በመጪው ዓመት ከውጭ የሚገባ ሴራሚክስን በሀገር ምርት ለመተካት ታቅዷል

አዲስ አበባ፡- መንግሥት በ2017 በጀት ዓመት ከውጭ የሚገባውን ሴራሚክስ በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት እቅድ መያዙን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽንና ካም ሴራሚክስ ማህበር የአክሲዮን ፊርማ ሥነሥርዓት ባካሄዱበት ወቅት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ባስተላለፉት የሥራ መመሪያ እንደገለጹት፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለጥቅል ሀገራዊ እድገት ያለው አበርክቶ ከሰባት በመቶ ያነሰ ነው።

እንደ አቶ ታረቀኝ ገለጻ፤ መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚሠራቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ የሴራሚክስ ምርትን ማሳደግ በመሆኑ ካም ሴራሚክስ በአጭር ጊዜ ወደ ምርት በመግባት ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ምርት መተካት ያስፈልጋል። የሴራሚክስ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ዕቅድ ተይዟል።

በሚቀጥለው ዓመት ሴራሚክስ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በመንግሥት በኩል እቅድ አለ፤ ይህ ስምምነትም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።

መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲያድግ ምቹ ፖሊሲዎችን አጽድቋል። የጸደቁት የፖሊሲዎች ዋነኛ አላማቸው በግሉ ዘርፍና በሽርክና የሚመራ የኢንዱስትሪ ሥርዓት እንዲገነባ ለማድረግ ነው ያሉት አቶ ታረቀኝ፤ በሽርክና የሚሠሩ ሥራዎች ከቀጣይነትና ከአትራፊነት አንጻር ትልቅ ቦታ ያላቸው በመሆኑ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሴራሚክስ ምርት የውጭ ጥገኛ ናት ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ እንደ ሀገር ያሉት ሁለት ኢንዱስትሪዎችም በውጭ ዜጋ የተያዙ ናቸው። ካም ሴራሚክስ የመጀመሪያው የሀገር በቀል በሽርክና የተጀመረው የሴራሚክስ ኢንዱስትሪ ነው። መንግሥት ትኩረት ከሰጠባቸው ከተኪ ምርት አኳያ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ እየተሠራ ነው። የመንግሥትን ዓላማ ከማሳካት አንጻር ስምምነቱ ጉልህ ሚና አለው፤መንግሥታዊ ፕሮጀክት በመሆኑ የቅርብ ክትትል እንደሚደረግለትም ገልጸዋል።

በፊርማ ሥነሥርዓት ወቅት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ አያሌው (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ የካም ሴራሚክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አጠቃላይ ካፒታል 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ነው። ከዚህ ውስጥ 30 በመቶ የአክሲዮን ድርሻውን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገዝቶታል ብለዋል።

ከካም ሴራሚክስ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ከአንድ ዓመት ከአምስት ወር በላይ መውሰዱን አመልክተው፤ ስምምነቱ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ያለበትን ችግር እንደሚቀርፍ ገልጸዋል።

የካም ሴራሚክስ ምርቶች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ ዋሪዮ ጋልጋሎ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር ለሴራሚክስ ምርት ቅድሚያ በመስጠት ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ መተካት ያስፈልጋል። የፕሮጀክቱ ግንባታ ላለፉት ሰባት ዓመታት በኮቪድ ፣በውጭ ምንዛሪ እጥረትና ከመሬት ጋር በተያያዘ ችግር የተጓተተ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ ካም ሴራሚክስ ቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው ፕሮጀክት ነው። ከሦስት ወራት በኋላ ወደ ሥራ ይገባል። ሲጠናቀቅም የማምረት አቅሙ በቀን 20 ሺህ ካሬ ሜትር ሴራሚክ ይሆናል፤ ይህም አቅርቦትና ፍላጎት በዘላቂነት ሚዛናዊ እንዲሆን ይረዳል። ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ በመተካት የሀገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ ይረዳል።

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You