በሰኔ ወር አጋማሽ የአገራችንን የቁርጥ ቀን ልጆች አጥተናል። በዚህም የአገሪቱ መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች ህይወታቸው አለፈ። ዕለቱ በአማራ ክልልም ከፍተኛ አመራሮች፤ ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን የክልሉ ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ እና የርዕሰ መስተዳድሩ የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴን ህይወት ነጥቆና በኢትዮጵያ ታሪክ ጥቁር ነጥብ አስቀምጦ አልፏል። በዚህ እኩይ ድርጊት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እና የአማራ ህዝብ ጥልቅ ኀዘን ተሰምቶታል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ለአማራ ክልልና ለአገራችን ህዝቦች ብሎም ለሰማዕታት ቤተሰቦች መፅናናትን ይመኛል።
በሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ላይ የደረሰው ግድያ ፍፁም ዘግናኝ እና ታቅዶበት የተፈፀመ እንደሆነ አደጋው በተፈፀመበት ወቅት እድለኛ ሆነው ከተረፉ አመራሮች ውስጥ ሶስቱ ፤የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌው፤ በም/ር/መ/ ማዕረግ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል እና የርዕሰ መስተዳድሩ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ አብርሀም አለኸኝ ከአማራ መገናኛ ብዙኃን ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። የግድያውን ሁኔታ ከማስረዳት ባለፈ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተውም ተወያይተዋል። እኛም ለንባብ በሚሆን መልኩ እንዲህ አቅርበነዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ለውጥ በምትገባበት ዋዜማ ብ/ጄነራል አሳምነው እና ሌሎች በርካታ ታስረው የነበሩ ጓዶች እንዲፈቱ እንደ ሀገርም እንደ ክልልም ሁሉም ትግል አድርጓል። በዚህም በርካቶች ከእስር ተፈተዋል። በተለይ ብ/ጄነራል አሳምነው እና ጀነራል ተፈራ ዘግየት ብለው ስለተፈቱ በወቅቱ ለምን እነሱ አልተፈቱም በሚል የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከፍተኛ ትግል ያደርግ ነበር።
ከተፈቱ በኋላም ለክልሉ እና ለሀገሪቱ ህዝብ ጥቅም ሲሉ የታገሉና የታሰሩ ናቸው ታሰሩ እንጂ ተጨባጭ ጥፋት አልነበራቸውም በማለት ህዝቡም አባላትም አመራሩም በየደረጃው ያነሳ ነበር። በመሆኑም ህዝብ በከፈለው መስዋዕትነት ተፈተዋል። በዚህም ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን መሪ ድርጅቱ ትግሉን ዳር በማድረስ ለውጥ መጥቷል። በዚህ ለውጥ ምክንያትም በርካታ ጓዶች ተፈተዋል።
እነዚህ ጓዶች በመፈታታቸው ሁሉም ደስተኛ ሆኖ የክልሉን ህዝብ እንዲያገለግሉ አመራር እንዲሰጡ እና ክልሉ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ከአሁን በፊት የተፈጠሩ ችግሮች ሁሉ ተወግደው የልማት ሥራ እንዲሰሩ ድርጅቱ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦዴፓ/ ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ ወሰነ። ሁሉም የድርጅቱ ኃላፊዎች በተለይ ማዕከላዊ ኮሚቴው ብ/ጄነራል አሳምነውን ሊመርጠው ችሏል። በመጨረሻም ጀነራሉ የአዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ሹመት ተሰጥቶታል።
‹‹ማን ያርዳ የቀበረ…››
ጄነራል አሳምነው ፅጌ ህዝብ ይህን የመሰለ እምነት ጥሎ ኃላፊነት ቦታ ቢያስቀምጣቸውም እርሳቸው ግን ድብቅ ሴራ እንደነበራቸው የሚያሳይ ተግባር ፈፀሙ። ጄነራሉ ሰኔ 15 ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የክልል ከፍተኛ አመራሮችን የያዘው አስተባባሪ ሰባት የኮሚቴ አባላት ስብሰባ ነበራቸው። በስብሰባው ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው አቶ ላቀ፣ አቶ እዘዝ ፣አቶ አብርሀም እና አቶ ዮሀንስ ቧያለው በስብሰባው የታደሙ ናቸው። በስብሰባው በአንድ ረድፍ የተቀመጡት አቶ ላቀ፣ አቶ መላኩ እና አቶ አብርሀም በመደዳ ተቀምጠው ነበሩ። ሟቾችን ጨምሮ ሌሎች ደግሞ በሌላ ረድፍ ተቀምጠው ነበር።
‹‹ከሰባታችን ውስጥ ሶስቱ ተሰውተዋል። አራታችን ደግሞ ተርፈናል። ሟችም ገዳይም ራሳችን ነን›› የሚሉት አቶ ላቀ ‹‹ለአማራ ህዝብ ብሎም ኢትዮጵያ እንታገላለን ብለን የተሰባሰብን አመራሮች ገዳይና ሟች ሆንን፤ እንኳን ለኢትዮጵያ ለራሳችን የማንሆንበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፤›› ብለዋል።
በወቅቱ ሶስት የልዩ ኃይል ልብስ የለበሱ ሰዎች ወደ ተሰብሳቢዎቹ መጡ፤ በሩን ለመክፈት ትግል አደረጉ፤ በሩ እንዳይከፈት ከውስጥ ሆኖ አቶ እዘዝ ደግፎ ይዟል። ገዳዮቹ በሩ አልከፈት ሲላቸው በሌላኛው በር ለመግባት አመሩ። ‹‹ከውስጥ እኛም ተደናግጠን ነበር፤›› አቶ ላቀ ይናገራሉ። በኋላ ዶክተር አምባቸው እና አቶ እዘዝ በሌላ በር አምልጠው ለመውጣት ሄዱ። ልዩ ኃይል የለበሱትም በተመሳሳይ በር ለመግባት ወደ በሩ በሚያቀኑበት ወቅት ከታጣቂዎቹ ጋር ፊት ለፊት ተገናኙ። በኋላም የታጠቁት ልዩ ኃይሎች ደጋግመው ተኮሱ ሲሉ እውነታውን ተናግረዋል።
‹‹ሁላችንም ቦታ ቦታ ያዝን ፤ተኩስ ተጀመረ። ተኩስ ሲጀመር ውጭ የነበሩት የታጠቁ ኃይሎች በልዩ ኃይሎቹ ታግተው በር ተዘግቶባቸው ነበር። ገዳዮቹ ሶስቱን አመራሮች ማለትም ዶክተር አምባቸው፣ አቶ እዘዝ እና አቶ ምግባሩን ከመቱ በኋላ አራታችን ሌላ ክፍል ውስጥ ስለነበርን ሳያገኙን ተመልሰው ሄደዋል። ከነበርንበት ክፍል ወጥተን ስንመለከት ጓድ ምግባሩ ከበደን በሕይወት አገኘነው።
‹‹መጋረጃ አውርደን የተመታበትን ቦታ አሰርንለት። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን የሁለቱ አመራሮቻችን ህይወት አልፎ ነበር። በኋላም በመስኮት ስናይ ሁለት ኤፍ ኤስ አር ሙሉ ልዩ ኃይል ሰራዊት እየተሳፈረ ዙሪያውን ከቧል። ከቦ ከነበረበት እየመጣ ወደ መኪናው ሲሳፈር ተመለከትን።›› ሲሉ አቶ ላቀ ምስክርነታቸው ሰጥተዋል። ዝርዝር ጉዳዩን ግን መርማሪ ቡድኑ የበለጠ ለህዝቡ ግልጽ ያደርጋል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ላቀ ጠቆም አድርገው አልፈውታል።
‹‹ድርጊቱ አፈጻጸሙ በጣም ዘግናኝ ነው፤ በአንድ ትግል አብሮ የታገለ ጓድ ይቅርና ጠላትም እንደዚህ ኢ-ሰብዓዊ በሆነ መንገድ ይፈጽማሉ ብዬ አልገምትም፤›› ሲሉ በወቅቱ በቦታው የነበሩት በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል ይገልፃሉ።
ግድያው የተፈጸመው 11 ሰዓት ላይ ፤ ከውጭ የተለየ ድምፅ ሰማን። ያ ድምፅ ሲሰማና በር ላይ የደረሱት የልዩ ኃይሉ ወታደሮች በሩን ለመክፈት ሲሞክሩ አቶ እዘዝ ትግል ያደርግ ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ በመሆን ችግር ይመጣል ብለው አለመገመታቸውን ያስታውሳሉ። ‹‹ሴራውን ብናውቅ ቢያንስ እንዘጋጅ ነበር። ለዚህ የሚያበቃ ምንም ነገር በሌለበት ይህ ይፈጠራል ብለን አናስብም። የራሳችን ጥበቃዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ከእነሱ አቅም በላይ እንደሆነ ለማየት ቻልን። በኋላም በመስኮት ለማምለጥ ስንሞክር ጄነራል አሳምነው ታች መሬት ላይ ሆኖ ልዩ ኃይሉን ያሰማራ ነበር። ታች በጣም በርካታ ሰው ነበር። አመራሮቹ የተገደሉት በሽጉጥም በክላሽም ነው።››ሲሉ አቶ መላኩ የድርጊቱንና የጭካኔ ሁኔታውን ያብራራሉ።
ጄነራሉን ምን ነካቸው?
ጄነራል አሳምነው ወደ ኃላፊነት እንዲመጣ የተደረገበትን እውነት የሚያስታውሱት አቶ ላቀ ይህ ሲሆን በተለይ በፀጥታው ዘርፍ ልምዱንና እውቀቱን ተጠቅሞ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር እና ለሀገርም ትልቅ ድርሻ እንዲኖረው ተብሎ የሾመው የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ነው ይላሉ። ከዚህ በኋላም የጄነራሉ አፈጻፀም እንደማንኛውም መስሪያ ቤት ይገመገማል። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ያለውን የሰላም እጦት፤ የህግ አለመከበር በተመለከተ ጄነራል አሳምነውን ብቻ ሳይሆን ፖለቲካውም ስለታመመ የፀጥታውም ሆነ ሌላው ሥራ በተለይ ከለውጡ ጋር ተያይዞ የክልሉ ህዝብ እየተቸገረ መምጣቱን ይገልፃሉ።
ህዝቡ ሰላሙ እየተናጋ ነው። ስለዚህ ህግና ስርዓት መከበር አለበት። የዜጎች ንብረት መጠበቅ አለበት። ዜጎች እንደልብ በሰላም ወጥተው መግባት አለባቸው። ስለ ህይወታቸው ስለሰላማቸው መጨነቅ ያለበት መንግሥት ነው። ዜጎች ሙሉ ጊዜያቸውን በኑሯቸው ላይ ማድረግ አለባቸው በሚል ይገመገማል፤ በዚህ ግምገማ ወቅትም ጄነራሉም ሆነ ሌላው ምንም ልዩነት የለም። ያሉ ችግሮችን ለማስተካከልም ጥረት ተደርጓል። ‹‹ነገር ግን ጄነራሉን ከዚህ በዘለለ ከኃላፊነት ትነሳለህ የሚል እንኳን ደብዳቤ ቃልም አልነበር›› ሲሉ አቶ ላቀ ያስገነዝባሉ።
ግምገማን በሚመለከት ህብረተሰቡ ፀጥታውን ለማገዝ አጋዥ እንዲሆን የፀጥታ ባለቤት የሆነው ደግሞ ከጄነራል አሳምነው ጀምሮ እስከ ታች መዋቅር ድረስ ተደራጅቶ መምራት እንዲችል እንደሌላው መስሪያ ቤት ሁሉ በተለመደው መልኩ ግምገማ መታቀዱን አቶ ላቀ ገልፀዋል። ‹‹ከዚህ ውጭ ጄነራል አሳምነው ከኃላፊነት የሚነሳበት ደብዳቤ አልተጻፈም። ‹ተነስተሀልም› አልተባለም። ይሁንና ችግሮች አሉ፤ ችግሮቹ እንዴት መስተካከል አለባቸው በሚል በየጊዜውና የደረጃው ይገመገማል። እነዚህ ግምገማዎችና ንግግሮች ይህን የመሰለ ችግር ይፈጥራሉ ብለን አላሰብንም፤›› ባይ ናቸው አቶ ላቀ።
ዝርዝር የወንጀል ድርጊቱን በሚመለከት በድርጊቱ የተሳተፉ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። በምን ሁኔታ ተነሳስተው እንደፈፀሙ በቀጣይ የሚገልፁት ይሆናል። ‹‹በእኔ እምነት ግን ጄነራሉን የሚያስኮርፍ ግምገማ አላደረግንም። ጄነራል አሳምነውም የክልሉ ህዝብ እንዲጠቀም፤ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባና ኢንዲጠበቅ በማለት ለእስር ተዳርጎ ቆይቷል። ስለሆነም የክልላችን ህዝብ ሰላም እንዲጠበቅ የእርሱም የእኛም ፍላጎት ነው።›› አቶ ላቀ ይናገራሉ።
ይህን እንዴት በማከናወን የድርሻቸውን እንደሚወጡ መገምገማቸውን አስታውሰዋል። በእነዚህ ግምገማዎች ምንም ልዩነት አልተፈጠረም። ከሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን ምንም ልዩነት ሳይፈጠር ተስማምተው ከግምገማ መውጣታቸውን አመልክተዋል።
‹‹ለዚህ ተግባር እንደርሳለን ብዬ የምገምተው ነገር የለም። ግምገማውን በሚመለከት ያልተለመደ ነገር አልመጣም፤ ይህ አሰራር ወደፊትም ይቀጥላል። ካልተገማገምን ደግሞ ለውጥ ማምጣት አንችልም። ይህ ባህል ከህዝቡም ይመጣል ወደ ህዝቡም ይሄዳል። ይህም የሚደረገው ለህዝብ ጥቅም እንጂ ተጠላልፈን እንድንወድቅ አልነበረም። ይህን ድርጊት ተደራጅተው የፈፀሙ ሰዎች ስለተያዙ እውነታው ወደፊት ይታወቃል።›› ሲሉ አቶ ላቀ በፍትህ ላይ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
‹‹እንደማንኛውም የልማት ሥራ ሕዝቡ ከስጋት ወጥቶ በነፃነት የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ መፍጠር የሚችልበትን ከየመድረኮች ማግስት ግምገማ እናደርጋለን። ይህ ግምገማ ተሳክቶልናል ፤አልተሳካልንም እያልን ሰኔ 12 ላይ የክልላችንን አጠቃላይ ሁኔታ በሚመለከት ተገማግመናል። በዚህ መድረክ የምናስተካክለውን ልናስተካክል፤ ተስማምተን ተለያየን። ስንወጣም ተገናኝተን ጄነራል አሳምነውን አናግሬዋለሁ። ‹ግምገማው የሚጠቅም ነው› አለኝ። ስለ ግምገማ ደግሞ ጄነራሉ በሚገባ ያውቃል። ስለዚህ በዚህ ምንም ቅር አይሰኝም፤›› ይላሉ አቶ መላኩ።
ከቦታ የመቀየር እና ከቦታ የማንሳት ጉዳይ በግምገማው አልተነሳም የሚሉት አቶ መላኩ ይህን የመሰለ አቋም አልነበረም ብለዋል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ‹‹ከአመራር ቦታ ላይ ያነሳኛል ብሎ ሰው መግደል ትክክል ነው ብዬ አላምንም። እነዚህ ሰዎች ስለሰብዓዊነት፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትህ ትግል አድርገዋል ብለን የምናምናቸው ሰዎች ናቸው። ይህ እስከሆነ ድረስ ማንኛውንም ጉዳይ በውይይት የመፍታት ልምድ መዳበር አለበት። በግጭትና የሰው ህይወት በማጥፋት ሊመጣ የሚችል ዴሞክራሲ ሊኖር አይችልም።››
የመረጃ ውዥንብር
በተከሰተው አደጋ ውዥንብር መንዛት ውስጥ የገቡት አመራሩን፤ ድርጅቱንና ህዝቡን ለመከፋፈል ነው። የከፋ ጥቃት ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ታስቦ ነው እየተሰራ ያለው። በአመራሩ መካከል ልዩነት እንዳለ ተደርጎ ይነሳል የሚሉት አቶ መላኩ በዚህ መካከል አንዱ ሌላውን የሚደግፍ ተደርጎ ይታሰባል። በዚህ ሁኔታ ህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ አግኝቶ የራሱን ልባዊ ውሳኔ ካልሰጠ በስተቀር አሉባልታዎችን እየተራገቡ ክልሉ ላይም ሆነ አገሪቱ ላይ የከፋ ችግር ሊመጣ ይችላል።
‹‹ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ። እንደሚባለው የነበርነውም የተረፍነውም እኛ ነን። ሰዉ ይህን ሀቅ ተረድቶና ከመንግሥት ጋር ቆሞ የተጋረጠብንን አደጋ በጋራ ብንመክት ነው ጥሩ የሚሆነው። አሉባልታዎች ግን ምንም መሰረት የላቸውም።›› ሲሉ አቶ መላኩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአዴፓ ጉዳት?
የርዕሰ መስተዳድሩ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ አብርሀም አለኸኝ አንድ ሊሰመርበት የሚገባ ነገር አለ ብለዋል። ‹‹ከጄነራል አሳምነው ጋር በአማራ ህዝብ ጥያቄ ላይ ምንም አይነት ልዩነት የለንም። የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ተለይተው ያደሩ ናቸው። ተለይተው ባደሩ ጥያቄዎች ላይ ምንም አይነት የሀሳብም የአቋምም ልዩነት የለንም። በተደጋጋሚ በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ተነጋግረናል ፤ተደጋጋሚ ሀሳቦች ተነስተዋል።››
ከሞላ ጎደል በዚህ ዓመት የተሰራው ሥራ የፀጥታ ጉዳይ ነው። የአማራን ህዝብ ከጥቃት እንከላከላለን በሚል በጋራ ወስነን ወደ ሥራ ገብተናል። በዚህም 65ቱም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አንዳችም ልዩነት የሌለን መሆኑ መታወቅ አለበት ሲሉ አቶ አብርሀም አፅንኦት ሰጥተዋል። አክለውም ይህ እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ የነበረ አቋም ነውም ብለዋል። በመሆኑም ‹‹ጄነራል አሳምነው የተለየ የያዘው አቋም አልነበረም፤ ሁላችንም ተመሳሳይ አቋም ይዘን በዚህ ዓመት የምንሰራበት ሁኔታ ላይ ነበርን። ይህንን ታሳቢ ማድረግ ይገባል፤›› ብለዋል።
‹‹አሁን ከገጠመን ችግር አኳያ አደጋው ትልቅ ጉዳት ነው። ሰባቱም የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ነበርን። ሟቾቹን እና አቶ ዩሐንስ ቧያለውን ጨምሮ ቁጭ ብለን ገና በአንዱ አጀንዳ ላይ እየተወያየን እያለ የተፈጠረ ክስተት ነው። እንግዲህ ይህ ክስተት የወለደው ውጤት አዴፓን በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳዋል። ይህ ቀላል ጉዳት አይደለም።›› ሲሉ አቶ አብርሀም ይናገራሉ።
ቅን ልቦናና ብሩህ አዕምሮ የነበራቸው በጣም ጠንካራ የአማራ ህዝብ ታጋዮችንና ለአማራ ህዝብ ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጡ ነበሩ ጓዶችን ነው ያጣነው። አንድን ካድሬ እዚህ ደረጃ ለማድረስ ምን ያህል ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቅ መገመት ከባድ ነው። ‹‹ለእኔ በተለይ ለአማራ ህዝብ ትልቅ ኪሳራ ነው። ጓድ አምባቸው፣ ጓድ ምግባሩ ከበደ፣ ጓድ እዘዝ ዋሴ ፣ ጄነራል አሳምነውም ቢሆን የአማራ ህዝብ ሀብቶችና ልጆች ናቸው። እነዚህ ልጆች ከሞላ ጎደል ትልቅ አቅሞቻችን ነበሩ። እነሱን ማጣት ለአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ትልቅ ጉዳት ነው። ይሁን እንጂ አዴፓ በህዝብ ንቅናቄ የተፈጠረ ፓርቲ በመሆኑ ትግሉ ይቀጥላል፤›› ሲሉ አቶ አብርሀም አስገንዝበዋል።
‹‹እኛና ሌሎች የድርጅቱ አመራሮችና አባላት በተመሳሳይም ከህብረተሰቡ እነዚህን የሚተካ፤ ባንተካቸውም የሚቀራረብ አባል በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እየገባ ድርጅቱን ወደ ፊት ማስቀጠሉ ግድ ይላል።›› ሲሉ የአቶ አብርሀምን ሀሳብ የሚያጠናክሩት አቶ ላቀ በመሆኑም የክልሉን ህዝብ በልማት ፣በሰላም በዴሞክራሲ ተጠቃሚ ማድረግ ግድ ነው ብለዋል። ‹‹ድርጊቱ መሆን የማይገባው እጅግ አሳፋሪና የትም የሌለ ነው። ትግሉ ግን አሁንም ይቀጥላል። በዚህ መካከል በተለያዩ አሉባልታዎች ብዙ ተብሏል ›› ባይ ናቸው።
በግምገማ ልዩነት እንዳለ፤ የህዝቡን ጥቅም የማናስቀድም ተደርጎ ይወራል። ይህ ሁሉ ውሸት ነው። ይህን ደግሞ ወደፊት ህዝቡ ይደርስበታል። እነኚህ አመራሮቻችን አናገኘቸውም የማይተካ አቅም ነበራቸው። ነገር ግን ስለማናገኛቸው ትግሉ ደክሞ ለጠላቶቻችን የተመቸ ክፍተት መፍጠር የለበትም። ስለሆነም ጠንክረን መታገል አለብን። የህዝብ ጥያቄ ከዳር እናደርሳለን የትም አንጥላቸውም፤ ሲሉ አቶ ላቀ ተናግረዋል።
የኃይል ቅንጅት
እንደ አቶ ላቀ ገለፃ ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የተሰራ የደህንነት ሥራ አለ። ለሁሉም በክልሉ ያሉ ዞኖች መረጃ ተሰጥቷል። ሁሉም መንገዶች እንዲዘጉ ተደረገ፤ በዚህ መሰረት ለፌዴራልም መረጃ ተሰጥቶ በዚህ መሰረትም ወንጀል ፈፅመው ሲንቀሳቀሱ የነበሩትም በዕለቱ አብዛኞቹ ተይዘዋል። ቀሪዎቹም በሂደት በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው። የክልል የፀጥታ ኃይል እና መከላከያ እስከ ወረዳ ድረስ ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ በመሆን ሥራው ይቀጥላል። በዚህም ውጤታማ ሆነናል ይላሉ አቶ ላቀ። ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት በየቦታው እንዲያዙ ተደርጎ መጨረሻም የመከላከያ ኃይል መምጣቱን ያስታውሳሉ። እነሱ ከመጡም በኋላ በመቀናጀት እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።
‹‹የምርመራ ቡድን አለ፤ ተጠርጣሪዎችን አድኖ የሚይዝ ቡድን አለ። ህብረተሰቡም ደግሞ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ጥበቃ የሚያደርግ ቡድን አለ። በዚህ መሰረት በጋራ በመሆን ፌዴራል አዲስ አበባ የነበሩ የአዴፓ አመራሮችም ከመከላከያ እና ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ሰፊ ሥራ እየተሰራ ነው።” በጋራና በቅንጅት እየሰራን እንገኛለን። ወንድሞቻችንን መመለስ አልቻልንም እንጂ ድርጊቱን የፈጸሙት አካላት ከእነ ትጥቃቸው በየቦታው በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው፤›› ብለዋል አቶ ላቀ።
ከምንም በላይ ደግሞ በየትኛውም አካባቢ ያለው የክልሉ ህዝብ ድርጊቱን አውግዟል። የሚጠረጥራቸውን ሰዎች በየቦታው እየያዘም አስረክቧል የሚሉት አቶ ላቀ በዚህ መሰረት የክልሉ የጸጥታ መዋቅር፤ የክልላችን ህዝብ፣ አመራሩና ከፌዴራል በኩልም ድጋፍ ያደረጉልን አካላት በክልላችን ህዝብና በመንግሥት ስም ሊመሰገኑ ይገባል።
አቶ መላኩ በበኩላቸው ይህ ችግር ባጋጠመበት ወቅት ለየት ያለ ሁኔታ አስተውለናል። ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው የፖሊስ፣ ሚሊሻና ልዩ ኃይል በከፍተኛ ሁኔታ የግዳጅ አፈጻጸም ነበራቸው። በፌዴራል በኩል የፌዴራል ፖሊስና መከላከያ ያደረጉት ድጋፍም በጣም ከፍተኛ ነው። በእያንዳንዱ ቀበሌ እና በእያንዳንዱ ወረዳና ዞን ህብረተሰቡን ከአደጋ በመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል። ይህ ለወደፊቱም ቢሆን ክልሉ የራሱን ሰላም በራሱ የሚያስከብርበትና የሚያጠናክርበት ሁኔታ መኖር አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
‹‹በፌዴራል ላይ ጥገኛ ሆነን በተቸገርን ቁጥር ኃይል እየጋበዝን ክልሉን ማረጋጋትና ማስቀጠል አንችልም። ሰሞኑን የታየው ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በክልሉ ውስጥ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ተቀናጅቶ መስራት ይጠይቃል ማለት ነው። ትንንሽ ልዩነቶች እንኳ ቢኖሩ የተጋረጠብንን አደጋ መወጣት አለብን። በተለይ ሁሉንም የፀጥታ መዋቅራችንን ያለመከፋፈል መጠቀም ይኖርብናል።›› ሲሉ አቶ መላኩ ጥሪ አቅርበዋል።
ከመንግሥትና ከህዝብ…
አቶ አብርሀም አለኸኝ እንደሚሉት መንግሥት ለህዝቡ ግልጽና ተጨባጭ የሆነ እውነቶችን በየሰዓቱ ማሳወቅ አለበት። ህዝቡ በአሁኑ ወቅት ከመንግሥት የሚጠብቀው እውነተኛ መረጃን ነው። ‹‹መረጃው በትክክለኛ ሰዓት ምን መሰራት እንዳለበት፤ ምን እንዳጋጠመን፤ እንዴት ችግሩን እንደምንወጣና መፍትሄውን በመንግሥት አፍ እና መድረክ ለህዝብ ማድረስን ይፈልጋል። ይህን ሥራ በመስራት በኩል የተለያዩ መረጃዎች ተሰጥተዋል። አሁንም በተከታታይ የሚሰጡ መረጃዎች አሉ። ትልቁ ነገር ግን የአማራ ህዝቦች ከመንግሥት የሚያገኙትን መረጃዎች በጥንቃቄ መሬት ማስነካት ይጠበቅባቸዋል›› ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት መንግሥት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አካላት መረጃን ማሰራጨታቸው አይቀርም። ስለዚህ አማራጭ የመረጃ ምንጮችን ከመከተል ይልቅ ባለቤቱን መስማትና በክፉ ጊዜ ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ መስራት ይጠቅማል። ያለንበት ጊዜ ክፉ በመሆኑ የአማራን ህዝብ ለጥቃት የሚያጋልጡ ሁኔታዎች አሉ የሚሉት አቶ አብርሀም ከውስጥም ከውጭም የተለያዩ የጠላት አሰላለፎች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ህዝብ ተረጋግቶ እንዳይሰራ፣ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖረውና በተፈፀሙት ተግባራት ሁሉ መንግሥትን እንዲጠራጠር ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ ነው ያለው። ይህን ጊዜ በጥንቃቄ ለማለፍ የመረጃ ግንኙነት አግባብ በመተማመን ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል። በተለይ ከአዴፓ እና እሱ ከሚመራው መንግሥት አኳያ የአማራን ህዝብ ልናገለግል የተቀመጥን በመሆኑ በዚህ በከፋ ሰዓት የምንሰራው እያንዳንዷ ነገር ለአማራ ህዝብ አጠቃላይ ጥቅም መሆኑን መረዳት ይገባል ሲሉ ለህዝቡ ጥሪ አቅርበዋል። በመጨረሻም በክልሉ በተከታታይ የሚሰጡ መረጃዎች ይኖራሉ ሲሉም ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2011
ሀብታሙ ስጦታው