በዚህ ዕለተ ሰንበት መጋቢ ሀዲስ አለማየሁ በebs ቡና ሰዓት ላይ ቀርበው፤ ከማር ከወለላ በሚጣፍጠው ወጋቸው ስለ እርቅ አስፈላጊነት ሲሰብኩ አደመጥኩ። እሳቸው በአውደ ምህረቱ ብቻ ሳይሆን በሄዱበትና በደረሱበት ቢያወጉ፣ ንግግር ቢያደርጉ፤ የዕምነት አጥርን የተሻገረ ስብከት ነው የሚያካሂዱት የሚል መረዳት አለኝ። በዚህ የebs”ስብከታቸው”ሰው መጀመሪያ ከፈጣሪው በማስከተል ከራሱ ከዚያ ከተፈጥሮ በመቀጠል ከማህበረሰቡ ጋር መታረቅ አለበት ሲሉ በየቤታችን ያለውን ግን ልብ ያላልነው፤ ልብ ብንለውም ቦታ ያልሰጠነውን ነጭ ዝሆን አስታወሱኝ።
ሕዝብ እንደ ሕዝብ አልተጣላም፣ ማን ከማን ጋር ነው የሚታረቀው፤ የተጣላው ያው ተማርሁ ፊደል ቆጠርሁ የሚለው እንጂ ሕዝብማ አብሮ እየተኗኗረ ነው። ነጮች white elephant in the room እንዲሉ። አወዛጋቢ ወይም አነጋጋሪ ነገር እንዳለ ልብ እያወቀ የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ይሁን ተብሎ ሲተው ነጮች በቤት ውስጥ ያለ ነጭ ዝሆን ይላሉ። በየቤታችን፣ በየቀዬው፣ በየጋራ፣ ሸንተረሩ፣ በየአውራ መንገዱ፣ በየአዳራሹ፣ በየቢሮው፣ በየስራ ቦታው፣ ወዘተረፈ በአካል ግዘፍ ነስቶ ባናየውም በሀሰተኛ ትርክት ምስ ተወልዶ የጎለመሰ ጥላቻ የሚባል አባት ነጭ ዝሆን አለ። መጠራጠር፣ መለያየት፣ መጠፋፋት፣ ግጭት፣ ማገት ውድመት፣ ጦርነት፣ ቀውስ፣ ወዘተረፈ የሚባሉ ዲቃላዎች አሉት።
ከግዝፈቱና ከንጣቱ አንጻር ባላየና ባልሰማ ሊያልፉት የማይችል። በአቋራጭና በተለዋጭ መንገድ ወይም ዲቶር ሊያልፉት ቢሞክሩ፤ በማለባበስ፣ ጭምብል በማጥለቅ፣ በማድበስበስ፣ በመሸፋፈን፣ በመቀባባትና በመኳኳል ሊያልፉት ቢሞክሩ ቀድሞ የሚገኝ አባት ነጭ ዝሆን። የሀገራዊ ምክክሩ አንዱ ምሰሶ ይሄን አባት ነጭ ዝሆን እንዳይመለስ አድርጎ ማሰናበት ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ ሀገራዊ ምክክሩን በማዕቀፍ ከአዳራሽ ባሻገር የማየት ድፍረት ይጠይቃል።
ከዚህ ቀደም ደጋግሜ እንደምለው ከአዳራሽ ባሻገር በማዕቀፍ ማየት ይሻል። በአዳራሽ ጀምረው በአዳራሽ የማይቋጩት። ማዕቀፉ ግልጽ ነው። ከፈጣሪ፣ ከራስ፣ ከተፈጥሮና ከጎረቤት ጋር መምከር፣ መግባባትና መቀባበል የሚጠይቅ ማዕቀፍ ወይም ፓኬጅ ነው። ከራስና ከፈጣሪ ጋር የሚደረግ እርቅ ቆም ብሎ ራስን በመመርመርና የመጡበትን መንገድ በመገምገም ከራስም ሆነ ከፈጣሪ ጋር ጸብና ቅራኔ ካለ እርቅ ለማውረድ የሚወሰንበት ሒደት ነው። ከራሱና ከፈጣሪው ጋር ሰላም የሌለው ከሌሎች ጋር ሰላም ሊኖረው አይችልምና የሀገራዊ ምክክርም ሆነ የእርቅም አካል ሊሆን አይችልም።
ከራስና ከፈጣሪ ጋር እርቅ ማውረድ ለሀገራዊ ምክክርና እርቅ መሠረት ነው። ከፈጣሪም ሆነ ከራስ ጋር የሚደረግ ሰላም ግለሰባዊ ውሳኔ ቢሆንም የሀይማኖት ተቋማትና ብዙኃን መገናኛዎች የበኩላቸውን እገዛ ሊያደርጉ ይገባል። ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ከተፈጥሮ ጋር በአረንጓዴ አሻራ አሸማጋይነት እያታረቅን ነው። ባለፉት አራት ዓመታት ከ25 ቢሊየን በላይ ችግኞችን የተከልን ሲሆን ከዘንድሮው ጋር 32 ቢሊየን እንደርሳለን። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ 50 ቢሊየን እንደርሳለን። በዚህ ከእናት ምድርና ተፈጥሮ ጋር ሰላም እያወረድን ነው ።
በነገራችን ላይ ሀገራዊ ምክክሩ ከማዕቀፉ አንዱን ካጎደለ ሙሉኡ አይሆንም። ይህ ማለት መሉ በኩሌ እንዲሆን ይጠበቃል ማለት አይደለም። የጎደለውን ተበድሮም ሆነ ተለቅቶ የመሙላት ኃላፊነትና ቁርጠኝነት ይጠይቃል። በዚህ ሀገራዊ ምክክር ሒደት ጎን ለጎን ሊሟሉ ከሚገባቸው አላባውያን አንዱና ዋነኛው ኢኮኖሚው ነው። ከእሱ ጋር ቁጭ ብሎ በጥሞና መነጋገርና መመካከር ይጠይቃል። የሀገራዊ ምክክሩ አካል ሊሆን ይገባል። ሆኖም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሀገራዊ ምክክር ማዕቀፎችን ሁሉ ይሸከም። ይወጣው አይባልም።
በተለይ መንግስት፣ ባለድርሻ አካላትና መላ ሕዝቡ በመቀናጀትና በመናበብ የኑሮ ውድነቱን፣ የዋጋ ግሽበቱን፣ አጉራ ዘለል የግብይት ስርዓቱን፣ ስራ አጥነቱን፣ ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍሉን፣ የተፈጥሮ ሀብት ብሔርተኝነቱን፣ ወዘተረፈ አደብ በማስገዛት የሀገራዊ ምክክሩ ቀልብ እንዳይወሰድ ማገዝ አለባቸው። በሀገሪቱ የሚስተዋለው የጸጥታ ችግርም ሀገራዊ ምክክሩ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳያድር በማያዳግም አግባብ ከወዲሁ መቀረፍ አለበት። የብሔር ጽንፈኝነትም ለሀገራዊ ምክክሩ እንቅፋት እንዳይሆን በጥበብና በማስተዋል ሊያዝ ይገባል። የዛሬ መጣጥፌ መነሻና መዳረሻ ወደ ሆነውና ከሀገራዊ ምክክር ማዕቀፎች አንዱ ወደሆነው “ነገረ ኢኮኖሚ” ልመለስ። ኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታው ከሀገራዊው ምክክሩ ጋር ያለውን መስተጋብር ላነሳሳ።
ኢኮኖሚያዊ ሁናቴ በተለይ በድህረ ግጭትና ቀውስ ወቅት በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ የማይተካ ሚና አለው። ሀገራዊ ምክክር በቀውስና በግጭት ወቅት በማህበረሰቦች መካከል የተፈጠሩ ቁስሎችና ልዩነቶች እንዲታከሙ በማድረግ መተማመን መፍጠር እንዲሁም ለግጭትና ለቀውስ የዳረጉ ቁርሾዎችን በዘላቂነት የመፍታት ሂደት ነው። በዚህ ወሳኝ ሂደት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ሁናቴው የሀገራዊ ምክክሩን ስኬትም ሆነ ውድቀት የመወሰን አቅም አለው። በማህበረሰቦች መካከል የተፈጠረ የኢኮኖሚ ኢፍትሐዊ ተጠቃሚነት ውጥረትንና ቅሬታን በመጎንቆል ወደ ለየለት ግጭት ሊያመራ ይችላል። የማህበረሰቦችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ፍትሐዊ በማድረግ ግጭቶችን አስቀድሞ ማምከን ይገባል። የሀገራዊ ምክክር ጥረቶች ሁሉም ዜጎች ፍትሐዊና እኩል የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ዕድል እንዲፈጠርላቸው ማለትም ለሀብት፣ ለትምህርት፣ ለስራ ዕድል፣ ወዘተረፈ እኩል ተደራሽነት እንዲኖራቸው ያበረታታሉ። ፍትሐዊነትን ይመክራሉ።
ሌላው በተለይ በድህረ ግጭትና ቀውስ መልሶ ግንባታና ልማት በስፋት ካልተካሄደ ሀገራዊ ምክክሩንም ሆነ ብሔራዊ እርቁን የተሟላ አያደርገውም ። መሠረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት፤ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማሟላት፤ በግጭቱ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ማነቃቃት እና ነገሮችን ቀድመው ወደነበሩበት መመለስ ለሀገራዊ ምክክሩ መደላድል ይፈጥራል። የመብራት የቴሌኮም የባንክ በቅርብ ደግሞ የአክሱም አውሮፕላን ተጠናቆ በረራ ጀምሯል። ስራ አቁመው የነበሩ ፋብሪካዎች ወደ ስራ ተመልሰዋል።
ከዚህ አኳያ መንግስት ከፊቱ ብዙ ስራ ይጠብቀዋል። በግብርናው፣ በኢንዱስትሪውና በንግድ እንቅስቃሴው በሰፊው መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ የስራ ዕድልና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ስለሚያመጣ መረጋጋት ይፈጥራል። ቅሬታን ያለዝባል። አንዳንድ የዘርፉ ልሒቃን የሽግግር ፍትሕ ስርዓት፣ የእርቅ አፈላላጊና የካሳ ስርዓቱን የሀገራዊ ምክክር ሒደቱ አካል አድርገው ያዩታል። የተጎዱትን መካስ፣ ሀብት የማፍራት መብትን እንደገና ማረጋገጥ፣ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ወይም ማህበረሰቦች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ቁስል እንዲጠግግና ምክክሩ ወደፊት እንዲራመድ ያግዛል።
ቀደም ሲል በተፈጠሩ ግጭቶችና ቀውሶች የተቃቃሩ ማህበረሰቦችን ለማቀራረብና ይቅር ለማባባል ኢኮኖሚያዊ ውህደትና ትብብር የላቀ አስተዋጾ አለው ይላሉ እነዚሁ የዘርፉ ምሁራን። ሌላው ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትና መልካም አስተዳደርም ለሀገራዊ ምክክሩ ጥሩ መደላድል ስለሚፈጥር ከወዲሁ ልዩ ትኩረት ይሻል። ይሁንና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ብቻ የተዋጣለት ሀገራዊ ምክክርና እርቅ ያሳካሉ ማለት አይደለም። የማህበራዊና የባህላዊ፣ የስነ ልቦናና የፖለቲካ ጉዳዮችም የላቀ ድርሻ እንዳላቸው በቅጡ ሊጤኑ ይገባል።
ኢኮኖሚው ችግሮቻችን የመፍቻ ዋና ቁልፍ (ማስተርኪይ) ነው። አሁን ከገባንበት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቅርቃር የመውጫ የማሪያም መንገዳችን ነው። ሀገርም ሕዝብም ሆኖ ለመዳን ፍቱን መድሀኒታችን ነው። የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት፣ ስራ አጥነት፣ ድህነት፣ ችጋር፣ ቸነፈር፣ ጠኔ፣ ርሀብ፣ እርዛት ብሔር ወይም ሀይማኖት የላቸውም። አማራም፣ ትግራዋይም፣ ኦሮሞም፣ ሶማሌም፣ አፋርም፣ ወዘተረፈ አይደሉም። ኦርቶዶክስ፣ እስላም፣ ክርስቲያን፣ ካቶሊክ፣ ዋቄ ፈናም አይደሉም። ያለልዩነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ችግሮች ናቸው። ቢቀረፉ ሁሉንም ያለልዩነት እልል የሚያሰኙ፤ ባይቀረፉ በአንድነት ጥያቄ የሚሆኑ ናቸው።
በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያውያንን በአሉታም ሆነ በአንድነት የሚያቆማቸው በኢኮኖሚው ላይ በሚመዘገው ስኬት ወይም ውድቀት ነው። ሰንደቅ ዓላማ፣ ሀገር፣ ብሔራዊ ጀግና፣ ታሪክ፣ ወዘተረፈ በ2ኛ ደረጃ የሚገኙ ናቸው። የዚህ ለውጥ አስኳል ኢኮኖሚው ነው። ሌሎች እሱን ተከትለውና በእሱ ዙሪያ የሚመሠረቱ ናቸው። ሀቀኛና እውነተኛ ብሔራዊ መግባባትና እርቅ ላይ ለመድረስም ኢኮኖሚው ወሳኝ ሚና አለው። ቻይናንና ቬትናምን ይዞ የተነሳው፤ ዜጎቿን ያግባባው፤ ሳይመካከሩ ያስታረቀው፤ ይቅር ያባባለው፤ አንድነታቸውን በጹኑ መሠረት ላይ ያቆመው፤ በኩራት ቀና ብለው እንዲራመዱ፤ ወዘተረፈ ያደረገው ኢኮኖሚው ነው። እንጂ ከቻይና የእርስ በርስ ጦርነቱና ከባህል አብዮቱ በላይ ደም ያቃባ ግጭት የለም። በኢኮኖሚው ያስመዘገቡት ተአምራዊ ዕድገት ጠባሳው እንዲሽር አድርጓል።
ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ማለትም የኑሮ ውድነቱ ፣ ስራ አጥነቱ ፣ ግሽበቱ ፣ ከትልቅ መንግስትነት ወደ ትንሽ መንግስትነት ማለትም መንግስት በሒደት ኢኮኖሚውን ለገበያውና ለዜጋው ትቶ እሱ ድንበር፣ የሕግ የበላይነት፣ መልካም አስተዳደር፣ ወዘተረፈ ላይ ሲያተኩር ዜጋው መሰረታዊ ፍላጎቱን አሟልቶ በሂደት ጥሪት፣ ሀብት ሲያፈራ፣ ተስፋ ሲሰንቅ ወዘተረፈ በሂደት ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊ ቀውሶችን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ያቀለዋል። ተስፋ ከሰነቀ፣ ስራ ካለው፣ በኑሮ ውድነትና በዋጋ ግሽበት ካልተማረረ፣ በየሰዓቱ በሚያሻቅብ የሸቀጥ ዋጋ ካልተራቆተ፣ የትርፍ ህዳግ ከተቀመጠለት እንደ አሽዋ ከበዛ ቀማኛ ደላላ ከተላቀቀ፣ ስለሚበላውም ሆነ ለልጆቹ ምሳ ስለመቋጠር ወዘተረፈ ሀሳብ ጭንቀት ከሌለበት እንዲሁም ከ5/11 ስሌት የተላቀቀ ሲቪል ሰርቫንት መፍጠር ከተቻለ ቁጭ ብሎ በተረጋጋ ሁኔታ ስለሰላም፣ ስለፍቅር፣ ስለእርቅ፣ ስለይቅርታ፣ ስለዴሞክራሲና ስለፖለቲካ ቢወራ መደማመጥ መቀባበል ይቻላል። ካልሆነ ግን ፈተናው ከባድ ነው የሚሆነው።
ኢኮኖሚው ብሔር፣ ማንነት፣ ዘውግ የለውም። የኦሮሞውም፣ የአማራውም፣ የወላይተውም ፣ ወዘተረፈ የጋር ወኪል፣ የጋራ አካፋይ ነው። የጋራ ችግር ነው። ኢኮኖሚው እንደ ጆከር ዘር፣ ማንነት ሳይለይ ሁሉንም ወክሎ ሊያጫውት ይችላል። የአንድነት ሆነ የንኡስ ብሔር ኃይላትን ሊወክል ይችላል። የሊበራል ዲሞክራቱንም ሆነ ሶሻል ዲሞክራቱን አልያም “ አብዮታዊ ዲሞክራቱን “ ያለ ልዩነት ይወክላል። ብልጽግናን፣ ኢዜማን፣ አብንን፣ የእነ ኦቦ ቀጀላን ኦነግ፣ እናትን፣ ወዘተረፈ ከፍ ሲልም ሀገርን ሕዝብን ያለ ልዩነት ይወክላል።
አዎ ! በዚህ ወሳኝ ሰዓት የሀገራችንን ዜጎች ለአንድነት፣ ለእርቅ፣ ለመነጋገር፣ ለመቀባበል፣ ለሰላም የሚያቀራርብ ለጊዜው (ታክቲካዊ ) እና እጃችን ላይ ከቀሩን ካርዶች ኢኮኖሚው አንዱ ነው። ምንከተለው ፖለቲካዊ ስርዓት በማንነት ላይ የተመሰረተው ፌደራሊዝም ይሁን በግለሰብ መብትና ነፃነት የተዋቀረው ሊበራል ዴሞክራሲ ወይስ ራሱን ሶስተኛ አማራጭ ብሎ የሚጠራ ይሁን ኢኮኖሚው ሁሉን ወክሎ ማጫወት፣ መጫወት ይችላል።
ይሄው መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ችግር በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ከመጣው የሕዝብ ብዛት ዕድገት፤ ከአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ፤ ከንግድ ስርዓቱ መረን የለሽነት፤ ከገብያ ስርዓቱ የተራዘመ ሰንሰለት፤ ከሕገ ወጥ ድለላ ጋር አብሮ፣ አድሞ ኢኮኖሚውን ፅኑ ታማሚ አድርጎታል። በዚህ የተነሳ የኑሮ ውድነቱ በሰዓታት፣ በቀናት ልዩነት ጣራ እየነካ ነው። የስራ አጡ ቁጥር እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ይገኛል። የእነዚህ ሁሉ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሁሉ ድምር ቅርሻ በሆነ ፖለቲካዊ ቀውስ እያለፍን ነው።
እስካሁን እዚህም እዚያም ያስተዋልናቸው ግጭቶች ለዓመታት ሲቀነቀን ከኖረው የልዩነት ተረክ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ቀውሱን ተከትለው የተከሰቱ ማህበራዊ ቀውሶች ለመሆናቸው ሞራ ገላጭ መሆን አይጠይቅም። የተሳሳተው ፖለቲካዊ አመራር ለኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርጎናል። ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ ማህበራዊ መፍረክረክን አሰከትሏል። መላ ካልተበጀለት በዚህ ይቆማል ተብሎ አይጠበቅም። ወደለየለት የፀጥታ፣ የደህንነት ስጋት ሊሸጋገር ይችላል። ይህ ከመሆኑ በፊት ከገጠመን ምስቅልቅል በጊዜ ለመውጣት መስራት አለብን። ከዚህ ለመውጣት ደግሞ ዜጋው፣ መንግስት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማህበራት ከፖለቲካው ይልቅ ኢኮኖሚው ላይ በአንድነት ሊረባረቡ ይገባል።
ሻሎም !
አሜን።
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2016 ዓ.ም