ዶክተር አምባቸው መኮንን ከአባታቸው ከአቶ መኮንን ሲሳይ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ አማን እንደብልሀቱ በጋይንት አውራጃ በአሁኑ የደቡብ ጎንደር ዞን ታች ጋይንት ወረዳ ልዩ ስሙ አቄቶ ኪዳነ ማርያም ቀበሌ ተወለዱ፡፡
እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአቄቶ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፣ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በታጠቅ ለሥራ መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በንፋስ መውጫ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እየተከታተሉ ባሉበት ወቅት በወቅቱ የነበረውን ስርዓት ጭቆና በመቃወም ወደትግል በመግባት ትምህርታቸውን ከሰላምና መረጋጋት በኋላ አጠናቀዋል፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን የከፍተኛ ትምህርታቸውን በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በምጣኔ ሀብት ሳይንስ ኢኮኖሚክስ፣ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በሁለት ከፍተኛ የውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም በደቡብ ኮሪያ ስኩል ኦፍ ፐብሊክ ፖሊሲ ኤንድ ማኔጅመንት እና በእንግሊዝ ሀገር ኬንት ዩኒቨርሲቲ በማስተርስ ኦፍ ሳይንስ ኢን ኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኤንድ ኢኮኖሚክ ዴቨሎፕመንት እጅግ በከፍተኛ ውጤት ተመርቀዋል፡፡ የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በእንግሊዝ ሀገር ኬንት ዩኒቨርሲቲ በምጣኔ ሀብት ሳይንስ በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቀዋል፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን በትምህርት ክትትላቸው ፈጣን ተማሪ የነበሩ ሲሆን፣ ትምህርታቸውን በተከታተሉባቸው ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተሸላሚና ተወዳዳሪ ነበሩ፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ በነበረበት ወቅት በወቅቱ የነበረውን ጭቆና በመቃወምና የህዝባዊ ትግሉ አካል በመሆን በለጋ እድሜያቸው የቀድሞውን የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ኢህዴን/ የአሁኑን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ በመቀላቀል ለትጥቅ ትግሉ ወሳኝ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
በሽግግር መንግሥቱ ወቅትና ህዝባዊ መንግሥት ከተመሰረተ በኋላ በድርጅትና በመንግሥት የተሰጧቸውን ኃላፊነቶች በቁርጠኝነትና በታማኝነት አገልግለዋል፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን ባለፉት 29 ዓመታት ከክፍለ ህዝብነት እስከ ከፍተኛ የመንግሥትና የህዝብ ኃላፊነት ያለመታከት አመራር ሰጥተዋል፡፡
ከ1982-1988 ዓ.ም በደቡብ ጎንደር ዞን ታች ጋይትና ፋርጣ ወረዳዎች፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በርና ሀገረማርያም ከሰም ወረዳዎች በክፍለ ህዝብነት በመስራት ህዝቡን በማደራጀትና ለመብትና ጥቅሞቹ እንዲታገል አድርገዋል፡፡
ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ዓመታት የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግሥት ሥራ አመራር ተቋም ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል፡፡በወቅቱ ፈታኝ የነበረውን የክልሉን መንግሥት የመፈፀም አቅም ለመገንባትና የፈፃሚ አካላትን አቅም ለማሳደግ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ብቃት ከፍ ለማድረግ ጉልህ አመራር ሰጥተዋል፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን በደቡብ ኮርያና እንግሊዝ የማስተርስ እና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከተከታተሉ በኋላ አቅማቸውን ይበልጥ በማሻሻል ከክልል እስከ ፌዴራል መንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል፡፡
በ1993 ዓ.ም ከደቡብ ኮርያ እንደተመለሱ የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግሥት ንግድ ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ በመሆን የክልሉ ንግድ ስርዓት ዘመናዊነትን እንዲላበስ በማስቻል ከፍተኛ ሥራ ሰርተዋል፡፡
ከ1994-95 ዓ.ም የቀድሞው ብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅ/ቤት ኃላፊ በመሆን ወቅቱ የሚጠይቀውን አመራር ሰጥተዋል፡፡ ለአንድ አመት ያህልም የጥረት ኮርፖሬት ም/ሥራ አስፈፃሚ በመሆን አመራር ሰጥተዋል፡
ከ1996-98 ዓ.ም የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግሥት ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ በመሆን በክልሉ የተጀመረውን የንግድ ሪፎርም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ክልሉ ለኢንቨስትመንት ምቹ እንዲሆን አመራር ሰጥተዋል፡፡
የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በምጣኔ ሀብት ሳይንስ አጠናቀው ከተመለሱ በኋላም ከ2003-2005 ዓ.ም የአማራ መልሶ መቋቋም ልማት ድርጅት /አመልድ/ ዋና ዳይሬክተር በመሆን የግብርና ሥራ ፣ምግብ ዋስትና፣ የተፈጥሮ ሀብት እና መሰል ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡
ከ2006-2008 ዓ.ም በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ
መንግሥት የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ሆነው አመራር ሰጥተዋል፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን የክልሉን ከተማ ልማት ቢሮ በመሩበት ወቅት ዛሬ በአማራ ክልል ከተሞች ተሞክሮ የሚወሰድባቸው በማህበራት የተደራጁ እና የየከተማውን ፕላን ጠብቀው የለሙ መኖሪያ ቤቶች እውን እንዲሆኑ በማድረግ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በኢፌዴሪ የከተማ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር እና በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰረተ ልማት አማካሪ በመሆን የሚወዷትን ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን በቅንነትና በታማኝነት አገልግለዋል፡፡
ከየካቲት 29/2011 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉን ህዝብ ጥያቄ በመቀበል የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በመሰየም ህዝባቸውን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን የታች ጋይንት ወረዳ ህዝብን በመወከል የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ም/ቤት አባል እንዲሁም የአማራን ህዝብ በመወከል የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ም/ቤት አባል በመሆን የተጣለባቸውን ህዝባዊ አደራ በብቃት ተወጥተዋል፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን ከመንግሥት ኃላፊነታቸው በተጨማሪ ላለፉት ዓመታት የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ የኢህአዴግ ም/ቤት አባልና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአዴፓ ምክትል ሊቀመንበር በመሆን በከፍተኛ የድርጅት ኃላፊነት ሰርተዋል፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን የልማት ድርጅቶችን ማለትም የአመልድ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የሰሩ ሲሆን ከፌዴራል ተቋማትም የኢትዮጵያ ምድር ባቡር፣ የኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ መብራት ኃይልን በቦርድ አባልነት እንዲሁም የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የብረታብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽንን በቦርድ ሰብሳቢነት መርተዋል፡፡ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሌሎች የትግል ጓዶቻቸው ጋር በመሆን በከፍተኛ ትግልና ቁርጠኝነት አመራር ሰጥተዋል፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን በአሁኑ ወቅት በሀገራችንና ክልላችን እየተካሄደ ባለው የለውጥ እንቅስቃሴ ከትግል ጓዶቻቸውና ከህዝቡ ጋር በመሆን የሀገሪቱንና የክልሉን ህዝቦች ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲከበር የታገሉ የህዝብ ልጅ ናቸው፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን ባለፉት ዓመታት በገጠሙ የፖለቲካ ብልሽቶች ምክንያት ያጋጠሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲታረሙ በፅናትና በከፍተኛ ህዝባዊ ስሜት ከትግል አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌን ጨምሮ በርካቶች ከእስር እንዲፈቱ ታግለዋል፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን ሰው አፍቃሪና ሀገርና ህዝባቸውን የሚያስቀድሙ የጠንካራ ሰብዕና ባለቤት ነበሩ፡፡ የህዝቡን የለውጥ ፍላጎትና ጥሪ ተቀብለው ከነበሩበት ኃላፊነት የክልሉን ህዝብ ለማገልገል ከየካቲት 29/2011 ዓ.ም ጀምሮ በርዕሰ መስተዳድርነት ተሰይመው በሀገሪቱና በክልሉ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ሌት ከቀን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን ቅዳሜ ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በክልሉ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ፅ/ቤት የርዕሰ መስተዳድር ም/ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ስብሰባ በነበሩበት በደረሰ ጥቃት ከሌሎች ሁለት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በጥይት ተመተው በተወለዱ በ48 ዓመታቸው ተሰውተዋል፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን ባለትዳርና የአራት ሴቶችና የአንድ ወንድ ልጅ አባትም ነበሩ፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2011