ኢትዮጵያ ሺህ ዓመታትን የተሻገረ ሀገረ መንግሥት የገነባች ሀገር ነች። ይሁን እንጂ የሀገረ መንግሥት ግንባታው የተጠናቀቀና ምሉእ አይደለም። በየዘመናቱ በትውልድ አለመግባባት፣ በተሳሳተ ትርክትና በመሳሰሉት እንቅፋቶች ጠንካራ መሠረት የመጣል ሂደቱን የሚያስተጓጉሉ ችግሮችንም እየተጋፈጠች እና መፍትሄዎችን እያስቀመጠች ነው ሉዓላዊት ሀገርነቷን አስጠብቃ እዚህ መድረስ የቻለችው። ዛሬስ?
ዛሬም የኢትዮጵያውያንን አንድነት የሚፈታተኑ፣ የሀገረ መንግሥቱን ጥንካሬ ለመናድ የሚግደረደሩ፣ የማህበረሰቡን አብሮ የመኖር እሴት የሚያዳክሙ አያሌ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች ትገኛለች። እነዚህ ችግሮች ባለፉት ዓመታት የሀገሪቱን ህልውና የተፈታተኑ ፣ የሕዝቦችን እምነት የሸረሸሩ፣ ጥርጣሬና አለመግባባት ያነገሡ ነበሩ። ችግሮቹ ግን ከኢትዮጵያውያን አንድነት፣ መተባበር፣ ጥንካሬና ፈተናዎችን በብልሀትና በጥበብ በጋራ ከማለፍ ባህል በላይ አይደሉም።
ለዚህ ነው ባለፉት 6 እና ከዚያ በላይ በነበሩ ዓመታት ኢትዮጵያውያን ባጋጠማቸው የውስጥ ችግርና ፈተና ሳይሰበሩ በሁለት እግራቸው መቆም የቻሉት። ከዚያም በላይ ለዘመናት የቆዩ የተዛቡ ትርክቶችን፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን እና ሌሎች የፍትሃዊነት እና በእኩልነት በጋራ የመኖር ቁልፍ ጥያቄዎች ላይ የማያዳግም መፍትሄ ለመስጠት በጋራ ለመምከር የወሰኑት።
ኢትዮጵያውያን ጎራ ለይተው ከሶስትና አራት ዓመታት በፊት ገብተውበት በነበረው የለየለት ግጭትና ቀውስ ያተረፉት፤ ውዱን የሰው ልጅ ሕይወት ማጣት፣ የንብረት ውድመትና የተዳከመ ኢኮኖሚ ውስጥ መዘፈቅ ነው። ለዚያም ነው ሰከን ወዳለው፣ በውይይትና በምክክር መፍትሄን ማምጣት ወደሚቻልበት የጠረጴዛ ዙሪያ ለመምጣት መንገዱን የጀመሩት። ለዚያም ነው በግጭትና ጦርነት ሳይሆን በምክክርና በውይይት የሚገነባ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት እንደሚያስፈልግ አምነው የሃሳብ ልዩነቶቻቸውን ለማስታረቅ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ያቋቋሙት።
ዛሬም ሁሉም ኢትዮጵያውያን (የፖለቲካ ሃይሉ፣ ባለሀብቱ፣ የግልና የመንግሥት ተቋማት፣ ግለሰብ ተፅእኖ ፈጣሪዎች፣ ወጣቶች ሴቶችና ወዘተ) በግጭት፣ በጉልበት አሊያም በውጭ ጣልቃ ገብነት የሚያገኙት ዘላቂ መፍትሄ እንደሌለ ሊገነዘቡ ይገባል። ይህንን እውነታ የተረዱ ብዙሃን ቢኖሩም ጥቂት የማይባሉ ሃይሎች ግን አሁንም ድረስ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለሚደረገው ውይይት ዝግጁ አይመስሉም። ይህንን ችግር መፍታት እና ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግ ወደ ምክክሩ የሚካተቱበት መንገድ ሊፈለግ ይገባል።
በተለይ እነዚህ ሃይሎች የሚያነሷቸውን ቅስመ ሁኔታዎች በማጤን፣ ፍላጎቶቻቸውንና ጥያቄዎቻቸውን ቀረብ ብሎ ለመገንዘብ በመሞከር ሁሉንም ሃይል የሚያካትት ምክክር ለማድረግ ወደ መፍትሄው መቅረብ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ሆደ ሰፊነትና ታጋሽነት መርህ ሊሆን ይገባል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን የሚመሩት አካላት ላለፉት ዓመታት ተከታታይ ሥራዎችን ሲያከናውኑ እንደነበር ተመልክተናል። ተሳታፊ ሃይሎችን በመለየት፣ አጀንዳዎችን በማሰባሰብ፣ ምክክር የሚመራበትን ሕግ፣ ፖሊሰ ከሚያወጡ አካላት ጋር በጋራ በመሥራት ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውን በተከታታይ በሚወጡ የመገናኛ ብዙሃን መረጃዎች ላይ መረዳት ችለናል።
በተቃራኒው ደግሞ የምክክር ኮሚሽኑ የሚሠራቸውን ሥራዎች፣ ተግባርና ሃላፊነት በቅጡ ያልተረዱ (አሊያም ከግንዛቤ እጥረት ብዥታ ውስጥ የገቡ) አካላት ሂደቱን ሲተቹ፣ አንዳንዴም እንቅፋት ሲሆኑ ይስተዋላል። ይህንን ድርጊት በተመሳሳይ ብብልሃት እንዲሁም በሆደ ሰፊነት መመልከትና ዓላማውን ለሕዝብ በግልፅ በተከታታይ ማስገንዘብ ይገባል።
ኢትዮጵያውያን በጋራ ችግሮቻቸውን መፍታት እንዲችሉ፣ ዘላቂ የሆነች ሉዓላዊት ኢትዮጵያን (ሀገረ መንግሥት) እንዲገነቡ በራሳቸው እሴቶች፣ የመከባበርና የመደማማጥ ባህል እንዲሁም በውስጥ አቅም መወያየትና መፍትሄዎችን ማስቀመጥ እንደሚኖርባቸው ኮሚሽኑ የማሳመን ሥራዎችን ሊሠራ ይገባል። ከዚያም ባለፈ ሁሉም አካላት የሚሳተፉበት እንደሆነ በግልፅ የሚያሳዩ አደረጃጀቶች መፈጠራቸውን ማሳየት ያስፈልጋል።
ባለፉት ዓመታት ኮሚሽኑ መቋቋሙንና ወደ ሥራ መግባቱን ተከትሎ ብዥታን የሚፈጥሩ የተለያዩ መረጃዎች ሲወጡ ተመልክተናል። ለውጤታማነቱ እንቅፋት የሚሆኑ እነዚህን ጉዳዮች ሁሉም ተሳታፊ አካላትና ኮሚሽኑ ያለመታከት ማጥራትና ግንዛቤ መፍጠር ይኖርባቸዋል።
በምክክሩ ላይ ጥርጣሬን የሚያጭር መረጃዎች ከሚወጡባቸው ጉዳዮች መካከል ሁለት ጉዳዮች ዋና ዋና መሆናቸውን የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ ያምናል። የመጀመሪያው አካታችነት (all inclusive) የሚለው ጉዳይ ሲሆን በዚህ ረገድ ኮሚሽኑ በምክክር ላይ የሚሳተፉ ሕዝባዊ መሠረት ያላቸው ማናቸውም ተቋማት፣ ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ አደረጃጀቶች፣ ምሁራን እና የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳታፊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። መፍትሄ ይሻሉ ብለው የሚያነሷቸው አጀንዳዎች፣ የማህበረሰቡ ጥያቄዎችም መካተታቸው ማረጋገጥ እንዲሁ ተገቢ ነው።
ከሰሞኑ ከሰማናቸው ጉዳዮች መካከል ጠንካራ ሕዝባዊ መሠረት እያላቸው፤ ለሀገረ መንግሥት ግንባታና ለኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ ሌሎች እሴቶች ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ሃቅ ሆኖ ሳለ በዚህ ሀገራዊ ምክክር ላይ ተሳታፊ ለመሆን ጥሪ እንዳልተደረገላቸው በይፋ ግልፅ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው የገለፁ አካላት እንዳሉ ነው። ለዚህ ምክንያታዊ ለሆነ ጥያቄ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ፈጣን ምላሽ እንደሚኖረው ቢታመንም ቅሬታው ሳይፈጠር በፊት መፍታት አለመቻሉ የፈጠረ ብዥታ ያደረሰውን ጉዳት አለመቀነስ መቻሉ እንደ ክፍተት ሆኖ ሊወሰድ ይገባል።
ምክንያቱም እራሱ ኮሚሽኑ እንደነገረን ‹‹አካታችነት እና ወካይነት›› መሠረታዊው መርሁ ነው። ኮሚሽኑ በጀመረው የምክክር ምዕራፍ በበርካታ ቡድኖች፣ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ተቋማት እና ግለሰቦች የሚቀነቀኑ የተለያዩ ሃሳቦችን በተገቢው መንገድ በማካተት ለሂደቱ ስኬት እየሠራ እንደሚገኝም ገልፆልናል፡፡ በሂደቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአግባቡ ወኪሎቻቸውን በመላክ በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ላይ እንዲንፀባረቅላቸው የሚፈልጓቸውን ሃሳቦች የማቅረብ መብታቸው የተጠበቀ መሆኑ በተደጋጋሚ ቃል በቃል ሲገልፅ ሰምተናል።
በመሆኑም የኮሚሽኑ መርህ ይህ ሆኖ ሳለ ለምን ከላይ በስም ያልጠቀስናቸው አካላት እንዳልተካተቱ አሊያም በሂደቱ ላይ ቅሬታ እንዴት ሊፈጠርባቸው እንደቻለ አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ ያስፈልጋል። ከዚያ ባሻገር እነዚህን ብዥታዎች በተገቢው መንገድ በማጥራት ይገባል።
ሌላውና ሁለተኛው ጉዳይ በምክክሩ ላይ የሚሳተፉ የተለያየ የሃይል ሚዛን ያላቸው አካላት በሂደቱ ላይ የሚፈጠርባቸው የእምነት ማጣትና የጥርጣሬ ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው በዚህ ምክክር ላይ የማይሳተፉ ጠብ መንጃን እንደ አማራጭ የቆጠሩ ሃይሎች አሉ። ከዚህ ባሻገር በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ በተመሳሳይ በዚህ መድረክ ላይ ለመሳተፍ ፍቃደኝነት የጎደላቸው አይጠፉም። እነዚህ አካላት በምክክሩ ላይ ለመሳተፍ የማይፈልጉበትን ምክንያት ሲጠቅሱ ከሚያነሷቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ መንግሥት በቁርጠኝነትና በፍፁም ቅንነት ምክክር ለማድረግ አይፈልግም የሚል ነው። በምክክሩ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ወደፊት ቀርበውም ይህንን መሰል ጥያቄ የሚያነሱ አሊያም እምነት ማጣትና ጥርጣሬ የፈተናቸው ባለድርሻዎች በርካቶች ናቸው።
ኢትዮጵያውያን መክረው አንድ ጠንካራና ሉዓላዊ የሆነች ኢትዮጵያን መገንባት እንዲችሉ ለትውልድ እንዲያስተላልፉ እርስ በእርስ መተማመንና ጥርጣሬን ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ በገለልተኛ ምሁራን እና ባለድርሻ አካላት የተቋቋመው ምክክር ኮሚሽን ሃላፊነት ሊወስድ ይገባል። ምንም እንኳን እየሠራ ያለው ሥራ ከእንከን የፀዳ ነው የሚል ግብታዊ ድምዳሜ ሁሉም ሊደርስ ባይችልም ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ግለሰብ ተፅእኖ ፈጣሪዎች እና ሌሎችን በተቋሙ ላይ የጋራ እምነት እንዲኖራቸው ተከታታይነት ያለው ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል።
ኮሚሽኑ ይህንን መሰል ጥርጣሬዎችን ለመቅረፍ ከዋና ዋና መርሆቹ መካከል ‹‹የባለድርሻ አካላትን ሃይል ማመጣጠን›› አንዱና ዋነኛ ግቡ እንደሆነ ደጋግሞ ነግሮናል። በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የተለያየ የሃይል ሚዛን ያላቸውን ባለድርሻ አካላት እያሳተፈ እንደሚገኝ ግልፆ፤ ይህንኑ መነሻ በማድረግ የተለያየ የሃይል ሚዛን ያላቸውን አካላት በእኩልነት እንደ ባለድርሻ አካል በመቁጠር ሂደቱን እየመራና እያስተባበረ እንደሚገኝ በመገናኛ ብዙሃን አድምጠናል። ይህንን ርምጃውን ለተሳታፊ አካላት በተደጋጋሚ ማስረዳት ሥራዎችንም በግልፅነት ማከናወን ይኖርበታል። ይህንን ማድረግ ሲቻል ከላይ እንደተቀመጠው ጥርጣሬንና እምነት ማጣትን የሚፈጥሩ ድርጊቶችን ቦታ እንዳይኖራቸው በተለያዩ አውታሮች የምንሰማቸው አሉባልታዎችም እንዲከስሙ ይሆናል።
ከላይ በዝርዝር ለማንሳት እንደሞከርነው ኢትዮጵያውያን ካለፉት ዘመናት ታሪኮቻቸው መረዳት እንደሚችሉት ተቀራርቦ በመነጋገር እንጂ በግጭት ሀገር ማፍረስ እንጂ መገንባት እንደማይቻል ነው። በቅን ልቦና ምክክር ለማድረግ፣ ልዩነት የፈጠሩ ትርክቶችን ለማረቅ እና ያዘነበለውን ለማቃናት መመካከር ምርጫ የሌለው መፍትሄ ነው። ለዚህ ነው እዚህም እዚያም የሚገኙ ፅንፎች በመካከላቸው የሚገኘውን ሰፊ ክፍተት ለማጥበብ ወደ ጠረጴዛው ዙሪያ መምጣት የሚጠበቅባቸው። ለዚህ ዓላማ ስኬት ደግሞ ስክነት እና ሆደ ሰፊነት መርሆች ናቸው። ኮሚሽኑ እየተገበራቸው የሚገኙ ሥራዎች ዳር የሚደርሱትም፣ እስካሁን የመጣንበት ውጥንቅጥም መቋጫና መቋጠሪያ የሚያገኘው በዚህ አግባብ ነው።
ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ከመንግሥት ጀምሮ ሁሉም የድርሻውን ጥረት ማድረግ ይገባዋል። ከሁሉ በላይ ግን ዛሬም ድረስ በዚህ አካሄድ እምነት ያጡና ሌሎች ዓሉታዊ አማራጮችን የተከተሉ ሃይሎች መንገዳቸውን ማጤን ይኖርባቸዋል። እነርሱ እንወክለዋለን የሚሉት የማህበረብ ክፍል፣ እንሰዋለታለን ያሉለት ዓላማ በጠብ መንጃ አፈሙዝ የሚሳካ ሳይሆን በቅንነት፣ በፍፁም ግልፅነት እና በጋራ ሆኖ መፍትሄ በመፈለግ መፍትሄ የሚያገኝ መሆኑን ማመን አለባቸው። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ፣ መንግሥትና ሌሎች የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያደርጉትን የምክክር ጥሪ መቀበል ይኖርባቸዋል። ይህ ሲሆን የሚጠፋ የሰው ሕይወት ሳይኖር፤ ሀብትና ንብረት ሳይወድም ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት ይቻላል።
ሰው መሆን
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም