ለዘላቂ የሌማት ቱሩፋት ምርታማነት- አስተማማኝ የገበያ አቅርቦት

ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉን ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ፤ በተለይ ደግሞ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ያለችውን የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በመተግበሯ በዘላቂነት ሊለውጡ የሚችሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ ጀምራለች:: መርሃ ግብሩ በሀገር ደረጃ ማዕዶችን በብዛትና በዓይነት ሙሉ ከማድረግ ባሻገር ለሌሎች መትረፍን ያለመ ሲሆን፤ ለዚህም እምቅ ሀብቶችን የማልማትና የመጠቀም አቅጣጫን ተከትሏል:: በዋናነትም የምግብ ዋስትና ችግርን ለመፍታት እና የሥነ ምግብ ሚዛን መዛባትን ለማስተካከል ፍቱን መፍትሔ እየሆነ መምጣቱንም የዘርፉ ተዋናዮች ይናገራሉ::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ የሌማት ትሩፋትን ባስጀመሩበት በወቅት፤ ‹‹ሌማት አርሶአደሩን አርብቶ አደሩንና ሸማቹን የሚያገናኝ ድልድይ ነው:: በቂ እና አመርቂ ምግብ ማግኘትን ያለመ ነው:: በቂ የመጠን፣ አመርቂ የይዘት ጉዳይ ነው፤ በምግብ ራስን መቻል ከሀገር ሉዓላዊነት ክብር ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው›› ሲሉ ስለመርሀ ግብሩ ፋይዳ መናገራቸውም ይታወቃል::

በመርሀ ግብሩ ገና ከአሁኑ ለውጦች እየተመዘገቡ ስለመሆናቸው ከየክልሉ የወጡ መረጃዎችን ዋቢ ያደረጉ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ያመለክታሉ:: የመንግሥት ሃላፊዎችም፣ የግብርና ባለሙያዎች ይህንኑ እያረጋገጡ ይገኛሉ::

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና እና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንዳሉትም፤ የሌማት ቱሩፋት በክልል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በሀገር ደረጃ ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጣ ነው:: መርሃ ግብሩ እንደሀገር ከፍተኛ እጥረት የነበረባቸው የወተት ፣ ስጋ፣ እንቁላል፣ ማር፣ ዓሳ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ መሠረታዊ የሚባል ውጤት እያስገኘ ነው::

እንደሀገር በመርሀ ግብሩ የአርሶአደሩ የማምረት ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ይጠቅሳሉ:: የአርሶ አደሩን ያመራረት ባህል ከመቀየር አኳያም ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ሲሉ ይገልጻሉ፤ ‹‹በልማት ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን፣ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ባለሀብቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ሳይቀሩ መነቃቃት ተፈጥሮባቸው ልማቱን መቀላቀላቸውንም አመልክተዋል::

የማዕከላዊ ኢትዮጵያን ክልል ተሞክሮ ጠቅሰውም ሲያብራሩ፤ ‹‹አርሶአደሩ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ የክልሉ ነዋሪ በጓሮው አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት፣ ዶሮና የተሻሻለ ዝርያ ባላቸው የወተት ላሞች በወተት ልማት እንዲሁም በንብ ማነብና በዓሳ እርባታ ላይ እንዲሰማሩ ተደርጓል፤ ይህም የቤተሰቡን የተመጣጠነ ምግብ ፍላጎት ከማሻሻሉም ባሻገር በእነዚህ ምርቶች ላይ የነበረውን የዋጋ ንረት ከማርገብ አኳያ የላቀ ሚና እየተጫወተ ነው፤ ሌማታችን በዓይነትም በብዛትም እየተትረፈረፈ ነው ያለው፤ በዚህ መነሻ ተርቦ የነበረው ገበያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በምርት ተጥለቅልቋል›› ሱሉም ይጠቅሳሉ::

ከወራት በፊት ከ180 ብር በላይ የነበረው የቀይ ሽንኩት ዋጋ አሁን ላይ ወደ 40 ብር፣ ቲማቲም ከ100 ብር ወደ 20 ብር ወርደዋል:: በሌሎችም የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የዶሮና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች ላይ የዋጋም የመጠንም መሻሻል ታይቷሉ ሲሉ ጠቅሰው፣ የዚህ ሁሉ ስኬት መርሃ ግብሩ መሆኑን ገልጸዋል:: ይህም የአርሶአደሩ የአመራረት ባህሉ መቀየሩን እንደሚያሳይ ተናግረዋል፤ ‹‹አትክልት በማይመረትባቸው አካባቢዎች ልማቱ መጀመሩ ሥነ-ምህዳሩ ሳይቀር እንዲቀየር ምክንያት ሆኗል:: የሌማት ቱሩፋት እንደአጠቃላይ ተስፋም እድልም ይዞ መጥቷል›› ሲሉ ይገልፃሉ::

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኢኮኖሚክስ ዳይሬክተር ዶክተር ታደለ ማሞ እንደሚሉት፤ የሌማት ቱሩፉት መሠረታዊ የሚባሉ አስተዋጽኦዎችን አበርክቷል:: በዋናነትም የእንቁላልና የወተት ምርት በከፍተኛ መጠን ጨምሯል:: በዚህም በእነዚህ ምርቶች ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋትም ተችሏል::

አምራቹም አዲስና ተጨማሪ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚያመርትበትን ሥርዓት እንዲከተል አድርጎታል:: ይህም አምራቹ ብዙ በማምረት ብዙ ገቢ እንዲያገኝ ከማድረጉም ባሻገር ሁሉም የተመጣጠነ ምግብ ተጠቃሚ እንዲሆን የመርሃ-ግብሩ መጀመር ወሳኝ ሚና ተጫውታል::

አቅርቦት ሲጨምር የሥነ-ምግብ ዋስትናም በዚያው ልክ እንደሚጨምር የሚያስረዱት ዶክተር ታደለ፤ ‹‹የሌማት ቱሩፋት ሥራዎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን የሥነ-ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥንም ጭምር የሚያመጡ ናቸው›› በማለት ይናገራሉ:: መርሃ-ግብሩን የተገበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለገበያ ብቻ ሳይሆን ለራሳቸውም ጭምር ምርቱን እንዲጠቀሙ ፣ አጠቃላይ የምግብ ሥርዓታቸውንም እንዲያስተካክሉ ማድረጉን ያስረዳሉ:: ምርት በብዛት እንደሚገባ ጠቅሰው፣ ሸማቹም ጥራት ያለውን ምርት መርጦ እንዲሸምት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ይላሉ::

ዶክተር ታደለ እንደሚሉት፤ ቀደም ሲል አርሶአአደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነቱን የማሳደግ ባህላቸው ኋላቀር ነው:: በተለይ በእንስሳት እርባታ ረገድ የተሻሻሉ ዝርያዎች ማቅረብ ባለመቻሉ አምራቹ ምርታማነቱ ከእጅ ወደ አፍ በሚባል ደረጃ ነበር:: አምራቹ ለገበያ የሚያቀርበው ቀርቶ፣ ለራሱም የሚጎርሰው አጥቶ ርዳታ ጠባቂ ሆኖ ቆይቷል::

ዶክተር ታደለ ከሌማት ቱሩፋቱ ጋር ተያይዞ ምእራብ ሸዋ አድአ በርጋ ላይ በተቋቋመው ማእከል የተሻሻሉ እንስሳት ዝርያዎች እጥረት እየተፈታ ነው ይላሉ:: የግብዓት እጥረቶችንም መርሃ ግብሩ መቅረፍ መጀመሩ ምርታማነት ላይ በጎ ተፅዕኖ አምጥቷል፤ ለሸማቹ የሚደረገው የምርት አቅርቦትም በእጅጉ ጨምሯል ሲሉ ያብራራሉ::

አርሶአደሩ ምርታማ ቢሆንም፣ ምርቱን ለገበያ የሚያቀርብበት ሥርዓት ካለመዘመኑ ጋር ተያይዞ የሚገባውን ያህል ተጠቃሚ መሆን አልቻለም፤ በተለይ የከተማው ሸማች የሚፈልገውን ምርት በመጠንም ሆነ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ሲቸገር ይስተዋላል::

በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች አምራችና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኝ ድልድይ ባለመኖሩ የግብርና ምርቶች ፍላጎትና አቅርቦት እንዲሁም ሰፊ የመረጃ ክፍተት እንደሚታይበት ይነገራል:: ይልቁንም የገበያ ሰንሰለቱ ረጅምና ውስብሰብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚጠቀመው ደላላ እንደሆነም ይጠቀሳል::

ከዚህ ጋር ተያይዞ አርሶአደሩ በየአካባቢው የምርት አይነትና መጠን ፍላጎት ልክ አለማምረቱ በሚገባ ተጠቃሚ እንዳይሆን አድርጎታል:: አሁን ባለው የገበያ ሥርዓት ዘመኑን የማይዋጅ አሠራር መንሰራፋቱ ተወዳዳሪነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረም ይገለጻል::

ምቹ የመሠረተ ልማት ባለመኖሩ ምርቱ ተጠቃሚው ዘንድ ሳይደርስ ለብልሽት የሚዳረግበት፤ በተለይ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የወተት ምርቶች ማቀዝቀዣ ባላቸው ተሽከርካሪዎች የማይጓጓዙበት ሁኔታ መኖሩን ዶክተር ታደለ ያመለክታሉ:: ይህ ደግሞ አርሶ አደሩንም ሆነ ተጠቃሚዎችን እንደሚጎዳና መርሃ ግብሩ ይዞ ከተነሳው ሃሳብ ጋርም እንደሚጣረስ ይጠቁማሉ፤ በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልጻሉ::

የአሁኑ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ቢሮ ሃላፊና የቀድሞው የህብረት ሥራ ኤጀንሲ /የአሁኑ ኮሚሽን/ ዋና ዳይሬክተርም የነበሩት አቶ ኡስማን የሌማት ትሩፋት ድምር ውጤትን ተከትሎ አዳዲስ ፍላጎቶች መፈጠራቸውን ይጠቅሳሉ፤ ምርት በስፋት መመረቱን ተከትሎ የገበያ ትስስሩም በዛው ልክ መስፋት ያለበት መሆኑ በሁሉም ልማቱ በተተገበረባቸው አካባቢዎች ያሉ አምራቾች ፍላጎት እንደሆነ ይጠቅሳሉ:: በዚህ ረገድ መንግሥት የገበያ ትስስር ለመፍጠርም ሆነ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፤ ፍላጎቱ ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሚፈለገው ደረጃና ጊዜ ምላሽ ለመስጠት አዳጋች ነው ብለዋል::

‹‹አሁን እየመጣ ያለው ልማት ሰፊና አስተማማኝ ገበያ ይፈልጋል›› የሚሉት አቶ ኡስማን፤ ምርቱ አስተማማኝ ገበያ ካላገኘ አጠቃላይ ልማቱን ሊያንገራግጨው ይችላል የሚል ስጋትም አላቸው:: በዋናነትም በዶሮና እንቁላል ገበያ ላይ የሚስተዋለው ችግር አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሻም ያስገነዝባሉ:: ‹‹የዶሮ መኖ በጣም ውድ በሆነበት ሁኔታ በርካታ አምራቾች ካመረቱ በኋላ አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው ገበያ ልንፈጥርላቸው ካልቻልን የሚመጣው ኪሳራ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ሲሉም ጠቅሰው፣ ጉዳቱ አምራቹ ላይ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ጭምር ሊሆን እንደሚችል ያብራራሉ::

ዶክተር ታደለ፤ አግሮ ኢንዱስትሪዎች ያለመስፋፋታቸው፤ ያሉትም ቢሆኑ በሙሉ አቅማቸው እየሠሩ አለመሆናቸው የአርሶአደሩን ምርት በሚገባው ልክ እየተረከቡ አይደለም የሚል እምነት አላቸው:: ይህም በተለይ በጥሬ ወተት ፍላጎት ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል ይላሉ:: በበየነ-መረብ የሚደረግ የገበያ ልውውጥ ያለመኖሩ አምራቹ ምርቱን የሚያስተዋውቅበት መንገድ እንደሌለም ተናግረዋል::

በዚህ ረገድ መሠራት ባለበት ላይም ዶክተር ታደለ ሲያብራሩ የመጀመሪያው ሥራ ሊሆን የሚገባው አርሶአደሩን በማህበር ማደራጀት መሆኑን ገልጸዋል:: ይህም አርሶ አደሮቹ ምርቶቻቸውን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት ለትራንስፖርት ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ምርቱም በተቀናጀና በተሳለጠ መንገድ እንዲሸጡ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል፤ ይህም ወጪና ድካምን ይቀንሳል፤ የግብይት ቅልጥፍናን ይጨምራል›› ሲሉም ያብራራሉ:: የምርት ብልሽት መጠን እንደሚቀንስም ያስረዳሉ::

እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለመፍጠርም በግብርና ውጤቶቹ ላይ የእሴት ሰንሰለት መጨመር ያስፈልጋል:: በተለይ እንደ ወተት ያሉ ቶሎ የሚበላሹ ምርቶችን ወደ ቂቤና አይብ በመቀየር የቆይታ ጊዜያቸውን መጨመር ይቻላል:: ይህ መሆን ያለበትም ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች ነው:: ለዚህም ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በመተሳሳር ቴክኖሎጂዎቹ በስፋት ለአርሶአደሩ የሚደርሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል::

ዶክተር ታደለ በአምራቹና በሸማች ማኅበራቱ መካከል የኮንትራት ውል ማሰር ያስፈልጋል ባይም ናቸው:: በዚህም ሁሉንም የሚጠቅም ሥርዓት መፍጠር ይቻላል:: አርሶ አደሩ ከዘመኑ ጋር በመራመድ የላቀ ተጠቃሚ እንዲሆን ገበያ ትስስር የመረጃ መረብ ተዘርግቶለት እንዲጠቀምበት ማድረግ ያስፈልጋል:: ይህም የግብይት ወጪን በመቀነስ ሁለቱንም ወገኖች ትርፋማ ያደርጋቸዋል::

ለአምራቾቹ በከተሞች የሰንበት ገበያን የመሰለ ቦታ በመስጠት በሳምንት አንዴና ሁለት ጊዜ ምርታቸውን የሚሸጡበትን፤ ተጠቃሚውም በእቅድ ባነሰ ዋጋ የሚገዛበትን ሁኔታ መፈጠር ይገባል ይላሉ::

እንደ አቶ ኡስማን ማብራሪያ፤ ገበያው ለአምራቹ የሚገባውን ያህል መክፈል ካልቻለ አጠቃላይ ልማቱ ይዳከማል፤ ወደኋላ ይመለሳል:: በመሆኑም ዘላቂ የገበያ ትስስር ሥርዓት መፍጠር የዘላቂ ገበያ መነሻ ደግሞ ዘላቂ የምርት አቅርቦት ነው:: ዘላቂ ገበያ የሌለው ዘላቂ ምርት ሊያመርት አይችልም:: አምራቹ አስተማማኝ ገበያ ካላገኘና የማምረቻ ወጪውን መሸፈን የሚያስችል ተመጣጣኝ ገቢ ካላገኘ ውጤታማ ሊሆን አይችልም::

ዘላቂ ገበያ ለመፍጠር የገበያ አማራጮችን ማስፋት ያስፈልጋል:: አምራቹ ከሸማች ሊገናኝ የሚችልባቸውን የምርት ማዕካላትንና ተቋማትን መገንባትም ይጠበቃል:: በዋናነትም የሸማች ማህበራት ማጠናከር አለባቸው::

ከዚህ ጋር በተያያዘም በሩቅ ምስራቅ ሀገራትና የአውሮፓ ሀገሮች አምራቹ በቀጥታ ምርቱን የሚያስረክባቸው የሸማች ማህበራት ጠንካራ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህ ሀገሮች በዚህ የየሀገራቸውን ሕዝቦች ፍላጎት ከማሟላት አልፈው ወደ ኢንዱስትሪ ያደጉበት፤ እሴት ጨምረው ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ምንጭ የሆኑበትን ስኬትም ጠቅሰዋል::

‹‹የእኛ ሀገር የገበያ ሥርዓቱ ጤንነት የጎደለው ነው›› የሚሉት አቶ ኡስማን፤ ‹‹አምራች፤ ሸማችም ሆነ አቀነባባሪ ለገበያው በጣም ወሳኝ አካላት ናቸው:: በሶስቱ አካላት መካከል ጤናማና ፍትሓዊ የሆነ ግኑኝነት ያስፈልጋል፤ በአንዱ ድጋፍ ሌላኛው አካል ብቻ የሚጠበቀምበት ሳይሆን አንዱ ለሌላው መኖር ዋስትና መሆኑን ማመን አለበት›› ይላሉ:: እሳቸው እንዳሉት፤ እነዚህ አካላት በመተማመን በመተሳሰብ በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል:: በተለይ አርሶአደሩ በብዙ ልፋት ባመረተው ምርት እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሚዛናዊ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል::

‹‹የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ምርታማነቱ ቢጨምረም፣ ከሚፈለገው አንፃር አሁንም ብዙ መሥራት ያስፈልጋል›› የሚሉት ዶክተር ታደለ፣ ምርቱን በሚገባ ወደ ተጠቃሚው ማድረስ ላይ ክፍተት እንዳለ ይገልጻሉ:: አሁን ምርቱ ተትረፍርፎ ያን ያህል ለገበያ ውድቀት ይዳርጋል የሚል ስጋት ባይኖራቸውም ቅልጥፍና የሚጎለው የገበያ ሰንሰለት በዚሁ ከቀጠለ አምራቹ ተጠቃሚ እንደማይሆን፣ አልፎም ተርፎ ተስፋ እንደሚቆርጥ፤ ማምረቱን እንደሚቀንስ ፤ ከገበያ ውጭም የሚሆንበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል፣ መርሃ ግብሩም የታሰበውን ላያሳካ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል::

በዶክተር ታደለ ሃሳብ የሚስማሙት አቶ ኡስማን፤ እንደሸማቹ ሁሉ አርሶአደሩም ተደራጅቶ ጥቅሙን የሚያስከብርበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ይላሉ:: በማህበር ሆኖ ያመረተውን በቀላሉና በአንድ ቦታ በመሰብሰብ ፤ በተደራጀ መንገድ ገበያና ኢንዱስትሪ ይልካል፤ ይህ ሲሆን የገበያ ሥርዓቱ ይታከማል ብለዋል::

ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን በተለይ የእንቁላልና ወተት ምርት ቀጣይነት ስጋት ውስጥ ይወድቃል:: ከውጭ የሚመጡ የግብርና ውጤቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የተያዘውን ትልምም ለማሳካት አዳጋች ይሆናል ይላሉ:: አሁን የሚታየውን ምርታማነት ማዝለቅ ካስፈለገ የገበያውን አስተማማኝነት ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል::

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You