የአብሮነት ምኩራብ ያስፈልገናል

ኦሪታዊው ታራ በካራን የሚኖር ጣኦት አምላኪ ነበር። በቤቱም ለእውነትና ለክብር የሚሆን ስፍራ አልነበረም። ከሁሉም ትልቁን እውነት አጥቶ በማይረባ ሀሳብ የማይረባ ሆኖ የሚኖር ሰው ነበር። የእኛን ከሰላምና ከአብሮነት የራቀ አካሄድ ከዚህ ሰው ታሪክ ጋር አዛምጄ እስከመቼ በታራ ቤት ስል መጣሁ።

ሰው የሕልሙ ፈጣሪ እንደሆነ በርካታ ጠቢባን ይናገራሉ። በዚያው ልክ ሰው የመከራው ፈጣሪም እንደሆነ የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም። ሀገር በዜጎች ሀሳብ፣ በትውልድ የበጎነት ስንቅ እንደምትፈጠር ሁላችንንም የሚያግባባ የጋራ መረዳት አለ። በዚህ መረዳት ውስጥም ከዓለም የገዘፈች፣ ከሰው ልጆች የበረታች ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገር ፈጥረን እናውቃለን። ከትላንት መለስ ብለን አሁንን ስንቃኝ ግን ትግላችን እንደበፊቱ ለአብሮነት ሳይሆን የብቻ ቤትን ለመስራት የምንፈራገጥ ነው የሚመስለው። ደግሞም እውነት ነው ተንፈራግጠን ከአምና የተለዩ መልከ ውይብ ማንነትን ፈጥረናል።

እኛስ እስከመቼ በሞትና ጦርነት ውስጥ እንኖራለን? መቼ ነው ማብቂያችን? መቼ ነው እንደአብርሃም መጥፎውን ትተን ወደመልካሙ ስፍራ የምናቀናው? ለምንድነው ከንቱ ድካም የማይደክመን? የሕይወት ፈተናዎች ካለመግባባትና ከእርስ በርስ ግጭቶች የሚነሱ ናቸው። ይሄን ሀሳብ አጽንኦት ለመስጠት በሀገራችን የተነሱትን የዜጎች መፈናቀል፣ ስደት፣ ርሀብ፣ ተረጂነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የስጋት እንቅስቃሴ፣ የጸጥታ ችግር ሌላም ሌላም መጥቀስ ይቻላል። እኚህ ማኅበራዊ ፈተናዎች ባለመግባባትና ቁጭ ብሎ ባለመነጋገር ጦርነት መር በሆነ አስተሳሰብ የተፈጠሩ ስለመሆናቸው የማይረዳ የለም።

የበላይነት በሚንጸባረቅበት የአሸናፊነት መንፈስ ውስጥ ያለንን ከማጣትና ከመጣል ባለፈ የተቀዳጀነው ድል የለም። ዛሬም ድረስ የትላንትና የከዛ ወዲያ የአፋችንን ፍሬ እየበላን ነው። ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ውስጥ እንደሆኑ ታላቁን መጽሀፍ ቅዱስ ጨምሮ የተለያዩ የእውቀት አፎች ይነግሩናል። ግን አውቀንና ተረድተን ራሳችንን ከስቃይ ትውልዱንም ከጥላቻ አልታደግነውም።

ወደመፍትሄአቸው ስንመጣ የምናገኘው አንድ የድህነት አቅጣጫን ነው። እርሱም በመነጋገር አብሮነትን ማስቀጠል የሚለው ነው። ያሸነፍንባቸውም ሆኑ የተሸነፍንባቸው የወንድማማች ግፊያዎች ዛሬ ላይ ማናችንም ከፊት አላቆሙንም። አቁመውናል? ስለእውነት እናገራለው አላቆሙንም። ይልቅ ማንም ያልከፈለውን የመከራና የስቃይ ዋጋ እያስከፈሉን ነው። አሁናዊ ስቃዮቻችን፣ አሁናዊ መለያየቶቻችን አሸናፊና ተሸናፊ በሌለው የእርስ በርስ ግጭቶታችን የመጡ ናቸው።

ሀገርን መታደግ ሕዝብን መታደግ ነው። ሕዝብን መታደግ ደግሞ ትውልድን መታደግ ሆኖ ከፊት የሚመጣ ነው። እኚህ ሁሉ ልዩ መሳይ አንድ አይነት መልኮች ወደቀደመ ኢትዮጵያዊ መልክና ክብራቸው እንዲመለሱ ሄደን ሄደን የምንወድቅበት ሳይሆን ሄደን ሄደን የምንደርስበት የአብሮነት ምኩራብ ያስፈልገናል። ይሄ እንዲሆን ሀገር ባቀና የጨዋነትና የአንተ ትብስ ልማዳችን ተረከዝ እስከመያዝ በሚያደርስ የክብር መንፈስ ውስጥ በመነጋገር ወጥተን የምንገባበት የእርቅና የተግባቦት እውቀት ያስፈልገናል።

እንዲህ ካልሆነ የምንደርስበት ሩቅ የለም። እንዲህ ካልሆነ የምንደርስበት ህልምና ራዕይ የለንም። ፍቅርና አንድነትን ባጎደለ ምኞትና ሕልም ውስጥ የሚመጣ የተሀድሶ ለውጥ የለም። ሀገራዊም ሆኑ ግለሰባዊ ለውጦች በፍቅር ጀምረው በአንድነት የሚያበቁ ናቸው። ተለያይተንና ተራርቀን ንፋስ የገባባቸው ቀዳዳዎቻችን እንዲጠቡ የፍቅር አፎችና የእርቅ አንደበቶች ያሹናል። እንዴትም ብናስብ እንደ እኛ የተቀራረበ ሕዝብ የለም። የታሪኮቻችን መነሻና መድረሻ የአብሮነት ደማቅ ስምን የታከኩ ናቸው።

ከስልጣኔና ከዘመናዊነት ጋር የተያያዘ አንድ ድንቅ ጥበብ አውቃለው..‹ጊዜ የሰውን ልጅ አይቀይረውም› የሚል። ይሄን እውነት ለመረዳት ዝግ ማለት ግድ ይሆናል። በአሁኑ ሰዓት ዓለም በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ሁለት የተለያዩ ጽንፎችን የምታራምድ ናት። ሰው እንደተረዳው ነው። ማንነቱ፣ ታሪኩ፣ ሕይወቱ፣ ሕልሙ ሳይቀር ይሄን እውነት ተደግፎ የቆመ ነው። ምን ለማለት ፈልጌ ነው.. በየትኛውም የሕይወት መንገድ ላይ በጽናትም ሆነ በእንግድጋዴ የምንራመደው በገባን ልክ ነው።

ብዙዎቻችን ዘመንን በተመለከተ ሁለት አይነት አረዳድ አለን። ‹ጊዜ የሰውን ልጅ ይቀይረዋል› የሚልና ‹የሰው ልጅ ጊዜን ይገዛዋል› የሚል። በምንም የሕይወት ደረጃ ላይ እንሁን ሁላችንም ከዚህ እውነት ጀርባ የቆምን ነን። ከሁሉም የሚልቀው እውነት ጊዜ በሰው ልጅ ቁጥጥር ስር ነው የሚለው ነው። ይሄ እውነታ የገባቸው በጊዜ ውስጥ የሚቀይሩት ታሪክ፣ ማንነት፣ ባህል፣ ስርዐት የላቸውም። ማንነታቸውን ተቀብለው ወደፊት የሚራመዱ እግረ ለሞች ናቸው። ይሄ እውነታ ያልገባቸው ግን ትላንትን እየናቁ ዛሬን የሚያደንቁ፣ ታሪክና ማንነታቸው ኋላ ቀር እየመሰላቸው ምንም ባላወቁትና ባልተረዱት የሚደናበሩ ናቸው።

ይሄን እውነት ወደእኛ ስናመጣው ብዙ የትዝብት አክርማን መምዘዝ እንችላለን። ዓለም በሌለው ክብርና ነጻነት ውስጥ የቆምን፣ የሰላምና የአብሮነት ደሴት ተብለን የተደነቅን ሕዝቦች ስለምን ዛሬ ሌላ ሆንን? ከኢትዮጵያዊነት ውጪ ሌላ የማናውቅ፣ ተጨማሪ ስምና መጠሪያ የሌለን ሕዝቦች ዛሬ ስለምን በማይረቡ እልፍ ስሞች ተከበብን? ተመካክሮ በጥቅምት እኩሌታ ወራኢሉ የከተመ፣ ተግባብቶና ተስማምቶ በኦጋዴንና በካራማራ የቆመ ሕዝብ ስለምን ዛሬ ሰላም ራቀው? ባህር ማዶ ተሻግሮ ስለሌላው ሰላም የሞገተ፣ ስለሌላው ነጻነት የተከራከረ ሕዝብ ስለምን ሰላም ናፋቂ ወጣው? ሊቀ ነብያት ሙሴን ያበረቱ ዮቶራዊ አፎች፣ የግሪክ ጸሀፍቶች በድርሰቶቻቸው ያሞካሿት ኢትዮጵያ ስለምን ዛሬ ክብር ራቃት?

“ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይቀይርም “ሲል አምላክ በቃሉ ያወሳት ምድር፣ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደእግዚአብሄር ትዘረጋለች ሲል የእምነቷን አጽናፍ የመሰከረ ቅዱስ አፍ ዛሬ ስለምን እንዳልነበረች ሆነች? ስለሀገሬ ጥቂቱን ተናገርኩ እንጂ ጥንተ ብኩርናዋንና ገናናነቷን የሚናገሩ እልፍ የታሪክ ሰነዶች አሉ። ዛሬ ለምን ምንም ሆንን? ስለምን ቀለልን? ስለምን ከክብራችን ተንሸራተትን?

ጥያቄዎቻችን ወደ አንድ አቅጣጫ ነው የሚመሩን..የጥንቱን ባህል ስለመሳት፣ መጤ በሆኑ አጉል አስተሳሰቦች ስለመወሰድ ነው የሚነግሩን። ራስወዳድነትንና ከየት እንደተማርነው የማናውቀውን እኔነትን ነው የሚገልጡልን። በብሄርና በዘር ተቧድነን ጣት ቀሳሪነታችንን ነው የሚነግሩን። ለማንም የማይበጅ የኃይልና የእልኸኝነትን ብርታትን ነው የሚያሳብቁን። ታሪክ ማጣመምን፣ እውነትን መሸሽን ነው የሚነግሩን። በትርክት መሽመድመድን፣ በሀሰት መለያየትን ነው የሚጠቁሙን። ተነጋግሮ አለመግባባትን፣ ተወያይቶ አለመስማማትን ነው የሚነግሩን። ለፍቅርና ለይቅርታ የተዘጉ ልቦቻችንን ነው የሚያስታውሰን። ከባህልና ከስርዐት ያፈነገጠ ጊዜ ወለድ ማንነታችንን ነው የሚያንጸባርቁልን።

እስከመች አንቀላፍተን፣ እስከመች የራሳችን ጠላቶች ሆነን እንዘልቀዋለን? የጦርነት ነጋሪት ስንጎስም፣ አታሞ ስንመታ እዚህ ደርሰናል። እስኪ ደግሞ በፍቅር ድካሞቻችንን እንርሳ። ተነጋግረንና ተፈቃቅደን ችግሮቻችንን ካልፈታን የጥንቱን አብሮነት የምንመልስበት ሌላ ሁነኛ መላ የለንም። ከድካሞቻችን ለመበርታት ብቸኛው መዳኛችን እርቀ ሰላም ነው። በእርቅ ሰላም ማውረድ ለእኛ አዲስ ነገራችን አይደለም። ስናስታርቅና ስንመክር፣ ስንገስጽና ስናስተቃቅፍ የኖርን ለዘመናዊው ዓለም ፋና ወጊ የሆንን የስርዐት ቀደምቶች ነን። ልባችንን በእልህና በክፋት ዘግተንው እንጂ ለዛውም ከወንድሞቻችን ጋር፣ ለዛውም አብሮ ከበላና አብሮ ከተዋለደ ሕዝባችን ጋር መተቃቀፍ አይከብደንም ነበር።

አሁን ላይ የሰላም መንገዶቻችንን የዘጉብን የኃይል አስተሳሰቦች ዘመን አመጣሽ ወይም ደግሞ ከዚህ የተሻለ ስም የሚሰጣቸው ናቸው። እንጂማ ማንና ምን እንደነበርን የምናውቅ ነን። ጥንተ መሰረታችን ፍቅርን አምጦ የወለደ ማህጸን፣ አንድነትን አቅፎ ያሳደገ ክንድ ነው። ጥንተ ማንነታችን አብሮነትን እሽሩሩ ያለ፣ ኢትዮጵያዊነትን ያስቀደመ ሀሳብ ነው። ዛሬ በጥላቻና በመለያየት ቆሽሸን የቆምነው አንደበቶቻችን እብለትን፣ እጆቻችን ግፍን፣ ልቦቻችን ጥላቻን ስለተለማመዱ ነው።

በጥላቻ የቆመ ትውልድ እንደ ሎጥ የክብር መንገድ የለውም። በመለያየት የቆመ ሕዝብ እንደ አብረሀም የበረከት ቤት የለውም። ሎጥ ከሰዶም ሲወጣ፣ አብረሀም ከካራን ሲጠራ በፍቅር ልብ በኩል ነው። እኛም የፍቅር ልብ ያስፈልገናል። ከድህነትና ከኋላቀርነት ብሎም ጦርነት እያስከፈለን ካለው አበሳ ለመራቅ ምክክርን እንደሁነኛ አማራጭ ልንቀበለው ግድ ይለናል።

ልዩነት ለምን ተፈጠረ ሳይሆን ልዩነትን እንዴት ማጥበብ እንዳለብን ማወቁ ነው የሚበጀን። ለውይይት ቢሮውን የከፈተ ባስልጣን፣ ለምክክር ፖለቲካውን ያዘጋጀ ፓርቲ ለሀገር ጥፋት የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ለእርቅና ለተግባቦት የተዘጋጀ ማህበረሰብ የልዩነት ጥዶች አዳልጠው አይጥሉትም። የእርቅና የሽምግልና ማኅበራዊ እሴቶቻችን አንድነትን ከማጠንከር ጎን ለጎን አብሮነትን ከማስቀጠል አኳያ የጎላ ድርሻ ነበራቸው። አሁንም ወደዛ የስልጣኔ አፋፍ ለመመለስ ሕዝባዊና ፖለቲካዊ ውይይት ክብር መላሽ ሆኖ ከፊት የሚመጣ ነው።

የሩዋንዳና የደቡብ አፍሪካን የብሄራዊ ምክክር አውድ ስንቃኝ መነሻው የልዩነት ጽንፍ ሆኖ መድረሻው ደግሞ ሀገራዊ ውጥንቅጥ ነበር። በሄዱበት ሁሉን አካታች የምክክርና የውይይት ቅብብሎሽ ችግራቸውን ቀርፈው ሀገራቸውን ወደሰላማዊ ይዞታዋ መመለስ የቻሉበትን ሁኔታ ማስታወስ ይቻላል። በእኛም ሀገር ተመሳሳይ ነገር ስለመንጸባረቁ የኮሚሽኑ ዓመታትን የዘለቀ ዝግጅት ጥቁምታን የሚሰጥ ነው። በሰፊ መድረክ፣ በሰፊ ተሳትፎ ሰፊዋን ሀገራችንን ከአስተሳሰብ ጥበት ለማውጣት እየተሰራ ያለው ስራ የሚደነቅ ሲሆን በእንዲህ አይነቱ አካታችና አሳታፊ፣ ገለልተኛና ነጻ መድረክ ፊት ካልሆነ ወደሰላም የሚያስገባን ቀዳዳ እንደሌለም የሚታመን ነው።

ብሄራዊ ምክክሩን ከሀገራችን አልፈን አውዱን አፍሪካዊ ለማድረግ እየተሰራም እንደሆነ ከኮሚሽኑ በኩል የተሰማ ሰሞነኛ መግለጫዎች ያሳያሉ። ለአንድነት በአንድነት ስንቆም ሰፍተን እንደምንገዝፍ ብዙ ያለፉ ታሪኮቻችን ምስክሮች አሉን። ከእኛ የማሰብና የመዋሃድ አቅም አንጻር ሲታዩ ችግሮቻችን እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም። የሰላም መንገዶቻችንን የዘጉብን እውቀት ማነስ ሳይሆን ለፍቅር አለመሸነፋችን ነበር።

ታሪክና እሴት፣ ወግና ልማድ የሳተ ፖለቲካ ለሀገር አይበጅም። በታላላቅ ባህልና ስርዐት ውስጥ በቅለን ፍሬ አልባ ዛፍ የሆነው ርካብ በሳተ ርምጃችን ነው። ሀገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ትልቁ ብቃታችን ሊሆን የሚገባው በምንም የማይሸራረፍ የአብሮነት መንፈስ ነው። ቀጣይ በሚኖረን የእርቅና የተግባቦት መድረክ ላይ እንዲህ አይነቱን መንፈስ በማራገብ ልዩነቶቻችንን ማጥበብ እንችላለን።

ሕይወት የአረዳድ መልክ ነው። እየኖርን ያለነው በተረዳነውና በገባን ልክ ነው። አረዳዳችንን ከኃይል ይልቅ ለሰላም፣ ከጥላቻ ይልቅ ለፍቅር እስካላስገዛን ድረስ ሕልሞቻችን ፍሬ አይቋጥሩም። በአንዳንድ ትርክቶችና አንድነት ጠል ቡድኖች ከመነሻችን ሸሽተን ሌላነትን እየተለማመድን ነው። ከእውነታ የራቀ አረዳድ ትርክት ከማድመጥ ባለፈ ትርክት የማጥራት አቅም የለውም። በሀሰትና በማስመሰል እውቀት ጥራዝ ነጠቆች ሆነን ትውልዱን እየመረዝን ያለነው ባልገባን እውቀት ነው።

አንዳንድ ነፍሶች አሉ..እጅግ በሰለጠነ ዓለም ላይ ቆመው ኢትዮጵያዊነት ያልጠፋቸው። ሀበሻነት ያልተዘነጋቸው። አንዳንድ አእምሮዎች አሉ በዚህ ማንነትን በሚያስት ጊዜ ላይ ተወልደው ታሪካቸውን ያረሱ፣ የመጡበትን ያልተው። አራዳነት ይሄ ነው። ኢትዮጵያዊነት መንፈሱ ይሄ ነው። ዓም እኛን ለመሆን በምትጥርበት ዘመን እኛ ከብቻነት በቀር ምንም የሌላቸውን አውሮፓውያንን ለመሆን የምናደርገው ጥረት እንደ ማንነታችን የሚያስተዛዝበን ነው።

በወሬ ሳይሆን በተግባር፣ በትርክት ሳይሆን በታሪክ ሀገር እንፍጠር። በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር፣ በመለያየት ሳይሆን በማበር ትውልድ እንታደግ። መጪውን ጊዜ በዚህ ለሁላችንም በሚበቃና በሚበጅ እውነትና እምነት፣ ሀሳብና ተግባር ስንቃኘው ብቻ ነው በአዲስ አረዳድ ወደፊት የምንቀሳቀሰው። በቀደመ ሀሳብ ኢትዮጵያን ካላስቀደምን ሌላ የፊተኝነት ሰርጥ የለንም።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You