የኢትዮጵያውያን መገለጫ እየሆነ የመጣው አረንጓዴ ዐሻራ

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡ በዘመቻ እየወጣ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን ማከናወን ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ነገር ግን የሥራውን ያህል በመላ ሀገሪቱ አመርቂ ውጤት መጥቷል ለማለት አያስደፍርም። በተለይም ክረምትን ጠብቆ በቁጥ ቁጥ የሚካሄደው የችግኝ ተከላው ለይስሙላ የሚካሄድ በመሆኑ ተጨባጭ ውጤቶችን ሳያመጣ ቆይቷል።

ከአምስት ዓመታት ወዲህ የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ሥራ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ያገኘ በመሆኑና የኢትዮጵያውያን ብርቱ እጆች በጽናት ታሪክ ለመሥራት ቆርጦ የተነሱ በመሆኑ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የችግኝ ተከላ ለዓመታት ሳያሰልስ መቀጠሉ አዎንታዊ ውጤት እንዲያመጣ አስችሏል ። በተለይም ከቁጥ ቁጥ አካሄድ ወጥቶ ባለፉት አራት ዓመታት 32 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ መትከል መቻሉ የስኬቱ አንዱ ማሳያ ነው።

በብሔራዊ ደረጃ የአረንጓዴ ዐሻራ ማስጀመሪያ ቀን መኖሩን፤ እያንዳንዱ ክልልም በየበኩሉ የችግኝ ተከላውን ቀን ማወጁ፤ የችግኝ ተከላዎቹ በየጊዜው መሪ ቃል አንግበው መነሳታቸው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ ሰፊ ሕዝባዊ ንቅናቄ እንዲፈጥር አስችሎታል። በዚህም የተነሳ በሕዝቡ ውስጥ ሰርጾ እንዲገባ እና ሁሉም በያገባኛል መንፈስ እንዲሠራም አስችሎታል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ተፈጠረው ስሜት የተተከሉትን ችግኞች ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ እንዲንከባከብም መነሳሳትን ፈጥሮለታል ።

ይህ እንደ ሀገር የያዝነው ችግኝ ተከላ የሚደገፍና የአየር ንብረት ለውጡ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ውጤትም አዎንታዊ እንደሚሆን የዘርፉ ባለሙያዎች የሚስማሙበት ሃቅ ነው፤ ከሙያው ውጪ ያለነውም ብንሆን ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ ያለውን የአየር ንብረት ሁኔታ ብሎም ከዓመት ዓመት ያለውን የአየር ጸባይ ለውጥና መስተካከል በማየት ውጤቱን መረዳት አይከብደንም።

የአረንጓዴ ልማት ሥራው በተጠናከረ ሁኔታ በተጀመረባቸው ጥቂት ዓመታት ውስጥም ኢትዮጵያውያን ስለ ጥቅሙ ተረድተው ከጫፍ ጫፍ በነቂስ ወጥተው ባደረጉት የችግኝ ተከላ መርሀ ግብርም በአንድ ጀምበር ብቻ ከ 669 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል ዓለምን ጉድ ማሰኘት የቻለ ጀብዱም ፈጽመዋል። ይህንን ምርጥ ተሞክሮ በማስፋት ዘንድሮም ከዚህ በላይ ሰርተን ውጤት በማስገኘት ለወዳጆቻችን ደስታን እምነት ላልጣሉብን ደግሞ ግርምትን ማጫር የሁላችንም የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል።

በዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ 92 ሺህ ሄክታር ደን ይጨፈጨፍ እንደነበር የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ ድርቅ እንዲከሰት ምክንያት ሆኖም ቆይቷል ። ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ተጋላጭ የሆኑት ዘርፎችም በተደጋጋሚ ሲጎዱ ተስተውለዋል። የዝናብ ጥገኛ የሆነው የግብርናው ዘርፍ፤ የውሃ አቅርቦቱ፤ ቱሪዝምም ሆነ የደን ይዞታው በአየር ንብረት ለውጡ ክፉኛ ሲጎዱ ቆይተዋል። ይህንኑ ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት ከፍተኛ በጀትና ሰው ኃይል በማሰማራትና በመመደብ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ፕሮጀክት ይፋ አድርጎ ላፉት አራት ዓመታት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። እስከ አለፈው አመት መጨረሻ ድረስም 32 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል ዓለምን ጉድ ማሰኘት ተችሏል።

ኢትዮጵያውያን አረንጓዴ ዐሻራን ባህል እያደረጉት መጥዋል። ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሯ በየአመቱ ብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል በዓለም ላይ ታዋቂ ሀገር ሆናለች ። በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ ተይዞ ሁሉም የድርሻውን ለመወጣትና ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ተፍ ተፍ ማለ ት ጀምሯል።

የግብርና ሚኒስቴር መረጃም እንደሚያሳየው ለመርሃ ግብሩ እስካሁን የተዘጋጀው ችግኝ ከታቀደው በላይ ነው ። ይህም የችግኝ ተከላውን ከእቅዱ በላይ ለመፈጸም መንደርደሪያ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ችግኞቹን ለመትከል የሚያስችለው የቦታ ዝግጅትም በመላው ሀገሪቱ 900 ሺ የሚሆን ሄክታር መሬት ስለመዘጋጀቱም ተነግሯል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ንቅናቄው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ በሚቻልበት አማራጭ ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ ከፍ ያለ ከመሆኑ አንጻርም ዘንድሮ ሊተከል ከታሰበው ችግኝ 60 በመቶ የሚሆነው ፍራፍሬና መኖ እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህም አርሶ አደሩ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኝበትን አማራጭና ገበያን ማረጋጋት የሚቻልበትን ሁኔታም ስለሚፈጥር ይበል የሚያሰኝ ነው።

በአብዛኛው የፍራፍሬ ችግኞች ላይ ትኩረት መደረጉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፤ የሥርዓተ ምግብ ሽግግር ለማድረግ፤ ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማስገኘት በተለይም ምርቶቹን ወደ ውጭ በመላክ ለሀገር ከፍ ያለ የውጭ ምንዛሪ በማምጣትም ጥቅሙ ከፍ ያለ ነው።

እንደሀገር በአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ እስከአሁን በተሠራው የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ በአብዛኛው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ፍራፍሬዎች ላይ ትኩረት ተደርጓል ውጤቱንም አይተናል፤ በዚህ ሀገራችን በአቦካዶ ምርት በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃን እንድትይዝ በር ከፍቷል። በሌሎችም ፍራፍሬዎች ላይም ተመሳሳይ ውጤት ለማምጣት መስራት ደግሞ ይጠበቅብናል።

ከሁሉ በላይ ደግሞ የዘንድሮው የችግኝ ተከላ ስራችን ለየት ያለ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ተነግሯል፤ እንደ አለፉት ዓመታት በርካታ ችግኞችን በአንድ ቀን ተከልን ብለን ከማለፍ ባሻገር በተለይም በነሃሴ ወር ላይ የምንተክለው ችግኝ ኢትዮጵያን በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ያስቀምጣታል የሚል እቅድ ተይዟል። ያለፉት አራት ዓመታት ልምዳችን እንደሚያሳየንም የታቀደውን ለማሳካት ምንም የሚገድ ነገር የለም።

በአንድ ጀንበር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች በመትከል በድንቃድንቅ መዝገብ ላይ የመስፈር ጥረታችን የአንድ ወገን ጥረት ብቻ ሳይሆን የመላው ሕዝብ ብሎም ክልሎችና ሌሎችንም ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑንም መገንዝብ ያስፈልጋል። በዚህ ልክ ተንቀሳቅሰን ግባችንን መምታት ከቻልን ደግሞ ሀገራችን በእስከ አሁኑ ሂደት ትታወቅባቸው የነበሩ የርሃብና የጦርነት ታሪኮች ሁሉ ይፋቃሉ ማለት ነው።

አረንጓዴ ዐሻራ እኛን በዓለም አደባባይ ከፍ ብለን እንድንታይ ከማድረግም በላይ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ጥቅምንም ያነገበ ነው። ብዙ ችግኝ ተክለን የዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስንሰፍር ጎን ለጎን ደግሞ በተከልናቸው ዛፎች አካባቢያችንን ከበርሃማነት መከላከል በተከልናቸው ፍራፍሬዎች ደግሞ በምግብ እህል ራሳችንን ከመቻል ጀምሮ ለዓለም ገበያ አቅርበን ዶላር በማግኘቱም በኩል ሚናው የላቀ ነው፡፡

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You