ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ላለፉት 42 ዓመታት አገራቸውንና ህዝባቸውን ያገለገሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን የህይወት ታሪክ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ጠቅላይ የጦር ኃይሎች አዛዥ፣ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ ፣የክልሎች ርዕሰ መስተዳድር ፣ሚኒስትሮች፣አምባሳደሮች መላው የመከላከያ ሰራዊት አባላት፡፡የጀግኖች ቤተሰቦች የሰማዕታት ቤተሰቦች ኮሎኔል ጽጌ አለማየሁ፣ወይዘሮ አበባ ዘሚካኤል እና ልጆቻቸው፣ ቤተዘመዶች በሙሉ በተገኙበት በሚሊኒየም አዳራሽ በተደረገው ስንብት መርሐ ግብር እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ጀነራል ሰዓረ መኮንን ከአባታቸው ከአስር አለቃ መኮንን ይመር እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ህይወት ይህደጎ ተድላ በትግራይ ክልል በሰሜን ምዕራብ ዞን አስገደ ጽንብላ ወረዳ በእንዳባጉና ከተማ በ1954 ዓ.ም ተወለዱ፡፡እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በእንዳባጉና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 6ኛ፣የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ሽሬ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡በወቅቱ አስከፊውን የደርግ ሥርዓት ለመገርሰስ በህወሓት በሚመራው የትጥቅ ትግል የሚካሄድበት ስለነበር የትጥቅ ትግሉን ተቀላቀሉ፡፡ወቅቱም 1969 ዓ.ም ነው ፡፡
ቡምበት በሚባል የስልጠና ማዕከል ውስጥ ገብተው ስልጠናቸውን ካጠናቀቁ በኋላም 1969 እስከ ታህሳስ 1971 ዓ.ም ድረስ በህወሓት 91ኛ እና 73ኛ የሚባሉ ሻምበሎችን በተራ ተዋጊነትና በጓድ አመራርነት በተለይም በ1970 ዓ.ም ክረምት ደርግ ባካሄደው የሰሜን ዘመቻ በተለምዶ ሶስተኛ ተብሎ በሚጠራው ዘመቻ የደርግ ዘመቻን በመመከት በጀግንነት ተዋግተዋል፡፡
ከታህሳስ 1971ዓ.ም እስከ ታህሳስ 1972 ዓ.ም ድረስ በህወሓት የተደራጁ የታጠቀ ፕሮፖጋንዳ አሀዱ በተለምዶ ‹‹ክብሪት›› በሚባለው የጋንታ አመራር ሆነው ግዳጃቸውን በብቃት ተወጥተዋል፡፡ ከታህሳስ 1972 እስከ ግንቦት 1973 ዓ.ም ድረስ 573 እና 753 ሻለቆች ውስጥ የሻምበል መሪ በመሆን የተሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት ተወጥተዋል፡፡
ጀነራል ሰዓረ መኮንን ከ1974 እስከ 1975 ዓ.ም ድረስ በብርጌድ 43 ውስጥ የሻለቃ አመራር በመሆን፣በኤርትራ የደርግ ሰራዊት የሻዕቢያ ሰራዊትን ለመደምሰስ ባካሄደው የቀይ ኮከብ ዘመቻ ለመከላከልና ለመቀልበስ እጅግ አኩሪና አስደናቂ ጀግንነት ከፈጸሙት አመራሮች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡
ከጥር 1974 ዓ.ም 1977 ዓ.ም በብርጌድ 43 እና 45 የሻለቃ አዛዥ እንዲሁም በ1978 ዓ.ም የብርጌድ 77 ምክትል ብርጌድ አዛዥ በመሆን በራያ አካባቢ ደርግ ያካሂዳቸው የነበሩ ተደጋጋሚ ዘመቻዎችን በመመከትና በልዩ ስምሪቶች ማለትም የታጋዮች ልዩ ጽናትን በፈተነው የሰርዶ ልዩ ስምሪት በጽናት በመምራት፣ ጥር 30 ቀን 1978 ዓ.ም ከመቐለ ከተማ የደርግ ወህኒ ቤት ውስጥ አንድ ሺ 300 እስረኞችን ነጻ ባወጣ ታሪካዊ የአግአዚ ኦፕሬሽን ብርጌድ ምክትል አዛዥ በመሆን ግዳጃቸውን በጀግንነት የፈጸሙ አርበኛ ናቸው፡ ፡ከ1979 እስከ 1981ዓ.ም የብርጌድ 70 አዛዥ ሆነው በ1980 ዓ.ም ዓመቱን ሙሉ በተካሄደው ተከታታይ ዘመቻ ብሩህ በሚል በተሰየመ ሙጉላት፣ስንቃጣ ውቅሮ፣ ገለበዳ ድረስ፣ ዘመቻ ደልድል በሚል የሚታወቀውን 17ኛ የደርግ ክፍለ ጦር በመደምሰስ አክሱም፣አድዋ፣ሽሬ ከተሞችን ነጻ ያወጣ ዘመቻ፣ ጥሙር ቅልጽም /የተባበሩት ክንድ/ ዘመቻ በሚል የሚጠራ ከኮረም እስከ አምባላጌ የደርግ አንደኛ ክፍለ ጦርን ለመደምሰስ በተደረጉ ውጊያዎች በተለይም ልዩ ጀግንነትና ብቃት ይጠይቅ በነበረው የአምባላጌ ውጊያ በብቃትና በጀግንነት ብርጌዳቸውን በመምራት ለድል ያበቁ ምርጥ ታጋይ ነበሩ፡፡
ከመስከረም 1981 ዓ.ም እስከ ግንቦት 1983 ዓ.ም የደርግ ሥርዓት እስኪወድቅ ድረስ የአውሮራ ክፍለ ጦር አዛዥ በመሆን፣ ከመስከረም 1981 ዓ.ም እስከ የካቲት 12ቀን 1981 ዓ.ም ሽሬና አካባቢው መሽጎ የነበረውን የደርግ 604ኛ ኮርን በተከታታይ ውጊያዎች አዳክሞ ለመደምሰስ የተደረጉ ውጊያዎች እንዲሁም አብዛኛው የትግራይ መሬት መቐለ ከተማን ጨምሮ የደርግ ሰራዊት ለቆ ከወጣ በኋላ ከነሐሴ መጨረሻ እስከ ጳጉሜ 1981 ዓ.ም ሰላም በትግል ዘመቻ ተብሎ በሚጠራው ከማይጨው እስከ ጎብዬ በተደረገው የደርግ 605ኛ የመደምሰስ ዘመቻ እና ለአንዴና ለመጨረሻ ትግራይን ነጻ ያወጣ ዘመቻ ክፍለ ጦራቸውን በብቃት በመምራት ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡
ከመስከረም 1982 ዓ.ም እስከ ጥር 1982 ዓ.ም ፋና ኢህአዴግ ተብሎ በሚጠራው መላ ደቡብ ወሎን ከፊል ሰሜን ሸዋንና ደቡብ ጎንደርን ነፃ ያወጣ ዘመቻን እንዲሁም ከፍተኛ ፅናት የጠየቀውን የጉና የመከላከል ውጊያ፣የደብረታቦር የማጥቃት ውጊያ ክፍለ ጦራቸውን በብቃት መርተው ለድል አብቅተዋል፡፡
በመጨረሻዎቹ የ1982 ዓ.ም ደርግ ይመካበት የነበረውን ሶስተኛ ክፍለ ጦርን ለመደምሰስ ሰሜን ሸዋ መራኛ ላይ በተደረገ ውጊያ በከፍተኛ ብቃት መርቷል ፤ለድልም አብቅቷል፡፡ በ1983 ዓ.ም አጋማሽ ዘመቻው ዋለልኝ ደሴና ከፊል ሰሜን ሸዋን ነጻ ለማውጣት በተደረገው ውጊያና ዘመቻ ወጋገን ተብሎ በተሰየመው የደርግን ሥርዓት ለመደምሰስ በተደረገው ተከታታይ እና አንጸባራቂ ድሎች እየታጀቡ ክፍለ ጦራቸውን መርተው እስከ ኦጋዴን የዘለቁ ጀግና የህዝብ ልጅ ነበሩ፡፡
ከደርግ ስርዓት ውድቀት በኋላ በሽግግር መንግስት ወቅት በኢህአዴግ ሀገራዊ የሰራዊት አደረጃጀት መሰረት የምሥራቅ ዕዝ ዘመቻ ኃላፊ በመሆን እንዲሁም ከየካቲት 1987 ዓ.ም በኢፌዴሪ የሀገር አቀፍ የሰራዊት ምስረታ የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ በመሆን ሀገራዊ ተልዕኳቸውን በብቃት ተወጥተዋል፡፡
በግንቦት 1990 ዓ.ም የኤርትራ መንግስት ሀገራችንን በወረረበት ወቅት የቡሬ ግንባር አዛዥ በመሆን የሀገራችንን ዳር ድንበር አስከብረዋል፡፡ በየካቲት 1991 ዓ.ም የኤርትራን ሰራዊት ከባድሜ ነጻ ባወጣው ዘመቻ ፀሀይ ግባት የባድሜ ግንባር ግራ ክንፍ አዛዥ በመሆን ዘመቻው እስኪጠናቀቅ አኩሪ ገድል ፈጽመዋል፡፡
ከ1992 ዓ.ም እስከ 1994 ዓ.ም የ107ኛ ኮር ዋና አዛዥ በመሆን ከ1994 ዓ.ም እስከ 1997 ዓ.ም የአርማሃንድ የሰሜን ግንባር ዋና አዛዥ በመሆን፣ከ1997 እስከ 2006 ዓ.ም የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ በመሆን ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት አገልግለዋል፡፡
ጀነራል ሰዓረ ከትጥቅ ትግሉ እና ከመደበኛ ሰራዊት ግንባታ ያገኙትን ዕውቀትና ልምድ ተጠቅመው በተለይም ሰራዊቱን በወታደራዊ ሳይንስ እና ጥበብ የተካነ እንዲሆን የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ሚናቸውን በይበልጥ እንዲጫወቱ ለማድረግ ከ2006 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በዚህም በትምህርትና ስልጠና ተቋማት በሰራዊት ግንባታችን ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ በብቃት የመሩ ጀነራል መኮንን ነበሩ፡፡
ጀነራል ሰዓረ ለረጅም ዓመታት የመከላከያ ካውንስል አባል በመሆን የመከላከያ ሰራዊታችን ህዝባዊ ወገንተኝነቱ ተጠብቆ ተልዕኮውን በአስተማማኝ ሁኔታ መወጣት የሚችል ሰራዊት ግንባታ ላይ ጉልህ ሚና የተጫወቱ ከመሆኑም ባሻገር በሀገር አቀፍ ደረጃ የሴኩሪቲ ካውንስል አባል በመሆን ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በሀገራችን አስተማማኝ ሰላም ለመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡
ጀነራል ሰዓረ በነበራቸው የአመራር ብቃት ከመጋቢት 2010 ዓ.ም እስከ ግንቦት 2010 ዓ.ም የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም በመሆን፣ ከግንቦት 2010 ዓ.ም ጀምሮ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም በመሆን የተሾሙ ሲሆን በዚህ ወቅት በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች አለመረጋጋት እና የህዝብ መፈናቀል የነበረበት በመሆኑ በአብዛኛው የሀገራችን አካባቢዎች ሰራዊታችን አሰራርን ተከትሎና ህዝባዊ ባህሪውን ጠብቆ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በማድረግ ህዝባችን በሰላም ወጥቶ እንዲገባ በማድረግ ሂደት የመሪነት ሚናቸውን ተጫውተዋል፡፡
የሀገራችንን የለውጥ ክስተት ተከትሎ በርካታ ውስብስብ ሁኔታዎች መከሰታቸው ይታወቃል፡፡ የእርሳቸው የመከላከያ ተቋም ጠቅላይ ኢታማጆር ሹምነት ከዚህ ጋር መያያዙ ደግሞ ኃላፊነታቸውን ድርብርብ አድርጎታል፡ ፡ በአንድ በኩል የውስጥ የጸጥታ ሁኔታን ማስተካከል በሌላ በኩል ደግሞ ተቋሙን ሪፎርም ማድረግ ነበር፡፡ የኢፌዴሪ መከላከያ ኃይልም በሁሉም የጦርነት አውዶች ተልዕኮውን በአስተማማኝ ሁኔታ መወጣት የሚችል ጠንካራ ዘመናዊ ሰራዊት አድርጎ ለመገንባት የሪፎርም ሥራ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ይህ የሪፎርም ሥራ ሲጀመርም ሀገራችን በበርካታ አካባቢዎች የጸጥታ መደፍረስ የሚታይበት ነበር ፡፡ ይሁን እንጂ ጀነራል ሰዓረ በአንድ በኩል በሀገራችን የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት እና ሰላምን ወደ ነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ በዚሁ ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ደግሞ ተቋማዊ ሪፎርም በማቀድና በመምራት የመሪነት ሚናቸውን ተወጥተዋል፡፡
ጀነራል ሰዓረ የመከላከያችን የሪፎርም ሥራ በተፈለገው መንገድ እና በውጤታማነት እንዲቀጥል ከማድረግ አንጻር በብዙ ጫና እና ተግዳሮት ውስጥ በማለፍ ከምንም በላይ ለውጡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን ፋይዳ በማስቀደም የበኩላቸውን ድርሻ ያበረከቱ ጉልህ ሚና የተጫወቱ ዕንቁ ኢታማዦር ሹም ነበሩ፡፡
ጀነራል ሰዓረ መኮንን በነበራቸው ከፍተኛ ተቋማዊ አስተዋጽኦ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሲመሰረት ከ1988 ዓ.ም የሙሉ ኮሎኔልነት ጀምሮ በ2010 ዓ.ም የሙሉ ጀነራልነት ማዕረግ የደረሱ ሲሆን፣ የትጥቅ ትግል ተሳትፎ አንደኛ ደረጃ የወርቅ ሜዳሊያን ጨምሮ በርካታ ሜዳልያና ኒሻኖች ከኢፌዴሪ መንግሥት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ጀነራል ሰዓረ በነበራቸው ከፍተኛ የመማርና እራስን በትምህርት የማሳደግ ፍላጎት ትምህርታቸውን በመቀጠል በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በለንደን ግሪን ዊች ዩኒቨርሲቲ በኢንፎርሜሽናል ሊደር ሺፕ የትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ የማንበብ ልምድ የነበራቸውና ሌሎች እንዲያነቡ የሚገፋፉ ምሳሌ የሆኑ መሪ ነበሩ፡፡
ታጋይ ጀነራል ሰዓረ መኮንን በወጣትነት ጊዜያቸው ወደ ትግል ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ሙሉ ህይወታቸውን ለህዝብ የሰጡ ለህዝብ የታገሉ ስለግላቸውና ቤተሰባቸው ሳይጨነቁ ለህዝብ ሲጨነቁና ሲታገሉ የኖሩ ለህዝብ ህይወታቸውን የሰጡ አኩሪ የህዝብ ልጅ ነበሩ፡፡
ታጋይ ጀነራል ሰዓረ መኮንን በትግል ወቅትም ሆነ በህገ መንግሥት ማስከበር የውትድርና ሥራቸው በግላቸው ፍጹም ጀግና፣ከተራ ወታደር ጀምሮ አሁን እስከነበሩበት ኃላፊነት ደረጃ ድረስ በሁሉም አውደ ውጊያዎች በጀግንነታቸው የታወቁ፣ በዋሉባቸው ውጊያዎች ሁሉ አኩሪ ጀግንነት የተወጡ በነበራቸው ፍጹም የጀግንነት ባህሪ አባ ሓዊ /አባ እሳቱ/ እየተባሉ የሚቆላመጡ ጀግና ታጋይ ሰው ነበሩ ፡፡
ጀነራል ሰዓረ አንድ ቀንም ራሳቸውን እንደ መሪ እና አዛዥ አይተው የማያውቁ ሁሉንም ህዝቦች በእኩል አይን የሚያዩና የሚታገሉ ከተራ ወታደር ጋር እራሳቸውን ተራ አድርገው የሚያዩ ከጓደኞቻቸው እና እኩዮቻቸው ደግሞ ተግባቢ ሳቂታ፣አንድ ቀንም በጥቃቅን ስሜቶች ለማንም ሰው ፊታቸውን አጥፈው የማያውቁ አኩሪ የህዝብ ልጅ ነበሩ፡፡
ጀነራል ሰዓረ ከውጊያ በፊት፣በውጊያ ውስጥና ከውጊያ በኋላ የተጋጣሚውን ኃይል ሁኔታ በጥልቀት የሚያውቁና የሚያነቡ በየደቂቃውና ሰኮንዱ የሚኖሩ ለውጦች ከዕውቀታቸው ውጭ የማይወጡ በመሆኑ ሁልጊዜም ፍጹም የቀደምትነት እና የድል አድራጊነት ብቃትና ውጤት እንዲኖራቸው ያስደረገው፣በአካሄዷቸው በሺ የሚቆጠሩ አውደ ውጊያዎች ሁሉ ውጤታማ ታጋይ እንዲሆኑ ያስቻላቸው ጀግና ታጋይና መሪ ነበሩ፡፡
ጀነራል ሰዓረ እራሳቸው ጀግና መሆን ብቻ ሳይሆን በሥራቸው የሚመደቡ ታጋዮችና ወታደሮችን በአምሳያቸው የመቅረጽ ባህሪ የነበራቸው በትግል ወቅትና ከትግል በኋላ የመሯቸው የሰራዊት ክፍሎች በጀግንነታቸው የታወቁና በድል አድራጊነታቸው ቅድሚያ የሚመደቡ አሀዶች ፣ ዩኒቶች እንደነበሩ ሁሉም የሚመሰክርላቸው ሀቅ ነው፡፡
ጀነራል ሰዓረ በጥቃቅን ችግሮች ፍጹም የማይንበረከኩ በአስቸጋሪ ወቅት እራሳቸው እንደብረት ቀልጠው /ጠብቀው በድል አድራጊነት የተወጡ፣ ሰርዶ በነበረው አስቸጋሪ ሁኔታም በተፈጥሮ ወይም በሰው ሰራሽ አስቸጋሪ ሁኔታ ሳይሸነፉ በድል አድራጊነት የተወጡ፣ የሚፈጠሩ እጅግ አስቸጋሪ የሚባሉ ሁኔታዎችን ወደ ድል የመቀየር ልምድና ባህሪ ያካበቱ ፍጹም የተዋጣላቸው ጀግና ተመሪና መሪ የህዝብ ልጅ ነበሩ፡፡
ጀነራል ሰዓረ በፍጹም ስነ ምግባር የታነጹ ለህዝብ ዓላማ ከመሞት ውጭ ስለ ግላቸው በፍጹም የማይጨነቁ ህዝብን አክብረው ለህዝቦች ልዕልና ሲሉ ህይወታቸውን የሰጡ ፍጹም ኢትዮጵያዊ ጀግና እና የህዝብ ልጅ ነበሩ ፡፡
ጀነራል ሰዓረ መኮንን ለህዝብና ለመንግሥት አሰራሮች ሁል ጊዜ እራሳቸውን ተገዢ በማድረግ ከህዝብና መንግሥት የተሰጠ ተልዕኮና ኃላፊነቶችን ለመወጣት ሌት ተቀን ሲለፉ የኖሩ፣ ለግል እረፍትና ጨዋታ ጊዜ ሰጥተው የማያውቁ፣በሁኔታ ውስጥ የተፈጠሩ፣ በሁኔታ ውስጥ ያደጉ፣ ሁኔታዎችን ለህዝብ ጥቅምና ልዕልና ሊቀይሩና ሲቀይሩ የኖሩ፣የሁኔታ ሰው ተብሎ ሊያሰራ የሚያስችል ባህሪ ያሳደጉ ምርጥ የህዝብ ልጅ ነበሩ፡፡
ታጋይ ጀነራል ሰዓረ መኮንን በመሪዎችም ቢሆን ፍጹም ተወዳጅ የአስቸጋሪ ሁኔታ ቀያሪ ተደርገው ሲመረጡና ሲሰማሩ የኖሩ ሲሆኑ፣ ህዝባዊና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት እየተወጡ በነበሩበት ወቅት በአንድ የጠላት ቅጥረኛ የጥበቃ አባል በተተኮሰባቸው ጥይት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በተወለዱ በ57 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ አኩሪ የህዝብ ልጅ ነበሩ፡፡
ጀነራል ሰዓረ ከባለቤታቸው ኮለኔል ጽጌ አለማየሁ አንድ ሴትና አንድ ወንድ ልጅ አፍርተዋል፡፡ በዚህ ሽኝት የተገኙ ሁሉ ለቤተሰቦቻቸው ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለትግል ጓዶቻቸው መጽናናትን እየተመኘን ፈጣሪ አምላክ ነፍሳቸውን በአብርሀምና ይሳቅ ጎን ያሳርፍልን እያልን እናስባቸዋለን፡፡ ዘላለማዊ ክብር ለጀግኖች ሰማዕታት ፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2011
ወንድወሰን መኮንን