‹‹ጨሞ›› – ልጅ አሳዳጊው ባለውለታ

ልጅነትን በትውስታ…

ደቡብ ምዕራብ ጊዲ ቤንች ዲዙ። ይህ ቀበሌ ሰላማዊት ካህሳይ ልጅነቷን ያሳለፈችበት፣ ክፉ ደግ ያየችበት መንደር ነው። እሷ በአቶ ካህሳይ አባትነት ስትጠራ በምክንያት ነበር። እኚህ አባወራና ቤተሰቦቻቸው ከመጠሪያነት ባለፈ እንደ ልጅ አሳድገዋታል። ዛሬ ሰላማዊት የልጅነት ጊዜ ውል ሲላት ትከፋለች። ልጅነት ለእሷ የእሾህ ላይ መንገድ ነበር። ሳይመቻት ኖራዋለች፣ ሳይደላት አልፋዋለች።

ሰላማዊት ‹‹እከሌ›› የምትለው ቤተሰብ የላትም። እሷና አሳዳጊዎቿ የመገናኘት ምክንያታቸውም ወላጅ አልባ መሆኗ ነበር። በአሳዳጊዎቿ እጅ መውደቋ ብዙ አሳይቷታል። በቤቱ ውላ ብታድርም እንደልጅ መብት ይሉትን አታውቅም። ለእሷ ተሰፍሮ የተሰጣት ግዴታ በጉልበቷ ማገልገል፣ ‹‹አቤት ወዴት፣›› ማለት ብቻ ነው።

ሰላም እንደ እኩዮቿ መማር፣ ትምህርት ቤት መሄድ ትሻለች። ባልንጀሮቿ ቀለም ቆጥረው ዕውቀት ገብይተው ሲመጡ እነሱን መሆን ምኞቷ ነበር። ይህ እውነት ግን ከእሷ ውስጠት አላለፈም። አሳዳጊዎቿ ከስራ ውጭ መማርን አልፈቀዱም። በጉልበቷ እያገለገለች በታዛዥነት ብቻ እንድትኖር ፈረዱባት።

ሰላማዊት ጊዜው ሲገፋ ዕድሜዋ ሲጨምር ሁሉ ነገር መረራት። በአሳዳጊዋቿ ቤት አገልጋይ ሆኖ መኖር ‹‹ይብቃኝ›› ስትል አሰበች። ተኝታ በተነሳች ቁጥር የምትጨነቅበት ጉዳይ ከአንድ ውሳኔ ሊያደርሳት ግድ ሆነ። ከራሷ መክራ ዘክራ የቆረጠችበት ሀሳብ ዕውን ሊሆን አልዘገየም።

አንድ ማለዳ…

አሁን ትንሽዋ ልጅ ልቧ ተነስቷል። ያደገችበትን፣ ክፉ ደግ ያየችበትን ቤት ርቃ ልትሄድ ነው። እንዲህ መሆኑ የልቧን ዕቅድ ይሞላል፣ ከገጠር ስትወጣ መማር ትችላለች፣ ከቀዬው ስትርቅ ሰርቶ ማግኘት፣ የእሷ ይሆናል። ሰላም እንዳሰበችው ሆነ። ማለዳውን ከቤት ጠፍታ ብዙ ራቀች። የኋላዋን ለጀርባዋ ትታ ወደፊት ገሰገሰች። አሁን ማንም እንዲያስቆማት ‹‹ተይ›› እንዲላት አትሻም። መሄድ መጓዟን ቀጥላለች። ከቆይታ በኋላ እግሯ ከተማ አዝልቆ ሚዛን አማን አደረሳት።

ሚዛን አማን…

ሚዛን አማን መልካም ከተማ ነች። ታሪኳ ልቆ፣. ውበቷ ደምቆ የምትታይ ድንቅ ስፍራ። አስተውሎ ላያት ተፈጥሮ ለእሷ ያደላ ይመስላል። ብዙዎች የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የአብሮነት ተምሳሌት መሆኗን ይመሰክራሉ። ቀድሞ ሚዛን ተፈሪ ትባል የነበረችው ከተማ ሚዛን አማን ተብላ ከተሰየመች ዓመታትን ቆጥራለች።

ዕድሜ ጠገቦቹ አዛውንቶች ዛሬም ድረስ ሰለከተማዋ ታሪክን ያጣቅሳሉ። ቀድሞ ሚዛን ተፈሪ ለመባሏ ምክንያቱ ከአፄ ሀይለስላሴ ስም ጋር ተያይዞ ነው። ስያሜዋን የቸሯት ደግሞ ልጅ እያሱ እንደሆኑ ታሪክ ይጠቁማል። ከተማዋን የቆረቆሩት ፊታውራሪ ዓለማየሁ ፍላቴን ጨምሮ ብዙዎቹ ስለአብሮነት ብዙ አሳይተዋል።

ሚዛን በደርግ ዘመን የከፋ ክፍለ ሀገር ዋና አስተዳዳር ጽህፈት ቤት መገኛና መቀመጫ ነበረች። ይህች ከተማ በብዙ ውጣውረድና ለውጥ እየተጓዘች መቀጠሏን እማኞቿ ይናገሩላታል። ከዙሪያ ገባ የሚመጡ እንግዶችን በማስተናገድም የሚያህላት የለም።

የቤንች ሸኮዋ ሚዛን አማን እንደስያሜዋ ናት። ብዙዎችን በጉያዋ አቅፋ አገር አማን ውሎ እንዲያድር ሰላሟን ታሳያለች። በከተማዋ በየጊዜው ከየገጠሩ የሚገባ ምርት ሲፈስባት ይውላል። ፍራፍሬው፣ አትክልቱ በረከቷ ነው። ቡናው፣ ቅመማቅመሙ፣ የጎማው ዛፍ ሲሳይ ከሌሎች ነጥሎ ይለያታል።

እስከዛሬ ያልጎደሉ ወንዝ ፏፏቴዎቿ፣ ምድርን አረንጓዴ እንዳላበሱ ዘልቀዋል። በሰፊው ገበያዋ ተጠይቆ፣ የሚታጣ የለም። ከዓመት እስከ ዓመት ደጇ ሙሉ ነው። ወደዚህች ስፍራ ማንም ጎራ ቢል ደግሞ እንግድነት አይዘውም። በጉልበቱ፣ ሰርቶ፣ በአቅሙ ሮጦ ለማደር ዕድል ከእሱ ጋር ነች።

ሰላማዊት ስለሚዛን አማን ሕይወት ስትሰማ ኖራለች። በዚህ ስፍራ ብትመጣ የልፋቷን አታጣም። ሰርታ ካደረች የላቧን ታገኛለች። እንዲህ ከሆነ የምትጓጓለት ትምህርት አይርቃትም። እየሰራች ትማራለች። ከተማረች ሕይወቷ ይለወጣል፣ ድህነትን ድል ነስታ ራሷን ታሸንፋለች።

ሚዛን አማንና ሰላማዊት በአካል ተገናኝተዋል። እሷ ከተማው ከነበረችበት ሕይወት ነጻ እንደሚያወጣት አልጠፋትም። የማደጎ ኑሮ መልከ ብዙ ነው። የሰው ቤት እንጀራ፣ እንደራስ መሶብ አይቆርሱትም። ሁሌም ግዞተኛና ታዛዥ ሆኖ መኖር ይሰለቻል፣ ሆድ ያስብሳል። አሁን ስለራሷ ሕይወት ልትወስን ነው። ያደገችበትን ቤትና ቀዬ ርቃለች፣ ከአሳዳጊዎቿ ጉያ ወጥታለች።

ሚዛን አማን ያገባት እግሯ ውሎ አድሮ ከፍጻሜው አድርሷታል። በሀያ አምስት ብር ደሞዝ ከሰው ቤት የተገኘላትን ስራ ወዳዋለች። በሰራተኝነት መቀጠሯ ገንዘብ ያስይዛታል፣ ለትምህርት ዕውቀቷ ይበጃታል። ሰላማዊትየልቧ እየሞላ የሀሳቧ እየደረሰ ነው።

የሀያ አምስት ብር ደሞዝተኛ…

ሰላም በተቀጠረችበት ቤት የሰራተኝነት ስራዋን ጀመረች። አሰሪዋ መልካም ወይዘሮ ናት። ከግዴታዋ የዘለለ ጉልበቷን አትጠይቅም። መላው ቤተሰብ ስለእሷ አሳቢና አዛኝ ሆኗል። ውሎ አድሮ ሰላም ለአሰሪዎቿ ፍላጎቷን አሳወቀች። አሁን እየሰራች መማር፣ ትፈልጋለች። በልጅነቷ ያጣችው እድል ዳግም እንዲያመልጣት አትሻም። በጉልበቷ ብታድርም ፊደል መቁጠር፣ ቀለም መለየት ትሻለች። አሰሪዎቿ ሀሳቧን አልተጋፉም። እየሰራች እንድትማር ይሁንታውን ሰጧት።

ተማሪዋ…

ሰላም ደብተር ገዝታ፣ እርሳስ እስክሪብቶ አሟልታ ትምህርት ቤት ተመዘገበች። ጥረቷን ያዩ ሁሉ እንደአሰሪዎቿ ‹‹አይዞሽ›› ሲሉ አበረቷት። የሥራ ግዴታዋ ከወጉ አልጎደለም። ኃላፊነቷን እየተወጣች ከትምህርት ገበታዋ ተገኘች። ከሀያ አምስት ብር ደሞዟ ላይ ሰባት ብሩን እያነሳች ለትምሀርት ቤት መክፈል ጀመረች። አልሰነፈችም። ዓመቱን ተምራ ከአንደኛ ወደ ሁለተኛ ክፍል ተሻገረች። የውስጧ ፍላጎት፣ የልጅነት ምኞቷ አንድ ሲል ጀመረ። ክረምት አልፎ መስከረም ሲጠባ ውሏን አልረሳችም። ዕቅዷን አልዘነጋችም። በአዲሱ ዓመት ደብተሯን ገዝታ ለሁለተኛ ክፍል ተዘጋጀች።

የሀያ አምስት ብር ተከፋይዋ ሰላም አሁን የወር ደሞዝተኛ ናት። በየግዜው ሰባት ብር ለትምህርት ቤቷ እያነሳች ቀሪውን ታስቀምጣለች። የሚተርፋት ሀያ ሶስት ብር ለልብስ ጫማዋ አያንስም። የዛኔ ይህ ገንዘብ ለእሷ ብዙ የሚባል ነበር። የፍላጎቷን ሞልቶ ለቁጠባዋ ይተርፋል።

ሰላም መማሯ አልተቋረጠም። በየዓመቱ ክፍሎችን በብቃት ማለፍ ይዛለች። ዛሬም ዓላማዋ ሩቅ፣ ዕቅዷ ሰፊ ነው። አሁን አራተኛን ተሻግራ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሆናለች። ለከርሞ ደግሞ የሚኒስትሪ ብሔራዊ ፈተና ይቆያታል።

ፊደል ከመለየት ያለፈው የወጣቷ ዕውቀት በብዙ ትልሞች ታጅቧል። ለእሷ ነገ ብሩህ ነው። በጥረቷ ብዙ ታይበታለች። ይህ እንዲሆን የዛሬ መንገዷ ተቃንቷል። እየሰራች ትማራለች። ሰላም አምስተኛ ክፍል እንደገባች አንዲት ሴት አገኘቻት። ይህችን ሴት አሳምራ ታውቃታለች። ልጅነቷ በእጇ ተቃኝቷል። የዛኔ ሕይወት በእሷ አጠገብ ሀዘንና ዕንባ ነበር። ስታሳድጋት በሙሉ ነጻነት አይደለም። ፍቅሯን ነጥቃታለች። ጉልበቷን ብትሻ ትምህርት ነፍጋታለች።

አሁን ፊት ለፊቷ የቆመችው ሴት ይህን የረሳች ይመስላል። ሰላምን መልሳ ለመውሰድ ማባበል ጀምራለች። ሰላማዊት የቀድሞ አሳደጊዋን አመነቻት። አብረው እንዲሄዱ በጠየቀቻት ጊዜ አልተቃወመችም። ሀሳቧን በይሁንታ ተቀብላ በመሄዱ ተስማማች።

አሁን ሰላም ሰባት ዓመታት የኖረችባቸውን መልካም ቤተሰቦች ልትሰናበት ነው። ዳር ያልደረሰው ትምህርቷ ከአምስተኛ ክፍል አላለፈም። ተመልሳ ወደገጠር ስትገባ ቅር አላላትም። አሳዳጊዋን ተከትላ፣ ልጅነቷን ካሳለፈችበት ‹‹ጊዲ ቤንች ዲዙ›› መንደር አመራች።

ኑሮ በዲዙ…

ሰላም ከሚዛን አማን ተመልሳ የገጠሩን ሕይወት ጀመረች። ኑሮ በሁለቱ ቦታዎች ይለያያል። የከተማ ቆይታዋ ብዙ አስተምሯታል። ሰርቶ ማደር፣ ጥሮ መቀየር እንደሚቻል አውቃለች። ዛሬ ዕድሜዋ እንደቀድሞው አይደለም። እሳቤዋ ተለውጧል። ዕውቀቷ ጨምሯል። እንደፊቱ በደልን የሚሸከም ትከሻ የላትም።

ዲዙና ሰላም ዳግም ተገናኝተው ሕይወት በልማዱ ቀጠለ። ውሎ አድሮ ከአሳዳጊዋ ጋር እንደታሰበው አልሆኑም። መሀላቸው መግባባት ጠፋ፣ ስምምነት ይሉት ታሪክ ሆነ። ይህኔ ሰላም ቆም ብላ አሰበች። ኑሮ እንዲህ ከሆነ ይከብዳል። ከዚህ በኋላ ሕይወት ከአሳዳጊዎቿ ቤት አይቀጥልም። አሁን የራሷን ትዳር መያዝ፣ ቤት መምራቱ እንደሚ በጅ ለ ውስጧ ነግራዋለች።

ዳግም በሚዛን…

አሁን ሰላም ሕይወት ክፉ ደግ አሳይቷታል። ከዚህ በኋላ ‹‹እከሌ›› የምትለው የቅርብ ሰው ጎኗ የለም። ሰባት ዓመታት ካሳለፈችበት ቤት ተመልሳ አትገባም። ብዙ የለፋችለት ውጥን ትምህርቷ ዳር ሳይደርስ ተቋርጧል። ሚዛን አማን ሰላምን ልትቀበል ፊት አላዞረችም። እንድትናንቱ እጇን ዘርግታላታለች። የአሁኑ ሕይወቷ ግን ብቻዋን አልሆነም። ለትዳር ካሰበችው ጓደኛዋ ጋር ኑሮን ጀምራለች። በሚዛን ግማሽ ዕድሜዋን የገፋችው ሰላም ለክፉ ደግ አጋጣሚዎች አዲስ አይደለችም። ሁሉን እንደአመጣጡ ችላ አቅሟ የፈቀደውን መስራት ችላበታለች።

የሶስት ጉልቻ ትኩሳት…

ሰላም ብቸኝነትን ሽሽት የጀመረችው አብሮነት ከትዳር አጋሯ አውሎ ያሳድራታል። ጥንዶቹ ጎጇቸው በልጅ በረከት ታድሶ የመጀመሪያውን ወንድ ልጅ ስመዋል። ኑሯቸው በአንድ ቢዘልቅም መሀላቸው ሰላም ይሉት የለም። መግባባት ርቋቸው በቅያሜ ያድራሉ።

ከመጀመሪያው ልጅ ሶስት ዓመታት በኋላ ሁለተኛው ሕጻን ተወልዷል። የእሱ መምጣት ብቻ ግን የቤቱን ሰላም አልመለሰም። አለመግባባቱ ቀጥሎ። ቅያሜው ብሷል። በዚህ ጅማሬ ያልገፋው ትዳር ወሎ አድሮ በፍቺ ሊቋጭ ግድ አለ። ባልና ሚስት ጎጇቸው ተፈታ፣ የአብሮነታቸው ገመድ ተበጠሰ።

ሕይወት ከልጆች ጋር…

ሰላም ባሏን ከፈታች ወዲህ የልጆቿ ኃላፊነት በእሷ ትከሻ ወድቋል። ሁለቱ ወንዶች ልጆች በልተው ለማደር፣ ተምረው ለመግባት ተስፋቸው እናት ብቻ ሆናለች። የተሻለ ሥራና ገቢ የሌላት ሰላም ዛሬም ከሚዛን አማን መሀል ልብ አልራቀችም። ያገኘችውን ሰርታ ልጆቿን ታጎርሳለች።

ሰላምን የኑሮ ውድነት፣ የቤት ኪራይ ችግር ይፈትናታል። ነፍስ ያላወቁ ልጆቿ የእሷን እጅ ናፋቂዎች ናቸው። ዛሬ እንደቀድሞው በሀያ አምስት ብር የሚሞላ ኑሮ የለም። ሁሉ ነገር ውድና ፈታኝ ሆኗል። ጊዚያት በጥረትና ሩጫ ተገፍተው ዓመታት ነጎዱ። ሰላም ልጆቿን ለማስተማር ደፋቀናውን ይዛለች።

ደግ አሳቢው ብላቴና…

የመጀመሪያ ልጇ ዛሬ ጎረምሳ ሆኗል። ከልጅነቱ አንስቶ ለእናቱና ለታናሽ ወንድሙ ሲያስብ ሲተክዝ ኖሯል። በዕድሜው የቀረበት የለም። እናቱ እየሰራች ታኖረዋለች፣ እየለፋች ታስተምረዋለች። ውሎ አድሮ ግን ይህን እውነት መሸከም ከበደው። የእናቱ ልፋትና ሩጫ ውስጡን ያሳዝነው ያደማው ያዘ። የዘወትር ሀሳቡ ከዕድሜው በታች አጫጭቶ አሳየው። በትካዜው ጉዞ አልቀጠለም። ትምህርቱን አቋርጦ የእናቱን ሸክም ሊያቀል ስራዎችን ፈላለገ። እንደሀሳቡ ሆኖ የልቡን አላጣም። እንጨት ቤት እየሰራ ታናሽ ወንድሙን ማስተማር፣ እናቱን መደገፍ ያዘ።

አንዳንዴ ወንድማማቹቹን የሚያስተውሉ ብዙዎች የትልቅነቱን መንበር ለታናሽ ወንድም ይሰጣሉ። የትልቁ የበዛ አሳቢነት ውስጡን ሰብሮት ቆይቷል። ትካዜው ማየሉ አካሉን ጎድቶታል። እንዲያም ሆኖ ያሰበውን ሊያደርግ አልታቀበም። ዛሬ የቤቱ ኑሮ በእሱ ላብ፣ በጉልበቱ ድካም ጸንቷል።

ትልቁ ልጅ ሁሌም ቢሆን ‹‹ለኔ›› ይሉትን አያውቅም። የእጁን አራግፎ ለቤተሰቡ ደስታ ያድራል። የእሱን ጥቅም ትቶ ለእነሱ ማለቱ ደግሞ አንዳች አላከሰረውም። በየቀኑ ምስጋና ልብሱ ነው። ዘወትር የእናቱ ምርቃት ይከተለዋል።

ጨሞ የቤቱ እህል ውሀ …

አማን ሚዛን በረከቷ ብዙ ነው። ለሚሰራ፣ ለሚለፋ የድካም ዋጋን አትነፍግም። ሰላማዊት ሕይወቷን ለመግፋት በሚዛን መንገድ ዳርቻ ውላ ታመሻለች። ይህ እውነት የየእለት ግዴታዋ ነው። እንዲህ ካልሰራች ኑሮ ይሉት የለም። ሕይወትን ለመምራት ልጆች አሳድጎ ለማስተማር በዚህ ቦታ መገኘት ግድ ይላል።

ሰላም ከማለዳ እስከ ምሽት የሚያዘልቃት ምክንያት ለደንበኞቿ ቀምማ የምትሸጠው ‹‹ጨሞ›› ነው። ጨሞ በአገሬው የሚዘወተር፣ እንደሻይ ተፈልቶ ‹‹ፉት›› የሚሉት መጠጥ። ጨሞ ለእሷና ለልጆቿ ባለውለታቸው ነው። የአንዱ ኩባያ በረከት ጎዶሎን ይሞላል፣ ችግርን ይፈታል፣ ኑሮን ይገፋል።

ጨሞ ከቡና ቅጠል የሚዘጋጅ ነው። እንደ ሻይ አፍልቶ በፍቅር ለመጠጣት ደግሞ ጥሩ ሙያን ይጠይቃል። ነጭ ሽንኩርት፣ ሚጥሚጣ፣ በሶብላ፣ ድንብላል ለጨሞ ጣዕም መፍጠር ወሳኝ ሆነው ይገባሉ። ይህን መጠጥ ሰላም ብቻ አትሸጠውም። ልክ እንደእሷ መተዳዳሪያ ሊያደርጉት የወደዱ በርካቶች ለገበያ ያቀርቡታል። አሁን ባለው ሸያጭ የአንዱ ኩባያ ዋጋ ከአምስት ብር አልተሻገረም። ሰላም አንዳንዴ ጨሞውን በቀን እስከ ሶስት መቶ ብር ትሸጣለች። እንዲህ ይቅናት እንጂ እንደምታስበው የረባ ተቀማጭ የላትም። መጠጡን ለማዘጋጀት በምትገዛቸው ቅመሞች መልሶ አቅሟ ይፈተናል።

ጨሞ ለእሷና ለልጆቿ ባለውለታ ነው። እሱን ሸጠው በሚያገኙት ገቢ ኑሯቸውን ይደጉማሉ። እሷ ባለቤቷን በፍቺ ከተለየች በኋላ ቋሚ መተዳደሪዋ ይኸው የተቀመመ የቡና ቅጠል ሆኗል። እርግጥ ነው ከልፋት አንጻር ዋጋው አይመጥንም። የአካባቢው ሽያጭ ተመሳሳይ መሆኑ ግን ሂሳብ ለመጨመር አላስቻላትም።

ቀና ልቦች…

በከተማው ወይዘሮ ሳላይሽን የመሰሉ ልበ ቀናዎች እነ ሰላምን ለመደገፍ ወደኋላ አይሉም። እንዲህ አይነት ሰዎች ሲበረክቱ የኑሮ ሸክም ይቀላል። ልክ እንደወይዘሮዋ ሁሉ የዓይኖችን ዕንባ የሚያብሱ፣ መልካም ሰዎች ከፊት ቀድመው ይገኛሉ። እናትና ልጆች ለዓመታት በኪራይ ቤት ኑሮ ተንከራተዋል። ኪራዩን አሟልቶ ለመስጠት እጅ ሲያጥር ደግሞ አንገት መድፋት፣ መተከዙ አይቀርም። አንዳንዴ ሰላም ሆድ ብሶ ሲመራት በከተማው ማዘጋጃ ቤት ደጃፍ ቆማ ዕንባዋን ታዘራለች። ይህን ከሚያዩት መሀል አንድ ወጣት ኃላፊ ሁሌም አብሯት ያዝናል፣ ያለቅሳል።

ይህ ከልብ የመነጨ ስሜት ውሎ አድሮ ለውጤት መድረሱ አልቀረም። ወጣቱ ለእሷና ለልጆቿ የቀበሌ ቤት እንዲያገኙ አገዛቸው። ዛሬ ሰላም ለአንገቷ ማስገቢያ ጎጆ አላት። ጨሞን ሸጣ ስትገባ በእፎይታ ፈጣሪዋን ታመሰግናለች። ጨሞ የእሷና የልጆቿ እህል ውሀ ሆኗል። እሷ በረከቷን አትንቅም፣ ዕለት በዕለት እሱን ሸጣ ነገን ተስፋ ታደርጋለች።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You