርዓቱን ስርዓት በማስያዝና የከተማውን ገቢ በመጨመር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። የመመሪያው ተግባራዊነት በየመንደሩ ህጋዊ የንግድ ፍቃድ ሳይኖራቸው የንግድ ሥራ የሚሰሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ፣ በተቃራኒው ደግም ህጋዊ ሆነው የሚሰሩ ነጋዴዎች ሥራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ ለማስቻል ትልቅ አቅም የሚፈጥር በመሆኑ ለንግዱ ዘርፍ ትልቅ አበርክቶ እንዳለውም ተናግረዋል።
‹‹ከተማዋ በቀጣይ ለማግኘት ያቀደችውን ገቢ ማሳካት የምትችለው መመሪያውን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ነው›› ያሉት አቶ ቢንያም፤ ለዚህም ቢሮውን ጨምሮ ክፍለከተሞች ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም መመሪያውን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግና የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ወረዳዎች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ዘሀራ መሀመድ በበኩላቸው በመንደር የንግድ ቁጥጥር የአሰራር ስርዓት መመሪያ ቁጥር 159/2016 ዓ.ም መመሪያ በተለይም ለንግዱ ማኅበረሰብ ምቹና ቀልጣፋ ከመሆኑም በላይ ትላልቅ ችግሮችን የሚያስቀርና ወደ ሥራ የሚያስገባ መመሪያ እንደሆነ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በአሁን ወቅት ሕገወጥ ንግድ እጅግ የተንሰራፋበትና በተቃራኒው ደግሞ ሕጋዊ ነጋዴ የተበደለበትና የተጨቆነበት የንግድ ስርዓት ነበር ያለው።
ይሁንና ይህ ወደ ሥራ እየገባ ያለው አዲስ መመሪያ በንግዱ ዘርፍ እየተስተዋሉ የነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ማቃለል የሚችል ነው። ለዚህም ዛሬ ላይ ከወረዳ ጀምሮ እየተሰሩ ያሉ የጋራ ሥራዎች ማሳያዎች ናቸው ብለዋል። ፖሊሲና ስትራቴጂ በማውጣት ሕግ አውጭውና ሕግ አስፈጻሚው አካል በጋራ በመሆን የሚሰሩት ሥራ ነው። በመሆኑም ሕገወጥና ሕጋዊ የሆነውን ነጋዴ በቀላሉ መለየት የሚያስችል የንግድ ቁጥጥር ስርዓት እንደሆነና ለንግድ ስርዓቱ ጤናማነት ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በተለይም ከታች ባለው የንግዱ ማህበረሰብ በንግድ ቁጥጥሩ ላይ ፍትሐዊ ያልሆኑና ጉራማይሌ የሆኑ አሰራሮች ይስተዋሉ እንደነበር ያነሱት ወይዘሮ ዘሀራ፤ ሕግ አስፈጻሚው ደስ ባለው ሰዓት ተነስቶ የንግድ ድርጅቶችን የሚያሽግበትና ለሙስና የሚጋበዝበት አሰራር እንደነበረም አልሸሸጉም። ሌላው ሕጋዊ ነጋዴው ሕገወጡን በመመልከት ወደ ሕገወጥ መንገድ እየወጣ የነበረና ሕገወጥ ንግድ በእጅጉ እየተንሰራፋ ያለበት ጊዜ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በመንደር የንግድ ቁጥጥር የአሰራር ስርዓት መመሪያ ቁጥር 159/2016 ዓ.ም ሕገወጡን ነጋዴ ወደ ሕጋዊ መስመር ለማስገባት፤ ሕጋዊ ነጋዴውን ደግሞ ደግፎ ለመስራት የሚያስችል ምቹ ሜዳ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ዘሀራ፤ መመሪያው በተለይም በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ባዕድ ነገሮችን መቀላቀል እና ሌሎች ጥፋቶችም በዝርዝር የተቀመጡና የሚያስቀጡ እንዲሁም ስርዓት ተበጅቶላቸው የተቀመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በንግዱ ማኅበረሰብ በርካታ ችግሮች ስለመኖራቸው ጠቅሰው፤ ነጋዴውን ጨምሮ ኅብረተሰቡንና መንግሥትን ጭምር የሚያውኩ በርካታ ሕገወጥ ነጋዴዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። ይሁንና መመሪያው እነዚህን ነጋዴዎች ጭምር ወደ ሕጋዊ መንገድ ለመመለስ የሚያስችል ዕድል ያለው መሆኑን አመላክተዋል።
መመሪያውን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች እንዳሉ የገለጹት ወይዘሮ ዘሀራ፤ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታትም የተለያዩ አማራጮች እንዳሉ ሲያስረዱ፤ በተለይም የንግዱ ማህበረሰብ፣ ንግድ ቢሮ፣ ገቢዎችና ፖሊስ በጋራ ተቀናጅቶ ታች ድረስ ወርዶ መስራት እንዳለበትና ከዚህ ቀደምም መሰል ሥራዎች ሲሰሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ እነዚህ አካላት ከዚህ ቀደም መርካቶ አካባቢ ተቀናጅተው በሰሩት ሥራ ከ24 ሺ በላይ የሚሆኑ ንግድ ፈቃድ ሳያወጣ የሚነግዱ ሕገወጥ ነጋዴዎችን በመለየት ሕግና ስርዓት ውስጥ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ መሥራት ተችሏል። አሁንም ቢሆን አዲሱን 159/2016 መመሪያ የተሻለና ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት የሚያስችል እንደመሆኑ በከተማዋ ጤናማ፣ የተረጋጋና ፍትሐዊ የሆነ የንግድ ስርዓት እንዲፈጠር ያስችላል።
‹‹በመንደር የንግድ ቁጥጥር የአሰራር ስርዓት መመሪያ ቁጥር 159/2016 ዓ.ም በዋናነት ሕጋዊ ነጋዴውን በእጅጉ የሚጠቅም ነው›› ያሉት ወይዘሮ ዘሀራ፤ ሕጋዊ ነጋዴው ግብር ከመገበር ጀምሮ የተለያዩ ወጪዎችን ተቋቁሞ ሲሰራ በተቃራኒው ሕገወጥ ነጋዴው የማይስተካከል ከሆነ ሕጋዊ ነጋዴው ወደ ሕገወጥ ንግድ የሚገባበት መንገድ ሰፊ መሆኑን አንስተው በዚህም በርካታ ችግሮች ተፈጥረው መመልከት እንደቻሉ ነው ያስረዱት። ስለዚህ ንግድ ቢሮ ከገቢዎች ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት የንግድ ስርዓቱን የሚያስተጓጉሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት፤ ሕጋዊ ነጋዴውን መደገፍና ማበረታታት፤ እንዲሁም ሕገወጥ ነጋዴውን ወደ ሕጋዊ መስመር የማስገባት ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን አመላክተዋል።
ነጋዴውና ሸማቹ አጠቃላይ የንግዱ ማኅበረሰብ መብትና ግዴታውን በአግባቡ እንዲያውቅና እንዲረዳ፤ የንግድ ሥርዓቱ የተረጋጋና ያለወከባ መስራት የሚችልበትን ዕድል መፍጠር እንዲያስችለው ታስቦና ታቅዶ የወጣው በመንደር የንግድ ቁጥጥር የአሰራር ስርዓት መመሪያ በተለይም በዚህ ሂደት ውስጥ ከቁጥጥር ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ወጥ በሆነ የቁጥጥር ስርዓት ለማስኬድ እንደሆነም ተመላክቷል።
ፍሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም