ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለ2016 የዒድ አል አድሃ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

እንኳን ለ2016 የዒድ አል አድሃ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

የኢድ አል አድሃ በዓል የፈተናና የመሥዋዕትነት በዓል ነው። ነቢዩ ኢብራሂም በአላህ ትእዛዝ ልጃቸውን ለመሥዋዕትነት ያዘጋጁበት፤ ጽናታቸው ተፈትኖ ያሸነፉበት በዓል ነው። ለዚህ ጽናታቸውም ከአላህ ዘንድ ምትክ በግ ያገኙበት በዓል ነው።

ከዚህ በዓል የምንማራቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ማንኛውንም ፈተና በጽናት ካለፉት ዋጋው ከፈተናው በላይ መሆኑን እንማርበታለን። ልጅን ያህል ነገር እንዲሰዋ መጠየቅ ከባድ ፈተና ነው። ልጅን ለመሥዋዕትነት ማዘጋጀት ደግሞ ከባድ ጽናት ነው። ከባድ ፈተና ከባድ ቆራጥነት ይፈልጋል። ከባድ ቆራጥነት ከባድ ውሳኔን ይጠይቃል፤ ከባድ ውሳኔም ታላቅ ዋጋን ያስገኛል።

ኢትዮጵያን ታላቅና የበለጸገች ሀገር ለማድረግ ስንነሣ ፈተናው ከባድ እንደሚሆን እናምን ነበር። ሳይፈቱ የተከማቹ ሀገራዊ ችግሮች አሉ። በዘመናችን የተፈጠሩ አሁናዊ ችግሮችም አሉ። እነዚህ ሁለቱን በአንድ ጊዜ መጋፈጥ ይጠይቀን ነበር። ተራራውን መጋፈጥ ሳይሆን ተራራውን ማንሣት ይጠይቀን ነበር። ይሄንን ፈተና ለመጋፈጥ ከባባድ ውሳኔዎችን መወሰን ይገባን ነበር። እንደ ልጅ የምንወዳቸውን ሰዎች፣ ነገሮች፣ ቡድኖች፣ ወዳጆችና አካሄዶች ለመሠዋት መወሰን ነበረብን። መወሰን ብቻ ሳይሆን ማድረግም ነበረብን።

ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸው ኢስማኤልን ሳይሆን በምትኩ ከአላህ የተሰጣቸውን በግ ሠውተዋል። የእኛ ፈተና ከዚህም የባሰ ነበር። ሀገራችን ባከማቸቻቸው ዕዳዎችና ስብራቶች የተነሣ፣ ያለን አማራጭ የራሳችንን ነገር መሠዋት ብቻ ነበር። ሀገራችንን ለማዳን፣ የሕዝባችንን ዘላቂ ጥቅሞች ለማስከበር እና ከዛሬው የተሻለ ነገን ለመፍጠር ስንል፣ ብዙ ነገሮችን ሠውተናል።

ችግሮቻችን ቀስ ብለን እንድንሄድ አይፈቅዱልንም። በጥንቃቄ እንድንሮጥ እንጂ። የልማት ጥያቄዎቻችንን ለመመለስ እንደ ሕዝብ ሁላችንም የምንወዳቸውን ነገሮች ሠውተናል። ከምንወደው አካባቢ ወደ ሌላ ሄደናል።

ትዝታዎቻችንን ሠውተናል። የባንዳውን ጩኸት ችለናል፤ ሀገርን ለመለወጥ ስንል ቤቶቻችንና ሕንፃዎቻችን እንዲፈርሱ ፈቅደናል። የመብራትና የውሃ መጥፋትን ታግሰናል፤ የመንገድ መዘጋትንና የአካባቢ መፈራረስን ተቀብለናል። ያለ መሥዋዕትነት የሚያድግ ሕዝብ፣ ያለ መሥዋዕትነት የሚበለጽግ ሀገር የለም። የኮሪደር ልማቱን በዚህ መልኩ በመሥዋዕትነት ነው የሠራነው። ፍሬው ግን እጅግ ጣፋጭ መሆኑን አይተናል።

ሰላማችንን ለማስፈን በዚሁ መንገድ ነው መቀጠል ያለብን። ነፍጥን መጣል፣ ከጫካ መውጣትና የራስን ዋሻ ትቶ ወደ መስኩ መውጣትን ይፈልጋል። የራስን ኢጎ መሠዋትን ይጠይቃል። ምቾትንና ፍላጎትን መተውን ይፈልጋል። ከመቀበል በላይ መስጠትን ይሻል። እንደ ኢብራሂም በጣም የምንሳሳለትን ነገር ለመሠዋት መቁረጥ ይፈልጋል። ሁላችንም ለመሥዋዕትነት ከተዘጋጀን የማይሳካ የሰላም መንገድ የለም። እንደ ልጅ ያሳደግናቸው ብዙ ልማዶች፣ ጠባዮች፣ አመለካከቶች፣ ርእዮተ ዓለሞችና አካሄዶች አሉን። እነርሱን ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም ስንል ለመሠዋት ዝግጁ ከሆንን፣ ውጤቱ ከሰላም በላይ ነው።

ምክክር የሚሳካው የተሻለ ሐሳብና የላቀ ዕውቀት በማዋጣት ብቻ አይደለም። የተሻለ ሐሳብና የላቀ ዕውቀት ስላለን ብቻ የሠመረ ውጤት አናገኝም። ሌላ ወሳኝ ነገር ይፈልጋል። እርሱም መሥዋዕትነት ነው። የራስን ፍላጎት ለመሠዋት መቻል አለብን። ለትልቅ ግብ ሲባል ይቅርብኝ ማለት አለብን። ከእኔ የተሻለ ሐሳብና ልምድ፣ ዕውቀትና ጥበብ ሊኖር ይችላል ብለን ማመንና መቀበል አለብን። ለተሻለው ሐሳብ መገዛት አለብን። ልክ ልኩን ከመንገር፤ ነጥብ ከማስቆጠር፤ ጀግና ጀግና ከመጨዋት የወጣ ትኁት ሰብእና መያዝ አለብን። ይሄ ሁሉ መሥዋዕትነትን ይጠይቃል።

እንደ ነቢዩ ኢብራሂም ያሳደግናቸውን ብቻ ሳይሆን አብረውን ያደጉትን ብዙ ጠባዮች ለመሠዋት መዘጋጀትን ይጠይቃል። መሥዋዕትነት የሚከፍሉ ዜጎች በበዙ ቁጥር፣ ምክክር የላቀ ውጤት ያስገኛል።

የኮሪደር ልማታችን በየከተሞቻችን እንዲስፋፋ፣ ሰላማችን የጸና እና የማይደፈርስ እንዲሆን፤ ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ተካሂዶ እንዲሳካ – ያሳደግናቸውንና ያደጉብንን አንዳንድ ነገሮች መሥዋዕት ለማድረግ እንዘጋጅ። ሐሳቦቻችን ትጥቅ ይፍቱ። ከመተኮሻ ወደ ማረሻ እንመለስ። ከጠመንጃ ወደ ማጨጃ እንዛወር። ከዲሞትፈር ወደ ምክክር እንምጣ። ከብሔር ግጭት ወደ ሐሳብ ፍጭት እንሻገር። የምንወደውን፣ የምንፈልገውንና ያሳደግነውን እንኳን ቢሆን – ለሀገር ስንል ለመሠዋት እንዘጋጅ።

መልካም በዓል ይሁን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ስኔ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You